Monday, April 15, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያ ከግለሰቦችም ሆነ ከፖለቲካ ፓርቲዎች በላይ ናት!

ከአገርና ከሕዝብ ህልውና በፊት ግላዊና ቡድናዊ ፍላጎቶችን ላለማስቀደም ህሊናዊና ሞራላዊ ኃላፊነቶች ሊኖሩ ይገባል፡፡ አንድ ነገር ለማግኘት ሌላ ነገር መስጠት እንደሚገባ ሁሉ፣ ለአገርና ለወገን ሲባል ደግሞ ብዙ ነገሮችን በመተው እስከ መስዋዕትነት ለመክፈል ራስን ማዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ለግል፣ ለብሔር/ጎሳ፣ ለፖለቲካ ውግንና፣ ለጥቅም ትስስርና ለሌሎች ፍላጎቶች ሲባል አገርና ሕዝብ መበደል መወገዝ ይኖርበታል፡፡ ለአገርና ለሕዝብ ሁለንተናዊ ጥቅም ሲባል ኃላፊነትን ለመቀበል ማቅማማትም ሆነ፣ ችግሮችን በማባባስ ቀውስ መፍጠር ኢትዮጵያን ይጎዳል እንጂ አይጠቅማትም፡፡ ኢትዮጵያዊያንን በብሔርም ሆነ በሃይማኖት በማጋጨት ማጋደል፣ ማፈናቀልና ውድመት መፈጸም አዘቅት ውስጥ ይከታል እንጂ ዕድገት አያመጣም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ወቅታዊ ችግሮችን ለመፍታት መነሳት አለባቸው፡፡ ሕዝብ እርስ በርሱ የሚያጣላውና የሚያጋድለው ችግር ሳይኖርበት ይህ ሁሉ መከራ የሚደርሰው፣ ሥልጣን በጨበጡ ወይም ለሥልጣን በሚታገሉ ኃይሎች እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ሕዝቡማ በመሀሉ ምንም ችግር እንደሌለበት በተደጋጋሚ በግልጽ ተነግሯል፡፡ ‹ፖለቲከኞች ጠባችሁን አብርዳችሁ ከታረቃችሁ እኛ በመሀላችን ምንም ችግር የለም› የሚል መልዕክት፣ በተለያዩ መድረኮች በተደጋጋሚ ተሰምቷል፡፡ ከአገርና ከሕዝብ የሚበልጥ የለም፡፡

ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ለማስገንዘብ እንደተሞከረው ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶቻቸውን ጌጥ አድርገው በአንድነት ዘመናትን አብረው የኖሩት፣ ለዘመናት የገነቡዋቸው የጋራ ማኅበራዊ እሴቶቻቸው የፈጠሩላቸው ቁርኝቶች በደም ስላስተሳሰሯቸው ነው፡፡ ከምንም ነገር በላይ ለአገራቸው ማንኛውንም ዓይነት መስዋዕትነት ለመክፈል የማያንገራግሩት ኢትዮጵያዊያን፣ በግልና በቡድን ጥቅም በሰከሩ ኃይሎች ግፍ ሲደርስባቸው ዝም መባል የለበትም፡፡ ሥልጣንን የመጨረሻ ግብ በማድረግ በሕዝብ ደም የሚነግዱ ኃይሎች አገር እንዲያተራምሱ ሊፈቀድላቸው አይገባም፡፡ በተደጋጋሚ ሕዝብን ሰላም በመንሳትና ደኅንነቱን ለአደጋ በመዳረግ፣ ግላዊና ቡድናዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ ወገኖችን ማስቆም ይገባል፡፡ እነዚህ ኃይሎች በገዥው ፓርቲና በተፎካካሪ ፓርቲዎች ውስጥ በመሰግሰግ፣ በሕዝብ ላይ እያደረሱት ያለው ሰቆቃ መግቻ ያስፈልገዋል፡፡ ኢትዮጵያ እነዚህን በመገላገል ወደ ዕድገት ጎዳና መገስገስ አለባት፡፡ አሁን ባለው አደገኛ ሁኔታ መቀጠል አይቻልም፡፡ ወጣቱ ትውልድ ከፍተኛ የሆነ የሥነ ምግባርና የሞራል ግንባታ ያስፈልገዋል፡፡ ከአጠቃላይ ሕዝቡ ቁጥር ከ70 በመቶ በላይ ታዳጊዎችና ወጣቶች ያሉዋት አገር፣ ከዘመኑ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ተቋዳሽ በመሆን ወደ ሥልጣኔ እንድትጓዝ ማድረግ ግዴታ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከአገር በላይ ምንም ነገር የለምና፡፡

መጪው ምርጫ በሚፈለገው ደረጃ ሊከናወን የሚችለው ሰላምና መረጋጋት ሲሰፍን ነው፡፡ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተሟላ ሁኔታ ሲከበሩና ሁሉንም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በእኩልነት የሚያስተናግድ ምኅዳር ሲኖር፣ ነፃና ተዓማኒ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል፡፡ አሁን በሚታየው ተጨባጭ ሁኔታ ግን በርካታ መሰናክሎች ተጋርጠዋል፡፡ እንደ ምሳሌ ከሚነሱት መካከል በገዥው ብልፅግና ፓርቲ ውስጥ አስተማማኝ አንድነት አለመኖሩ፣ በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት መካከል የሚስተዋሉ ጤናማ ያልሆኑ ፉክክሮች፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶች ለተፎካካሪ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ሥጋት መሆናቸው፣ በግብፅ ሴራ እየተዘወረች ያለችው ሱዳን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመድፈር ድንበር ጥሳ በመግባት የጦርነት ዳመና ማንዣበቡ፣ በትግራይ ክልል በተካሄደው ዘመቻ ሳቢያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖች ለረሃብ መጋለጣቸውና በርካታ መሠረተ ልማቶች መውደማቸው፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከል ዞን በተለያዩ ሥፍራዎች በተደጋጋሚ ጭፍጨፋዎች መፈጸማቸውና ሌሎች በርካታ ተደራራቢ ችግሮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እንደሚታወቀው ዓለም አቀፋዊ መመዘኛዎችን ያሟላ ምርጫ ለማካሄድ ሰላማዊ ድባብ ያስፈልጋል፡፡ ዜጎች ማንንም ሳይፈሩ በነፃነት መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ አገር ከማንም በላይ ስለሆነች፡፡

በአሁኑ ጊዜ መንግሥት በርካታ ችግሮች ከፊቱ እንደተደቀኑበት ግልጽ ነው፡፡ በትግራይ ክልል በተካሄደው ዘመቻ ምክንያት ከአገር ውስጥም ሆነ ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት በርካታ ጥያቄዎች ይነሱበታል፡፡ በተለይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እና የአውሮፓ ኅብረት በሩን እንዲከፍት እየወተወቱ ነው፡፡ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት እስከ ጦር ወንጀል ድረስ ስለመፈጸሙ ሪፖርቶች እየደረሰን ነው እያሉ ናቸው፡፡ የዓለም መገናኛ ብዙኃንም ገብተን እንዘግብ በማለት ጥያቄዎችን እያጎረፉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የረድዔት ድርጅቶችም ኮሪደሮች እንዲከፈቱላቸው በመጠየቅ ላይ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ሦስተኛ ወገን ጣልቃ የገባበት ስለመሆኑ ማሳያዎች አሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ ችግሮች እንደ አመጣጣቸው መፍታት የሚቻለው ግን፣ መረጃ በመደበቅ ወይም በማድበስበስ አይደለም፡፡ መንግሥት ከማንም በፊት ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በመሆኑ እያንዳንዱን እንቅስቃሴውን በግልጽነት ማስረዳት አለበት፡፡ የመረጃ ፍሰት በመዝጋት የሚታወቀውን ኋላቀር ቢሮክራሲውን በማስወገድ፣ እየቀረቡ ላሉ ጥያቄዎች አሳማኝ ምላሽ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት ማስታወስ ይገባል፡፡ ከአገር ህልውና የሚበልጥ ግለሰብ ወይም ቡድን ስለሌለ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የማወቅ መብት መከበር ይኖርበታል፡፡ አገር የምትከበረው እንዲህ ነውና፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ትልቁ የመንግሥት ችግር ለግልጽነትና ለተጠያቂነት የሚሰጠው ግምት ነው፡፡ ለብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት ሊሆኑ ከሚችሉት ውጪ፣ ማናቸውም የመንግሥት ተግባራት ለሕዝብ ግልጽ መሆን አለባቸው፡፡ በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥትም ይህ መሆን እንዳለበት ያስገድዳል፡፡ ግልጽ መሆን ብቻ ሳይሆን ኃላፊነትና ተጠያቂነት የግድ ይሆናል ማለት ነው፡፡ መንግሥት ተግባሩን ለሕዝብ ግልጽ ከሚያደርግባቸው ዘዴዎች መካከል ዋነኛው ሚዲያ ነው፡፡ ሚዲያው ደግሞ ሁሉንም የመንግሥት ተቋማት ማግኘት መቻል አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ በጣም ውስን ከሆኑ መንግሥታዊ ተቋማት በስተቀር ብዙዎቹ በራቸው ዝግ ነው፡፡ ጠንካራ ተቋማትና የሕግ ማዕቀፍ በሌለበት ግለሰቦች እንዳሻቸው የሚሆኑት፣ ሥልጣናቸው ተጠያቂነት ስለሌለበት ነው፡፡ ለዚህም ነው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚፈጠሩ ቀውሶች የባለሥልጣናት እጅ እንዳለበት በይፋ ሲነገር፣ ለማስተባበል ለመሞከር ድፍረት የማይኖረው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ጥቃት በተፈጸመባቸው አካባቢዎች የሚሰሙ የሰቆቃ ድምፆች፣ በባለሥልጣናት ፊት ሳይቀር ነውረኛ ድርጊቶችን ሲያጋልጡ ይሰማል፡፡ የፀጥታ አስከባሪዎች ሊታደጉን አልፈለጉም ሲባልም በተደጋጋሚ ተሰምቷል፡፡ ከተለያዩ ጥቃቶች በስተጀርባ ባለሥልጣናት ጭምር መኖራቸው ይታወቃል፡፡ አገር የምትጎዳው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

በመላ አገሪቱ የሚኖረው ሕዝባችን ሰላም ያስፈልገዋል፡፡ ሰብዓዊ ክብሩ ተጠብቆ በነፃነት መኖር አለበት፡፡ ሥልጣን ላይ የሚወጡ ግለሰቦች ሥልጣናቸው ልጓም ያስፈልገዋል፡፡ በሕዝብ ስም መነገድ ማብቃት አለበት፡፡ በተለይ ገዥው ፓርቲ ብልፅግና ውስጥ ጥቅም ለማጋበስ የተሰገሰጉ ኃይሎች መጥራት አለባቸው፡፡ ከዚህ ቀደም የኢሕአዴግ አባልነትን ተገን በማድረግ ሕዝብ ሲያሰቃዩና የአገር ሀብት ሲዘርፉ የኖሩ ጭምር፣ ዛሬም ካባቸውን ቀይረው በሕዝብ ደም እየነገዱ ነው፡፡ ከአገር ውስጥም ሆነ ከተለያዩ አገሮች ሥልጣን ለማግኘት ሲሉ ብቻ፣ ለአገር በማይመጥን ሰብዕና እየተሰገሰጉ ያሉ ግለሰቦች ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ማንነትን መሠረት አድርገው የተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላቶቻቸውም፣ ለዘመናት አንድ ላይ በሰላም ሲኖር የነበረን ሕዝብ በብሔርና በሃይማኖት በመከፋፈል አገር ማተራመስ ወንጀል መሆኑን ይረዱ፡፡ ኢትዮጵያ ከሸፍጠኞች ስትፀዳ የማደግ ዕድሏ ሰፊ ነው፡፡ ሕዝቧ ጠላትን የመመከት ድንቅ ብቃቱን በልማቱ መስክ እንዲያሳይ ዕድል ቢያገኝ፣ ለማመን የሚያዳግቱ ገድሎችን ማከናወን ይችላል፡፡ ታላቁን የዓድዋ ድል በመጎናፀፍ ታሪክ ሠሪ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የድህነትን ቀንበር ለመሰባበር ምንም ዓይነት መሰናክል አያግደውም፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ከግለሰቦችም ሆነ ከፖለቲካ ፓርቲዎች በላይ ናት የሚባለው! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

ስለዘር ፖለቲካ

በሀብታሙ ኃይለ ጊዮርጊስ  ‹‹በቅሎዎች ዝርያችን ከአህያ ነው እያሉ ይመፃደቃሉ›› የጀርመኖች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...

የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይዳፈን ጥንቃቄ ይደረግ!

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር አሁንም ጤና አልባ ሆኖ የተለመደው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ሊሻሻል ያልቻለው የፖለቲካ ምኅዳር ሰሞኑን አዲስ...