Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከሕወሓት ጋር ለውይይት መቀመጥ የሚቻለው የዘመቻው ግቦች ሲሳኩ ብቻ መሆኑ ተገለጸ

ከሕወሓት ጋር ለውይይት መቀመጥ የሚቻለው የዘመቻው ግቦች ሲሳኩ ብቻ መሆኑ ተገለጸ

ቀን:

የሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ ማክሰኞ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጥቃት በፈጸሙት የትግራይ ልዩ ኃይልና የሕወሓት አመራሮች ላይ ዕርምጃ እንዲወሰድ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት፣ እየተካሄደ ያለው ዘመቻ ሲጠናቀቅ ብቻ ስለድርድር እንደሚታሰብ መንግሥት አስታወቀ ፡ ፡

በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለውን ዘመቻ በተመለከተ ማክሰኞ ኅዳር 1 ቀን 2013 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መግለጫ የሰጡት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ሴክሬታሪያት ኃላፊ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር)፣ በትግራይ የታለፈውን ‹‹ቀይ መስመር›› ተከትሎ እየተወሰደ ባለው ዕርምጃ የውይይት በር ሙሉ ለሙሉ የተዘጋ ባይሆንም፣ ይኼ የሚሆነው ግን የሚወሰደው ዘመቻ ግቦቹን ከመታ በኋላ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዘመቻው በሕወሓት እጅ የወደቁና እስከ 700 ኪሎ ሜትር ሊወነጨፉ ይችላሉ ተብሎላቸው የነበሩ መሣሪያዎችን ከጥቅም ውጪ ማድረግ ወይም ማውደምና ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት የፈጸሙትን ኃይሎች ለፍትሕ ማቅረብ የሚሉ ግልጽ ዓላማዎች አሉት  ያሉት ሬድዋን (አምባሳደር)፣ በሕወሓት እጅ ያለው ሚሳይል ባህር ዳርን፣ ወይም አስመራን ለማጥቃትና በዚህም የውጭ አካላት ወደ ግጭቱ ገብተው ወደ ቀጣናዊነት እንዲቀየር የማድረግ ፍላጎቶች ነበሩ ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን  ሬድዋን (አምባሳደር) ሕወሓት 700 ኪሎ ሜትር መወንጨፍ የሚችል ሚሳይል አለኝ ማለቱን በመግለጽ ይኼንን ማውደም እንደሚገባ ያሳሰቡ ቢሆንም፣ ይኼንን ያህል መጓዝ የሚችል መሣሪያ አገሪቱ እንደሌላትና ሕወሓት ታጥቆትም ከሆነ ሌላ የውጭ ኃይል አስታጥቆት ስለሚሆን፣ ይኼ በራሱ የአገር ክህደት ወንጀል ነው ሲሉ አስምረዋል፡፡ ይሁንና እስከ 300 ኪሎ ምትር መወንጨፍ የሚችሉ የመከላከያ ሠራዊት ሚሳይሎች ያሉባቸው ቀጣናዎችን ማጥቃትና መሣሪያዎቹም ከጥቅም ውጪ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

‹‹መቀሌን ሳይቀር አጥቅተው መንግሥት አደረገው ብለው ሊከስሱ ይችላሉ፤›› ያሉት ሬድዋን (አምባሳደር)፣ ግጭቱ ወደ ቀጣናዊ ችግር ሊሰፋ ይችላል የሚል ሥጋት ግን እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

በግጭቱ የተከሰቱ ጉዳቶችን በዝርዝር ባይገልጹም በመጀመርያው ቀን ጥቃት፣ በተኩስ ልውውጥና በተደረጉ የተለያዩ ሥፍራዎች ውጊያዎች የደረሱ ሰብዓዊና ሌሎች ጉዳቶች መኖራቸው አይካድም ሲሉ የገለጹት ሬድዋን (አምባሳደር)፣ ከሕወሓት ወገንም ቢሆን ከባድ ጉዳት ደርሷል ብለዋል፡፡ ይኼ እጅግ የሚሳዝን እንደሆነና እየተጎዱ ያሉት እጅግ ልጆች የሆኑ ወታደሮች ናቸው ያሉት አምባሳደሩ፣ ኃላፊነት የሚሰማው ቤተሰብ እነዚህን ልጆች ለውጊያ ይቅርና የጦርነት ፊልም እንዳይመለከቱም ይከለክላቸዋል ብለዋል፡፡

‹‹ሕወሓት እኔ ካልመራሁ አይሆንም በማለት ከእኛ እንደ አንዱ ሆኖ በእኩልነት ለመቀጠል ባለመፈለጉ የፈጠረው ችግር ነው፤›› ብለው፣ ባለፉት ሁለት ዓመት ከግማሽ የተደረጉ የሰላም ሙከራዎችን ሙሉ ለሙሉ ወደ ጎን በማለት ቆይቷል ሲሉም አክለዋል፡፡ አሁን ግን የአገሪቱን ህልውና ሥጋት ላይ የሚጥል የተደራጀ ኃይል በመሆኑ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አገሪቱን እየታደጓት እንደሆነና ይኼም እሳቸው ከተሸለሙት የሰላም የኖቤል ሽልማት ጋር የሚጣጣም ዕርምጃ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

አምባሳደሩ አክለውም ማክሰኞ ዕለት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጥቃቱ ከመፈጸሙ አንድ ቀን አስቀድሞ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ጋር በስልክ መገናኘታቸውንና አዲሱን ብርም እንደሚልኩ ተወያይተው እንደነበር በማስታወስ፣ ከዚህ ውይይት በኋላ ባልታሰበ ጊዜና ሁኔታ የሰሜን ዕዝ በተለያዩ ግንባሮች ጥቃት እንደተፈጸመበት ገልጸዋል፡፡ በመቀሌ ያለው የሰሜን ዕዝ ማዕከል ተዋጊዎችን ያልያዘ በመሆኑ በቀላሉ ሊቆጣጠሩት እንደቻሉ፣ ነገር ግን በተለያዩ ሥፍራዎች ያሉ ግንባሮች ላይ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ተደርጎ የመከላከያ ሠራዊት አባላት አምልጠው ወደ ኤርትራ ድንበርና ወደ ሌሎች አካባቢዎች መሄዳቸውን አውስተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...