Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የገቢዎች ሚኒስቴር ፋብሪካዎችን በሩቅ እንዲከታተል የሚያስችለው መመርያ ፀደቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የገቢዎች ሚኒስቴር የኤክሳይስ ታክስ የተጣለባቸውን ምርቶች የሚያመርቱ አምራቾችን በሩቅ መቆጣጠርና መከታተል የሚያስችለው ቴክኖሎጂ፣ በአምራቾች እንዲገጠም የሚያስገድድ መመርያ ፀደቀ፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር የወጣው ይኼ መመርያ ‹‹የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ የአፈጻጸም መመርያ›› የሚሰኝ ሲሆን፣ በአንቀጽ 13 ሥር ‹‹የተፈቀደለት አምራች በፋብሪካው ውስጥ የሚከናወነውን እንቅስቃሴ በሩቅ ማየት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ሥርዓት መግጠም አለበት፤›› በሚል የሚደነግግ ሲሆን፣ የታክስ ባለሥልጣን ይኼንን ቴክኖሎጂ የመጠቀም ያልተገደበ መብት እንደሚኖረው በመመርያው ተደንግጓል፡፡

‹‹የታክስ ባለሥልጣን በዚህ መመርያ መሠረት ሊገጠም የሚገባውን የቴክኖሎጂ መሣሪያ ዝርዝር ባህርያ ይወስናል፤›› በሚል ድንጋጌ በተመሳሳይ አንቀጽ ሥር የያዘው መመርያው፣ ይኼ የቴክኖሎጂ ሥርዓትም የታክስ ባለሥልጣኑ (የገቢዎች ሚኒስቴር አልያም የክልል የታክስ ባለሥልጣናት) በሚጠይቀው መሠረት ደኅንነቱ የተጠበቀ የምሥል ማከማቻና ማስተላለፍ ሌላን መረጃ በዲጂታል ሥርዓት በቀጥታ ማስተላለፍ የሚችል መሆን እንደሚኖርበትም ተመላክቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከታክስ ነፃ የሆኑ፣ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡና ሌሎች የኤክሳይስ ታክስ የሚከፈልባቸው ዕቃዎች ማሸጊያዎች ለመከታተልና ለይቶ ለማወቅ በሚያስችል አኳኋን የተለየ ምልክት ሊደረግባቸው እንደሚገባ በማስገደድም፣ ለጅምላ ሽያጭ የሚውል ዕቃም ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ከሆነ የመዳረሻ አድራሻ፣ በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ የሚውል ከሆነ ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል እንደሆነ ማመላከቻ፣ እንዲሁም ከታክስ ነፃ የሆኑ ዕቃዎች ለሚሸጡበት መደብር አልያም ለዲፕሎማቲክ ሱቆች የሚቀርብ ከሆነ ከታክስ ነፃ የሚል ጥቆማ ሊደረግበት እንደሚገባ ያስገድዳል፡፡

መመርያው አክሎም የኤክሳይስ ታክስ የሚከፈልባቸውን ዕቃዎች ለማምረት የሚውሉ ጥሬ ዕቃዎች መጠናቸውን በትክክል ለማወቅ ለሚደረግ ቁጥጥር በሚያመች አኳኋን ደኅንነቱ በተጠበቀ ክፍል ወይም መጋዘን መቀመጥ ይገባዋል በማለት፣ በተፈቀደለት ማምረቻ ውስጥ ለምርት ተግባር እንዲውሉ ለማድረግ ወይም አደጋ በማጋጠሙ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ማናቸውም ሰው በታክሱ ባለ ሥልጣን ሳይፈቀድ ጥሬ ዕቃዎችን ማውጣት አይቻልም ሲል ይከለክላል፡፡

ለውጨ ገበያ (ኤክስፖርት) የተመረቱ ዕቃዎች በኢትዮጵያ ውስጥ የተሸጡ እንደሆነ፣ አልያም ከታክስ ነፃ ሆነው ስለሚሸጡበት ወይም ታክሱ ተመላሽ ስለሚደረግበት ሁኔታ በአዋጁ የተመለከተው ያልተሟላ ከሆነ፣ የተፈቀደለት አምራች በዕቃዎች ላይ ታክሱን እንደሚከፍል ተገልጿል፡፡

በኤክሳይ ታክስ አዋጅ መሠረት የተከፈለ የኤክሳይ ታክስ ተመላሽ የሚሆነው ዕቃዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ጥቅም ላይ ከመዋላቸው በፊት በመጓጓዝ ላይ እያሉ፣ ከጥቅም ውጪ የሆኑ ወይም የተሰረቁ እንደሆነ፣ ገዥው ዕቃውን ለሻጩ በውላቸው መሠረት የመለሰ እንደሆነና፣ የኤክሳይስ ታክስ ከተከፈለ በኋላ ፈቃድ በተሰጠው ወይም በተመዘገበ አምራች ከኤክሳይስ ታክስ ነፃ የሆኑ ዕቃዎችን ለማምረት የዋሉ እንደሆነና በተመሳሳይ ምክንያቶች ነው፡፡

የኤክሳይስ ታክስ የሚከፈልበት ዕቃ ከፋብሪካ በሚወጣበት ጊዜ የሚዘጋጀው የዕቃ ማስረከቢያ ሰነድ ወይም ደረሰኝ ዕቃው ከፋብሪካ የወጣበት ቀን፣ የዕቃው ማስረከቢያ ቦታ፣ የደንበኛውን ስም ወይም ሽያጭ ከመከናወኑ በፊት፣ ከፋብሪካ የሚወጣ ከሆነ ይኼንኑ፣ ደንበኛው ከተፈቀደለት አምራች ጋር ግንኙነት ያለው ሰው ከሆነ ይኼንኑ የኤክሳይስ ታክስ የሚከፈልባቸው ዕቃዎች ዓይነት፣ የዕቃዎች ስፋት፣ የእያንዳንዱ የኤክሳይ ታክስ የሚከፈልበት ዕቃ ዋጋ እንዲሁም ሊከፈል የሚገባው የኤክሳይ ታክስ መጠን በግልጽ ሊሰፍርባቸው ይገባል ይላል መመርያው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች