Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በትብብርና ሕግ በማክበር መፍታት ይቻላል

ከወቅታዊ ጉዳይ አንፃር በብርቱ ሊታሰብበትና ሊሠራበት የሚገባው ዓብይ ጉዳይ ኢኮኖሚው ነው፡፡ ቅንጦትና አለመረጋጋቶች ኢኮኖሚውን በእጅጉ ጎድተውታል፡፡ በቅርቡም በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ሕግ ከማስከበር ሥራ ጋር ተያይዞ የተካሄው ጦርነት፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳትም እንዲህ በቀላል የማይታይ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኢኮኖሚው ላይ ሊፈጠር የሚችለው ተፅዕኖውም ከዚህ በኋላ መታየቱ አይቀርም፡፡ ከሰሞኑ እንደተሰማውም የአገሪቱ የዋጋ ግሽበት ከ20 በመቶ በላይ መድረሱም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ስለዚህ ኢኮኖሚያችንን ሊፈትኑ የሚችሉ ብዙ መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮች ከፊታችን መኖራቸውን ያመላክተናል፡፡

ባለፉት ሁለት ሦስት ዓመታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሆን ተብለው በተፈጠሩ ግጭቶችና ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተስተዋሉ ችግሮች በየጊዜው ኢኮኖሚ ላይ ያሳረፉት ተፅዕኖ ሲደማመር፣ ብዙ ወደ ኋላ እንዳስቀረንም ይታመናል፡፡ አሁን ላይ ደግሞ የጦርነቱ ዳፋ ይዞብን የሚመጣው ጣጣም የኢኮኖሚውን አካሄድ በብልኃት መምራት የሚጠይቅ ይሆናል፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ያጣነው ብቻ ሳይሆን መልሶ ለመተካትና የተጎዳውን ለመጠገን፣ ድጋፍ የሚፈልጉትን ለመደገፍና ለማቋቋም እንዲሁም ለመሰል ሥራዎች የሚጠይቀው ወጪ ቀላል ያለመሆኑን ካሰብን፣ እንደ አገር የሚከፈለው ዋጋ የመንግሥትን ካዝናና የኅብረተሰቡን ኪስ መዳበሱ አይቀርም፡፡

በጥቅሉ ሲታይ አገሪቱ ያስተናገደቻቸው ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶችና ሌሎች የመሰናክሎች ይብዛም ይነስም በኢኮኖሚው ላይ ጫና ማሳረፋቸው ግልጽ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ አገር ባልተዘጋጀችበት ወይም ይመጣሉ ተብሎ በማይታሰቡ ሁኔታዎች የሚፈጠሩ ሳንካዎች በሌለ ሀብት ያልታሰበ ወጪ የሚጠይቁ በመሆኑ፣ ይህንን ክፍተት ለመድፈንና ገበያን ለማረጋጋት ኢኮኖሚውንም ከውድቀት ለመታደግ ሁለንተናዊ ትብብር ያስፈልጋል፡፡

የተጠረቃቀሙ ችግሮቻችን ሊያስከትሉ የሚችሉ ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም ሲባል፣ ለአንዱ የታሰበን ሀብት ለሌላ ማዋልን የሚጠይቅም ነው፡፡ አንደኛውን ከአንደኛው በማመዛዘን የበለጠ ለሚባለው ችግር ቅድሚ ይሰጥ ካልተባለ በቀር፣ ያልታሰቡ ወጪዎች መኖራቸው አንዳንድ ዕቅዶችን ሊያዛቡ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ በዕቅድ የተያዙ ሌሎች ሥራዎችን መነካካቱ አይቀርም፡፡ ይህም ሌላ ፈተና ነው፡፡

ለፋብሪካ ጥሬ ዕቃ ሊሰጥ የታሰበ የውጭ ምንዛሪ ለድንገተኛ አደጋ ያስፈልግና በውጭ ምንዛሪ እጥረት አንዳንድ ማምረቻዎች በወጉ ለማምረት የሚቸገርበት ዕድል ሊፈጥርም መቻሉን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ወትሮም ብዙ ችግር ያለበት የውጭ ምንዛሪ ግኝት አሁን ሊባባስ እንደሚችልና በአፋጣኝ መፍትሔ የሚሰጥ ጊዜያዊ የአሠራር ሥልት መተግበር ወቅታዊ ችግሮችን የሚያሸጋግር ፖሊሲ መቅረፅን ሁሉ ሊጠይቅ ይችላልና በዚህ ረገድ ብዙ መሠራት ይኖርበታል፡፡

የቢዝነስ እንቅስቃሴዎች ተያያዥ ናቸውና የአንዱ ዘርፍ መጎዳት ሌላውንም የሚነካ በመሆኑ በጥቅል ሲታይ ጉዳቱ ሰፊ ስለሚሆን ይህንን ታሳቢ ያደረገ መፍትሔ ፈጠን ብሎ ማበጀትና ጉዳቱ እንዲመጠን ማድረግ ግድ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ሰሞኑን መንግሥት ያፀደቀውን የአሥር ዓመት የኢኮኖሚ መሪ ዕቅዱን ከግብ ለማድረስ፣ አሁን ላይ ያለውን ችግር ቀድሞ ማስተካከልን የሚጠይቅ ነው፡፡ አሁናዊውን በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ችግር መፍታት የግድ ያስፈልጋል፡፡ ሳይታሰቡ ለአላስፈላጊ ወጪ የዳረጉን አገራዊ ጉዳዮች የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ቀላል አይሆንምና የረዥም ጊዜ ዕቅዱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አሁን ላይ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ የአጭር ጊዜ ፖሊሲዎች ሊያስፈልጉን ግድ የሚል ይሆናል፡፡

ምክንያቱም ጤናማ ኢኮኖሚ እንዲኖር እንዲሁም የበለጠ የዋጋ ግሽበት እንዳይኖርና  እንዳይቀጥል ከተፈለገ በአሁናዊው ችግር መፍትሔ ማበጀት ያስፈልጋል፡፡ በውጭ ምንዛሪና በሌሎች የመሠረተ ልማት ችግሮች ሳቢያ ምርታማነት እንዳይታጎል፣ ጅምር ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች እንዳይደነቃቀፉ፣ ዜጎችም የሥራ ዋስትናቸው እንዳይነካ ወቅታዊ ሁኔታውን መነሻ በማድረግ፣ ኢኮኖሚውን ጤናማና ሁሉን ያገናዘበ ዕድገት እንዲኖር በብልኃት መሥራቱ ጊዜ የሚጠይቅ አይደለም፡፡

ኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ ሊያሳርፉ የሚሉችና በቀላሉ ሊስተካከሉ የሚችሉ ክፍተቶችን በመድፈን፣ የተሻለ ምርታማ መሆን የሚቻልበትን ዘዴ መቀየሱ ተፅዕኖውን ይቀንሰዋል፡፡

ከዚህ አንፃር ሰሞኑን መንግሥት ገለልተኛ የኢኮኖሚ አማካሪ ምክር ቤት  መመሥረቱን መግለጹንና አባላቱን ማሳወቁ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች ዋነኛ ተግባራቸው ከዚሁ ጋር የተያያዘ ቢሆን ይመረጣል፡፡ ጥቅል ተግባራቸው የአገሪቱን ቀጣይ የኢኮኖሚ አቅጣጫ ምን መምሰል አለበት የሚለውን ማመላከት ቢሆንም፣ ከዚህ ባሻገር ግን አገር ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ በማየት ምን ዓይነት መፍትሔ ያስፈልጋል ለሚለው ወሳኝ ጉዳይ መልስ መስጠት መሆን አለበት፡፡

እዚህ ላይ ግን መረሳት የሌለበት መንግሥት የምሁራኑን ምክረ ሐሳብ ለመቀበል የተሄደበት መንገድ መልካም የመሆኑን ያህል፣ ለዛሬም ሆነ ለነገ ችግሮች እንደ መፍትሔ የሆኑ ፖሊሲዎችንም በቶሎ በመተግበር ኢኮኖሚውን ማነቃቃት ቢዝነሱን ሊያቀላጠፉ የሚችሉ አሠራሮችን መተግበር ያስፈልጋል፡፡

አገር በተለያዩ ተፅዕኖዎች የምታጣውንና ያጣችውን ጥቅም ለመመለስ ብሎም ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆንበት ኢኮኖሚያዊ ዓውድ እንዲኖር ሲታሰብ ግን፣ ሁሉንም ነገር ለመንግሥት ጥሎ ከእርሱ መፍትሔ መጠበቅ ያለመሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡

ካለንበት ችግር ለመውጣት ብቻ ሳይሆን ቀጣይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሊኖር የሚችለው ጨዋ የንግድ ኅብረተሰብ ሲኖር ጭምር ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ በሙሉ አቅም ማምረት እንዲቻል የግል ዘርፉ ሚና ከፍተኛ መሆን አለበት፡፡

 የእያንዳንዱን የግል ጥረት የሚጠይቅ ሲሆን፣ ከግል ጥቅም በላይ እንደነበር በማሰብ መሥራት የተሻለ ተጠቃሚ እሆናለሁ ብሎ አሁን ላይ በቀጥታ መሥራትንም ይጠይቃል፡፡ ከዕለቱ ትርፉና ልክ ከሌላው የትርፍ ህዳግ ለማግኘት እሳቤ ወጥቶ ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት መሥራት ያስፈልጋል፡፡ አዳዲስ የቢዝነስ ኢንቨስትመንቶችም ከዚሁ አንፃር መቅረፅም ያስፈልጋል፡፡ አሁንም እንተባበር፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት