Wednesday, June 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቴሌኮም ዘርፍ የሽያጭና የአገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥ ሒደት እንዲቀጥል መመርያ ተሰጠ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለቴሌኮም አአገልግሎት ፈቃድ የመስጠትና የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ የመሸጥ ሒደት፣ ከአማካሪ ምክር ቤትና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሥር ከሚገኘው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ቡድን ጋር ምክክር እየተደረገ ሒደቱ እንዲቀጥል መመርያ ተሰጠ፡፡

መመርያውን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶች ከተደረጉ በኋላ በማጠቃለያው መድረክ ለተገኙ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ቡድን አባላትና ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሽያጭ አማካሪ ምክር ቤት (ፕራይቬታይዜሽን ካውንስል) አባላት በመመካከር ቀጣዩን ሥራ እንዲያስኬዱ አሳስበዋል፡፡

ይኼንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን መመርያ ተከትሎ በአንድ ወር ውስጥ የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ጨረታ እንደሚወጣ አንድ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ባለሙያ ለሪፖርተር ያስታወቁ ሲሆን፣ በጨረታውና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ በፍላጎት መግለጫ ወቅት ፍላጎታቸውን ካስታወቁ 12 ኩባንያዎች ጋር በቅርቡ ምክክር እንደሚደረግም ታውቋል፡፡

ጳጉሜን 2 ቀን 2012 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከባለድርሻ አካላትና ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሽያጭ አማካሪ ምክር ቤት (ፕራይቬታይዜሽን ካውንስል)፣ እንዲሁም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር የተደረገውን ውይይት ተከትሎ በየዘርፉ ያሉ ሐሳቦች በፋይናንስ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣንና በኢትዮ ቴሌኮም ከተሰበሰቡ በኋላ ማክሰኞ ጥቅምት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የማጠቃለያ ሪፖርት ቀርቧል፡፡

በዚህ የጥቅምት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ሪፖርት የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይዴክተር አቶ ባልቻ ሬባ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶችን ማድረግ እንደቻሉና በርካታ ጥያቄዎችንና ሥጋቶችን፣ እንዲሁም አስተያየቶችን እንደሰበሰቡ አስታውቀዋል፡፡ መስከረም 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ከባለድርሻና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በነበራቸው የግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይት፣ ከቴሌኮም ዘርፍ ማሻሻያ የፖሊሲ ዓላማዎችን፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት በዘርፉ የተሠሩ ሥራዎችን፣ አዳዲስ ለሚገቡ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎች የሚሸጡ የፍሪኩዌንሲ ሞገድ (Frequency Band)፣ አዳዲስ የሚሰጡ የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃዶች፣ የአገልግሎት ማዳረስ፣ ለቴሌኮም አገልግሎት የሚሰጡ ፈቃዶች ዓይነትና ስፋት፣ የጨረታ ሒደትና የአገር ውስጥ ሮሚንግ (ከአንዱ አገልግሎት ሰጪ ወደ ሌላው የሚደረጉ ጥሪዎች ጥምረት) የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ውይይቶችን ማካሄዳቸውን አስረድተዋል፡፡

ተሳታፊዎች በብዛት ከኢንቨስትመንት አዋጅና ደንብ ጋር ሊቃረኑ የሚችሉ እንደ አገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች ግንባታና የችርቻሮ ሥራን የተመለከቱ ተግባራት፣ ከሚሰጠው የቴሌኮም ዘርፍ ፈቃድ ጋር በተያያዘ በተለይም የመሠረተ ልማት ገንብተው የሚያከራዩ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾችን በተመለከተ፣ ከኢትዮ ቴሌኮም መሠረተ ልማት አቅርቦትና ብቃት ጋር በተገናኘ፣ የተቆጣጣሪ ባለሥልጣኑን አቅም በተመለከተ፣ እንዲሁም ከብሔራዊ ደኅንነት ጋር የተገናኙ ጥያቄዎችን አንስተዋል ያሉት አቶ ባልቻ፣ በባለሥልጣኑ የተሰጡ ምላሾችም እንደነበሩ አውስተዋል፡፡

አሁን ፈቃድ ተሰጥቷቸው ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ አገልግሎት ሰጪዎች የሞባይል ቀፎዎችን ከሲም ካርድ ጋር አጣምረው መሸጥ፣ ከጥገናና ከሽያጭ በኋላ ያሉ ድጋፎችን ማድረግ እንደሚችሉና ለዚህም የሚረዷቸውን ቢሮዎችና የአገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችን መገንባት እንደሚችሉ አቶ ባልቻ ጠቁመው፣ የሞባይል ቀፎ ለብቻው አስመጥተው መሸጥና ማከፋፈል ግን ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተተወው የችርቻሮ ንግድ ውስጥ እንዲገቡ ስለሚያደርግ አይፈቀድም ብለዋል፡፡ እነዚህ የተለመዱ ዓለም አቀፍ አሠራሮች በመሆናቸው፣ እንዲሁም ኢትዮ ቴሌኮምም የሚሠራበት አሠራር ስለሆነ አይከለከልም ብለዋል፡፡ ለትርፍ ላልተቋቋሙና ለተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎት የሚያስፈልጉ አገልግሎቶችን በነፃ እንዲያቀርቡ የሚያደርጉ የሕግ ማዕቀፎች መዘጋጀታቸውንም አቶ ባልቻ አውስተዋል፡፡

በጠቅላላው አምስት ፍሪኩዌንሲ ሞገዶች ዝግጁ መደረጋቸውን የጠቆሙት አቶ ባልቻ፣ ኢትዮ ቴሌኮም ከእነዚህ ውስጥ 100 ሜጋ ኸርዝ፣ እንዲሁም አዳዲሶቹ አገልግሎት እያንዳንዳቸው 80 ሜጋ ኸርዝ ሞገዶች እንደሚሰጧቸው ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ከ800 ሜጋ ኸርዝ ሞገድ እያንዳንዱ አገልግሎት ሰጪ ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ 10 ሜጋ ኸርዝ እንደሚደርሳቸው፣ ከባለ 900 ሜጋ ኸርዝ ሞገድ 10 ሜጋ ኸርዝ ሞገድ ለሌሎች አገልግሎት ሰጪዎች፣ እንዲሁም 15 ሜጋ ኸርዝ ሞገድ ለኢትዮ ቴሌኮም፣ ከ1,800 ሜጋ ኸርዝ ሞገድ 20 ሜጋ ኸርዝ ለሚመጡት አገልግሎት ሰጪዎች የሚሰጡ እንደሆነ፣ እንዲሁም ኢትዮ ቴሌኮም 35 ኸርዝ ሞገድ እንደሚሰጠው አስረድተዋል፡፡ ከባለ 2,100 እና ባለ 2,600 ሜጋ ኸርዝ ሞገድ ደግሞ ሁሉም አገልግሎት ሰጪዎች እያንዳንዳቸው 20 ሜጋ ኸርዝ ሞገድ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

ይሁንና የኢትዮ ቴሌኮም ድርሻ ከፍ ማለቱንና ውድድሩን ፍትሐዊ እንዳይሆን ያደርጋል ያሉ ሥጋት የገባቸው አስተያየት ሰጪዎች እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ባልቻ፣ እያንዳንዱ አዳዲስ አገልግሎት ሰጪ የሚፈልገውን ያህል ካገኘ የኢትዮ ቴሌኮም ድርሻ ሊያሳስበው አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አዳዲስ የሚገቡት የዘርፉ አገልግሎት ሰጪዎች በዲጂታል ፋይናንስ (የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት) ውስጥ አይሳተፉም መባሉ የሽያጩን ዋጋ አይጎዳውም ወይ የሚሉ ሥጋቶች ቀረቡ መሆኑን በመጠቆም፣ አሁንም ድረስ ይኼ ውሳኔ ያልተዋጠላቸው ጠንካራ ተቃውሞ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይኼ ውሳኔ በብሔራዊ ባንክ መጤን ያለበት እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ባልቻ፣ ለኢትዮ ቴሌኮም ፈቅዶ ለሌሎቹ መከልከል ፍትሐዊ አይደለም የሚል መከራከሪያ ስላለ፣ ‹‹ትልቁ የሥጋቶች ምንጭ መሆኑን ዓይተናል፤›› ብለዋል፡፡ ሰዎች ኢትዮ ቴሌኮም ዘንድ ብቻ ለፋይናንስ አገልግሎት የሚሄዱ ከሆነ፣ ለሌሎችም አገልግሎቶች በግድ መመዝገብ ሊጠበቅባቸው ይችላልና ከደንበኞች ወገን ክፍተት እንደማይፈጥር መታየት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ሌላው ትልቁ ጉዳይ ሆኖ ያገኙት የመሠረተ ልማቱ ብቃትና የኢትዮ ቴሌኮም መሠረተ ልማቶች ያንን መሸከም ይችላል ወይ የሚለው እንደሆነ በመግለጽ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ንብረቶች ቆጠራና ይዞታ ታይቶ ይፋ ቢደረግ ያግዛል የሚሉ ጥያቄዎች ቀርበው ነበር ብለዋል፡፡ ‹‹ይኼ አለመታወቁ ከቁጥጥር ሥጋት (Regulatory Uncertainty) ወደ ኢንቨስትመንት ሥጋት (Investment Uncertainty) እየከተተን ነውና መታየት አለበት፤›› ሲሉም አውስተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም አዳዲስ የሚገቡት አገልግሎት ሰጪዎች በድምፅና በአጭር የጽሑፍ መልዕክት፣ እንዲሁም በብሮድባንድ ዳታ በየጊዜው ሊደርሱበት ይገባል ተብሎ የተቀመጠው መጠንና ጊዜ ላይ ጥያቄዎች እንዳሉ አስታውቀዋል፡፡ በተቀመጠላቸው መመርያና በሚቀርብላቸው ስምምነት መሠረት አዲስ የሚገቡት አገልግሎት ሰጪዎች በ12 ወራት 25 በመቶ አካባቢዎችን እንዲደርሱ፣ በ24 ወራት 40 በመቶ፣ በ36 ወራት 55 በመቶ፣ በ48 ወራት 70 በመቶ፣ በ60 ወራት 80 በመቶ፣ በ84 ወራት 90 በመቶ፣ በ120 ወራት 95 በመቶ፣ እንዲሁም በ180 ወራት 97 በመቶ ዕድገት እንዲያስመዘግቡ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በዚህም አግባብ በሁሉም ክልሎችና ገጠራማ አካባቢዎች በአምስት ዓመታት ውስጥ እንዲያዳርሱ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይኼም ይበዛብናል የሚል ሥጋት ከአገልግሎት ሰጪዎች ዘንድ እንደተደመጠ ተናግረዋል፡፡

የአገልግሎት ማስፋፊያ ለማድረግም የዩኒቨርሳል አክሰስ ፈንድ እንደሚቋቋም በተገለጸው መሠረት፣ እያንዳንዱ አገልግሎት ሰጪ ለዚህ ዓላማ የሚውል ከዓመታዊው ገቢ ላይ 1.5 በመቶ ወደ ፈንዱ ገቢ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡

ከብሔራዊ ደኅንነት ጋር በተያያዘ እየተነሱ ያሉ የሥጋት ጥያቄዎች መኖራቸውን በመጥቀስ የሚጠረጠር ኔትወርክ፣ አጠራጣሪና የሚፈለግ ግለሰብ ካለ በየትኛውም የዓለም ክፍል እንደሚደረገው ሁሉ ሕጋዊ ጠለፋ (Lawful Interception) እንደሚደረግና ለዚህ ፈቃደኛ ያልሆኑ አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃዳቸውን እስከ መሰረዝ የሚያደርሱ ቅጣቶች ይጣሉባቸዋል ብለዋል፡፡ ለዚህ ይረዳ ዘንድም የሲም ካርድ ምዝገባ ሥርዓቱን ጠንካራና የተደራጀ አድርጎ መዘርጋት ያሻል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ይሁንና ከሁሉም በላይ ወሳኙ የአቅም ግንባታ ስለሆነ በሳይበር ዘርፉ ይኼንን በማድረግ የመረጃ ለውውጦችን ደኅንነት ለማረጋገጥ፣ ከመጀመርያ እስከ መዳረሻ ድረስ ቴክኖሎጂን መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮምን የውይይት ግኝቶች ያቀረቡት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ከ210 የዘርፉ ተወካዮች ጋር በአካል ውይይቶችን ያደረጉ መሆኑን በመግለጽ፣ ተወያዮቹ የዘርፉ መከፈት የተሻለ ውድድርንና የግል ዘርፍ ተሳትፎ ያመጣል፣ የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማትን ያፋጥናል፣ የአገልግሎትና የመሠረተ ልማት ጥራትና የሰው ኃይል ልማት ያመጣል የሚሉ ከዘርፉ መከፈት ይገኛል የሚሏቸው ተስፋዎች እንዳስታወቁ ተናግረዋል፡፡

ከተነሱት ጥያቄ መካከል ከኢትዮ ቴሌኮም የ40 በመቶ ድርሻ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ለመንግሥት የተለያዩ ዘርፎች ነው የሚውለው? ወይስ ኢትዮ ቴሌኮምን ለማጠናከር የሚል? እንደሚገኝበትና ለዚህም መንግሥት ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

የቴሌኮም አገልግሎት መሠረተ ልማት ዘርጊና አከራይ ኩባንያዎችን በተመለከተም ብዥታ መኖሩን በመጠቆም፣ አሁን የሚገቡ አገልግሎት ሰጪዎች ለአገልግሎት የሚያስፈልጋቸውን መሠረተ ልማት የመዘርጋት መብት እንዳላቸው ነገር ግን መሠረተ ልማት ዘርግቶ ማከራየት ብቻ ሥራው የሆነ ድርጅት እንደማይኖር አስረድተዋል፡፡ የዚህ ዓይነቱ ሥራ ኢትዮ ቴሌኮም የሠራውን የመሠረተ ልማት ዝርጋታ በመጠቀምና አነስተኛ አዳዲስ መሠረተ ልማቶችን በመዘርጋት የሚሠራ ስለሚሆን አያዋጣም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በዘርፉ ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር ያደረጉት ውይይት ፍሬያማ እንደነበር በማስታወቅ፣ በተለይ ከሚሰጡ የአገልግሎት ፈቃዶችና ከአገር ደኅንነት ጋር በተያያዘ ሥጋቶች መነሳታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በማጠቃለያው በሰጡት ማብራሪያና መመርያ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የጋበዘው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችን እንደሆነና ባንኮች ከመረጡት አገልግሎት ሰጪ ጋር መሥራት እንደሚችሉ በመግለጽ፣ አገልግሎት ሰጪዎች ግን ባንክን ተክተው መሥራት የለባቸውም ብለዋል፡፡

የሚሰጠው ፈቃድም ከብሔራዊ ጥቅም አንፃር እየታየ በመሆኑ፣ ባንኮች ላለፉት 20 ዓመታት ሲሠሩ ቆይተው እነሱ ሳይጠነክሩና ሳይዘጋጁ መጉዳት ስላልተፈለገ የተሰጠ ውሳኔ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የደኅንነት ጉዳይ በተመለከተ አገሮች እየተጠቁና እየተከላከሉ አቅም እንደሚያሳድጉ በማሳሰብ፣ ኢትዮጵያም የአቅም ግንባታ ላይ በማተኮር እየሠራች እንደምትገኝ ገልጸው፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲና በመከላከያ ሠራዊት ሥር የተቋቋመ የሳይበር ኃይል መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡

ሕጋዊ ጠለፋ በሕግ የተፈቀደ እንደሆነ በማስታወቅም፣ እነዚህ አገልግሎት ሰጪዎች መምጣታቸው እንዲያውም በአገሪቱ ያለውን ክፍተት ለማየት ይረዳል ብለዋል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን መቶ በመቶ በዲጂታል ዓለም ደኅንነቴ የተጠበቀ ነው ለማለት እንደማይቻል በማሳሰብ፣ የተቋም ዝግጅት እየተደረገ ሥጋቱን ለመቀነስ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች