Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየአደባባዩ ክብረ በዓል ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ

የአደባባዩ ክብረ በዓል ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ

ቀን:

በኢትዮጵያና በኮፕቲክ አብያተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ጥር 11 ቀን 31 .ም. በአጥማቂው ቅዱስ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቁን ተከትሎ በየዓመቱ በየአጥቢያው ይከበራል፡፡ በመጽሐፈ ስንክሳር እንደተገለጸው፣ ቅድስት ሥላሴ ስለ ተገለጠም በዓሉ በግሪክ የቴዎፋኒ/ኤጲፋኒያ በዓል ወይም የአስተርእዮ (መገለጥ) በዓል ይባላል፡፡

ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የአደባባይ በዓላት አንዱ ጥር 11 ቀን ላይ የሚውለው የጥምቀት በዓል ነው፡፡ ዋዜማው ከተራ እና ማግስቱ ቃና ዘገሊላም የአከባበሩ አካላት ናቸው፡፡ በዓሉ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እስከ ሦስት ቀናት ይከበራል፡፡  የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንም በየሰበካዋ በዓሉን በምታዘጋጀው ባሕረ ጥምቀት ታከብራለች፡፡

በየዓመቱ በመላ ኢትዮጵያ የሚከበረው የጥምቀት በዓል፣ ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው፣ በየጥምቀተ ባሕሩ የሚከበሩ በመሆናቸው፣ አገሬውን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ መስህብነትን በመጎናጸፉ፣ ቱሪስቶችን መሳቡ አልቀረም። ከጣና እስከ ዝዋይ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ጎንደር፣ ከላሊበላ እስከ አክሱም፣ ከሐዋሳ እስከ ጅማ፣ ከአሶሳ እስከ አሳሳ፣ ከሐረር እስከ ጋምቤላ ወዘተ በሁሉም ሥፍራዎች በዚሁ ዓይነት ደምቆ ይከበራል። የምዕመናኑም ሆነ የካህናትና ዲያቆናት አለባበስ  በሚማርኩ ባህላዊ አልባሳትና ልብሰ ተክህኖ የተዋበ በመሆኑ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ለሚመጡ ጎብኚዎች ሠርክ አዲስ ነው።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ጥር 10 ቀን፣ በከተራ፣ በገጠርም ሆነ በከተማ ታቦታት ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ወደየባሕረ ጥምቀቱ የሚያደርጉት ጉዞና መንፈሳዊ አዳር በማግስቱ የጥምቀት ዕለት ‹‹ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ›› ሰማያዊው በመሬታዊው እጅ ተጠመቀ ይዞ የሚኖረው ያሬዳዊ ዝማሬ የበዓሉ ገጽታ ነው፡፡

ከሃይማኖታዊው ሥነ ሥርዓት በኋላ ካህኑ በሃሌታ፣ ወንዱ በሆታ፣ ሴቱ በእልልታ ታቦተ ሕጉን አጅበው፣ እንደያመጣጣቸው ወደየአጥቢያቸው ይመለሳሉ።

ሊቃውንቱ እንደሚናገሩት፣ ዘመነ አስተርእዮ የሚባለው፣ ከጥር 11 ቀን ጀምሮ እስከ ጾመ ነነዌ ዋዜማ (ለዘንድሮ የካቲት 14) ያለው ጊዜ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ አምላክ ሰው ሆኖ በሥጋ መገለጡ፣ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ የአንድነትና የሦስትነት ምሥጢር መታወቁ፣ በቃና ዘገሊላ በተደረገው ሠርግ ላይ የመጀመሪያው ተዓምር በመፈጸሙ፣ አምላካዊ ኃይሉ መገለጡ፣ እየታሰበ ምሥጋና ይቀርባል። ይህ ኩነት ኢትዮጵያ ብሂልን ከባህል ጋር አዛምዳ ከሌላው የክርስቲያን ዓለም በተለየ አከባበር በዓሉን ማክበሯ ልዩ አድርጓታል፡፡

ሥዕላዊ ከሆነው ከሃይማኖታዊና መንፈሳዊ አከባበሩ በተጓዳኝም ባህላዊ  ገጽታው  ይታያል፡፡ ወጣቶች የሚተጫጩበት የትዳር አጋራቸውን የሚመርጡበት አጋጣሚዎችን ከመፍጠሩም ባለፈ በከተማም ሆነ በገጠር ሰውን የሚያገናኝ ድልድይ ነው፡፡

ያኔ የሎሚ ውርወራው፣ የከተራው ሽልምልም ዱላ አሁን አሁን በከፊል ሎሚው ወደ ፕሪም፣ ሽልምልሙ ዱላ ወደ ረዥም ቄጠማ (ጨፌ ላይ የሚበቅል) ተለውጦ መታየቱ፣ ከባህላዊ ጭፈራው በተጓዳኝ ወጣቱ በአመዛኙ ከመንፈሳዊ ማኅበራት (ሰንበት ትምህርት ቤቶች) መዘምራን ጋር ወደ ዝማሬ አዘንብሏል፡፡

በዓለም አቀፍ የፌስቲቫሎች መድበል የአፍሪካ ኤጲፋኒያ/ጥምቀት (The African Epiphany) እየተባለ የጎንደሩ፣ የላሊበላው፣ የአዲስ አበባውየጥምቀት አከባበር በዓለም የክብረ በዓላት (Festivals) ድርሳን ላይ በየጊዜው የሚተዋወቀው፣ ቱሪስቶችም እየመጡ የሚያደንቁት ነው፡፡

የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ በግዙፍ ቅርስነት ከተመዘገቡት ከአክሱም፣ ላሊበላ የጎንደሩ ፋሲል ግቢ ጋር በጥብቅ ተሳስሮ የሚከበር የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ መሆኑ፣ እንዲሁም በዓሉ ከ1,500 ዓመታት በላይ በተከታታይ የአገሪቱ ትውልዶችና ሥልጣኔዎች እየተከበረ ያለ ሕያው ቅርስ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ዓለም አቀፉ የባህል ተቋም ዩኔስኮ፣ በወርኃ ጥር የኢትዮጵያ አደባባዮች ደምቀው እንዲታዩ የሚያደርገውን የጥምቀት ክብረ በዓልን በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት በቦጎታ ኮሎምቢያ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች የበይነ መንግሥታት ኮሚቴ ዓምና ታኅሣሥ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. መመዝገቡ ታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...