መንግሥት በትግራይ ክልል እየወሰደ ባለው ‹‹ሕግ የማስከበር ዕርምጃ››፣ በተለያዩ መንገዶች እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ 167 ግለሰቦች ላይ በፌዴራል ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ መውጣቱን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታወቀ፡፡
ዋና ዓቃቤ ሕግ ጌዴዎን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ቃል አቀባይ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳስታወቁት፣ በክልሉ የሚገኘውን የሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የተሰነዘሩ የሮኬት ጥቃቶችን ጨምሮ የተለያዩ ወንጀሎችን ፈጽመዋል በማለት ነው በእነዚህ ተጠርጣሪዎች ላይ የእስር ማዘዣ የወጣባቸው፡፡
እንደ ጌዴዎን (ዶ/ር) ገለጻ፣ ተፈጸሙ የተባሉት ወንጀሎች የአገር ክህደት፣ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸም፣ በትጥቅ የሚፈጸም አመፅ፣ በአገሪቱ ፖለቲካዊ አንድነት ላይ የተፈጸመ ጥቃት፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ ማመፅ፣ በጎንደርና ባህር ዳር ሮኬት በመተኮስ የተፈጸሙ የአሸባሪነት ተግባሮች እንዲሁም በወዳጅ አገር ላይ የተቃጣ ጥቃት የሚሉ ናቸው፡፡
ከተጠርጣሪዎቹ ውስጥ በርካቶች መያዛቸውን የተናገሩት ዋና ዓቃቤ ሕጉ፣ በብዛትም የመከላከያ ሠራዊት አባላት ናቸው ብለዋል፡፡ በተያያዘም ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉ 343 ሰዎች መካከል 116 ሰዎች በዋስትና ተለቀዋል ብለዋል፡፡