Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሻሸመኔ ከተማ በደረሰ ጉዳት ከ37 ሚሊዮን ብር በላይ የገቢ ግብር መታጣቱ ተገለጸ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ሳቢያ በሻሸመኔ ከተማ በደረሰ ጉዳት፣ ከሆቴሎች መገኘት የነበረበት 37 ሚሊዮን ብር በላይ የገቢ ግብር መታጣቱ ተገለጸ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በከተማዋ በንግድና በሆቴል ዘርፍ ላይ ተሰማርተው ከሚገኙ ተቋማት ማግኘት የሚገባውን የሐምሌ ወር የገቢ ግብር ማጣቱን፣ የሻሸመኔ ከተማ አስተደደር ከንቲባ አቶ ጉታ ላታሮ ለሪፖረተር አስረድተዋል፡፡

በከተማዋ በሁከቱ ምክንያት በርካታ መኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ ተቋማትና ከ15 በላይ ትልልቅ ሆቴሎች ላይ ቃጠሎ እንደ ደረሰባቸው የገለጹት ከንቲባው፣ ሁከቱ  በከተማው ገቢ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ማድረሱን ጠቁመዋል፡፡

በከተማዋ ባጋጠመው ውድመት መኖሪያ ቤታቸውን አጥተው በቤተ ክርስቲያንና በመስጊድ የተጠለሉ ነዋሪዎች፣ በመካከለኛና በጥቃቅን ንግድ ላይ የተሰማሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ እንዲሁም በሆቴል ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ተጎጂዎች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡

ጉዳቱ እንደ ደረሰ ነዋሪዎች ገሚሶቹ ከተማዋን ለቀው ሲወጡ፣ የተቀሩት በቤተ እምነቶች ተጠልለው መቆየታቸውን የከተማዋ ከንቲባ አቶ ጉታ አስታውሰዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥም ከተማዋን ወደ ቀደሞ ይዞታዋ ለመመለስ 17 መኖሪያ ቤቶች ዳግም ተገንብተው ቤታቸው ለወደመባቸው ነዋሪዎች የተመለሱ መሆኑን፣ በከፊል ጉዳት የደረሰባቸው ማለትም መስኮትና በር የተሰበረባቸው፣ ዝርፊያ የተፈጸመባቸውና ከፊል ቃጠሎ የደረሰባቸው ቤቶች በከተማዋ ነዋሪ በተሰበሰበ ገንዘብ መታደሳቸውን አቶ ጉታ አስረድተዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በመካከለኛና በጥቃቅን ንግድ ላይ የተሰማሩ ባለንብረቶች በከፊል ወደ ሥራ እንደተመለሱ የገለጹት ከንቲባው፣ የሆቴል ባለንብረቶችን ችግር ለመፍታት ግን ከከተማው አስተዳደር አቅም በላይ መሆኑን አልሸሸጉም፡፡ ሙሉ በመሉና በከፊል ውድመት የደረሰባቸውን ዳግም ወደ ሥራ ለመመለስ የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ  እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ምንም እንኳን የከተማ አስተዳደሩ ከሆቴል ባለቤቶቹ ጋር በውይይት ላይ እንዳለ ቢገለጽም፣ የድምፃዊውን ግድያን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በተከሰተው አለመረጋጋት ለወደሙ ንብረቶችና ኢንቨስትመንቶች የሚከፈል ካሳ አለመኖሩን የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

በወቅቱ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች 89 ኢንቨስትመንት ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል መውደማቸው ተነግሯል፡፡

በሌላ በኩል ሻሸመኔ ከተማ አሁን ወደ ቀድሞ ሰላሟ መመለስ መቻሏንና በአገር ሽማግሌዎች፣ በአባ ገዳዎች፣ በወጣቶች፣ እንዲሁም በእምነት አባቶች አማካይነት ውይይት መደረጉንና ወደፊት ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይከሰቱ ከከተማው ማኅበረሰብ ጋር በጋራ እየተሠራ መሆኑን ከንቲባው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች