‹‹አዎ ሁሌ እጠጣለሁ፡፡ አዎ ሁሌ እጠጣለሁ፡፡ አንቺማ ሳቂ፣ አንተም ሳቅ፡፡ ለምን ትጠጣለህ አትበለኝ፡፡ መጀመርያ ምን እንዳቃጠለኝ ምክንያቱን ጠይቀኝ፡፡ ይገርምሃል እኔም እኮ ገበሬ ነበርኩ ከዚያ ከገጠር፡፡ ከተማ ጥሩ ነው፡፡ ከተማ መልካም ነው፡፡ የከተማ ሰው መልካም ነው ብለው ይኼው አምጥተውኝ፣ ይኼው እንዲህ አሳብደው ጎዳና አስቀሩኝ፡፡ እህትም ነበረኝ፡፡ እህትም ነበረኝ እኮ፣ ታዲያ ምን ያደርጋል ከተማ ጥሩ ነው ብለው አምጥተው ደፍረው ጣሏት እንጂ፡፡ እንደ እኔ እና እሷ ብዙ ሕፃናት አሉ፡፡ ከተማ ጥሩ ነው ተብለው ተታለው የመጡ ጎዳና የቀሩ፤››
ኅዳር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. በሲዳማ ክልል ሐዋሳ ከተማ የዓለም ሕፃናት ቀን ታስቦ ውሏል፡፡ ከላይ ያለው ንግግር የተወሰደውም ዕለቱ በተከበረበት ቀን ሕፃናት ከጎዳና እያሰባሰበ በሚረዳ ግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ ሔኖክ አበበ የተባለ ታዳጊ ሕፃናት ላይ የሚደርሰውን እንግልት ለመግለጽ ካቀረበው ቴአትር ላይ ነው፡፡
ሰው በበርካታ ውጣ ውረዶች ማለፍ የተፈጥሮ አንዱ ስጦታ ነው፡፡ የሰው ልጅ የተሻለ ኑሮ ለመመሥረት ሲል መከራ ሳይበግረው ደፋ ቀና ማለትም ይጠበቅበታል፡፡ በበርካታ እንቅፋቶች የተሞላው የሰው ልጅ ሕይወት ለአንዳንዱ መንገዱ ቀላል ሲሆን ለአንዳንዶች ደግሞ ጨለማ ይሆናል፡፡ ገሚሱ የተንደላቀቀ ሕይወት ሲኖር፣ ሌላው የዕለት ጉርሻ ሲማፀን መመልከት የዚህ ዓለም የሁለት ሳንቲም አንድ ገጽታ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
በተለይ በሕፃናት ላይ የሚደርሰው የከፋ የሕይወት ዕድል ችግሩን የበለጠ አስከፊ ያደርገዋል፡፡ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ለጎዳና ሕይወት የሚጋለጡ ሕፃናት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ከዓመታት በፊት ይፋ በሆነ ጥናት በኢትዮጵያ 11 ከተሞች ከ88 ሺሕ በላይ ጎዳና ተዳዳሪዎች መኖራቸው ተረጋግጧል፡፡ ከእነዚህም መካከል 50 ሺሕ ያህሉ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ እንደሚኖሩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ለከተማ ጎዳና ሕይወት ከተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው ወጣቱ ክፍል ሲሆን፣ የመሥራት አቅም ያላቸው እንደሆኑም ይነገራል፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ ከሚፈልሱት ወጣቶች ባሻገር በማኅበረሰብ ጎጂ ባህል የተገለሉ፣ አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው፣ የአዕምሮ ውስንነት ያለባቸውና ከተወለዱ በኋላ በጨርቅ ተጠቅልለው የተጣሉ ሕፃናት ጉዳይ ደግሞ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም እነዚህን ሕፃናት ለመታደግ በማሰብ ተጓዳኝ ችግር የደረሰባቸውን ሕፃናት በመሰብሰብና በመንከባከብ ሥራ ላይ የተሰማሩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አሉ፡፡
ከእነዚህ በሐዋሳ ከተማ በ1998 ዓ.ም. የተቋቋመው አቤኔዘር የድጋፍና የልማት ማኅበር ተጠቃሸ ነው፡፡ ማኅበሩ ከተቋቋመበት ወቅት ጀምሮ ላለፉት 14 ዓመታት ለሴቶች፣ ሕፃናትና በማኅበረሰብ ለተገለሉ አካላት ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
በተለይ በተለያዩ ማኅበረሰቦች ዘንድ ባለው ጎጂ ልማድ ምክንያት የተገለሉ፣ እንዲገደሉ የተፈረደባቸው፣ የተጣሉ፣ በኤችአይቪ ኤድስ የተያዙና የአዕምሮ ውስንነት ያለባቸውን ሕፃናት ሲደግፍ ሰንብቷል፡፡
አቶ አራጋው አየለ ትውልዳቸውና ዕድገታቸው በሲዳማ ክልል ሲሆን፣ በአሜሪካ ኑሮውን ካደረገ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ የበጎ አድራጎት ሥራ ላይ መሰማራቱን ይናገራል፡፡ የአቤኔዘር ድጋፍና የልማት ማኅበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ አራጋው እንደሚሉት በርካታ ሕፃናትን ከጎዳና ላይ በማንሳት የትምህርት፣ የሕክምናና የምግብ ድጋፍ በማድረግ የሕፃናቱን ሕይወት በመታደግ ላይ ይገኛሉ፡፡
ማኅበሩ ከጎዳና ላይ አንስቶ ድጋፍ ካደረገላቸው በኋላ ወደ ቤተሰባቸው ከመለሳቸው ሕፃናት ባሻገር በአሁኑ ሰዓት በማኅበሩ ውስጥ ከ86 በላይ ሕፃናት ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡ ከእነዚህም መካከል ደቡብ ኦሞ ሐመር አካባቢ ‹‹ሚንጊ›› በሚባለው ጎጂ ልማድ ሊገደሉ የነበሩ 12 ሕፃናትን መታደግ መቻላቸውን ያስረዳሉ፡፡
አቶ አረጋው፣ በሐመር ማኅበረሰብ ዘንድ ያለውን ጎጂ ልማድ ማለትም ከዚያ ማኅበረሰብ ውጪ ባለው ኅብረተሰብ ላይ ያላቸውን ከፍተኛ ጥርጣሬና እምነት ማጣት ለውጦ ቶሎ ለውጥ ማምጣት አዳጋች እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
‹‹ሐመር አካባቢ ያለው ማኅበረሰብ በውስጡ ከሚኖረው ኅብረተሰብ ወጪ ላለው ሰው እምነት የለውም፡፡ ከሌላ ሥፍራ ወደ በማኅበረሰቡ የሚሄድ ሰው ተቀባይነት አያገኝም፡፡ በዚህም ምክንያት ‹‹ሚንጊ›› የሆኑትን ሕፃናት ለመቀበል የማሳመኑ ሒደት በጣም አልፊ ነበር፤›› በማለት ያሳለፉትን አስቸጋሪ ጊዜ ያስታወሳሉ፡፡
ምንም እንኳን ልፋት ያለው ሥራ ቢሆንም የተወሰኑ ሕፃናትን አትርፈው ወደ ማኅበሩ በማስገባት አስፈላጊው እንክብካቤ ተደርጎላቸው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ አክለዋል፡፡ እነዚህ ሕፃናት የዘጠነኛና የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ሲሆኑ ወደ ቤተሰባቸው በማቅናት ዕረፍት ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ አስችለናል ይላሉ፡፡
በአገር ውስጥ ጉዲፈቻ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው አቤኔዘር የድጋፍና የልማት ድርጅት ኤችአይቪ ኤድስ የሚገኝባቸውን ሕፃናት ጨምሮ ከፍተኛ የአዕምሮ ውስንነት ችግር ያለባቸውንና ጤናማ ሆነው አቅም የሌላቸውን ሕፃናት ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ከዚህም ባሻገር ሸካ አካባቢ ‹‹ማንጃዎች›› ናቸው ተብለው በማኅበረሰቡ በእጅ እንኳን የማይነኩና ከሰው በታች የተባሉ ሕፃናትን በማሰባሰብ ከአብራክ ልጆቹና በማኅበሩ ውስጥ ካሉት ታዳጊዎች ጋር ቀላቅለው እያኖሩ እንደሚገኙ ነግረውናል፡፡
‹‹እኔ አሜሪካዊ ዜግነት ካላት ባለቤቴ ጋር አምስት ልጆች አፍርቻለሁ፡፡ በዚህ ማዕከል ውስጥ ያሉት 86 ታዳጊዎች ከልጆቼ ጋር በእኩል ዓይን እየታዩ ነው የሚኖሩት፤›› ይላሉ አቶ አረጋው፡፡
ማዕከሉ ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን፣ አራት የማዕከሉ ተማሪዎችም ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ዘንድሮ በሕግ ተመራቂ የሆነች ዓይነ ሥውር እንዳለች አቶ አረጋው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከባለቤታቸው ጋር በመሆን በአሜሪካ የሚገኙ የተለያዩ በጎ አድራጊ አካላት ጋር ደጅ እየጠኑ በሚያሰባስቡት ገንዘብ ሕፃናትን የሚታደገውን ማዕከል ያስተዳድራሉ፡፡ ምግብ የሚያበስሉ፣ የሕክምና ባለሙያዎች፣ የአዕምሮ ችግር ያለባቸውን ሕፃናት አንደ እናት የሚንከባከቡ፣ የሥነ ልቦና ድጋፍ የሚያደርጉና ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን ሕፃናት ሆስፒታል ውስጥ እንክብካቤ የሚያደርጉትን ጨምሮ 56 ሠራተኞችም በማዕከሉ ይሠራሉ፡፡
የልማት ማኅበሩ በማዕከሉ ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር በደቡብ ኦሞ ሐመር፣ ምዕራብ ዓባያ እንዲሁም ሲዳማ ላይ በድርቅ ምክንያት የምግብ እጥረት ማጋጠሙን ተከትሎ ለ51 ትምህርት ቤቶች ለ31,700 ተማሪዎችን መመገብ ችሏል፡፡
በተጨማሪም ለሲዳማ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ሻሸመኔና ዝዋይ ከተሞች ግምቱ 250 ሺሕ ዶላር የሚያወጣ ለአካል ጉዳተኞች የሚሆን ዊልቸር፣ ክራንችና ለዓይነ ሥውራን ድጋፍ አድርጓል፡፡
ሕፃናት አንዴ ወደ ጎዳና ከወጡ በኋላ ወደ ቤት መመለስ ከባድ እንደሆነ የሚገልጹት አቶ አረጋው፣ ሕፃናቱ ወደ ጎዳና ከመውጣታቸው በፊት መከላከል ቢቻል በርካታ ሕፃናትን መታደግ እንደሚቻል ይመክራሉ፡፡
ለ14 ዓመታት የዘለቀውን ሕፃናትን ከስቃይና ጎዳና ኑሮ የመታደግ ሥራ የሚያከናውኑት ቤት ተከራይተው ሲሆን፣ አሁን ላሉበት የሕፃናቱ መኖሪያ ለቤት ኪራይ 80 ሺሕ ብር በወር እንደሚከፍሉ አክለው፣ ለከተማው አስተዳደር የቦታ ጥያቄ ቢያቀርቡም የለም የሚል ምላሽ ሲሰጣቸው እንደነበር አቶ አርጋው ያስረዳሉ፡፡
የክልሉ ሴቶችና ሕፃናት ቢሮም ሆነ ሚኒስቴሩ የተቸገሩ ሕፃናትን ወደ ማዕከሉ ከማምጣት በስተቀር ይኼ ነው የሚባል ድጋፍ እንደማያደርጉላቸው አልሸሸጉም፡፡
ተጨማሪ ሕፃናትን ወደ ማዕከሉ ለማምጣት ዕቅድ ቢወጥኑም በቂ ቦታ ለማግኘት የከተማ አስተዳደሩን ደጅ ቢጠኑም፣ ነገ ዛሬ ከማለት ባሻገር ምንም መፍትሔ እንዳላገኙ አቶ አረጋው ያስታውሳሉ፡፡
በርካታ ተስፋ አስቆራጭ ችግሮች እንደሚገጥማቸው የሚያስረዱት ሥራ አስኪያጁ በቅርቡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ከእንግሊዝ አገር የተላከላቸውን አራት ሙቀት መለኪያ ጉምሩክ ይዞት ማስገባት አትችሉም መባላቸውን ይናገራሉ፡፡
ከተለያዩ የዓለም አገሮች ለማዕከሉና ለቀይ መስቀል የተላኩ የሕፃናት ልብሶችና ቁሳቁሶች ከጉሞሩክ ወደ ክልሉ ቢላክም የሐዋሳ ከተማ የአደጋና ዝግጁነት ግን ቁሳቁሱን ለሌሎች ድርጅቶች እንደሰጡባቸው ጠቅሰዋል፡፡
ምንም እንኳን ሕፃናቱን በመታደግ ውስጥ መንገዶች አልጋ ባልጋ ባይሆኑም ሕፃናቱ ከወደቁበት አንስቶ ሕይወት ዘርቶባቸው፣ በትምህርት ክፍተኛ ደረጃ ደርሰው እንደማየት ደስታን የሚያጭር ነገር እንደሌለ የሚገልጹት ሥራ አስኪያጁ ተስፋ አስቆራጭ ነገር ቢኖርም ሕፃናትን መታደግ እንደሚቀጥሉ መቁመዋል፡፡