ቻይና የእግር ኳስ መፍጠሪያ፣ እንግሊዝ የእግር ኳስን ሕግ አስተዋዋቂ መሆናቸው ቢነገርላቸውም የእግር ኳስ ጥበብና ውበት ግን የደቡብ አሜሪካኖች እግር ዘንድ ነው ያለችው በሚለው በርካቶች ይስማማሉ፡፡ ይኼን ለማረጋገጥ የዓለማችን ሁለት ዕንቁ ተጫዋቾች ፔሌና ዲያጎ ማራዶና ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከሁለቱ ማን ይበልጣል ሲባልም እከሌ ይበልጣል፣ እከሌ የሚለው የዘመናት ክርክር ምስክር ነው፡፡
ዓለም የእግር ኳስ ጥበበኛውን ሰው ዲያጎ ማራዶና አጥታ ሐዘን ተቀምጣለች፡፡ ማራዶና የእግር ኳሱ ፈጣሪ ረቡዕ ኅዳር 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ተሰምቷል፡፡ ማራዶናን ለመግለጽ ጥሩ ቃል እንደተጠቀመ የተመሰረከለት ኤድዋርዶ ጋሌኖ፣ ማራዶና ‹‹የእግር ኳሱ ፀሐይና ጥላው›› በሚል ቃል ገልጾታል፡፡
ከጥፍሩ ጀምሮ መላ ሰውነቱ ዓይን እንዳለው የሚነገርለት አክሮባቲክ፣ አዝናኝና ኳስን እንዳሻው የማሾር አቅም ያለው የዓለማችን ድንቅ ተጫዋች ነበር፡፡ በልብ ሕመም በ60 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ማራዶና፣ ከእግር ኳስ በኋላ የነበረው ሕይወቱ ጥሩ የሚባል እንዳልሆነ ሲነገር መሰንበቱ ይታወሳል፡፡ አደንዛዥ ዕፅ መጠቀሙና ሰውነቱ ከመጠን በላይ መጨመሩ ለሕልፈተ ሕይወቱ ምክንያት ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡
እ.ኤ.አ. ኦክቶበር 30 ቀን 1960 ቦይነስ አይረስ የተወለደው ማራዶና በእግር ኳስ ሕይወቱ እንዲሁም ከእግር ኳስ ውጪም በርካታ አወዛጋቢ ነገሮች አብረውት ይነሱ ነበር፡፡ በውጣ ውረድ ከተሞላው ሕይወቱ ባሻገር ለሰው ልጆች መብት የታገለበት ጊዜም ነበረው፡፡ የመሰለውን ከመናገር የማይቆጠበው ማራዶና ኢምፔሪያሊዝምን አጥብቆ ይቃወም ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ሁሌም ላቲን አሜሪካ ራሷን በራሷ ታስተዳድር በሚል ይሟገት ነበር፡፡ በተለይ ለደሃ አገሮች እንዲሁም ለሕፃናት መብት በመቆምም ይታወቃል፡፡ ለቤተሰቡ አምስተኛ ልጅ የሆነው ማራዶና ልጀነቱን ኤሌክትሪክና በቂ ውኃ በሌለበት መንደር ነው ያደገው፡፡
ማራዶና በሕይወት ዘመኑ ቀላል የማይባሉ የፖለቲካ አቋሞች ነበሩት፡፡ በአንድ ወቅት የሮማ ካቶሊካዊ ቤተ ክርስቲያን ፓፕ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጋር ተገናኝተው ጳጳሱ ስለተቸገሩ ሕፃናት ሲያወሩ ካዳመጠ በኋላ፣ ‹‹ሕፃናቱ እንደተቸገሩ ካወቃችሁ ለምን በቤተ ክህነት ውስጥ ያለውን ወርቅና ሀብት ሸጣችሁ ሕይወታቸውን አትታደጉም፤›› በማለት የተናገረው ንግግር አነጋጋሪ ነበር፡፡
ማራዶና በተለይ ለፍልስጤሞች ያለው ፍቅር የተለየ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. 2018 ‹‹ሁሌም በልቤ ውስጥ እንዳሉ ይኖራሉ፡፡ እኔ ፍልጤማዊ ነኝ፤›› ሲል ለፍልስጤማውያን ያለውን ፍቅር ገልጿል፡፡
በተለይ እስራኤል በጋዛ ላይ የምትወስደውን ጦርነት በመቃወም ትችት ይሰነዝራል፡፡ እንዲሁም እ.ኤ.አ. በ2015 ላይ የፍልስጤምን እግር ኳስ ቡድንን በእስያ ዋንጫ ላይ አሠልጣኝ ሆኖ ይመራዋል ተብሎ ሲወራ ነበር፡፡ ማራዶና የግራ ዘመም ፖለቲካን እንደሚከተል ይነገርለታል፡፡ በዚህም የቀድሞ የኩባ ፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮና የነፃነት ታጋዩ ቼጉ ቬራ ምሥል ተነቅሷል፡፡ ማራዶና ኩባን ሊወድ የቻለበት ምክንያት ሕይወቱን የታደገ መድኃኒት ስለተገኘለት እንደሆነ ይነገራል፡፡ በአንድ ወቅትም የቬንዙዌላውን መሪ ሆጎ ቻቬዝ በአገሪቱ ለሚያደርገው የመሠረተ ልማት እንቅስቃሴ ድጋፍ አድርጎለታል፡፡ ለአሜሪካ ጥላቻ እንዳለው የሚነገርለት ማራዶና የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የሆኑትን ይቃወም ነበር፡፡ በዘመነ ቡሽ አሜሪካ ከኢራቅ ጋር በነበራት ጦርነት፣ ‹‹ቡሽ ወንጀለኛ ነው፤›› ሲልም ተደምጧል፡፡ ‹‹ከአሜሪካ የሚመጣ ሁሉንም ነገር እጠላለሁ፡፡ ይኼ ውስጤ ያለ ስሜት ነው፤›› በማለት ለአሜሪካ ያለውን ጥላቻ በይፋ አሳውቋል፡፡
በእግር ኳስ ሜዳ ላይ ስላለው በርካቶች ሊናገሩ፣ ሊመሰክሩና ሊጽፉ እንደሚችሉ ዕሙን ነው፡፡ እ.ኤ.አ. 1986ቱ የዓለም ዋንጫ አርጀንቲና ከእንግሊዝ በተጫወቱበት ወቅት በእጁ ባስቆጠራት ግብ ‹‹ባለ እግዜር እጅ›› የሚል ስም እንዲሰጠው አስችሏል፡፡
የ20ኛ ክፍለ ከተማ ዘመን የእግር ኳስ ፈርጥ ማራዶና ዛሬ የለም፡፡ የረዥም ጊዜው ተፎካካሪውና ለዘመናት እኔ ነኝ፣ እኔ ነኝ የዓለማችን ምርጥ በመባል ከፔሌ ጋር የቃላት ጦርነት ውስጥ ሲገቡ ከርመዋል፡፡ የማረፉ ዜና ከተሰማ በኋላ ፔሌ ‹‹አንድ ቀን በሰማይ ቤት ኳስ እንደምንጫወት ተስፋ አደርጋለሁ፤›› የሚል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ የእግር ኳስ ዘመኑን በአርጀንቲና የጀመረው ማራዶና ለአገሩ እንዲያውም ለተለያዩ ክለቦች ተሠልፎ በመጫወት ጥሩ ጊዜ አሳልፏል፡፡ ማራዶና በናፖሊ፣ በባርሴሎና፣ ሲቪያና ቦካ ጁኔርስ ክለቦች መጫወት ችሏል፡፡ ለአገሩ አርጀንቲና በተሠለፈበት 91 ውድድሮች 34 ጎሎችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል፡፡
እ.ኤ.አ. 1994 ለአርጀንቲና በዓለም ዋንጫ ላይ ከተሳተፈ በኋላ በደሙ ውስጥ የተገኘው አበረታች ንጥረ ነገር ምክንያት ከውድድር ታግዶ ነበር፡፡ በግል አሠልጣኙ የሚያነቃቃ መጠጥ እንጂ ኃይል የሚሰጥ መጠጥ እንዳልጠጣ ቢከራከርም የእግር ኳስ ሕይወቱ ማብቂያ ጊዜው ሆነ፡፡ ማራዶና አርጀንቲናን ጨምሮ በርካታ የእግር ኳስ ቡድኖችን ማሠልጠን ቢችልም ስኬታማ ግን መሆን አልቻለም፡፡
ይልቁንም በሚያሳያቸው አዳዲስ ባህሪዎቹ በየመዲናው መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ ሕልፈቱን ተከትሎ በርካታ ታዋቂ ሰዎች ሐዘናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩም ወዳጆቹም አስከሬኑን እየተሰናበቱ ይገኛሉ፡፡ ስታዲዮሞችን ጨምሮ አየር ማረፊያ ሥፍራዎች ከወዲህ በዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ስም እንዲሰየሙ ተደርገዋል፡፡ እሱ ለብሶት የደመቀበትን 10 ቁጥር ማሊያም የእሱ ብቻ ሆኖ እንዲቀርና ሌላ ተጫዋች እንዳይለብሰው ይደረግ የሚል ሐሳብም እየቀረበ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያውያን እግር ኳስ አፍቃሪዎች ዘንድም ተወዳጅ መሆኑን ከሚያሳዩ አገላለጾች መካከል ‹‹በሸዋ ላይ ደሴ ታቹን በቦረና፣ ናና ማራዶና›› እያሉ አራዶች ያቀነቀኑት ይጠቀሳል፡፡ በሕይወት የሌለው ደምሴ ዳምጤ፣ ‹‹የምን ማራዶና የምን ፔሌ ፔሌ እኛም አገር አለ ገብረ መድኅን ኃይሌ›› ብሎ በንፅፅር ማቅረቡም አይዘነጋም፡፡