ሎዛ አበራ የዓለማችን 100 ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ውስጥ ተካተተች
ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ የሴቶች የዓለም ዋንጫን እንድትመራ ተመረጠች፡፡
እ.ኤ.አ. በ2023 በአውስትራሊያና ኒውዝላንድ የሚከናወነውን የሴቶች ዓለም ዋንጫን እንዲመሩ ፊፋ የስም ዝርዝራቸውን ይፋ ካደረጋቸው 19 የአፍሪካ ዳኞች መካከል ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ተካታለች፡፡
ዓርብ ኅዳር 11 ቀን 2013 ዓ.ም. የዳኞችን ስም ዝርዝር ይፋ ያደረገው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ)፣ ከ15 አባል አገሮቹ መመረጣቸውን አስታውሷል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ስምንት ዋና ዳኞችና 11 ረዳት ዳኞች ከአጠቃላይ 156 ኢንተርናሽናል ዳኞች ውስጥ መመረጣቸውን ካፍ አሳውቋል፡፡ ኢትዮጵያዊቷ ዳኛ ሊዲያ ውድድሩን በዋና ዳኝነት ለመምራት ከተመረጡት አንዷ ሆናለች፡፡
በአገር ውስጥ ውድድሮች ዳኝነትን የጀመረችው ሊዲያ፣ የሴቶች አፍሪካ ዋንጫን ጨምሮ በርካታ ውድድሮች መምራት ችላለች፡፡
እ.ኤ.አ. በ2019 ፈረንሣይ ባዘጋጀችው የሴቶች ዓለም ዋንጫ ዳኝነቱን በብቃት መወጣቷ አይዘነጋም፡፡
ለመጀመርያ ጊዜ ለስድስት አኅጉሮች 32 ቡድኖች የሚሳተፉበት የ2023 ዓለም ዋንጫ ከሐምሌ 3 እስከ ነሐሴ 14 ቀን እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡
በሌላ ዜና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አጥቂዋ ሎዛ አበራ ቢቢሲ ባወጣው የዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ስም ዝርዝር ውስጥ አካቷታል፡፡
ኅዳር 14 ቀን የዓለማችን 100 ሴት ተፅዕኖ ፈጣሪ ስም ዝርዝር ይፋ ያደረገው ቢቢሲ ዘንድሮ ስማቸው በቀዳሚነት ሲነሳ ከነበሩትና ለውጥ ማምጣት ከቻሉት መካከል ሎዛ እንዳለችበት ዘግቧል፡፡
ሎዛ የቀድሞ የሐዋሳ ከተማ፣ ደደቢት፣ አዳማ ከተማ፣ እንዲሁም በማልታ የሴቶች ሊግ የቢሪኪሪካራ እግር ኳስ ክለቦች ውጤታማ ጊዜን ማሳለፏ ይታወሳል፡፡ በማልታ ሊግም ስኬታማ ጊዜን ከማሳለፏም ባሻገር የዓመቱ ምርጥ ተጫዋችና ኮከብ ግብ አግቢ ሽልማትን አግኝታለች፡፡
በቅርቡም የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ለሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እግር ኳስ ክለብ በከፍተኛ ክፍያ ፊርማዋን አኑራለች፡፡ ከአራት ዓመት በፊት ኤውብ የተባለ አገር በቀል ተቋም በኢትዮጵያ ሴት ተፅዕኖ ፈጣሪ ብሎ ከሰየማቸው ሎዛን አንዷ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል፡፡