Saturday, July 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት 1.1 ቢሊዮን ዶላር ቢገኝም የ12 በመቶ ቅናሽ መመዝገቡን ተመድ ይፋ አደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና ልማት ጉባዔ ይፋ የተደረገው ሪፖርት፣ እ.ኤ.አ. በ2020 ግማሽ ዓመት ኢትዮጵያ 1.1 ቢሊዮን ዶላር ያስመዘገቡ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን መሳብ እንደቻለች አመላከተ፡፡ የተመዘገበው መጠን ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት አኳያ የ12 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡

በግማሽ ዓመቱ የተመዘገበው የኢንቨስትመንት መጠን ከሰሃራ በታች አፍሪካ ከሚገኙ አገሮች አኳያ ሲታይ፣ ያን ያህል እንዳልቀነሰና የተረጋጋ የውጭ ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ እየታየ እንደሚገኝ አመላክች እንደሆነ ተመድ ‹‹ኢንቨስትመንት ትሬንድስ ሞኒተር›› በተሰኘው ሪፖርቱ አስፍሯል፡፡

ሪፖርቱ በአብዛኛው የዓለም ክፍል ሲመዘገብ የቆየውም ሆነ ወደፊትም ሊኖ የሚችለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ተስፋ የሚሰጥ እንዳልሆነ ሲያመላክት፣ በኢትዮጵያ መጠነኛ ቅናሽ ቢታይበትም በአብዛኛው በቻይና ኩባንያዎች የሚካሄዱ በርካታ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ለኢትዮጵያ የተረጋጋ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ትልቁን አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ አስገንዝቧል፡፡

በቅርቡ የሦስት ወራት የአገሪቱን የኢንቨስትመንት አፈጻጸም በተመለከተ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜን የቻይኖች ኢንቨስትመንት ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ገልጸው ነበር፡፡ ከቻይና ባለሀብቶች ባሻገር፣ የአውሮፓ፣ የአሜሪካና የአፍሪካ ባለሀብቶችም በኢትዮጵያ የተለያዩ መስኮች መሰማራታቸው ተመልክቷል፡፡

በሦስት ወራት የተመዘገበው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት 500 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር መግለጻቸውም ተዘግቧል፡፡ በሦስት ወራት ከመጣው የውጭ ኢንቨስትመንት 36 ፕሮጀክቶች መመዝገባቸውን ኮሚሽነሯ ገልጸዋል፡፡ በዚህም 14,659 የሥራ ዕድል መፈጠሩን አብራርተዋል፡፡ ከተፈጠሩት የሥራ ዕድሎች ውስጥ 3,795ቱ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት መስኮች የተከፈቱ ናቸው፡፡ የተቀሩት 10,864 ሥራዎች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የተገኙ ናቸው፡፡

ይህም ሆኖ አፈጻጸሙ ከዕቅዱም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አኳያም ያነሰ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በሥራ ዕድል ረገድ 20,500 በላይ የሥራ ዕድል ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቅ የነበረ ቢሆንም የተሳካው 71.3 በመቶ መሆኑን ኮሚሽነሯ አስታውቀዋል፡፡ ከገቢ አኳያም 2012 .. የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ከተገኘው 700 ሚሊዮን ዶላር አኳያ፣ የዘንድሮው 20 በመቶ ቀንሶ 500 ሚሊዮን ዶላር ላይ ተወስኗል፡፡ 2012 .. በጠቅላላው ከሚጠበቀው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አኳያ 50 በመቶ ቅናሽ መመዝገቡም ተወስቷል፡፡ ባለፈው ዓመት 2.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያስመዘገቡ የውጭ ኢንቨስትመንቶች ተገኝተዋል፡፡ ካቻምና 3.3 ቢሊዮን ዶላር ያስመዘገቡ ኢንቨስትመንቶች እንደነበሩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ 

አብዛኛው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ተፅዕኖ እንዳረፈበት ያስታወቁት ኮሚሽነሯ፣ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮችንና መስህቦችን ለማስተዋወቅ የገፅ ለገፅ ገለጻ ማድረግ ያለተቻለበት ይልቁንም በዲጂታል ዘዴዎች መጠቀም ውይይቶች ሲካሄዱ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ የኢንቨስትመንት ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ አገሮች ላይ ያሳደረው ተፅዕኖም ከፍተኛ ስለነበር በርካቶችን ለኪሳራ ዳርጓል፡፡ ይህ በመሆኑም እዚህ የሚመጡ ባለሀብቶች በብዙ ጥረት በመሆኑ የተገኘው የግማሽ ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ፍሰት ቀላል እንዳልሆነ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ሐሳቦችን በመጥቀስ ለቀረቡላቸው የተለያዩ ጥያቄዎችም ምላሾችን ሰጥተዋል፡፡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በፀጥታ መደፍረስ ሳቢያ የሚደርስባቸውን ጉዳት ሲያብራሩ፣ በዚህ ረገድ በሁለት ወገን የሚታይ ችግር እንደሚያጋጥም አመላክተዋል፡፡ አንደኛው ኢንቨስትመንቱ በሚገኝበት አካባቢ የሚኖረው ማኅበረሰብ ከኢንቨስትመቱ ስለሚያገኘው ተጠቃሚነት ስለ ኢንቨስትመንቱ ያለው ግንዛቤ ነው፡፡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ኅብረተሰቡን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርጉበት መንገድ በግልጽ መቀመጥ እንዳለበት፣ በልማት ተነሺ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የመጀመሪያዎቹ ተጠቃሚ መሆን እንደሚኖርባቸው፣ ይህም እንደሚፈጸም ከኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ ተቋሙ የሚከተላቸውን መንገዶች አብራርተዋል፡፡

በኮሮና ዳፋ ከፍተኛ መቀዛቀዝ የታየበት የዓለም የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አኳያ፣ በግማሽ ዓመቱ የ49 በመቶ ቅናሽ ማስዝገቡን ተመድ አመላክቷል፡፡ ትልቁ ቅናሽ በአውሮፓና በአሜሪካ መመዝገቡን ይህም የሆነው አዳዲስ የተመዘገቡና ይፋ የተደረጉ ፕሮጀክቶች ብዛት በ37 በመቶ በማሽቆልቂሉ ነው፡፡

ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገሮችም የ21 በመቶ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ቅናሽ ተመዝግቧል፡፡ በዚህም ወደ 12 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ያለ የኢንቨስትመንት መጠን ሲታይ፣ በናይጄሪያ በተለይ የ29 በመቶ ቅናሽ የታየበት የ1.2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ኢንቨስትመንት ሊመዘገብ እንደቻለ ተመድ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች