አካባቢው አጠር አጠር ባሉ ዛፎች ተሞልቷል። የመሬቱ እንደ ጥጥ የነጣ አሸዋ ጫማ አንቆ እስከመያዝ ያህል ለመራመድ ያስቸግራል። ወደ ውስጥ ሲዘልቁ አካባቢውን የሸፈኑት ዛፎች ውኃ ተጠምተው የሚያውቁ አይመስሉም፡፡ ከነፋሱ ጋር ተደምረው ድምፅ ያሰማሉ፡፡ ከዘንባባ ዛፎች ጋር እየተላተመ የሚመለሰውና ለዕይታ የሚያስቸግረው ሐይቅ ደፍርሷል። ለወትሮው ተመልካች የማያጣው ሐይቁ አሁን ብቻውን ይዳክራል።
ከአዲስ አበባ 218 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የላንጋኖ ሐይቅ ከዓመታት በፊት በተለይ ቅዳሜና እሑድ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች በሚመጡ እንግዶች ይጨናነቅ ነበር፡፡ የሥፍራው ነፋሻማ አየር የእንግዶችን ስሜት አድሶ እንደሚመልስ ይነገርለትም ነበር።
ከጥቅምት 21 እስከ 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የዓለም ቱሪዝም ቀንን ምክንያት በማድረግ ባዘጋጀው ባህልን የማስተዋወቅ የዝክር ጉዞ ተገኝተን የታዘብነው ሥፍራው በጎብኚዎች እጥረት መፈተኑን ነው፡፡ በዝክር ጉዞው ላንጋኖ፣ ሻላና አብጃታ ሐይቅ፣ የባሌ ተራሮች፣ የዲንሾ ፓርክ፣ የሶፍ ሁመር ዋሻና ሳንቴ ቱሉ ዲምቱ ተራራን ቃኝተናል፡፡
ከላንጋኖ ሐይቅ የጀመረው ቅኝት ዓላማው እነዚህ የቱሪስት መዳረሻዎችን የጎብኝዎች ቁጥር ዳግም እንዲያንሰራራ ለማድረግ ነው።
ላንጋኖ ሐይቅና ሆቴል
ላንጋኖ ሐይቅ ርዝመቱ 18 ኪሎ ሜትር፣ ስፋቱ 16 ኪሎ ሜትር ጥልቀቱ 46 ሜትር አጠቃላይ ስፋቱ ደግሞ 230 ስኬር ኪሎ ሜትር ነው፡፡ የሐይቁን ዙሪያ ለግል ሆቴል ኢንቨስትመንት ከመሰጠቱ በፊት፣ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ጀምሮ ላንጋኖ ፍል ውኃ ሆቴል በሚል አገልግሎት ይሰጥ ነበር። በውስጡም ለደንበኞቹ የምግብ፣ የመጠጥ፣ የመኝታና በሐይቁ ላይ የዋና አገልግሎቶችን ሲሰጥ ቆይቷል።
ወደ ሐይቁ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ከሚመጡ ጎብኝዎች ባሻገር በርካታ የውጭ አገር ጎቢኝዎች ይተሙ እንደነበር አቶ ቱጂ ኮልቢ የላንጋኖ ፍል ውኃ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ ይናገራሉ፡፡ ከሁለት ዓመታት ወዲህ ግን በኢትዮጵያ የነበረው አለመረጋጋትና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የጎብኝውን ቁጥር አመንምኖታል።
በላንጋኖ ዙሪያ በግል ባለሀብቶች አማካይነት ከተያዙት ሪዞርቶችና ሆቴሎች ባሻገር ላንጋኖ ፍል ውኃ ሆቴል ብቻውን በዓመት ከአገር ውስጥ ከ500 በላይ እንዲሁም ከውጭ ከ100 በላይ ጎብኝዎች እንደነበሩት አቶ ቱጂ ያስታውሳሉ። በተለይ በኅዳር፣ በታኅሣሥና ጥር ወር ላይ በበርካታ የውጭ አገር ጎብኝዎች ይዘወተር ነበር።
በመንግሥት እጅ እየተዳደረ ለ35 ዓመታተ በማገልገሉ፣ መመገብያ ቤቶች፣ መኝታ ቤቶች፣ መፀዳጃ ቤቶች እንዲሁም የተለያዩ መዝናኛ ቦታዎች ነትበው ይስተዋላሉ። ለበርካታ ጊዜያት እንደሚታደስ ቃል ቢገባም፣ ሊታደስ አለመቻሉን አቶ ቱጂ ያስረዳሉ። ለላንጋኖ ተፈጥሯዊ መስህብ መንግሥት ዕድሳት ሊያደርግለት እንዲሚገባም አቶ ቱጂ ያክላሉ።
በላንጋኖ ዙሪያ ለግለሰቦች የተከራዩ 60 ቤቶች ሲኖሩ ስድስቱ በግል ሆቴሎች ሥራ ዘርፍ አገልግልት ይሰጣሉ። ከእነዚህም ሆቴሎች ሁለቱ ብቻ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን፣ በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ምክንያት በተከሰተው ሁከት አፍሪካ ቫኬሽን ቃጠሎ ደርሶበታል።
አብጃታ ሻላ ፓርክና ሐይቅ
የአብጃታ ሻላ ሐይቅንና የጨቱን ሐይቆች ጨምሮ 887 ስኩዌር ኪሎ ሜትር መሬትን የሚሸፍነው ፓርክ ‹‹ሆራ ቀሎ›› በመባል ይታወቃል፡፡ ከዚህ ውስጥ 482 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሆነው በውኃ የተሸፈነ ነው፡፡ ፓርኩ በዋነኝነት የሚታወቀው በአዕዋፋት ነው፡፡ በርካታ ዝርያ ያላቸው አዕዋፋትና አጥቢ እንስሳትም ይገኙበታል፡፡ በፓርኩና በሐይቁ ዙሪያ 453 የአዕዋፍ ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል 108 የሚሆኑት ከአውሮፓ፣ ከእስያና ከአፍሪካ ይተማሉ፡፡ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኘው ይህ የተፈጥሮ መስህብ ከጊዜ በኋላ የውኃ ዕጦት ገጥሞታል፡፡ ከፊል ሥፍራውም ደረቅ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በዓምናው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት በተወሰነ ደረጃ በውኃ እንደተሞላ የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ፡፡
ፓርኩ በየዓመቱ ከአገር ወስጥ እንዲሁም ከአገር ውጭ የሚተሙ ጎብኝዎችን እንደሚያስተናግድ በምዕራብ አርሲ ዞን ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ልማት ባለሙያ አቶ አወል ሁሴን ለሪፖርተር አስረደተዋል፡፡
በአንፃሩ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ የነበረው አለመረጋጋትና በተለይ በዞኑ የከፋው ሁከት የጎብኝውን ቁጥር እንደቀነሰው አቶ አወል ይናገራሉ፡፡ በተፈጥሮ መስህብ የታደለው አብጃታ ሻላ ሐይቅ ምንም እንኳን እንደ ቱሪስት መዳረሻ ተደርጎ ቢወሰድም አመቺ መንገድ ማጣት፣ ለጎብኝዎች ማረፊያ ሆቴሎች አለመኖርና በፓርኩ ውስጥ ኑሯቸውን ያደረጉ የአካባቢው ነዋሪዎች መገኘት ከፓርኩ ጋር አብሮ የዘለቀና መፍትሔ የታጣለት ችግር ሆኖ መቆየቱን አቶ አወል ይጠቁማሉ፡፡
ከእዚህም ባሻገር ከፓርኩ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው የሶዳ-አሽ ፋብሪካ ለፋብሪካው ግብዓት የሚሆነውን ውኃ ከሐይቁ መጠቀም መጀመሩ ፓርኩ ላይ ከፍተኛ ችግር መፍጠሩንም ያክላሉ፡፡ ‹‹በተለያዩ ጊዜያት ፋብሪካው ውኃውን እንዳይጠቀም ለማድረግ ሞክረናል፡፡ ፓርኩ በውኃ፣ በድርቅ በተመታበት ወቅት እንዳይጠቀሙ ማድረግ ብንችልም፣ ዳግም የውኃው መጠን ሲያንሰራራ ውኃውን መጠቀማቸውን ቀጥለዋልም፤›› ይላሉ፡፡
የፋብሪካውን የውኃ ችግር ለመፍታት እየተሞከረ እንደሆነ በመጠቆም በፓርኩ ውስጥ ኑሯቸውን ላደረጉት ግን መልስ የታጣለት እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡
ቱሪዝም በበዓላት እንቅስቃሴ ብቻ የተገደበ ነው ከሚለው የጋራ ግንዛቤ ባሻገር፣ ሰዎች ከተለመደው አካባቢያቸው ውጭ ባሉ ቦታዎች ለመጓዝና ለመቆየት ከአንድ ተከታታይ ዓመት በላይ ለመዝናናትና ከ24 ሰዓታት ባላነሰ፣ ለቢዝነስ እንዲሁም ለሌሎች ዓላማዎች የሚያሳልፉት ጊዜ ነው።›› በማለት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ትርጓሜውን ያስቀምጣል።
በዓለም ላይ ያሉ ሁሉም አገሮች ሰው ሠራሽ የሆኑ ወይም ተፈጥሮ የለገሰቻቸው የተለያዩ መስህቦች አላቸው። ተፈጥሮ ያላደለቻቸው አገሮች ደግሞ የሰውን ልጅ አዕምሮ መግዛትና መንፈስ ማደስ የሚችል የቱሪስት መዳረሻ በረብጣ ዶላሮች ለመገንባት ሲዳክሩ ይስተዋላል።
እ.ኤ.አ. በ2010 በተደረገ ጥናት በዓለም ላይ ከ952 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ጎብኝዎች የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎችን መጎብኘት የቻሉ ሲሆን፣ ይኼም ቁጥር ዓምና 996 ሚሊዮን መድረሱን መረጃዎች ያስቀምጣሉ፡፡
በአንፃሩ ኢትዮጵያም በየዓመቱ ከተለያዩ ዓለም አገሮች የሚተሙ ጎብኝዎች ቢኖራትም አስፈላጊውን የመሠረተ ልማትና ማረፊያ ሆቴሎች አለመሟላቱ ‹‹በእጅ የያዙት ወርቅ›› ሆኖባታል ሲሉ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ይሰነዝራሉ፡፡