Thursday, June 1, 2023

የጉራፈርዳው ጥቃት የፈጠረው ሰቆቃ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን በአገሪቱ ከምዕራብ ወለጋ እስከ ጉጂ፣ ከምሥራቅ ሐረርጌ እስከ ምዕራብ ሐረርጌና ምሥራቅ አርሲ፣ ከአፋር እስከ ሶማሌ፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ከማሽና መተከል ዞኖች እስከ ደቡብ ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ድረስ የንፁኃን ዜጎች ሕይወት ሲቀጠፍ መስማት የተለመደ ክስተት ሆኗል፡፡ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በሳምንታት ልዩነት በተፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ቁጥራቸው በግልጽ የማይታወቁ ዜጎች ሕይወት ማለፉ የሚታወስ ሲሆን፣ ከእነዚህ ጥቃቶች በአንዱ ብቻ 20 ገደማ ሰዎች መገደላቸው ይታወቃል፡፡ በእነዚህ ጥቃቶች ሳቢያ ሲፈስ የቆየው እንባ ሳይታበስ፣ በደቡብ ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ የ31 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ጥቃት ተፈጽሟል፡፡

ይኼ የጉራፈርዳ ጥቃት በሦስት ቀበሌዎች የተፈጸመ ሲሆን፣ ከ13 በላይ ሰዎች ከባድ አደጋ እንዲደርስባቸው፣ አምስት ሺሕ ገደማ ሰዎች እንዲፈናቀሉ፣ በቁጥር ያልታወቁ መኖሪያ ቤቶች እዲቃጠሉ፣ እንዲሁም በጎተራ የሞላ እህል ዶግ አመድ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል፡፡ በዚህ አካባቢ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በሚዛን አማን ከተማ፣ በጋምቤላ ክልል ሜጢ አካባቢ፣ እንዲሁም በጉራፈርዳ ወረዳ ቢፍቱ ቀበሌ በትምህርት ቤቶች፣ በተለያዩ የቤተሰብና የጎረቤት ቤቶች ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡

እነዚህ የተፈናቀሉ ሰዎችን ለመደገፍ የአካባቢው ኅብረተሰብ ገንዘብ፣ አልባሳትና ምግብ በማሰባሰብ 600 ሺሕ ብር ገደማ የሚገመት ድጋፍ ያደረገላቸው ሲሆን፣ መንግሥት በበኩሉ የሚፈጠሩትን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ያስችለኛል ያለውን ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ የተዘረጋ ቡድን አቋቁሞ እየሠራ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ ለዚህ ኮሚቴ መቋቋም ምክንያት የሆነው ጥቅምት 8 ቀን 2013 ዓ.ም. እና ጥቅምት 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ሹጊና ቤኒካ በተባሉ የወረዳው ቀበሌዎች የተፈጸሙ ጥቃቶችን ተከትሎ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬ ዓለም ሽባባው፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሐመድ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳውና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው ጣሰው በሥፍራው ያደረጉት ጉብኝት ነው፡፡

ጥቅምት 8 ቀን 2013 ዓ.ም. በሹጊ በተፈጸመው ጥቃት 13 ሰዎች ተገድለው ያደሩ ሲሆን፣ ጥቃቱ በሒደት ወጀምታና ቢኒካ ወደ ተባሉ ሥፍራዎች ከሁለት ቀናት በኋላ ተዳርሷል፡፡

በወጀምታ ቀበሌ ነዋሪ የነበሩትና አሁን በተፈጸመው ጥቃት ተሰድደው፣ በዚያው የጉራፈርዳ ወረዳ ቢፍቱ ቀበሌ ውስጥ በሚገኝ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጠልለው የሚገኙት አቶ አሰፋ መኳንንት ክስተቱን ያስታውሱታል፡፡ እሑድ ጥቅምት 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ለሰኞ አጥቢያ በተፈጸመ ጥቃት ሥጋት ከአካባቢው ሸሽተው ለመውጣት በመሰናዳት ላይ ሳሉ፣ ማክሰኞ ጥቅምት 10 ቀን 2013 ዓ.ም. የአካባቢው ማኅበረሰብ ከዞኑ የፖሊስ ኮሚሽንና አመራሮች ጋር ባደረገው ውይይት ሰላም ይመለስላችኋልና አትሄዱም ተብለው እንዲቀሩ መደረጉን ያወሳሉ፡፡

‹‹ሁለተኛው ጥቃት የተፈጸመው ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ነው፡፡ ማክሰኞ ሹጊ የሞቱትን ስንቀብር ትንሽ ግር ግር ተፈጥሮ ነበር፡፡ ይሁንና ተረጋግቶ ሳለ ወጀምታ አካባቢ ሸሽተው ተጠልለው ካሉት ጋር ከዞኑ የፀጥታ ኃላፊና ሌሎች ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ተደርጎ ዋስትና እንሰጣችኋለን ተመለሱ ብለውን ተመልሰን ሳለን ነው ማታ ይኼ ጥቃት የተፈጸመው፡፡ ቀን ተሰብስበን ማታ ሞትን፤›› በማለት ይገራሉ፡፡

አጥቂዎቹ በመሣሪያ፣ በጦርና በገጀራ (ቆንጨራ) የታጠቁ ሲሆን፣ በስለት የታረዱና የተከተከቱ እንዳሉም አቶ አሰፋ ተናግረዋል፡፡ የጦር መሣሪያዎችም ከነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች ከፍ ያሉ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሲተኮሱ በሚያወጡት ድምፅ ግምት ሰጥተዋል፡፡

‹‹የእኔ ቤተሰብ በመደበቃችን ተርፈናል፡፡ ነገር ግን ከጎረቤቶቼ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ አሉ፡፡ ከስድስት ቤተሰብ ሁለት ሰዎች ብቻ የተረፉላቸው አሉ፡፡ አንዱ እንዲውም የአዕምሮ ሕመምተኛ ነው፤›› በማለት በሐዘን ያስታውሳሉ፡፡

እሳቸው በአካባቢው ለ22 ዓመታት የኖሩ መሆናቸውን ወደ አካባቢው የመጡት ከደቡብ ጎንደር ስማዳ አካባቢ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በሥፍራው በእርሻ ሥራ የሚተዳደሩት አቶ አሰፋ አሁን ቤታቸውን፣ 20 ሔክታር ቡና፣ እንዲሁም የተለያዩ ሰብሎችን ጥለው እንደተሰደዱ ያስረዳሉ፡፡ ከእርሳቸው ሰብሎች በተጨማሪም በወጣቶች ማኅበር የተመረተ 600 ኩንታል ሩዝ በእሳት መቃጠሉንና የብዙኃኑም እርሻ በእሳት መውደሙን ያወሳሉ፡፡

በተመሳሳይ ለስድስት ሰዓታት ያህል በጫካ ተጉዘው ቢፍቱ ትምህርት ቤት ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙና ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ቀዬአቸውን ትተው እንደ ነጎዱ የሚናገሩት አቶ ደሳለኝ ተሾመ፣ የመጀመርያውን የጥቅምት 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ጥቃት ተከትሎ በነበረው የኅብረተሰቡና የፀጥታ አካላት ስብሰባ እንኳን ጥይት የርችት ድምፅ አትሰሙም ተብለው እንደነበር በማለት ያስታውሳሉ፡፡

‹‹የነበረውን ሁኔታ በመገንዘብ የሥጋት ሪፖርት በተደጋጋሚ እናቀርብ ነበር፡፡ ይሁንና ሰሚ ጆሮ አላገኘንም፡፡ ተጠርጣሪዎች ቢያዙም ምስክር የለም በሚል ምክንያት በቂ ምርመራ እንኳን ሳይደረግባቸው ይለቀቃሉ፡፡ ይኼው አሁን ድረስ ቤቶችና እርሻዎች እየተቃጠሉ ነው ያሉት አልቆመም፤›› በማለት ከሪፖርተር ጋር ረቡዕ ጥቅምት 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ባደረጉት ቆይታ አስረድተዋል፡፡

አሁን ባሉበት መጠለያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉና ለመጠለያ የሚሆን ክፍል ስለሌለ፣ በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙና እስካሁን ዝናብ ስላልዘነበ እንጂ ቢዘንብ ደግሞ የባሰ ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ ይሁንና ለእነሱ የአልባሳት፣ የምግብና የተለያዩ ድጋፎችን ከማድረግ ባለፈ ሊያጓጉዟቸው ለቻሏቸው ከብቶች መኖ የሚሆን ሳር ሁሉ እያቀረበላቸው ላለው ኅብረተሰብ ምሥጋናቸውን ያቀርባሉ፡፡

‹‹በቅርብ ያሉት ከብቶቻቸውን እየነዱ መምጣት ችለዋል፡፡ ማምጣት ያልቻልናቸው በርካቶች ሲሆኑ፣ መንገድ ላይ የቀሩም በርካታ የቤት እንስሳት አሉ፡፡ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ከብቶቻችንን የምናደርግበት ቦታ ስለሌለ ካሁን ቀደም 15,000 ብር ይሸጥ የነበረው ከብት አሁን በ2,000 ብር እየተሸጠ ነው ያለው፡፡ እህልና ንብረታችንን እንዲሁም አልባሳት ትተን ነው የመጣነው፤›› ይላሉ፡፡

ለመንግሥት የደረሰውን አዝመራ ማውጣት እንዲችሉ መኪና ራሳችን እናቅርብና ጥበቃ ተደርጎልን እንሰብስብ፣ የተሰበሰበውንም እናስጭን ቢሉም ፈቃድ ማግኘት ባለመቻላቸው ምክንያት እንደ ተቃጠለባቸው ገልጸው፣ በዚህ ሳቢያ ከባድ ኪሳራ እንደ ደረሰባቸው ይናገራሉ፡፡

‹‹መቼ እንደምንመለስ እርግጠኞች አይደለንም፡፡ ምኑን አውቀንስ እንመለሳለን?›› ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

ከቤኒቃ ቀበሌ በተመሳሳይ ምክንያት የተሰደዱት አቶ ክንዱ ጫኔ የተባሉ ግለሰብ በበኩላቸው በጥቃቱ ሳቢያ እናታቸውን፣ አባታቸውን፣ ሴት አያታቸውን፣ እንዲሁም አንዲት የ13 ዓመት እህታቸውን እንዳጡ ተናግረዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸው በሥፍራው ለ36 ዓመታት የኖሩ እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ ክንዱ እሳቸው ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት እንደሆኑና በሌላ ቀበሌ እንደሚኖሩ የገለጹ ሲሆን፣ የቤተሰቦቻቸውን መገደል ሲሰሙ ልባቸው ተሰብሮ ሳለ እሳቸውም ለስደት መዳረጋቸውን ይናገራሉ፡፡ እሳቸው ከእነ ቤተሰባቸው ፖሊስ ጣቢያ ባይጠለሉ ይተርፉ እንዳልነበረም ያምናሉ፡፡

‹‹ምሽት ሁለት ሰዓት ላይ ነው ቤታቸው ሄደው ያፈኗቸው፡፡ አባቴን በጥይት ሲሆን የገደሉት ሲሆን ሌሎቹ በስለት ነው የተገደሉት፡፡ በቀበሌያቸው እንኳን መቀበር ስላልቻሉ ቢፍቱ መጥተው ነው የተቀበሩት፡፡ አባቴ ደግሞ መገንጠያ ተብሎ የሚጠራው ቦታ አካባቢ ቤተሰብ ስለነበረው እዚያ ሄዶ ነው የተቀበረው፤›› ብለዋል፡፡

በአካባቢው ያሉ ሰዎች ትጥቅ መያዝ እንዳልተፈቀደላቸውና በ2001 ዓ.ም. ያሏቸውን መሣሪያዎች በሙሉ እንዲፈቱ መደረጋቸውን ገልጸው፣ መሣሪያ ያልነበራቸው ሳይቀሩ ደብቃችኋል ተብለው ሲገረፉ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ አሰፋ፣ ‹‹እኔ መሣሪያ አልነበረኝም ግን ከተገረፉት ውስጥ አንዱ ነኝ፤›› ይላሉ፡፡ በወቅቱ ከአካባቢው ነዋሪዎች 800 መሣሪያዎች ተሰብስበው እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡

‹‹መሣሪያ ቢኖረን ኖሮ ቢያንስ እንደ ርችት አጩኸን የፀጥታ ኃይል እንዲደርስልን ማድረግ እንችል ነበር፤›› ይላሉ፡

የአካባቢው አስተዳደር አሁንም ድረስ የትም አትሄዱም፣ ሰላም ይመለሳልና ወደ ነበራችሁበት መመለስ ትችላላችሁ ቢሏቸውም ሥጋት እንዳለባቸው ግን አልሸሸጉም፡፡

‹‹መንግሥት የሚወስደውን ዕርምጃ ወስዶ ወደ ቀዬአችን ይመልሰን፡፡ ወይም ያስታጥቁንና ራሳችንን እንጠብቅ፡፡ አሁንም ሥፍራው እየተቃጠለ ነው ያለው፡፡ ማስቆም ያልተቻለበት ምክንያት ምንም ግልጽ አይደለም፤›› የሚሉት አቶ አሰፋ፣ ‹‹ለዘላቂ ሰላም የመከላከያ ሠራዊት ካምፕ በአቅራቢያ ይሠራልን፣ በአቅራቢያ ካለው ቴፒና አካባቢው የሚነሱ ታጣቂዎች ስላሉ ሕግ ይከበርልን፡፡ እንዲሁም መንግሥት ትጥቅ ያስታጥቀን፤›› ሲሉ ጥሪ ያቀርባሉ፡፡

በፀጥታ አካላት እየታጀቡ ወደ አካባቢያቸው ለቅኝት ገባ ወጣ የሚሉ የተወሰኑ ሰዎች እንዳሉ ያልሸሸጉት አቶ ክንዱ፣ አሁንም ድረስ የፀጥታው ሁኔታ ያሳስባል፣ መቼ ሊረጋጋ እንደሚችል ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው ይላሉ፡፡

እንዲህ ያለ ጥቃት ለእርሳቸው አዲስ እንደሆነባቸውና አባታቸው ለ36 ዓመታት በኖሩበት አካባቢ እሳቸውም እዚያው መወለዳቸውን በማውሳት፣ ወደዚያ ተመልሶ መኖር ግን እንደሚያዳግታቸው ይናገራሉ፡፡

‹‹የእናትና የአባቴ ደም የፈሰሰበት ቦታ ገብቼ አልቀመጥም፡፡ ይኼን ያህል ቤተሰብ አጥቼ እዚያ መቀመጥ አልችልም፤›› ሲሉም ያማርራሉ፡፡

ችግር በተፈጠረባቸው አካባቢዎች የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ሰላም ለማስከበር የተሰማሩ መሆናቸውን ለሪፖርተር ያስረዱት የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ነቢዩ ኢሳያስ፣ ከሁለቱ ጥቃቶች በኋላ ምንም የተከሰተ ችግር አለመኖሩንና የተፈናቀሉትንም ሰዎች ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹አካባቢውን ከሽፍቶች ለማፅዳት እየተሠራ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ምንም እንኳን ቁጥራቸው ትንሽ ቢሆንም ወደ አካባቢያቸው እየተመለሱ ያሉ አሉ፤›› ይላሉ ኮሚሽነር ነቢዩ፡፡

በወረዳው ሦስት ቀበሌዎች በተከሰተው ችግር ሸሽተው የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች፣ በብዛት ወንዶች እርሻቸውንና ቤታቸውን ለመቃኘት መመለሳቸውን ኮሚሽነሩ የገለጹ ሲሆን፣ በጠቅላላው በግጭቱ የተፈናቀሉ ሰዎች ግን 4,600 እንደሚሆኑ አክለዋል፡፡

ከግጭቱ ጋር ተያያዥነት አላቸው ተብለው በተሳታፊነት ተጠርጥረው 54 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ለሪፖርተር የተናገሩት ኮሚሽነር ነቢዩ፣ ከእነዚህ ውስጥ ሰባቱ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ የፖሊስ አባላት ናቸው ብለዋል፡፡

ይሁንና በአካባቢው ሥጋቶች እንደነበሩና ሪፖርትም ይደረግላቸው ነበር የተባለው ትክክል አይደለም ይላሉ፡፡ በተለይም በ2007 ዓ.ም. በተመሳሳይ ሥፍራ ከተፈጠረው ግጭት በስተቀር ባለፉት አምስት ዓመታት አካባቢው ሰላማዊ እንደነበር የሚናገሩት ኮሚሽነሩ፣ በዞኑ በሌሎች አካባቢዎች ነው እንጂ በጉራፈርዳ ወረዳ ችግር ሊፈጥር የሚችል ክስተት አልታየም ይላሉ፡፡

በተለይ ከዞንና ከወረዳ መዋቅር ጋር በተያያዘ የቀድሞው ቤንች ማጂ ዞን ምዕራብ ኦሞና ቤንች ሸኮ ተብሎ ሲዋቀር ውጥረቶች ተከስተው እንደነበር የሚያስታውሱት ኮሚሽነር ነቢዩ፣ ለውጡን ተከትሎ ዞንና ወረዳ እንሆናለን የሚል ጥያቄ ቢኖርም ይኼኛው ክስተት ግን ከዚህ ጥያቄ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም ብለዋል፡፡

ከመታ በተባለ ቀበሌ ጥቅምት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. አንድ ሰው በስለት በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሉን ተከትሎ መንግሥት ጉዳዩን እያጣራ ባለበትና ምናልባትም ወደ ግጭትና ጥቃት ሊያመራ ይችላል በሚል ሲከታተለው የቆየ ቢሆንም፣ በሌላ ሥፍራ (ሹጊ ቀበሌ) ያልታሰበ ጥቃት መፈጸሙን ይናገራሉ፡፡

‹‹የበቀል ጥቃት ሥጋት የነበረው በከመታ ቀበሌ ሲሆን፣ ጥቅምት 8 ቀን 2013 ዓ.ም. የተፈጸመው ጥቃት ደግሞ በሹጊ ቀበሌ ነው፤›› የሚሉት ኮሚሽነሩ፣ የዚህ ግለሰብ ገዳይ አሁንም ድረስ አለመያዙን ገልጸዋል፡፡

ቅድሚያ ትኩረት የተሰጠው ክስተቱን ማስቆም ስለነበርም ሰላምና ፀጥታውን መመለስ ላይ እንዳተኮሩ ገልጸው፣ ዘላቂ ሰላም ማምጣት ይቻል ዘንድም ከተፈናቀሉት ሰዎችና ከአካባቢያቸው፣ እንዲሁም ከአጎራባች አካባቢዎች ነዋሪዎች ጋር ውይይቶች እየተደረጉ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በእነዚህም ውይይቶች የተያዙትን እየጠቆሙ የነበሩት የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደሆኑ ገልጸው፣ ‹‹ያልተያዙትንም እያሰስን እንገኛለን፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም መንግሥት በፖለቲካ ኃላፊዎች ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድ ጠቁመዋል፡፡

ኮሚሽነር ነቢዩ የተፈናቀሉትን ነዋሪዎች ከ15 እስከ 20 ባሉት ቀናት ውስጥ ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ እንደታቀደ አስረድተዋል፡፡

‹‹ጥቃት የፈጸሙትን በቁጥጥር ሥር ካዋልን በኋላ ኅብረተሰቡ ራሱን በራሱ የሚጠብቅበትን አሠራር ለማምጣት እየሠራን ነው፤›› የሚሉት የፖሊስ ኮሚሽነሩ፣ በመንግሥት ታጥቀው ኅብረተሰቡን የሚያገለግሉ የሚሊሻ ታጣቂዎች ሚናቸው ኅብረተሰቡን ባካተተ መንገድ ተገምግሞና ኅብረተሰቡን በሚያሳምን ሁኔታ በድጋሚ እንዲዋቀሩ ይደረጋል ብለዋል፡፡

‹‹ጠንካራ የሚሊሻ አባላት ቢኖሩም፣ አመኔታ የማይጣልባቸው እየተገመገሙ በተገቢው መንገድ ለማደራጀት ነው የታቀደው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ይኼ የሚሊሻ መዋቅር ከፖሊስ ጋር ቅርብ፣ ጥብቅና ፈጣን የመረጃ ልውውጥ ማድረግ እንዲችል፣ አካባቢው በሚገባ እንዲጠበቅና ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ እንደሚደረግ፣ እንዲሁም ተመሳሳይ ሥጋት ሲኖር አስቸኳይ መፍትሔ መስጠት እንዲቻል ይደረጋል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -