የዘር ማጥፋት የሚለውን የወንጀል ድርጊት ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀው ፖላንዳዊው የሕግ ባለሙያ ራፋኤል ለምኪን፣ እ.ኤ.አ. በ1944 ባሳተመው “Axis Rule in Occupied Europe” በተሰኘ መጽሐፉ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ራፋኤል ለምኪን ለዚህ የወንጀል ድርጊት ስያሜ ለመስጠት ያነሳሳው ከፊል ምክንያት በወቅቱ ሥልታዊ በሆነ መንገድ የአይሁድ ማንነት የነበራቸውን ሕዝቦች በመለየት የመግደል ድርጊት እንዲፈጸም ያደረገውን የጀርመኑን የናዚ ፖሊሲን ለመውቀስ፣ በሌላ በኩልም ከዚያ አስቀድሞ በታሪክ የሚታወቁ በአንድ ማንነት ላይ ለተቃጡ ጥቃቶች ምንነት መልስ ለመስጠት እንደነበር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከያ ጽሕፈት ቤት የሰነዳቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይህ የፖላንዱ የሕግ ባለሙያ የግል ጥረትና ቅስቀሳም የዘር ማጥፋት ድርጊት ዓለም አቀፍ የውይይት ርዕስ እንዲሆን፣ በኋላም በዓለም አቀፍ ወንጀልነት ሕግ እንዲወጣለት አድርጓል።
ፖላንዳዊው የሕግ ባለሙያ ለምኪን ‘ጄኖሳይድ’ (Genocide) የሚለውን ቃል ሁለት የግሪክና የላቲን ቃላቶችን አዳቅሎ ትርጉም የሰጠው ሲሆን፣ ‘ጄኖ’ (Geno) በግሪክ ቋንቋ ዘር ወይም ብሔር የሚል ትርጓሜ ሲኖረው፣ በሁለተኛ ደረጃ የሚመጣው ሳይድ (Cide) የሚለው የላቲን ቃል ደግሞ መግደል የሚል ትርጓሜ አለው።
የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ ወንጀል ሆኖ ዕውቅና ያገኘው እ.ኤ.አ. በ1946 ሲሆን፣ ከሁለት ዓመት በኋላ የሕግ ማዕቀፍና ትርጓሜ ወጥቶለት የመንግሥታቱ ድርጅትም በ1948 የዘር ማጥፋት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቅጣት የተደረገ ስምምነት በሚል የዓለም አገሮች የሕግ ስምምነት ሰነድ ዓለም አቀፍ ሕግ ሆኖ መጽደቁን መረጃዎች ያመለክታሉ። ስምምነቱን እ.ኤ.አ 2019 ድረስ 149 አገሮች ተቀብለው ሲያፀድቁት፣ የስምምነቱ መሠረታዊያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸውና በርካታ አገሮችም በውስጥ ሕጎቻቸው የተቀበሏቸው በመሆናቸው፣ ስምምነቱን ባልተቀበለ አገር ላይም ቢሆን ተፈጻሚነት የሚኖረው ዓለም አቀፍ ሕግ እንዲሆን አድርጎታል።
የዓለም አገሮች የሚገዙበትና እ.ኤ.አ. በ1948 የጸደቀው የዘር ማጥፋት ወንጀልን የመከላከልና የመቅጣት ዓለም አቀፍ ስምምነት (Convention on the Prevention and Punishment of the Crime of Genocide)፣ በአንቀጽ ሁለት ላይ ለዘር ማጥፋት ወንጀል ዓለም አቀፍ ትርጓሜ አስቀምጧል።
በዚህም መሠረት የዘር ማጥፋት ወንጀል ማለት ብሔርን፣ ብሔረሰብንና ዘርን ወይም ሃይማኖትን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለማጥፋት ሆን ብሎ በማሰብ በተጠቀሱት ማንነቶች ማኅበረሰብ አባላት ላይ ግድያ መፈጸም፣ ከፍተኛ የአካል ወይም የአዕምሮ ጉዳት ማድረስ፣ በማንነት ላይ አካላዊ ጉዳት ሆን ብሎ በማድረስ ጉዳት የደረሰበት ማኅበረሰብ አባላት ቀጣይ ሕይወት ላይ የሚዘልቅ ጉዳት ማድረስ፣ በማንነት ላይ የወሊድ ክልከላ በማድረግ ዘሩ እንዳይቀጥል ማድረግና ሕፃናትን ከመሠረታዊ ማንነታቸውን አስገድዶ በመነጠል ወደ ሌላ ማንነት አሳልፎ የመስጠት ድርጊቶችን መፈጸም እንደሆነ ይደነግጋል።
የዘር ማጥፋት ወንጀል በአመዛኙ በአገሮች መካከል ወይም በአገር ውስጥ በሚነሳ የትጥቅ ትግል ወቅት ሊፈጸም የሚችል ነው፡፡ ነገር ግን ምንም እንኳ ያልተለመደ ቢሆንም፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል በሰላማዊ ወቅትም እንደሚፈጸም የተመድ የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የብሔር ማንነትና የሃይማኖት ማንነት ላይ ያነጣጠሩ በርከት ያሉ ወንጀሎች ተፈጽመዋል፣ አሁንም ጥቃቶቹ እየተፈጸሙ ይገኛሉ።
የቅርብ ጊዜ ጥቃቶችን ለአብነት ለመጥቀስ ያህልም በትግራይ ክልል በማይካድራ ማንነት ላይ ባነጣጠረ ጥቃት በዋናነት በአካባቢው በሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ጭፍጨፋ የተፈጸመ ሲሆን፣ በአንድ ቀን ውስጥ ከ600 መቶ በላይ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተጨፍጭፈው መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በአካባቢው ተገኝቶ ባደረገው ማጣራት ማረጋገጡን ይፋ አድርጓል።
በተመሳሳይ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከል ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ እየተሰነዘረ ባለ ማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት፣ በአመዛኙ በአካባቢው የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ተገድለዋል።
ታዋቂው የኦሮሚኛ ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ በድንገት በአዲስ አበባ ከተማ መገደሉን ተከትሎ፣ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞችም ተመሳሳይ ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት መፈጸሙን ባለፈው ሳምንት ይፋ ከተደረገው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የምርመራ ሪፖርት መገንዘብ ይቻላል።
ኮሚሽኑ የሃጫሉን ግድያ ተከትሎ በ40 የኦሮሚያ ከተሞች የተከሰቱን ግጭቶች በመመርመር ባቀረበው ሪፖርት በአጠቃላይ የ123 ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ ቢያንስ በ500 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን፣ በግለሰቦች፣ በንግድ ድርጅቶችና በመንግሥት ንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ መፈጸሙን ይፋ አድርጓል። ከሞቱት ውስጥ 35 የሚሆኑት በቡድን የተደራጁ ግለሰቦች ማረድን ጨምሮ በፈጸሙት አሰቃቂ ግድያ ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ገልጿል።
በቡድን የተደራጁ ሰዎች ከቦታ ቦታ እየተንቀሳ ቀሱ ብዙ ሲቪል ሰዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደላቸውና ጥቃቱ ያነጣጠረውም በከፊል በብሔርና ሃይማኖታቸው ተለይተው የተመረጡ ሰዎችን ከየቤታቸው ለይቶ በማሳደድና በማጥቃት፣ በከፊል ብሔርና ሃይማኖት ሳይለይ ሰላማዊ ነዋሪዎችን ወይም ሲቪል ሰዎችን ሆነ ብሎ በማጥቃት መፈጸሙን የኮሚሽኑ የምርመራ ሪፖርቱ ይገልጻል።
የኮሚሽኑ ሪፖርት በማከልም፣ ‹‹በጥቃቱ ወቅት በማኅበራዊ ሚዲያና በተወሰኑ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ይተላለፍ ከነበሩት መልዕክቶችና በወንጀል ድርጊቱ ይሳተፉ የነበሩ ሰዎችና ቡድኖች ያሰሟቸው ከነበሩት መፈክሮች አንፃር፣ በወንጀል ድርጊቱ ሲሳተፉ የነበሩት ሰዎች ተግባራቸው ሥልታዊና የተቀናጀ ወይም የሰፊ ጥቃት አካል መሆኑን በማወቅ የተሳተፉበት ነበር፤›› ብሏል።
የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የድምፃዊውን ግድያ ተከትሎ የተፈጸሙ ጥቃቶች የምርመራ ሪፖርትን ባቀረቡበት ወቅት፣ ምርመራው በተካሄደባቸው 40 የኦሮሚያ ከተሞች ከተሰበሰበው መረጃ በመነሳት የተፈጸመው ድርጊት በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል እንደሆነ ኮሚሽኑ መደምደሙን ገልጸዋል።
የተፈጸመው ወንጀል ማንነት ላይ ያነጣጠረ መሆኑን በማውሳት እንዴት የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዳልተባለ በወቅቱ መግለጫውን የተከታተሉ የሚዲያ ባለሙያዎች ላነሱት ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ የዘር ማጥፋት ወንጀልን እንደማያሟላ ገልጸዋል።
ነገር ግን በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመውና በሌሎች አካባቢዎች የተፈጸሙ ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል ምልክቶች የታዩባቸው እንደነበር ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።
‹‹ኮሚሽኑ እስካሁን በተከታተላቸው የፀጥታ ችግሮች ጭካኔና ግፍ የተሞላባቸው ወንጀሎች ቢፈጸሙም፣ የዘር ማጥፋት ወንጀልን የሚያቋቁሙ ናቸው ብሎ አያምንም፤›› ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ነገር ግን እየታዩ ያሉ ጭካኔ የተሞላባቸው የወንጀል ድርጊቶች የዘር ማጥፋት ወንጀል አደጋ ምልክቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በመሆኑም መንግሥት ጭካኔና ግፍ የተሞላባቸው ወንጀሎችን ለመከላከል፣ ብሔራዊ ስትራቴጂ ቀርፆ መንቀሳቀስ እንዳለበት ምክረ ሐሳብ መቅረቡን ገልጸዋል።
ኮሚሽነር ዳንኤል (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተፈጸሙ ያሉ ወንጀሎች የዘር ማጥፋት ወንጀልን አያቋቁሙም የሚል ድምዳሜ ላይ ቢደርሱም፣ ሌሎች የሕግ ባለሙያዎች ግን ይህንን የኮሚሽነሩን ድምዳሜ ይቃረናሉ።
የዘር ማጥፋት ወንጀልን በተመለከተ የተቀሰቀሱ ሙግቶች
በኢትዮጵያ የተፈጸሙ ጥቃቶች የዘርማጥፋት ወንጀልን ያሟላሉ የሚል ሙግት ከሚያቀርቡት መካከል፣ የሕግ ባለሙያው አቶ ውብሸት ሙላት አንዱ ናቸው።
እሳቸው እንደሚሉት በኦሮሚያ የተፈጸመውም ሆነ በትግራይ በማይካድራ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በአማራ ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች የዘር ማጥፋት ወንጀልን ያቋቁማሉ፡፡ ነገር ግን የወንጀሉ ፈጻሚዎችና ደጋፊዎች ይህንን እውነታ አይቀበሉም፣ እውነታውን አለመቀበልና እውነታውን ለማደናገር መሞከርም የዘር ማጥፋት ወንጀል ከተፈጸመ በኋላ የሚደረግ የተለመደ ተግባር መሆኑን ያወሳሉ።
በማይካድራና አካባቢው በአማራ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመፈጸሙ፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል ባህሪያትን ደረጃዎችን በማነፃፀርም በማይካድራ ወንጀሉ መፈጸሙን ይገልጻሉ።
የዘር ማጥፋት ወንጀል ከመፈጸሙ አስቀድሞ የማንነት ልየታ (classification) እንደሚካሄድ የጠቀሱት አቶ ውብሸት፣ በማይካድራ አማራና ትግሬ የሆኑትን ለይታ (Classification) ‹‹እኛ›› እና ‹‹እነሱ›› በማለት እንደተካሄደ ያስረዳሉ።
የተለዩት ጥቃቱ የሚፈጸምባቸው ማኅበረሰቦችም በተለያዩ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተቋማት እንዳይሳተፉ የማግለልና የአድልኦ ተግባራት (Discrimination) ሲፈጸሙባቸው እንደቆየ፣ የአማራ ማኅበረሰብን ከሰውነት (ከሰብዓዊነት) የማውረድና የማሳነስ፣ በእንስሳት እየመሰሉ መስደብ (Dehumanization) ለበርካታ ዓመታት ሲካሄድ እንደከረመም ይጠቅሳሉ።
የዘር ማጥፋት ዕቅዱ ዕውን እንዲሆንም፣ በሩዋንዳና በደቡብ ሱዳን የወንጀል ድርጊቱን የሚፈጽሙ ቡድኖች እንዳዋቀሩት ሁሉ በኢትዮጵያም ይህ እንደተፈጸመ ያወሳሉ።
በሩዋንዳ በተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ሁቱዎቹ ኢንተርሃምዌ የተባለ የዋናው ፓርቲ የወጣት ተቀጥላ አደራጅተው ነበር፡፡ በሱዳን ዳርፋር መንግሥት ድጋፍ የሚያደርግላቸው ጃንጀዊድ ቡድኖች ተደራጅተው የማጥቃት ወንጀል ፈጽመዋል፡፡ በኢትዮጵያ በማይካድራ ለተፈጸመው ወንጀልም በሕወሓት ልዩ ኃይል ፖሊስና በሚሊሻ የሚደገፍ ‹‹ሳምሪ›› የሚባል ገዳይና ጨፍጫፊ ቡድን ተደራጅቶ የማይካድራ ጭፍጨፋ መፈጸሙ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ በሌሎች ሰብዓዊ መብት ተቋማት መረጋገጡን ገልጸዋል።
በሚፈጠሩ አደረጃጀቶችና ሚዲያዎችን (digital and mainstream) እንዲሁም ሌሎች ማኅበራዊ መገናኛዎች ጭምር በመጠቀም፣ የማራራቅና የማጽነፍ (Polarization) ሥራ መከናወኑም ሌላ ሀቅ እንደሆነና በዚህም ተግባር ሚስት ባሏን (ባል ሚስቱን) ለመግደልና ለማረድ መጨከን እስኪችሉ ድረስ ጽንፍ መያዛቸውን ይገልጻሉ።
‹‹ከማይካድራና አካባቢው አማራን ለማፅዳት የመጨረሻው ዝግጅት በተደራጀው ገዳይ ቡድን (ሳምሪ)፣ እንዲሁም በጠቅላላው በእዚያ አካባቢ በሚኖረው ትግሬ ልብ ውስጥ ‘አማራን ከአካባቢው ካላጠፋን ይጨርሷችኋል፣ ይገድሏችኋል፣ ያባሯችኋል’ ወዘተ የሚል ፍርኃት በመንዛት፣ የሚገድሏቸውን ሰዎች ዘርዝረው መቼ መግደልና እንዴት መግደል እንዳለባቸው ተዘጋጅተውበታል። ይህም የመጨረሻው መዳረሻ ዝግጅት (Preparation) ነው፤›› ብለዋል።
ዝግጅቱ ተገባዶ የመጨረሻውን የማጥፋትና የማስወገድ ድርጊት ከማከናወኑ አስቀድሞ ማሳደድ (Persecution) የተለመደ መሆኑን፣ ንብረት መቀማት፣ ከአካባቢው ማባረር፣ በተናጠል መግደል፣ ወዘተ መፈጸማቸውን የሚናገሩት አቶ ውብሸት፣ እነዚህ ሒደቶች ማይካድራ ብቻ ሳይሆን በወልቃይትም መፈጸማቸውን ይናገራሉ።
በኦሮሚያ የተከሰተውን ጥቃት አስመልክቶ ኮሚሽኑ ያቀረበው የምርመራ ሪፖርትም፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል ስለመፈጸሙ በቂ ማስረጃዎችን እንደያዘ አቶ ውብሸት ይገልጻሉ።
ሪፖርተር የተመለከተው የኮሚሽኑ የምርመራ ሪፖርት የጽምፃዊ ሃጫሉ መገደል በኦሮሚያ ለተከተሰተው ግጭት የቅርብ ጊዜ መነሻ ምክንያት (triggering factor) እንደነበር የሚገልጸው ኮሚሽኑ፣ ከዚያ አስቀድሞ በብዙ ቦታዎች የብሔር ማንነትንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ የጥቃት አዝማሚያ እንደነበር ይገልጻል።
ጥቃቱን የፈጸሙት ቡድኖችና ሰዎች ተጠቂዎችን በዋነኝነት በብሔር ወይም በሃይማኖት ሆነ ብለው እየለዩና እየመረጡ ያጠቁ እንደነበር አስረድቷል፡፡
የድምፃዊውን መገደል ተከትሎ በተከሰተው ግጭት ወቅትም አጥቂዎቹ ለጥቃት በተንቀሳቀሱበት ወቅት ሲያሰሙት ከነበረው መፈክርና የቅስቀሳ ንግግሮች ውስጥ፣ ‹‹ጎንደሬ ውጣ››፣ ይህ የኦሮሞ ነው አትንካ››፣ ‹‹አማራ ነው/አማራ ናት››፣ ‹‹ክርስቲያንን አጥፉ››፣ ‹‹አማራ ውጣ››፣ ‹‹ክርስቲያን ውጣ››፣ ‹‹መንዜ ውጣ›› ይሉ እንደነበር የኮሚሽኑ መርማሪዎች ከምስክሮች ከተቀበሉት ቃል መረዳት መቻላቸውን ይገልጻል።
የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ዳንኤል (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል በሚል ባለሙያዎች የሚያቀርቡትን ሙግት በተመለከተ ሰሞኑን በሚዲያ ምላሽ ሰጥተውበታል።
በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ከሚገኙ ግጭቶች ጋር በተያያዘ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል የሚል ክርክር በማኅበረሰቡ ልሂቃን፣ ፖለቲከኞች፣ ሚዲያዎችና የመንግሥት ባለሥልጣናትም ጭምር ሲቀርብ እንደሚሰሙ ኮሚሽነሩ በመግለጽ፣ ይህ ዓይነቱ ክርክር በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለመደ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ምክንያታቸውንም ሲገልጹ የዘር ማጥፋት ወንጀል ዓለም አቀፍ ስምምነት ሲፀድቅም ሆነ ከፀደቀ በኋላ እስካሁን ድረስ የወንጀሉ መፈጸምን በተመለከተ ክርክሮች እንደቀጠሉ መሆናቸውን፣ የዚህም መነሻ ምክንያት ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽኑ ለወንጀሉ የሰጠው ትርጓሜ በጣም ጠባብ በመሆኑ ነው።
ስለወንጀሉ በማኅበረሰብ ደረጃ ያለው ግንዛቤ (Popular Understanding) እና ወንጀሉን ለማቋቋም በሚያስችሉ ሕጋዊ መሠረቶች መካከል ልዩነት እንዳለ የሚገልጹት ኮሚሽነር ዳንኤል (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የሚሰማው ክርክርም በማኅበረሰብ ደረጃ ስለወንጀሉ የተያዘ ግንዛቤ ነው ብለው እንደሚያምኑ አስረድተዋል፡፡
‹‹እንደ እኛ ባለ ጉዳዩን በተመለከተ ሙያ ውስጥ ለምንሠራ ባለሙያዎች ግን፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል በሕግ ሥነ ሥርዓት መሠረት ትርጉሙ ምንድነው ብለን የምንረዳበት መለኪያዎችን የለየ ነው፤›› ብለዋል።
የዘር ማጥፋት ወንጀልን የሚያቋቋሙ የሕግና የፍሬ ነገር መሠረቶች እንዳሉ የሚገልጹት ኮሚሽነሩ፣ የፍሬ ነገር መሠረት ማለት ምን ሆነ? ምን ተፈጸመ? የሚለውን የተመለከተ እንደሆነ፣ የሕግ መሠረቱ ደግሞ ሁለት ነገሮችን ሊያሟላ እንደሚገባ ይገልጻሉ።
የሕግ መሠረት የሚባሉት ሁለት ነጥቦች አንዱና ዋነኛው “Mental Element of the Crime” (ወንጀሉን ለመፈጸም የተያዘ የሐሳብ ዝግጅት ወይም የሐሳብ ፍሬ ነገር) እንደሆነ፣ ሁለተኛው ደግሞ የአካላዊ ድርጊት (Physical element of the crime) ወይም በአዕምሮ ደረጃ የተያዘውን የወንጀል ጥንስስ ለመፈጸም የተከናወነ አካላዊ ድርጊት መሆናቸውን አስረድተዋል።
በተለይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ለማቋቋም መሟላት ካለባቸው የሕግ ፍሬ ነገሮች መካከል የሐሳብ ፍሬ ነገሩ ከሌለ ወንጀሉ ተፈጽሟል ለማለት እንደማይቻል የሚገልጹት ኮሚሽነር ዳንኤል (ዶ/ር)፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዘር ማጥፋት ወንጀል ዓለም አቀፍ ስምምነት ከፀደቀበት ወቅት አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የዘር ማጥፋት ወንጀል ፍርድ የተሰጠው በሁለት ክሶች ላይ ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል።
የተለያዩ የዘር ማጥፋት ወንጀል ክሶች ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ቢቆይም ከሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀልና ከዩጎዝላቪያ ውጪ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል የሚል ፍርድ እንዳልተሰጠ በመግለጽ፣ ወንጀሉ በጠባቡ እንዲተረጎም ተደርጎ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
የዘር ማጥፋት ወንጀል ስሜታዊ (emotive) ጽንሰ ሐሳብ በመሆኑ በብሔር ወይም በሃይማኖት ማንነቱ ተለይቶ ጥቃት የደረሰበት ማኅበረሰብ፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደደረሰበት መግለጽና መከራከሩ የተለመደ እንደሆነ ይናገራሉ።
ሐሳቡ መነሳቱ በራሱ ችግር አይደለም የሚሉት ኮሚሽነሩ፣ ነገር ግን ጥንቃቄ ካልተደረገ ጥቃት የደረሰበት ማኅበረሰብን ሥጋት ውስጥ በመክተት የዘር ማጥፋት ወንጀል መከሰትን ሊፈጥር እንደሚችል ይገልጻሉ።
በተመድ የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከልና ጥበቃ የማድረግ ጽሕፈት ቤት (UN office on genocide prevention and the responsibility to protect) መረጃም፣ የዘር ማጥፋትን ለማቋቋም ጥቅም ላይ ከሚውሉት የሕግ መለኪያዎች መካከል የሐሳቡን ፍሬ ነገር መሟላቱን ማረጋገጥ እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነ ያስረዳል።
በአንድ ማንነት ላይ በተፈጸመ ጥቃት ማኅበረሰብን ማፈናቀል ወይም በማኅበረሰቡ ባህላዊ እሴቶች ላይ ጉዳት ማድረስ፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሙን እንደማያሟላ ይገልጻል።
ምንም እንኳን ዓለም አቀፉ የዘር ማጥፋት ወንጀል ስምምነት ላይ ባይጠቀስም፣ በጉዳይ ላይ የተሰጠ የሕግ ብያኔ የዘር ማጥፋት ወንጀልን ለማቋቋም ከሐሳብ ፍሬ ነገር መሟላት በተጨማሪ፣ የመንግሥት ወይም የድርጅት ዕቅድና ፖሊሲ መኖር እንዳለበት መወሰኑን ተቋሙ ይገልጻል።
በቶሮንቶ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህርና በዘር ማጥፋት ወንጀል ጉዳዮች ተመራማሪ የሆኑት ፋውስቲን ነቶባንዲ (ዶ/ር) “Uncovering the Components and Elements of Genocidal Acts” በሚል ርዕስ ባሳተሙት የጥናት ጽሑፋቸው፣ የዘር ማጥፋት ወንጀልን ማቋቋም በተለየ ሁኔታ አስቸጋሪ እንደሆነና ለዚህም ወንጀሉን ለማቋቋም በመሥፈርትነት የተቀመጠው የሐሳብ ፍሬ ነገር ካልተሟላ ወንጀሉ ተፈጽሟል ለማለት እንደማይቻል ገልጸዋል።
ወንጀሉ ለመፈጸሙ የሐሳብ ፍሬ እንደተያዘ በተጨባጭ የሚያስረዳ ማስረጃ ከሌለ፣ የተፈጸመው ወንጀል ሊፈረጅ የሚችለው በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ወይም ጭካኔ የተሞላበት ግድያ እንደሚባል ያስረዳሉ።
ነገር ግን የወንጀል የሐሳብ ፍሬ ነገርን ማቋቋም ከተቻለ፣ የወንጀል ድርጊቱ በተሟላ ሁኔታ መፈጸሙ ወይም አለመፈጸሙ የዘር ማጥፋት ወንጀልን ለማቋቋም ዕክል ሊሆን እንደማይችል ይገልጻሉ።