መኳንንት ጌጡ በከብት ንግድ ላይ ከተሰማራ ከአሥር ዓመት በላይ አልፎታል። በጎችና ፍየሎችን ከገበሬዎች እየገዛ ለአዲስ አበባ ነጋዴዎች የሚያከፋፍለው መኳንንት በሥራው ላይ ብዙ ጊዜያትን ቢያሳልፍም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገበያው ተገማች ባለመሆኑ ኪሳራ ውስጥ እየወደቀ መሆኑን ይናገራል።
ለአብነትም ባለፈው የአዲስ ዓመት በዓል ገበያ ይኖራል በሚል ዕሳቤ በከፍተኛ ዋጋ በጎችና ፍየሎችን ከገበሬዎች ገዝቶ የነበረ ቢሆንም፣ ሸማቾች ዋጋ በመወደዱ እንዳልገዙት ያስታውሳል።
‹‹ገበሬዎች ዋጋ በመጨመራቸው የተነሳ እኔም ይህንን ማካካስ ነበረብኝ፤›› የሚለው መኳንንት፣ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት ሸማቾች ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም፣ ሊገዙት እንዳልቻሉ፣ ምንም እንኳን በጎቹን ከበዓል በኋላ በአነስተኛ ዋጋ ቢሸጣቸውም፣ ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶበት እንደነበር ያወሳል።
ታዲያ ለዘንድሮ ገና በዓል ከአዲስ ዓመት ገጠመኙ ትምህርት በመውሰድ ረከስ ባለ ዋጋ ከገበሬዎች ቢገዛም፣ የሸማቾች ፍላጎት በጣም ወርዷል ይላል። ‹‹ከጊዜ ወደ ጊዜ ገበያውን መገመት አዳጋች እየሆነ ነው፤›› የሚለው መኳንንት፣ በተለይ በአገሪቱ የሚስተዋለው አለመረጋጋት ሸማቾች በተረጋጋ መንፈስ እንዳይሸምቱ እንዳደረጋቸው ምልከታውን ያጋራል።
የገና ገበያ ምን ይመስላል?
በዘንድሮ የገና በዓል ገበያ ከአዲስ ዓመት አኳያ የምግብ ምርቶች ዋጋና የአቅርቦት መረጋጋት ቢያሳዩም፣ የሸማቾች ቁጥር ብዙም ጭማሪ አለማሳየቱን ነጋዴዎች ይናገራሉ። የሪፖርተር ዘጋቢዎች በቦሌ፣ ሾላ፣ መርካቶና ቄራ በሚገኙ ገበያዎች ባለፉት ሁለት ቀናት ያደረጉት ዳሰሳ እንደሚያሳየው፣ በተለይም የዶሮ፣ የበግና የፍየል አቅርቦት ካለፈው በዓል አንፃር ጭማሪ አሳይቷል።
በአዲስ ዓመት ወቅት እስከ 550 ብር ሲሸጥ የነበረው የዶሮ ዋጋ በገና ወደ 400 ብር የወረደ ሲሆን ከወላይታ፣ ከአርባ ምንጭ እንዲሁም በአዲስ አበባና ዙሪያ ከተሞች የዶሮዎች ቁጥር መጨመሩ እንደ ምክንያት ተነስቷል። ከበግና በፍየል ገበያ መረጋጋት ታይቷል።
‹‹ባለፈው በዓል (አዲስ ዓመት) ከኦሮሚያ አንዳንድ ከተሞች ይመጡ የነበሩ በግና ፍየሎች በነበረው አለመረጋጋት የተነሳ ቁጥራቸው ቀንሶ የነበረ ሲሆን፣ በገና በዓል ይህ ችግር ተቀርፏል፤›› የሚለው በቄራ አካባቢ የሚሠራው ሰዒድ መሐመድ የተባለ ነጋዴ ነው፡፡ ይህም ዋጋ እንዲረጋጋ ትልቅ ሚና እንደተጫወተ አስረድቷል። የሸማቾችም አስተያየት ከዚህ ብዙ የተለይ አይደለም።
‹‹በአዲስ ዓመት ሁሉ ነገር ተወዶ ነበር፤›› የሚሉት ተመሥገን ቢተው የሚባሉ ሪፖርተር በቦሌ አካባቢ ያገኛቸው ሸማች፣ የበግና የፍየል ዋጋ ከፍተኛ ቅናሽ ማሳየቱንና የተሻሉ አማራጮቹም በዘንድሮ በዓል መታየታቸውን ተናግረዋል።
በአዲስ ዓመት ወቅት እስከ 6,000 ብር ሲሸጥ የነበረው መካከለኛ መጠን ያለው በግ በዘንድሮ ገበያ ወደ አራት ሺሕ ብር ዝቅ ያለ ሲሆን፣ ሙክት የሚባል የሰባ በግ ከ9,000 ብር ወደ 6000 ዝቅ እንዳለ ነጋዴዎች ተናግረዋል። በተመሳሳይ ከፍተኛው የፍየል ዋጋ ከ12,000 ብር ወደ 8,000 ብር ዝቅ ማለቱን፣ አነስተኛ ክብደት ያለው የፍየል ዋጋ ከአንድ ሺሕ ብር በላይ ቅናሽ በማሳየት በ3,000 ብር ሲሸጥ ተስተውሏል።
እንደ ገበያው ቅርበት ቢለያይም በአዲስ አበባ ሲሸጡ የነበሩ ፍየሎችና በጎች በብዛት ከደብረ ብርሃን፣ ከዱበር፣ ከጊንጪ፣ ከደሴና ከጅማ የመጡ ናቸው፡፡ ሠንጋዎች በአብዛኛው ከምሥራቅ ኦሮሚያ በተለይም ሐረርጌ ዞን ውስጥ ከሚገኙ አነስተኛ ከተሞች የመጡ እንደሆኑ ሪፖርተር በከተማው ያደረገው ዳሰሳ አመላክቷል። በተጨማሪ ቅልብ ሠንጋዎች በአብዛኛው ከአዳማ፣ ከባሌና ከአርሲ የገቡ ሲሆን ከጎንደርና ከወለጋ የመጡ ሠንጋዎች ቁጥር ላይ ቅናሽ መታየቱን ለማወቅ ተችሏል።
በግና ፍየል ላይ የታየው የዋጋ መቀነስ ሠንጋዎች ላይ የታየ ሲሆን፣ እስከ 5,000 ብር የሚደርስ ቅናሽ ተስተውሏል። የሐረር ሠንጋዎች ከ34,000 ብር አንስቶ እየተሸጡ የነበረ ሲሆን፣ ዝቅተኛ ዋጋ ያላቸው ሠንጋዎች ደግሞ ከ10,000 ብር እስከ 12,000 ብር ድረስ ሲሸጡ ተስተውሏል። ያላቸው ክብደት መካከለኛ የሚባሉት ሠንጋዎች ደግሞ ከ12,000 ብር እስከ 18,000 ብር ሲሸጡ ተስተውሏል።
ይሁን እንጂ በአዲስ አበባ በቅርጫ ሠንጋ የመግዛት ልማድ እየቀነሰ በመምጣቱ፣ በብዛት ሠንጋዎችን የሚገዙት ልኳንዳዎች መሆናቸውን ማወቅ ተችሏል። በሌላ በኩል ከአቅርቦት አኳያ ከአዲስ ዓመት መሻሻል ቢታይም፣ የገዥዎች ቁጥር ላይ እምብዛም ለውጥ እንዳልታየ አሸናፊ ሽፈራው የተባሉ የከብት ነጋዴ ለሪፖርተር ተናግረዋል። ለዚህም እንደ ምክንያት ያነሱት፣ ‹‹በዓሉ በሐሙስ ቀን መዋሉን›› ሲሆን፣ በማግሥቱ የፆም ቀን በመሆኑ የገዥዎች ፍላጎት ቀንሷል ብለዋል፡፡
የሠንጋ ዋጋ መረጋጋት ቢያሳይም ልኳንዳ ቤቶች በሥጋ ዋጋ ላይ ቅናሽ ማድረጋቸው አልታየም። በአንዳንድ አካባቢዎች ከወዲሁ ጭማሪዎች እየታዩ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ የአንድ ኪሎ ሥጋ ዋጋ ከ200 ብር እስከ 600 ብር እየተሸጠ መሆኑን ሪፖርተር ያደረገው ዳሰሳ ያሳያል፡፡
በሌላ በኩል በዓልን ተከትሎ በስፋት በጥቅም ላይ ከሚውሉ ምርቶች መካከል የሆነው ቅቤ ዋጋ ላይ እስከ 20 ብር ጭማሪ የታየ ሲሆን፣ በመርካቶና በሾላ ገበያዎች በኪሎ እስከ 290 ብር ሲሸጥ ተስተውሏል። ከአቅርቦት አኳያ ካለፈው በዓል አንፃር የተሻለ ሁኔታ እንደነበር ነጋዴዎች ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በኮረሪማ አቅርቦት ላይ መሻሻል መታየቱን ተከትሎ ከአዲስ ዓመት አኳያ እስከ 80 ብር የሚደርስ ቅናሽ ታይቷል። በሾላና በመርካቶ ሪፖርተር ባደረገው ዳሰሳ በኪሎ እስከ 170 ብር ሲሸጥ ተስተውሏል። በአዲስ ዓመት ወቅት እስከ 38 ብር ሲሸጥ የነበረው የሽንኩርት ዋጋ ወደ 17 ብር የቀነሰ ሲሆን፣ የነጭ ሽንኩርት ዋጋም ከ160 ብር ወደ 100 ብር ወርዷል፡፡
በምግብ ምርቶች ላይ የታየው መረጋጋት ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች ላይ ሊታይ አልቻለም። ለአብነት አልባሳቶችን ማንሳት ይቻላል።
በመርካቶ፣ በፒያሳና በሃያ ሁለት አካባቢዎች የሪፖርተር ዘጋቢ ባደረገው ዳሰሳ መሠረት፣ ከውጭ የሚገቡ ሱሪዎች ላይ ከ100 ብር እስከ 200 ብር የሚደርስ ጭማሪ የታየ ሲሆን፣ የወንድና የሴት ጫማዎች ላይ ከ50 ብር እስከ 150 ብር ጭማሪ ታይቷል።
ከቻይና የሚገቡ ምርቶች በውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ አቅርቦታቸው መቀነሱ እንደ ምክንያት ተወስቷል።
በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከውጭ ከሚገቡ አልባሳት ውስጥ 90 በመቶ ከቻይና በመሆናቸው፣ ያለው የአቅርቦት ችግር ካልተፈታ የታየው የዋጋ ጭማሪ ከፍተኛ ሽያጭ ይኖራል ተብሎ በሚገመትበት የጥምቀት በዓል ላይ የበለጠ ሊጨምር እንደሚችል፣ አብሽሮ አወል የተባሉ በልብስ ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴ ተናግረዋል።
ባለፉት ሦስት ወራት የታየው የምርት እጥረት በዓይነቱ የከፋ መሆኑን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነጋዴዎች የተናገሩ ሲሆን ከዱባይ የሚገቡ ምርቶች ላይ የሚጣለው ቀረጥ ከፍ ማለቱም ለታየው የዋጋ ጭማሪ ምክንያት እንደሆን አስረድተዋል፡፡
የታየው የዋጋ ግሽበት በዚህ አያበቃም
በአገር ውስጥ የሚመረቱ ጫማዎች የችርቻሮ ዋጋ ላይ እስከ 100 ብር የሚደርስ ጭማሪ ታይቷል። በተለይም ጫማ ለማምረት የሚውሉ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች አቅርቦት በመቀነሱና የፋብሪካዎች የማምርት አቅም በመውረዱ የጫማ ዋጋ ሊጨምር እንደቻለ፣ አማኑኤል መንግሥቱ የተባሉ በአመዴ አካባቢ የጫማ ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴ ተናግረዋል።
የሸማቾች ልበ ሙሉነት
በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚታየው አለመረጋጋት፣ የሸማቾች ልበ ሙሉነት (consumers’ confidence) ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ግልጽ ነው። በተለይም አለመረጋጋቶች በሚከሰቱ ጊዜ ሸማቾች የምግብ ምርቶች ይጠፋሉ በሚል ፍራቻ በብዛት ሲገዙ ማየት የተለመደ ሲሆን፣ በእንዲህ ዓይነት ወቅቶች እንደ አልባሳት ላሉ ምግብ ነክ ላልሆኑ ምርቶች ያለው ፍላጎት ሲቀንስ ይስተዋላል። በገና በዓል የዋዜማ ገበያ ላይ የታየው ከዚህ የተለየ እንዳልሆነ ነጋዴዎች ያስረዳሉ፡፡
በአገሪቱ ያለው አለመረጋጋት በከፋ ቁጥር ሸማቾች ልበ መሉነታቸው ስለሚቀንስ የሚያወጡት ገንዘብ ይቀንሳል የሚሉት የጫማ ነጋዴው አማኑኤል፣ አለመረጋጋቶች በተከሰቱ ቁጥር የሽያጭ ገቢያቸው ወዲያውኑ እንደሚቀንስ ይናገራሉ፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ የተከሰተ ሰሞን ሸማቾች በመደናገጣቸው ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶችን መግዛት አቁመው እንደነበር ያወሱት አማኑኤል፣ ከዚያም የሃጫሉን ሞት ተከትሎ በተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋትና በትግራይ በነበረው ግጭት የተነሳ ተመሳሳይ ችግር ገጥሟቸው እንደነበር ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ አሁን በአገሪቱ አንፃራዊ ሰላም እየታየ በመሆኑ የሸማቾች ልበ ሙሉነት ስለጨመረ የንግድ እንቅስቃሴው የተሻለ መሆኑን የሚናገሩት አማኑኤል፣ በገና በዓል ገበያ ከአዲስ ዓመት የተሻለ ሽያጭ ማስመዝገባቸውን አውስተዋል።
በሌላ በኩል በአገሪቱ አንፃራዊ ሰላም ቢታይም ሸማቾች ከፍተኛ ገንዘብ ለማውጣት ያላቸው ፍላጎት ብዙም አላደገም የሚሉት በከብት ንግድ ላይ የተሰማሩት መኳንንት፣ አሁንም መንግሥት ይህንን ለመቅረፍ መሥራት እንደሚገባው አውስተዋል።
በተመሳሳይ የሸማቾች ልበ ሙሉነት ወሳኝነት እንዳለው የሚናገሩት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ አየለ ገላን ሲሆኑ፣ ለኢኮኖሚ ዕድገት ሞተር በመሆን እንደሚያገልግል ያስረዳሉ።
‹‹ሸማቾችና ነጋዴዎች በምጣኔ ሀብት ላይ ያላቸው መተማመን የተሻለ ሲሆን፣ የኢኮኖሚው ዕድገትም የተሻለ ይሆናል። ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ደግሞ አገሪቱ የምታሳየው ዕድገት ይቀንሳል፤›› በማለት፣ የሸማቾች ልበ ሙሉነት ለኢኮኖሚ ዕድገትና መረጋጋት ያለውን የማይተካ ሚና የመንግሥት የፖሊሲ አውጪዎች ሊረዱት ይገባል ሲሉ አቶ አየለ ሐሳባቸውን ለሪፖርተር አጋርተዋል።
በሳምሶን ብርሃኔ