በመጪው ሐምሌ በሚከናወነው የቶኪዮ ኦሊምፒክ እየተዘጋጀ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ የደቡብ ክልል አምስት ሚሊዮን ብር አበረከተ፡፡ የገንዘብ ድጋፉ የተገኘው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ብሔራዊ የዝግጅት ኮሚቴ የቶኪዮ 2020 ዝግጅት እንዲሁም በዚህ ወር መጨረሻ በአዲስ አበባ ስለሚካሄደው የአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር (አኖካ) ጠቅላላ ጉባዔን አስመልክቶ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት ነው፡፡
ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና ስፖርት ኮሚሽን እንዲሁም የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ዝግጅት ኮሚቴ ባለፈው እሑድ በሐዋሳ ከተማ በመገኘት ከክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይረዳው ጋር ተወያይቷል፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) እና የስፖርት ኮሚሽነር አቶ ኤልያስ ሽኩር፣ የቶኪዮ 2020 ዝግጅት ያለበት ደረጃ እንዲሁም ኅዳር 27 ቀን 2013 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የሚካሄደው የአኖካ ጉባዔን አስመልክቶ የተከናወኑ ሥራዎችን ለምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ አድርገዋል፡፡ ገለጻውን ያዳመጡት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚያደርጉ፣ የመጀመርያ ያሉትን አምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸው በመግለጫው ተካቷል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን የልኡካን ቡድኑ በሚቀጥለው ዓመት የሚካሄደውን የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክን እንዲያስተናግድ ዕድሉን ካገኘው የሲዳማ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር ስለዝግጅቱ ውይይት ማድረጉን በመግለጫው ተካቷል፡፡