የዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ታኅሣሥ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. በተመረጡ ስታዲየሞች እንደሚጀመር የሊጉ አክሲዮን ማኅበር አስታወቀ፡፡ ውድድሩን በቀጥታ ስርጭት ለማስተላለፍ ያሸነፈው ዲኤስቲቪ የባለሙያዎች ቡድን ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ ባለፈው ባለፈው ሐሙስ ምሽት አዲስ አበባ መግባቱ ታውቋል፡፡
ቀደም ሲል የፕሪሚየር ሊጉን ስያሜ ጨምሮ በአጠቃላይ ወደ 68 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ማግኘት የቻለበትን ስምምነት ከዲኤስቲቪ ጋር መፈራረሙን ያስታወቀው የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማኅበር፣ በአሁኑ ወቅትም ውድድሮቹ የሚደገረጉባቸውን የተመረጡ ስታዲየሞች የዲኤስቲቪ ሙያተኞችን በማካተት ጭምር በመገምገም ላይ ይገኛል፡፡
ጨዋታው የሚደረግባቸው ስታዲየሞች በአጠቃላይ ስድስት ሲሆኑ፣ የአዲስ አበባ ስታዲየምን ጨምሮ የመቐለ፣ የባህር ዳር፣ የጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ የሐዋሳና የድሬዳዋ ስታዲየሞች መሆናቸውም ታውቋል፡፡ ቡድኑ እሑድ ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም. የባህር ዳር ስታዲየምን እንደሚጎበኝ አክሲዮን ማኅበሩ አስታውቋል፡፡