Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የትራንስፖርት ሥርዓቱ የሚሠራው ዕድልን በመሞከር ነው›› አቶ ዓቢዩ ብርሌ፣ የትራንስፖርት ቴክኖሎጂ ባለሙያ

አቶ ዓቢዩ ብርሌ ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ በምድረ አሜሪካ የኖሩ በኒውዮርክና በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በትራንስፖርት ዘርፍ የሚያማክሩ ባለሙያ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ወታደራዊ ክንፍ የነበረው ኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ሠራዊት (ኢሕአሠ) መሪ የነበሩትና በዝነኛው የትግል ስማቸው ‹‹ጌራ›› ተብለው የሚታወቁት አቶ ዓቢዩ፣ በተለይ ኢንተሊጀንት ትራንስፖርት ሲስተምስ (አይቲኤስ) የሚባለውን ቴክኖሎጂ በመተግበር የተካኑ ሲሆን፣ በኢትዮጵያም በዚሁ ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ የመንግሥት ተቋማትን በዘርፉ ከማማከር ባለፈም የአዲስ-አዳማ የፍጥነት መንገድ፣ እንዲሁም አዲስ እየተገነባ የሚገኘው የሞጆ-ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ ላይ ቴክኖሎጂው እንዲተገበር አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ፣ በተለይም የአዲስ አበባን የብዙኃን ትራንስፖርት ዘርፍ ለማሻሻልም በርካታ ድጋፎችን ሲያደርጉ የነበሩ ሲሆን፣ ከዚህ ባለፈም የተለያዩ ተቋማትን ይደግፋሉ፡፡ የከተማይቱ የብዙኃን ትራንስፖርት በበርካታ ችግሮች የተተበተበ እንደሆነና ችግሩን ለመቅረፍ ረዥም ርቀት ሊያስኬድ እንደሚችል ቢናገሩም፣ በዋናነት ግን የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ ሊተኮር ይገባል ይላሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም ዘርፉን ከያዙት ችግሮች አላቅቆ አስተማማኝ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ቀልጣፋ፣ ተደራሽና ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖር ከመንግሥት በተጨማሪ የግል ዘርፉ ተሳትፎ ጉልህ ሊሆን እንደሚገባም ምናሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም በተለይ ወጣቶችን በዘርፉ እንዲሳተፉ በማድረግ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን በማጎልበት ቀላልና ቀልጣፋ የመረጃ ልውውጥን በማድረግ ለተቆጣጣሪዎችም ሆነ ለአገልግሎት ሰጪዎች እንዲሁም ለተጠቃሚዎች የሚስማማ የትራንስፖርት ሥርዓት መዘርጋት የግድ ይላል ይላሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ በደመነፍስ ከሚሰጡ ውሳኔዎች ራስን ማላቀቅ ያስፈልጋል ባይ ናቸው፡፡ በጥናት ላይ የተመሠረተና ፍላጎትን ያገናዘበ መፍትሔ እንጂ የታሰበው ሁሉ ይሠራል የሚል ዕርምጃ፣ ከመፍትሔ ይልቅ ችግር ይዞ ሊመጣም ይችላል ይላሉ፡፡ በዚህ ዘርፍም የአዲስ አበባንም ሆነ የአገሪቱን የትራንስፖርት ዘርፍ በቴክኖሎጂ የተደገፈና ዘመናዊ ለማድረግ ድጋፍ የሚያደርግ ኢትዮጵያዊ ማኅበር አቋቁመው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ እነዚህንና የዘርፉን ችግሮች ከመፍትሔዎቻቸው ጋር ከብሩክ አብዱ ጋር በድረ ገጽ የስብሰባ መስመር (ዙም) ባደረጉት ቆይታ ዳስሰዋቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ መንግሥት የተለያዩ ዕርምጃዎችን ሲወስድ የነበረ ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ በበርካታ ችግሮች የተተበተበና በተጠቃሚዎች ዘንድ ምሬትን እየፈጠረ ያለ ችግር ነው፡፡ ዝርዝር የመዲናይቱን የትራንስፖርት ጉዳዮች ከመመልከታችን በፊት የእርሶን የዘርፉን ግምገማ ለመመልከት እንዲረዳን፣ እርስዎ ዘርፉን በቅርበት መከታተል ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በከተማይቱ ያለውን የብዙኃን የትራንስፖርት አገልግሎት ገጽታውን እንዴት ያዩታል ከየት ወዴትስ እየሄደ ነው?

አቶ ዓቢዩ፡- ለብዙኃን ትራንስፖርት ስኬታማነት መለኪያዎች አሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች ከተሟሉ ስኬታማ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ዞሮ ዞሮ ሁሉም ዕርምጃዎች በገጠርም ሆነ በከተማ ሲተገበሩ የሕዝቡን የትራንስፖርት ችግር መቅረፍ አለባቸው፡፡ አንደኛው የብዙኃን ትራንስፖርትን ተደራሽ ማድረግ ነው፡፡ ተደራሽ ማለት ለተጓዡ ከቤቱ አልያም ከሥራው ወደ የሚሄድበት አድራሻ ያለ ምንም እንቅፋት ሊደርስባቸው የሚችልባቸው መንገዶችን ማመቻቸት ይጠበቅበታል፡፡ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት መውሰድም ሆነ ወደ ሥራ ለመጓዝ እንዴት አድርጌ ነው የምሄደው ለሚለው አስተማማኝ ምላሽ መስጠት ይኖርበታል፡፡ በባቡርም ሆነ በአውቶቡስ ተጉዘው ከፈለጉት ሥፍራ በጊዜ መድረሱ ነው ዋናው፡፡ ሁለተኛው አስተማማኝ መሆኑ ነው፡፡ አንድ ሰው በሦስት ሰዓት ሥራ መጀመር ቢኖርበትና ከሥራ ቦታው ለመድረስ የሚጠቀመው ትራንስፖርት በጊዜ እንደሚያደርሰው ያለውን አስተማማኝነት የሚመለከት ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ ከኒውዮርክ ከተማ አሥር ማይልስ አካባቢ ወጣ ብዬ ነው የምኖረው፡፡ ወደ ኒውዮርክ ሥራም ሆነ ሌላ ቀጠሮ ቢኖርብኝና በጊዜ መድረስ ካለብኝ ሰዓቴን መወሰን መቻል አለብኝ፡፡ ከቤቴ ተነስቼ የትኛውን አውቶቡስ አልያም ባቡር መጠቀም እንዳለብኝም ማወቅ አለብኝ፡፡ ይኼንን ለማቀድ ገና ከቤቴ ነው የምጨርሰው፡፡ ለዚህ የሚሆን መረጃ ግን አስተማማኝ የትራንስፖርት ሥርዓት ሲኖር ከቤቴ ቁጭ ብዬ ነው ዕቅዱን የምጨርሰው፡፡ መረጃውን በስልክም ሆነ በኮምፒዩተር በግልጽ የተቀመጠ የምጠቀመው የትራንስፖርት መንገድ፣ መቼ ተነስቶ መቼ የት ይደርሳል የሚለው መርሐ ግብር ስላላየሁ አያለሁ፡፡ በተጨማሪም የአየር ለውጥና ሌላ ችግሮች ካለም ወቅታዊና ቋሚ መረጃ ማግኘት እችላለሁ፡፡ ያንን ተመክልቼ እየተጓዝኩም መረጃውን መከታተል የሚያስችለኝ መንገድ አለ፡፡ የምጠቀመው የትራንስፖርት መንገድ (ባቡርም ሆነ አውቶቡስ) በተባለው ሰዓት ከፌርማታው ይደርሳል ወይ የሚለውን ከደቂቃዎች ባነሰ የመረጃ ልውውጥ ማወቅ እችላለሁ፡፡ ይኼ መረጃ በተባለው ሰዓት ካልኩበት እንደምደርስ ማስተማመኛ ይሰጠኛል፣ አስተማማኝ ሆነ ማለት ነው፡፡

ሦስተኛው ምቹነት ነው፡፡ ሰው በብዙኃን ትራንስፖርት ሲጠቀም ተቸግሮና ተጨናንቆ መሆን የለበትም፡፡ ወንበር ባይኖር እንኳን ያለ ብዙ መተፋፈግ ቆሞ መሄድ፣ ከተቻለ ተቀምጠው እያነበቡ መሄድ የሚያስችል መሆን አለበት፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ የብዙኃን ትራንስፖርት ተብሎ ለደኅንነት የሚያሳስብ ከሆነ፣ ወንጀል የሚበዛበት ከሆነ ወይም ሥርቆት የሚበዛበት ከሆነ ለመጠቀም ያስቸግራል፡፡ እናም ደኅንነቱ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ ተመጣጣኝ ታሪፍ ሊኖረው ይገባል፡፡ ይኼ በተለይ በቂ ሥራ ለሌላቸውና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ወሳኙ መሥፈርት ነው፡፡ በተጨማሪም ቀልጣፋና ብቁ መሆን አለበት፡፡ አሁን እነዚህን መመዘኛዎች ይዘን የአዲስ አበባን ትራንስፖርት የባቡሩን፣ የአውቶቡሱን፣ የሚኒባሱንም ሆነ የታክሲ የትራንስፖርት አገልግሎቶችን ስንመለከት እነዚህን መሥፈርቶች በብዛት አያሟሉም፡፡ አንዳንዶቹን ሊያሟላ ይችላል፣ ለምሳሌ ተመጣጣኝ ዋጋ የሚለውን፡፡ ባቡርን ብንወስድ ለብዙዎቹ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብ አገልግሎት ነው፡፡ ነገር ግን ምቾት አለው ወይ? የሚለው ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ ደኅንነቱ የተጠበቀ ነው ወይ? በተፈለገ ሰዓት የሚገኝ ነው ወይ? ለንብረትና ለግል ደኅንነት ሥጋት አይፈጥርም ወይ? እነዚህ ሁሉ አጠያያቂ ናቸው፡፡ ከሁሉ በላይ ግን የትኛው ነው አስተማማኝ? ወደ ሥራዬ ለመሄድ ስወጣ አግኝቼ እንደምጠቀምበት እርግጠኛ የምሆንበት ትራንስፖርት አለ ወይ? ሊዘገይ፣ ላይኖር ወይም አደጋ ደርሶ ሊሆን ይችላል፡፡ የትራንስፖርት ሥርዓቱ የሚሠራው ዕድልን በመሞከር ነው፡፡ አስተማማኝነቱ ችግር ነው፡፡ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት እነዚህ ችግሮች አሉት፡፡ በጠቅላላው ያለኝ ግምገማ እንግዲህ ይኼ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ ከተማን የሕዝብ ትራንስፖርት ችግር የሚያጠኑ ተመራማሪዎችና አማካሪዎችም ሆኑ መንግሥት ለችግሩ ምንጭ የሚሏቸውን የሕዝብ ቁጥር በየጊዜው ማደግ፣ በከተማው ሕዝብ አሠፋፈር ለውጥ፣ እንዲሁም የመንገድ መሠረተ ልማት ምሉዕነት ማጣትን ያነሳሉ፡፡ በእርስዎ አተያይ ግን ከላይ ባስቀመጧቸው መሥፈርቶች መሠረት ሲመዘን ጉድለቶች የሚታዩበት የከተማይቱ የብዙኃን ትራንስፖርት ሥርዓት ችግር ምንጩ ምንድነው ይላሉ? መፍትሔዎቹስ ምንድናቸው?

አቶ ዓቢዩ፡- አሁን አንተ ያነሳሀቸውን ምክንያቶች ብናይ፣ ለምሳሌ የሕዝብ ብዛት ችግር ነው፡፡ ግን እንደ ሰበብ መቅረብ የለበትም፡፡ አንድ ችግር ሲኖር ችግር መፍታት መለመድ አለበት፡፡ የሕዝብ ብዛት ልናስቀረው የማንችለው ነገር በመሆኑ እንደ ሰበብ መቅረብ የለበትም፡፡ ይኼ ችግር ሳይሆን ፈተና ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ እንደሚታየው ከተሞች በጣም እያደጉ ነው፡፡ ወደ አዲስ አበባም ለመኖር የሚገቡ ሰዎች በርካታ ናቸው፡፡ ነገር ግን ይኼ የሕዝብ ብዛት ነው መፍትሔ ለመስጠት ያላስቻለኝ ብለህ በዚያ ከሄድክ ከመፍትሔ ልትደርስ አትችልም፡፡ ይኼ የሚያሳየው የአስተሳሰብ ችግር ነው፡፡ በተለይ የባለሙያዎችና የመሪዎች፡፡ እነዚህን ነገሮች እንደ ሰበብ ሁልጊዜ ማምጣት የለባቸውም፡፡ በእርግጥ በአገራችን ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ለአንድ ነገር ቶሎ ተብሎ መደበቂያ ምክንያቶችን ማምጣት ላይ ነው ትኩረቱ፡፡ የሚባለው ችግር ስላለ ያንን ችግር እንዴት ነው የምንፈታው ተብሎ ነው መታሰብ ያለበት፡፡ ለምሳሌ ለመኪና አደጋ የሰውን አለመማርና አለማወቅ እንደ ምክንያት ልናቀርብ እንችላለን፡፡ ግን ያንን እንዴት ነው የምፈታው ተብሎ ነው መወሰድ ያለበት፡፡

እነዚህ እንዳሉ ፈተና ናቸው እንጂ ችግር አይደሉም፡፡ ለዚያም ነው ለአሥርና ለሃያ ዓመታት ዕቅድ የሚዘጋጀው፡፡ የወደፊቱንም የምንተነብየው ለዚያ ነው፡፡ ከትንበያው ጋር የተናበበ ዕቅድ መሥራት የተለመደ መሆን አለበት፡፡ የአሰፋፈርም ጉዳይ ከዚህ ተመሳሳይነት አለው፡፡ የሕዝቡ አሠፋፈር የከተማው አስተዳደር ተጠያቂነት ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አንዱ ትልቅ ችግር የመሬት አጠቃቀምና የትራንስፖርቴሽን ግንኙነት የተስተካከለ አለመሆን ነው፡፡ በአደጉት አገሮች አንድ ቦታ ለማልማት ወይም ሰዎችን ለማስፈር ሲታሰብ ዙሪያ መለስ የሆነ ዕቅድ ነው የሚደርጉት፡፡ የሚተገበረው ዕቅድ የሥራ ዕድልን፣ የኢኮኖሚ ዕድገትን፣ የተሻለ የሕዝቦችን አኗኗር ሊያመጣ ይችላል ወይ? ተብሎ ሕዝቡን ባሳተፈ መንገድ ይታቀዳል፡፡ በሌላው ወገን ደግሞ ጥፋት ሊያስከትል ይችላል ወይ? የመንገድ ትራፊክ መጨናነቅ ሊያስከትል ይችላል ወይ? እንዴትስ ነው ትራንስፖርት የማቀርበው? ተብሎ መታሰብ አለበት፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ትልቅ ችግር የሆነ የመሬት ወረራ አለ፡፡ ሰው በፈለገበት ይሠፍራል፡፡ እንደገና የከተማው አስተዳደር ከቁጥጥር ውጪ ይሆንበታል፡፡ ከተማ ሲሰፋም ዝም ተብሎ አይለጠጥም፡፡ ማስፋት ላያስፈልግም ሁሉ ይችላል፡፡ እንደ ዋሽንግተን ያሉ ከተሞች ከአዲስ አበባ ያነሱ ናቸው፡፡ ዋናው ቦታ ሳይሆን ያለውን ቦታ በአግባቡ መጠቀም ነው፡፡ ወደ አዲስ አበባ በብዛት የሚፈልሰውን ሰውም ያለ ገደብ እየተቀበሉ ኮንዶሚኒየም እየገነቡ መያዝ ችግሩን እያባባሰው ይሄዳል፡፡ የአሠፋፈር ችግር ለሚባለው መፍትሔ ማቀድ መቻሉ ነው፡፡ የመሬት አጠቃቀሙ የመኖሪያ ሥፍራን፣ የቢዝነስ፣ ወዘተ አካባቢን አስተያይቶ ነው መሠራት ያለበት፡፡ ሌላው ቀርቶ የትምህርትና የጤና ተደራሽነት አብሮ ነው መታየት የሚገባው፡፡

የሕዝብ ትራንስፖርቴሽን ያሉበትን ችግሮች ስንመለከት፣ የተቋማዊ አደረጃጀት ችግር አለ፡፡ የትራንስፖርትና የመሬት ሥሪት አለመቀናጀት የሚለው ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ኃላፊነት ያላቸው መሥሪያ ቤቶች በሚገባ አይቀናጁም፡፡ አንዳንዴ ግንኙነታቸው ሁሉ ግልጽ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ የትራንስፖርት ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ አምስት ገደማ  ተቋማት አሉ፡፡ የእነዚህ ተቋማት ኃላፊነት ግልጽ ነው ወይ? አንዱ ከሌላው ጋርስ ያለው ግንኙነት ምንድነው? ተደራራቢነትስ አለው ወይ? የሚለው ከችግሩ ጋር በቅርበት መታየት ይገባዋል፡፡ ሌላው የፕሮጀክት ማኔጅመንት ችግር አለ፡፡ ይኼ በእርግጥ በትራንስፖርት ብቻ ሳይሆን በብዙ ዘርፎች የሚታይ ነው፡፡ መጀመርያ ሲጀመር ባለድርሻ አካላትን በማካተት ማቀድ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ለአዲስ አበባ ትራንስፖርቴሽን መፍትሔው የብዙኃን ትራንስፖርት ነው ከተባለ፣ አውቶቡስ እየተገዛ መቀጠል ማለት አይደለም፡፡ ወይም ባቡር ነው መፍትሔው ከተባለ ለማን ነው አገልግሎት የሚሰጠው? ለምን ያህል ጊዜ? ሊያመጣ የሚችላቸው ተፅዕኖዎችስ ምንድናቸው? ወዘተ የሚሉት በአግባቡ መታቀድ ይገባቸዋል፡፡ ይኼንን ዕቅድ ተከትሎ ነው እንግዲህ የትግበራው ዲዛይን የሚመጣው፡፡ ስለዚህ ለማቀድ ሰፊ ጊዜ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ባለሙያዎችን፣ ባለድርሻ አካላትንና ውሳኔ ሰጪ የመንግሥት ባለሥልጣናትን በመያዝ መሠራት ይኖርበታል፡፡ ትልቁ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ችግር ይኼ ነው፡፡ በቂ የዕቅድ ዝግጅት አይደረግም፡፡ በሚሠራው ዲዛይን ላይም የተለያዩ አማራጮችን በማቅረብ ማስተያየትና መምረጥ ያስፈልጋል፡፡ የተለያዩ የደኅንነትና ተያያዥ ጉዳዮች ከግምት መግባት ይኖርባቸዋል፡፡

ለምሳሌ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘውን ባቡር ብንመለከት፣ ባቡሩ ሲሠራ የነበረው ዕሳቤ ባቡሩ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ሰው መኪና እየተወ ወደ ባቡር ይኼዳል የሚል ነበር፣ የሞዳሊቲ ለውጥ ይመጣል በማለት፡፡ ይኼ ግን አሁን በአዲስ አበባ አይታይም፡፡፡ ገቢያቸው ዝቅተኛ የሆኑትን አገዘ እንጂ የመኪናውን ሚና አልቀነሰም፡፡ እነዚህ ሁሉ ከዕቅድና ከቅድመ ትንበያ ጋር የሚገናኙ ናቸው፡፡ ቀጣዩ የዚህ አካል ትግበራ ነው፡፡ በተወሰነ ዋጋ፣ በተወሰነ ጊዜ፣ የጊዜ ሰሌዳውንና ዲዛይኑን በጠበቀ መልኩ እንዴት ተደርጎ ነው የሚተገበረው የሚለው ራሱን የቻለ ችግር ነው፡፡ እንግዲህ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ችግር ለምን ኖረ ካልን ራሱን የቻሉ ማብራሪያዎች ይኖሩታል፡፡ የአመራር፣ የቴክኒክ፣ የዕውቀት ማነስ፣ እንዲሁም ከሌሎች አገሮች ልምድ አለመውሰድ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ የፕሬጀክት ማኔጅመንት አንዱ ራሱን የቻለ ችግር ነው፡፡ ከዚያ ጋር በተያያዘ ሌላ ትልቁ ችግር የሚመስለኝና እዚህ አገር የተቀሰሙ ልምዶች በማለት የሚያትቷቸው ከስህተት ወይም ከስኬት አለመማር ናቸው፡፡ ይኼ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ አንድ ፕሮጀክት ከወደቀ በኋላ ከእርሱ በመማር ሁለተኛና ሦስተኛው ይሻሻላሉ እንጂ፣ እንደገና በራሱ ላይ አይደገምም፡፡ ይኼ ባህል እጅግ አነስተኛ ነው እኛ አገር፡፡

የትራፊክ ማኔጅመንቱም ትልቅ ችግር ነው፡፡ ከፍተኛ የሆነ መጨናነቅ አለ፡፡ በተለይ ደግሞ ቴክኖሌጂና ዕውቀት በአግባቡ አለመጠቀም አለ፡፡ በተጨማሪም የሕግ ማስከበር ክፍተቶች አሉ፡፡ ለአብነትም አሽከርካሪዎች በፍጥነት ሲነዱ፣ መብራት ጥሰው ሲሄዱ፣ እግረኞች ያለ ቦታ መንገድ ሲያቋርጡ፣ ወዘተ የሚታይ ነው፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ አሁን እየተተገበረ እንዳለው የፈጣን አውቶቡስ ትራንዚት (አርቢቲ) ፕሮጀክት መሰል አዳዲስ አሠራሮች በአግባቡ ከታቀዱና ከተሠሩ ከፍተኛ ጥቅም ሊያስገኙ ይችላሉ፡፡ እንደ ባቡር ከፍተኛ ወጪ የለውም፣ በርካታ ሰዎችንም ሊያጓጉዝ ይችላል፡፡ ይሁንና ከላይ አስቀድመን ያነሳናቸውን የውጤታማነት መሥፈርቶች እንዲያሟላ ለማድረግ በአግባቡ ማቀድ ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም ቀጣይነት ያለው ማሻሻያ ያስፈልጋል፡፡ በየጊዜው ሲገመገም ለውጥ ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡

ሪፖርተር፡- የከተማይቱን የብዙኃን ትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ በማለም የተለያዩ ዕርምጃዎች ሲወስዱ ይታያል፡፡ እነዚህ ዕርምጃዎች አዳዲስ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎችን እስከ ማቋቋም ድረስ ይሄዳሉ፡፡ የዚህ አንዱ ማሳያ የሸገር ባስ የብዙኃን ትራንስፖርት ድርጅት ነው፡፡ ራሱን የቻለ የአውቶቡስ መስመር መለየትም አንዱ መፍትሔ ተብሎ የተወሰደ ዕርምጃ ነው፡፡ ነገር ግን በእነዚህ ዕርምጃዎች መካከል የከተማይቱ የብዙኃን ትራንስፖርት ችግር ሲባባስ እንጂ ሲቃለል አይታይም፡፡ ቅድም ያነሷቸው ጠቅላላ ችግሮች ቢኖሩም፣ ለእነዚህ ዕርምጃዎች አለመሳካት ሊጠቀሱ የሚችሉ ምክንያቶች ይኖራሉ?

አቶ ዓቢዩ– እኔ ይኼንን በተመለከተ ግምገማ ስላልሠራሁ ይኼ ነው ብዬ አንድ ጉዳይ ብቻ መናገር አልችልም፡፡ ለምሳሌ አንበሳ አውቶቡስ እያለ ለምንድነው ሸገር ባስ የተቋቋመው? በሚኒባሱም ቢሆን ሰው ይኼን ያህል ጊዜ በሠልፍ ላይ የሚያጠፋው ለምንድነው? ሚኒባስ ስላነሰ ነው? ወይስ መስመሩን በሥርዓት ማስተዳደር ስላልተቻለ ነው? የሚለው ዝርዝር ጥናት ይጠይቃል፡፡ ሚኒባሶችን በክላስተር አድርገዋቸው የተሻለ ውጤት ቢመጣም ውጤቱ በሚጠበቀው ደረጃ አልሆነም፡፡ ለዚህ ምላሽ በየጊዜው ጥናቶችን ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን ጥናቶች ተከታታይና ቀጣይነት ባለው መንገድ ለማከናወን ደግሞ ብቃት ያለው የሰው ኃይል ያስፈልጋል፡፡ አንድ ነገር ተተግብሮ በቂ ውጤት ካልመጣ ችግር አለው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ያንን እያዩ የሚከታተሉ፣ የሚቆጣጠሩና የሚያጠኑ አመራሮችና ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ዕርምጃ ነው የሚያስፈልገው፡፡ አንዳንዴ ዕርምጃዎች ፖለቲካዊ ነው የሚመስሉት፡፡ ሕዝቡ ሮሮውን ሲያሰማ ብር አውጥቶ አውቶቡስ መጨመር ነው የሚቀናቸው፡፡ ደመነፍሳዊ ነው ዕርምጃው፡፡

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት አንዱ ችግር የሆነው ቴክኖሎጂን በአግባቡ አለመጠቀም ነው፡፡ ለምሳሌ በናይሮቢ ሁካታ የሚበዛባቸውና ደማቅ ቀለም ያላቸው ማታቱ የሚባሉ ሚኒባሶች ስላሉ እነርሱን ሥርዓት ለማስያዝ ፈለጉ፡፡ አብዛኛው ሰው ደግሞ ይጠቀምባቸዋልና በአንዴ ማስወገድ ደግሞ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ሥርዓት ማስያዝ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እና ምንድነው ያደረጉት? የናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ ከኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲና ከማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ (ኤምአይቲ) ጋር በመተባበር በመጀመርያ ማጥናት አለብን ብለው አጠኑ፡፡ ሚኒባሶቹ ከየት ተነስተው የት ይሄዳሉ? በየትስ በኩል ነው የሚሄዱት? ለምን ያህል ሰዎች አገልግሎት ይሰጣሉ? ወዘተ የሚሉትን በቴክኖሎጂ ማጥናት ፈለጉ፡፡ ተማሪዎችን በማሳተፍና በስልካቸው ላይ ያለውን የጂኦግራፊካል ፖዚሽኒንግ ሲስተም (ጂፒኤስ) በመጠቀም መስመሩን መከታተል ጀመሩ፡፡ ይኼንን መረጃ ሰብስበው በጉግል ማፕ ላይ አስቀመጡት፡፡ ያንን መሰል መረጃ ማግኘት እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ምክንያቱም ከቢሮ ቁጭ ብለው ቢገምቱ ደመነፍሳዊ ስህተት ነው ሊሠሩ የሚችሉት፡፡ አሁን ያንን መረጃ በደንብ ሰብስበው በኢንተርኔት አድርገው ለተጠቃሚዎች እንዲደርሳቸው አደረጉ፡፡ በዚህኛው መንገድ መጠቀም ለማይችሉት ደግሞ በወረቀት ላይ ካርታ አትመው አሰራጩ፡፡ የሚገርመው ነገር ለብዙዎቹ ዓይን ገላጭ ነበር፡፡ አንዳዶቹ ሳያውቁ ረዥሙን መስመር ይጠቀሙ ነበርና መስመራቸውን ሁሉ አስተካከሉ፡፡ አሁን ይኼ መረጃ ዕቅድ ለሚመሩ፣ ለኃላፊዎችና ለሕዝቡ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ እንዲህ ያለ የቴክኖሎጂ መፍትሔ በዘርፉ ሲተገበር በአፍሪካ የመጀመርያው ነው፡፡ በኢትዮጵያም የሚኒባስ አሠራር አስቸጋሪ ነው፡፡ መስመር እንደፈለጉ ይቀይራሉ፣ ትርፍ ይጭናሉ፣ ታሪፍም አያከብሩም፣ ያለ ቦታ አውርደው ይጥላሉ፡፡ እንዲህ ክትትል ማድረግ ከተቻለ ተጠያቂነትን ማምጣት ይቻላል፣ ችግሩንም በደንብ ለማወቅ ይጠቅማል፡፡ በነገራችን ላይ ይኼ ለአውቶብስም ይጠቅማል፡፡ በዚህ አግባብ ማጣጣምም ይቻላል፡፡ አውቶቡስ አልያም ሚኒባስ ከመጨመር መስመር ማስተካከል መፍትሔው ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲህ ያለ አሠራር ግልጽነትን ያመጣል፡፡

ሪፖርተር፡- በሌላ በኩል ደግሞ የትራንስፖርት ዘርፉን ችግሮች ለመቅረፍ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች በውጭ ሲተገበሩ ስለታዩ ብቻ እዚህም ይሠራሉ በሚል ዕሳቤ ተገልብጠው፣ ከአገሪቱና ከከተማይቱ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር ሳይጣጣሙ የሚተገበሩ ናቸው የሚሉ አስተያየቶች ይደመጣሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በዘርፉ የሚተገበሩ ዕርምጃዎች ደግሞ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ በመሆናቸውም ውጤታማነታቸው ላይ ጥያቄ ይነሳል፡፡ የአውቶቡስ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶችም በሙሉ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ ናቸው፡፡ አንድ የግል አውቶቡስ አገልግሎት በከተማ ውስጥ ይሰጥ የነበረ አሊያንስ ትራንስፖርት የተባለ ድርጅትም ከገበያው ወጥቷል፡፡ እነዚህስ ችግሮች ምን ያህል የችግሩ ምንጮች ናቸው ይላሉ?

አቶ ዓቢዩ፡- ከውጭ መማር ጥሩ ነው፡፡ ግን ዝም ብሎ መጥቶ ይኼም እኛ አገር ይሠራል ተብሎ ቢተገበር ለውጥ አይመጣም፡፡ የአገሪቱን ችግር የሚፈታው ባቡር ነው? አውቶቡስ ነው? ወይስ ሚኒባስ ነው ወይ? የሚለው መታየት አለበት፡፡ ባቡሩ የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ያላመጣባቸው ምክንያቶች አሉ፡፡ ቅድም ካልኳቸው የዕቅድ ሥራዎች ጋር የሚያያዙ ናቸው፡፡ ከውጭ ሲመጣ እኮ እንዳልከው ለአገሪቱ በሚስማማ መንገድ ነው የሚሆነው፡፡ ባቡሩ በርካታ ገንዘብ ነው የወጣበት፡፡ ግን የወጣበትን ገንዘብ ያህል አገልግሎት እየሰጠ ነው ወይ የሚለው ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡ በእርግጥ ለብዙ ሰው አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ባቡሩ በዲዛይኑ ላይ ችግሮች አሉ፡፡ ምሳሌ ብናነሳ መንገድ ማቋረጫ ሥፍራዎች አደገኛ የሆኑ አሉ፡፡ የሰውም የመኪናም ማቋረጫዎች ላይ የግጭት አደጋዎች ሁሉ ይከሰታሉ፡፡ ሁለተኛ ጥገና ላይ ችግር አለ፡፡ የባቡር መስመሮችና ፉርጎዎች ላይ ለሚደረጉ ጥገናዎች መለዋወጫዎች ከቻይና ስለሚመጡ፣ ከጠቅላላው አገልግሎት መስጠት የሚገባው ባቡር ቁጥር 20 እና 30 በመቶው አይሠራም፡፡ ስለዚህም ያለውን አቅም በአግባቡ መጠቀም አልቻለም፡፡ ባቡሮቹ መጀመርያም አነስተኛ መጠን ያላቸው ናቸው፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ ሲበላሹ በፍጥነት አይጠገኑም፡፡ ከዚያ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ መጨናነቅ የፈጠረባቸው አካባቢዎች አሉ፡፡ ባበሩ የያዘው ቦታ ይሁን ቢባልም በግራና በቀኝ ያሉ መንገዶች ላይ ከፍተኛ የሆነ መጨናነቅ አለና እንዴት ነው ይኼንን ወደ ሌላ መስመር መስደድ ይቻላል ወይ ብሎ ማቀድ ያስፈልጋል፡፡ በዲዛይን ላይ አንዳንድ ሥፍራዎች በመሬት ውስጥ መሄድ ሲገባው፣ በምድር ላይ ሄዶ ያበላሻቸው አካባቢዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ከሜክሲኮ አደባባይ ጀምሮ እስከ መስቀል አደባባይ የከተማዋ ታሪካዊ ሥፍራ ነውና ያንን ሁሉ ግንባታ እዚያ ከማኖር፣ ሌላ አማራጭ ሊኖር አይችልም ወይ ብለን መጠየቅ እንችላለን፡፡ ቀለል ባለ መንገድ በብዙ የአውሮፓ አገሮች ከተሞች ውስጥ ያሉ መስመሮች ባቡርም መኪናም የሚጠቀምባቸው ናቸው፡፡ በመብራትና በሌሎች ቴክኖሎጂዎች እየታገዙ፡፡ ስለዚህ ከአገሪቱ ጋር በሚጣጣም ሁኔታ መሠራት ይችል ነበር፡፡

በሁለተኛነት ያነሳኸው የግል ዘርፉ ተሳትፎን የሚመለከተው አሠራር ቁልፍ ተግባር ነው፡፡ መንግሥት ለብቻው ይኼንን ሊወጣው አይችልም፡፡ የመንግሥትና የግል ዘርፍ ጥምረት የሚታይባቸው ናቸው ባደጉት አገሮች ያሉ አሠራሮች፡፡ የግል ዘርፉን ለማበረታታት መደገፍና ማበረታቻ መስጠት ይቻላል፡፡ ወይም ታሪፍ መጨመር የሚኖርባቸው ከሆነ መንግሥት የተወሰነውን እየሸፈነ የተቀረውን ወደ ሕዝቡ እንዲሄድ ያደርጋል፡፡ ይኼ መሆኑ ለመንግሥትም ለሕዝቡም ጠቀሜታ አለው፡፡ በተለይ በትራንስፖርት ዘርፉ የግል ዘርፉን በስፋት ማሳተፍ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም መንግሥት መሠረተ ልማት ማቅረብ ላይ ነው ማተኮር ያለበት፡፡ ሌሎች አገልግሎቶችን የተመለከቱ ሥራዎች በግል ዘርፉ እንዲሰጡ ነው መበረታታት ያለበት፡፡ ብቸኛው የነበረው የአውቶቡስ የከተማ ትራንስፖርት የሚሰጥ ድርጅት ከገበያው ከወጣ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ እና መዋዕለ ነዋይ አፍሳሾችን ማበረታታት ይስፈልጋል፡፡ በተለይ ወጣቶች አሉ ብዙ መሥራት የሚችሉ፡፡ እነሱ ቴክኖሎጂ ታክሎ ወደ ትራንስፖርት ዘርፉ እንዲገቡ የተወሰነ የመነሻ ገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላቸው በተሻለ ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ የግል ዘርፉ መክሰር ስለማይፈልግና ለትርፍ ስለሚሠራ መውደቅ አይፈልግም፡፡ መንግሥት ግን እየከሰረም ኃላፊነት አለብኝ ብሎ ሊሠራ ይችላል፡፡ ስለዚህም አንዱ ሲወድቅበት ሌላውን ያመጣል፡፡ የግል ዘርፉ ግን ለባለ አክሲዮኖች ተጠያቂ ስለሚሆን መክሰር አይፈልግም፡፡ ከዚያም በላይ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ብዙ ጊዜ በግል ዘርፉ ነው የሚመጡት፡፡ ገበያው ነፃ ከሆነ ብቁ ያልሆነው ቢወድቅ እንኳን ሌላ ይመጣል፡፡ እዚህ ላይ የሚገቡ ድርጅቶች አመራረጥ ላይ የመልካም አስተዳደርና የመሳሰሉ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ግን ይህንን መሰል ችግሮች ቢስተካከሉና በተለይም ወጣቶች ቢገቡ ብዙ ለውጥ ሊመጣ ይችላል፣ ዘርፉንም ሊያግዘው ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- የከተማይቱን የሕዝብ ትራንስፖርት ዘርፍ ችግር ይቀርፋል በማለት መንግሥት እየወሰዳቸው ካሉ የተለያዩ ዕርምጃዎች መካከል የአውቶቡስ አግልግሎት ነው፡፡ የተለየ የአውቶቡስ መስመር ከመዘርጋት በተጨማሪ አሁን በከተማይቱ ተጨማሪ 3,000 አውቶቡሶችን አስመጥቶ ለማሰማራት ዕቅድ ተይዟል፡፡ እንዲያው ይኼ ሁሉ ኃይልና ገንዘብ እየፈሰሰበት ያለው የአውቶቡስ ትራንስፖርት የተሰጠው ትኩረት ሁሉ ይገባዋል ይላሉ?

አቶ ዓቢዩ፡- አውቶቡስ አስፈላጊ ነው፡፡ ምን ያህል ገንዘብ ነው የሚወጣበት የሚለውና የት የት ነው ይኼ ገንዘብ ሊወጣ የሚገባው የሚለው ጥናት ያስፈልጋዋል፡፡ ለምሳሌ የዋሽንግተንና የኒውዮርክን ትራንስፖርት ወስደን ብናነፃፅር የአዲስ አበባ ትራንስፖርት የሚጎድለው ትልቁ ነገር ቅንጅት ማጣት ነው፡፡ የተለያዩ የትራንስፖርት አማራጮች አሉ፡፡ ባቡሩን፣ አውቶቡሱንና ሚኒባሱን ጨምሮ፡፡ ዋሽንግተን የአዲስ አበባ እህት ከተማ ናት፡፡ በከተማይቱ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ባቡር አለ፡፡ ባቡሩ ቅድም የጠቀስኳቸውን ብዙዎቹን መሥፈርቶች ያሟላል፡፡ ግን ባቡሩ ሁሉንም ያዳርሳል ማለት ግን አይደለም፡፡ የማይደርስባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ ያንን የሚሸፍኑት በሜትሮ ባስ ነው፡፡ የሜትሮ ባስ መስመር ኔትወርኩ ከባቡሩ ጋር የተቀናጀ ነው፡፡ እንደገና አውቶቡሱ የማይደርስባቸው አካባቢዎች ደግሞ የአካባቢ አውቶቡሶች አሉ፡፡ ይኼ ነው እንግዲህ ቅንጅት የምንለው፡፡ የአዲስ አበባ አንዱ ትልቁ ችግር እርሱ ነው፡፡ ቅድም እንዳልኩት በጥናት ላይ ከተመሠረተ ሁሉም የትራንስፖርት አማራጮች የት እንደሚሄዱ መስመራቸውን ማወቅና ምን ያህል ሰዎችንም እንደሚያገለግሉ ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ ያንን በቴክኖሎጂና በዕውቀት ከደገፍነው አውቶቡስ የት የት ነው የሚያስፈልገው የሚለውን በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ መወሰን ይቻላል፡፡ በዚህም ከሌሎች የትራንስፖርት አማራጮች ጋር በማቀናጀት ይህንን ሥርዓት አንዴ ከዘረጋን በኋላ ፍላጎትን ማወቅ ይቻላል፡፡ የት ሥፍራ እጥረት እንዳለ፣ የት የተደራሽነት ችግር እንዳለ በቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ማስተካከል ይቻላል፡፡

ያ ሳይሆን ግን በደመነፍሳዊ ውሳኔ አውቶቡስ ነው የሚያስፈልገው ካልንና በየጊዜው የምናስገባ ከሆነ ውጤቱ ከፍላጎቱ ጋር ላይጣጣም ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን በርካታ የዘርፉን ችግሮች አነሳን፡፡ በእርስዎ ግምገማ እስከ ዛሬ በዘርፉ ከተሠሩ ሥራዎች ውጤታማ ነው የሚሉት አለ?

አቶ ዓቢዩ፡- በመንገድ ሥራ ላይ በርካታ ጥሩ ነገሮች አሉ፡፡ በእርግጥ ለሕዝብ ትራንስፖርት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡ ግን በተመሳሳይ ጊዜ በአዲስ አበባ የመንገድ እጥረትም ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ለውጦች አሉ፡፡ አሁን ትልቁ ችግር የሆነው የብዙኃን ትራንስፖርት ነው፡፡ ባቡሩም ምንም እንኳን ችግር ቢኖርበት በርካታ ሰዎችን ያገለግላል፡፡ ምን ያህል ነው ስኬቱ የሚለው ጥናት ይጠይቃል በእርግጥ፡፡ ግን በሙሉ ሊነቀፍ የሚችል አይደለም፡፡ ባቡር ባይኖር ያ ሁሉ ሰው በምን ይጓዛል? ግን የበለጠ ብቁና ውጤታማ ለማድረግ ይቻል ነበር፣ ለዚህም በርካታ አማራጮች ይኖራሉ፡፡ ለዚህም ነው የፈጣን የባስ ትራንዚት (አርቢቲ) መስመር ሲሠራ ጥንቃቄ ያስፈልጋዋል የምለው፡፡ የባቡሩን ያህል ወጪ የማያስወጣ ቢሆንም ባቡሩ የሚይዘውን ያህል ሰው ግን ማጓጓዝ ይችላል፡፡ በታንዛኒያ በዓለም ባንክ አማካይነት እየሄድኩ አግዛቸዋለሁ፡፡ ለአርቢቲና ለአይቲኤስ ጥናት ሲደረግ የዚህ አርቢቲ መተግበር ትልቅ ለውጥ ነው ያመጣው በትራንስፖርቴሽን ዘርፉ፡፡ ወጪውም ደግሞ ከባቡር እጅግ ያነሰ ነው፡፡ የአዲስ አበባም በደንብ ተጠንቶ ከተሠራ ጥሩ ውጤት የሚያመጣ ይመስለኛል፡፡ የሚኒባሱም ቢሆን በፊት ከነበረበት ኋላ ቀር አሠራር ለውጥ አለ፡፡ አሁን ሥርዓት ይዟል በዞን ከተደረገ በኋላ፡፡ እጥረትና የተለያዩ መሰል ችግሮች ቢኖርበትም፡፡ የትራንስፖርት አስተዳደር ለራሱ የተበታተነና የተበጣጠሰ ነው የነበረው፡፡ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ከተቋቋመ በኋላ በርካታ ለውጦች አሉ፡፡ የትራንስፖርት ፕሮጀክት ማኔጅመንት ቢሮም አብሮ ነው የተቋቋመው፡፡ ይኼ ለውጥ አምጥቷል፡፡ ነገር ግን ግራ በሚያጋባ ሁኔታ አዲስ የትራፊክ ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ተብሎ ተቋቁሟል፡፡ ለምን እንደዚያ እንዳደረጉ አይገባኝም፡፡ አንዳንዴ እንዲህ ያሉ ተደራራቢ ተቋማት ናቸው ችግር የሚፈጥሩት፡፡ ይሁንና የሕዝብ ትራንስፖርት ዘርፉ አሁንም ቢሆን በርካታ ችግሮች ያሉበትና ረዥም ርቀት መጓዝን የሚጠይቅ ነው ለማሻሻል፡፡

ሪፖርተር፡- አዲስ አበባ ልትማርባቸው የምትችላቸው ልምዶች ያሏቸው እንደ ዋሽንግተን ያሉ እህት ከተሞችና ሌሎች አካባቢዎች አሉና ከየት ምን ትምህርት ሊቀሰም ይችላል? የሚቀሰመው ልምድስ እንዳይከስም ምን ይደረግ ይላሉ?

አቶ ዓቢዩ፡- ዕውቀቱንና ቴክኖሎጂውን ለማየት የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ በተግባር በዓለም ባንክ ድጋፍ ወደ አሜሪካ እንዲመጡ አድርገናቸው ነበር አመራሮቹን፡፡ ከትራንስፖርት ባለሥልጣን፣ አአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ከትራንስፖርት ሚኒስቴርና ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ነበሩ እነዚህ ሰዎች፡፡ በጣም ጥሩ መርሐ ግብር ነበር፡፡ ለስድስት ወራት ነበር ጥናት የተደረገበትና በኢንተለጀንስ ትራንስፖርቴሽን ሲስተምስ (አይቲኤስ) ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ከጉብኝት በኋላ ማታ ማታ ውይይቶችን እናደርግም ነበር፡፡ ጉብኝቱ የነበረው በዋሽንግተን ዲሲና በኒውዮርክ ሲሆን፣ በመካከል ያለውን መንገድና ቴክኖሎጂም ዓይተናል አብረን፡፡ ከዚህ ጉብኝት በኋላ የተሰናዳውን ሪፖርት ለትራንስፖርት ሚኒቴር አቅርበን አሁን በዚያ ላይ በመመርኮዝ መመርያ አድርጎ ለመተግበር እየተሠራበት ነው ያለው፡፡ በልምድ ልውውጥ ወቅት በፊት የነበረው ልምድ ጥሩ አልነበረም፡፡ አውሮፓም አሜሪካም ሰዎች ይሄዳሉ፡፡ ግን የተቀናጀ አይደለም፡፡ ዕውቀቱንና ልምዱን አምጥቶ የመተግበር ልምዱ አናሳ ነበር፡፡ ቻይናና አሜሪካ ለልምድ ልውውጥ እየተኬደ አምጥቶ ለመተግበር ምንድነው የሚያስቸግራችሁ እል ነበር፡፡ ምክንያቱን ለማወቅም ያስቸግረኛል፡፡ ከዚህ ጋር የሚያዙ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡ ቁርጠኝነት፣ ተነሳሽነት፣ እንዲሁም ለአገር ተቆርቋሪነት ያስፈልጋል፡፡ መሪዎች ደግሞ የፖለቲካ ተlሚዎች ስለሚሆኑ በኃላፊነት ላይ ብዙ አይቆዩምና ሥራዎች ቀጣይነት የላቸውም፡፡ እነሱ የጀመሩትን ነገር ሌላው ሲመጣ ከዜሮ ይጀምራል ወይም ይረሳል፡፡ ስለዚህ የሲቪል ሰርቪሱን ማሻሻልና ቴክኖሎጂውን ማጎልበት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ወጣቶችን አበረታትቶ እንዲሳተፉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋርም ማስተሳሰር ያስፈልጋል፡፡ ትምህርቱን፣ ዕውቀቱንና ቴክኖሎጂውን ማስተሳሰር ያስፈልጋል፡፡ መሪዎችንና ባለሙያዎችንም በስፋት ማፍራት ያስፈልጋል፡፡ ሌላው ደግሞ ባህሉንም መቀየር ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ግልጽነት ይጎድለዋል የኢትዮጵያ አሠራር፡፡

ሪፖርተር፡- ከላይ እንዳነሱት ቴክኖሎጂ አንዱ የከተማይቱን የብዙኃን ትራንስፖርት ዘርፍ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያግዝ ነው፡፡ የእርስዎ ሙያ የሆነው የኢንተለጀንስ ትራንስፖርቴሽን ሴስተምስ (አይቲኤስ) ደግሞ አንዱና ዘመናዊ የትራንስፖርት ዘርፍ ቴክኖሎጂ ነውና ይኼ ቴክኖሎጂ እንዴት ችግሩን ሊቀርፍ እንደሚችል ቢያብራሩልን?

አቶ ዓቢዩ፡- የብዙኃን ትራንስፖርቴሽኑን መቀየር የሚቻልባቸው በርካታ ቴክኖሎጂዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የአውቶቡስ ትራንስፖርቱን፡፡ መስመሩን በጂአይኤስ ማስቀመጥ፣ የመረጃ ሥርዓቱን ማጠናከር፣ ካስፈለገም ለደኅንነት የሚሆኑ መከታተያዎችን ለመተግበር፣ እንዲሁም ቅድም የዘረዘርናቸውን ምቹነት፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆን፣ አስተማማኝነትና የመሳሰሉት እንዲኖሩ አይቲኤስ ብዙ ይጠቅማል፡፡ አውቶቡሶችን ለመከታተል የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችን በመተግበርም፣ የት የት እንዳሉ ለመከታተልና በሚያስፈልግበት ሥፍራ በፍጥነት ለማሠራጨት፣ ለተሳፋሪዎች መረጃ ለመስጠት፣ ወዘተ ይረዳል፡፡ ይኼ እንግዲህ ለትራፊክ ማኔጅመንት ይረዳል፡፡ ስለዚህ አይቲኤስ ለትራፊክ ማኔጅመንት፣ ለደኅንነት፣ ለተሳፋሪ መረጃ፣ ለአደጋ መረጃና መፍትሔ፣ እንዲሁም የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት ሁሉ ለማቀናጀት ይረዳል፡፡ ተቋማቱ ግልጽነት በታከለበት ሁኔታ ጠቃሚ መረጃዎችን እንዲለዋወጡና በቅንጅት እንዲሠሩ ያግዛል፡፡ ለምሳሌ የመንግሥት መዘጋት ቢከሰት እነዚህ ተቋማት መረጃ አግኝተው እንዴት ይፈቱታል ለሚለው አይቲኤስ ይረዳል፡፡ ይኼንን ለማድረግ በርካታ ቴክኖሎጂዎች አሉ፡፡ አይቲኤስ ኢትዮጵያን ያቋቋምነውም ለዚሁ ዓላማ ነው፡፡ የሕዝብ/የመንግሥትና የግል ባለድርሻ አካላትን ለማገናኘት ነው ዋና ዓላማችን፡፡ እነሱን ስታገናኝ ፕሮጀክቶች በቶሎ እንዲሠሩ፣ መረጃና ዕውቀትም በፍጥነት መለዋወጥ እንዲቻል ያግዛል፡፡ እነሱን ብቻ ሳይሆን የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ለማገናኘትም ያግዛል፡፡ በአይቲኤስ ኢትዮጵያ አማካይነት የዘርፉን ሲምፖዚየም ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ፍላጎትም አለን፡፡ በአይቲኤስ ኢትዮጵያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኩባንያዎችን ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ማምጣት ይቻላል፡፡ በዚህም ለአዲስ አበባም ሆነ ለሌሎች ከተሞች የሚጠቅሙ ቴክኖሎጂዎችን ያሳያሉ፡፡ የውይይት መድረኮችንም በማዘጋጀት የብዙኃን ትራንስፖርትን ለማሻሻል የሚረዱ አማራጮችን፣ የሌሎችንም ከተሞች የሕዝብ ትራንስፖርት እንዴት ማሻሻል እንደሚቻል፣ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ልውውጦችን ማድረግ ያስችላል፡፡ ስለዚህ አይቲኤስ በርካታ ለውጦች በደኅንነት፣ በሕግ ማስከበር፣ በብቁነትና ቀልጣፋነት፣ በፈጠራና ቴክኖሎጂ ልውውጥ፣ አደጋን በተመለከተ፣ እንዲሁም በመሰል ዘርፎች ሰፊ ዕድል ይፈጥራል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...