Wednesday, June 7, 2023

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተጀመረው ነዋሪውን የማስታጠቅ ዘመቻና ክርክሮቹ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በሚከሰቱ ግጭቶች፣ አመፆችና ጥቃቶች ንፁኃን መሞታቸውና ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው የተለመደ ክስተት መሆን ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይባስ ብሎም የፀጥታ አካላት ተሰማርተው ባሉበት ሥፍራ የሚፈጠሩ ግጭቶች በፍጥነት መረጋጋት ሲገባቸው በተቃራኒው የሚባባሱበትና የበርካቶችን ሕይወትም የሚቀጥፉበት ሁናቴ እየተበራከተ መጥቷል፡፡

ዜጎች ራሳቸውን መከላከል የማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ሳሉ በሚሰነዘርባቸው ጥቃቶች ሳቢያ የሚደርስባቸውን ሰቆቃ ሃይ ባይ አጥቶ እየገዘፈ ይገኛል፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፀጥታ አካላት በተሰማሩባቸው ሥፍራዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች እየተባባሱ መምጣታቸው ደግሞ የነዋሪዎችን መከራ አባብሶታል፡፡ ይኼንንም መንግሥት ያመነባቸው ክስተቶች ያሉ ሲሆን፣ በተለይም የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በሻሸመኔ፣ ባቱ፣ ሐረርና ባሌ አካባቢዎች የተፈፀሙ ጥቃቶች የዚህ መሰሉ ክስተት ማሳያ ናቸው፡፡ የድምፃዊውን ግድያ ተከትሎ በተፈጠሩ ግጭቶችና ጥቃቶች ከ230 በላይ ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ ከአራት ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙ በወቅቱ መገለጹ ይታወሳል፡፡ መንግሥት ጥቃት አድርሰዋል ብሎ የጠረጠራቸውን ከ3,500 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የገለጸ ሲሆን፣ በርካቶች ላይም ክስ ተመሥርቶ ክሳቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙም ይታወቃል፡፡

መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት የፀጥታ አካላትን እያጠናከረ እንደሚገኝና በሥልጠናና በሕግና ዶክትሪን እያደራጀ እንዳለ ቢያስታውቅም ይኼንን በሚያሳይ መልኩ ግጭቶችና ጥቃቶች ሳይከሰቱ ተንብዮና ተንትኖ የመከላከልም ሆነ ሲከሰቱ የከፋ ጉዳት ሳያስከትሉ የማስቆም ብቃታቸው እስካሁን በተግባር አልተገለጸም የሚሉ ትችቶች በተደጋጋሚ ይደመጣሉ፡፡ ግጭቶች በተከሰቱባቸውና ጥቃቶች በተፈጸሙባቸው ሥፍራዎች፣ የፀጥታ ኃይሎች ቀድመው ተሰማርተው ተደጋጋሚ ግጭቶችና ጥፋቶች መከሰታቸውንም ተቺዎች እንደማሳያ ይጠቅሳሉ፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በንፁኃን ላይ በተደጋጋሚ የተፈጸመው ጥቃት የዚህ አንዱ መገለጫ ሲሆን፣ በክልሉ በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ ኤጳር ቀበሌና በወንበራ ወረዳ መልካን ቀበሌ ከጳጉሜን 2 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ መስከረም 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ቢያንስ ሁለት ጥቃቶች መፈጸማቸውን እንዲሁም መስከረም 15 ቀን 2015 ዓ.ም. በመተከል ዞን ማንኩር ከተማ በድጋሚ ጥቃት መፈጸሙ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መስከረም 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እየደረሰ ያለው ጥቃት ችግሩ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ኮሚሽኑ ‹‹በሕገ መንግሥቱና እንዲሁም ኢትዮጵያ ተቀብላ ባፀደቀቻቸው የቃል ኪዳን ሰነዶች ማለትም በአፍሪካ የሰብዓዊና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር፣ በዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን (ICCPR) እና በሌሎች አግባብነት ባላቸው የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶች የተደነገጉትን በሕይወት የመኖር መብቶች እንዲከበሩ ይጠይቃል፤›› በማለት ጥሪ አቅርቦ ነበር፡፡

በተጨማሪም ‹‹በክልሉ ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ጥቃቶች በተደጋጋሚ ማጋጠማቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት ገለልተኛ፣ ፈጣንና ውጤታማ ምርመራዎችን በማካሄድ ግድያው በተከሰተባቸው ሁኔታዎች ላይ የጥፋተኞችን ተጠያቂነት እንዲያረጋግጡ፤›› ያለው ኮሚሽኑ፣ መሠረታዊ የሆነው በሕይወት የመኖር መብት ይረጋገጥ ዘንድ የሚመለከታቸው የክልሉ የመንግሥት አካላት እንዲሠሩ ሲል አሳስቧል፡፡

በመጀመሪያው ዙር ጥቃት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ባይገለጽም በሁለተኛው ዙር ጥቃት ግን ከ15 ሰዎች በላይ መሞታቸውን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በወቅቱ አስታውቋል፡፡

በቅርቡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ከክልሉና ከመተከል ዞን አመራሮች ጋር በክስተቶቹ ዙሩያ ውይይት ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ ‹‹በዚህ አካባቢም ሆነ በሌሎች ሰላምና ፀጥታን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመፍጠር የሴረኞችን ገመድ መበጣጠስ፣ ጠንካራ የሕግ የበላይነት ማስከበር ኅብረተሰቡ ራሱን የመከላከል አቅም እንዲኖረው ማድረግ ወሳኝ ተግባር ነው፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡ በማከልም ‹‹የአካባቢው ነዋሪ ራሱን አደራጅቶ አስፈላጊውን ትጥቅ ታጥቆ የጠነከረ የመከላከል አቅም መገንባት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፤›› ብለው ነበር፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጥቃቶችን እየሰነዘረ ያለው በግልጽ ባይነገርም፣ በተለይ የአማራና የአገው ብሔር አባላት የጥቃቱ ሰለባ በመሆናቸው የተቆጡ የሚመስሉት የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ‹‹እነሱ መግደል ብቻ ሳይሆን መሞት ምን ማለት እንደሆነም ሊያዩ ይገባልና ይኼንኑ እናሳያቸዋለን፤›› በማለትም መስከረም 16 ቀን 2013 ዓ.ም. በመግለጫ ተናግረው ነበር፡፡ ‹‹ከዚህ በኋላ መሞት ብቻ ሳይሆን ገዳዮች ሞት ምን ያህል አስከፊና መራር እንደሆነም የሚቀምሱበት ጊዜም ይሆናል፤›› በማለት ለመስቀል በዓል እንኳን አደረሳችሁ ካሉበት መልዕክት ጋር አባሪ አድርገው ተናግረዋል፡፡

የሁለቱን ባለሥልጣናት ንግግሮች ተከትሎ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን 3,560 ነዋሪዎች ትጥቅ የማስታጠቅና በማደራጀት የሚሊሻ ሥልጠና እንደሚሰጣቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል 1,282 ሰዎች የሦስት ቀናት ሥልጠና ተሰጥቷቸው እንዲታጠቁና ራሳቸውን እንዲከላከሉ መደረጉ ተነግሯል፡፡ የተቀሩት በመከላከያ ሠራዊቱና በክልሉ የፖሊስ ኃይል እየሠለጠኑ ይገኛሉ፡፡

ይሁንና ይኼ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የማስታጠቅ ዕርምጃ በተለያዩ ሰዎች ዘንድ ግርታን የፈጠረ ሲሆን፣ መንግሥት የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅና ዘላቂ ለማድረግ ለምን ይኼንን መንገድ መረጠ ሲሉ በርካቶች እየጠየቁ ይገኛሉ፡፡

አንድ ሪፖርተር ያናገራቸው የሰላምና ደኅንነት ባለሙያና ተንታኝ እንደሚሉት፣ ችግር በተፈጠረበት ሁሉ የአካባቢውን ሰው እያስታጠቁ ራሳችሁን ጠብቁ ማለት የመንግሥትን ኃይልን በብቸኝነት የመቆጣጠር (Monopoly of Violence) ይሸረሽራል ሲሉ ሥጋታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ሰዎችም በፀጥታ መዋቅሩ ላይ ያላቸውን አመኔታ እንዲሸረሸር ሊያደርግ ይችላል ብለዋል፡፡

‹‹መንግሥት ራሳችሁን ተከላከሉበት ብሎ የሰጣቸውን ትጥቅ ለሌላ ዓላማ ቢያውሉትስ? እነዚህ የታጠቁ ኃይሎች ከዕዝ ውጪ ቢሆኑስ ምን ሊደረግ ነው?›› ሲሉ ባለሙያው ይጠይቃሉ፡፡

በኢትዮጵያ አንዱ የሰላምና ደኅንነት ሥጋት የሚደቅነው የትጥቅ መብዛት እንደሆነ በመጥቀስ ትጥቅ ማስታጠቅ ከችግሩ ጋር የማይጣጣም ዕርምጃ ነው በማለት ባለሙያው ይተቻሉ፡፡ በየክልሉ ያሉ ሕዳጣን በሙሉ መንግሥት ሊጠብቀኝ አልቻለምና ያስታጥቀን ማለት ከጀመሩ መጥፎ ልማድን ይፈጥራል፣ ስለዚህም በጥንቃቄ ነው መታየት ያለበት ሲሉም ይመክራሉ፡፡

እነዚህ ታጣቂዎች ሲጠናከሩ ወረዳውን ቢቆጣጠሩ ምን ሊፈጠር እንደሚችል የሚጠይቁት ባለሙያው መንግሥት ሳያስበው በገዛ እጁ የጦር አበጋዞችን እየፈጠረ አለመሆኑን ሊያስተውል ይገባል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ፡፡

ከዚህ ዕሳቤ በተቃራኒው የቆሙት የአብን አባልና የቀድሞ ሊቀ መንበር እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚፈጸሙ ክስተቶችን በቅርበት የሚከታተሉት ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)፣ ‹‹አቶ ደመቀ መኰንን ይታጠቁ ማለታቸውን ተከትሎ ለምን ጩኸት በረከተ? ጥቃቱ እየተፈጸመ ያለው ቀድሞውኑም ታጣቂ የነበረው የኅብረተሰብ ክፍል ትጥቅ እንዲፈታ በመደረጉ ነው፡፡ የሕዝብን ደኅንነት የማስጠበቅ ክፍተት ከተፈጠረ ዜጎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ማስታጠቅ የመንግሥት የደኅንነት ማስጠበቅ ተግባር አካል ነው፤›› ሲሉ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ለማስታጠቅ የተላለፈውን ውሳኔ ይደግፋሉ፡፡

የጥቃቶቹ ገፊ ምክንያቶች የአካባቢው ማኅበረሰብ ያልታጠቀና ያልተደራጀ ስለነበር እንደሆነ የሚጠቅሱት ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) የመንግሥትን አቅም ማጠናከር ትልቁና በትኩረት ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊ የቆዳ ስፋት ያላትና ከ100 ሚሊዮን ሰዎች በላይ የሚኖሩባት በመሆኗ በፀጥታ ኃይሎች ብቻ ሰላምና ደኅንነቷን ማስጠበቅ አይቻልም ይላሉ፡፡

‹‹ማስታጠቅና ማደራጀት ምክንያታዊ ነው ብዬ አስባለሁ፤›› ሲሉም ደሳለኝ (ዶ/ር) ይከራከራሉ፡፡

ነገር ግን የፀጥታና ደኅንነት ዋስትና መስጠት የመንግሥት ኃላፊነት በመሆኑ ማስታጠቅና ማደራጀቱ ብቸኛው መፍትሔ ነው ብለው እንደማያምኑ ይናገራሉ፡፡

ኤትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ዓመታት የተፈጠሩ ተቋማት፣ የሕግ ሥርዓቶች፣ እንዲሁም ቋንቋን መሠረት ያደረገው ፌዴራሊዝም ማንነትን መሠረት ላደረጉ ጥቃቶች አስተዋጽኦ አድርገዋል ብለው የሚያምኑት ደሳለኝ (ዶ/ር)፣ ለዚህም የቤኒሻንጉል ጉሙዝና የኦሮሚያ ክልሎችን ሕገ መንግሥቶች እንደ ማሳያ ያቀርባሉ፡፡

‹‹ሕገ መንግሥቶቹ ውስጥ የክልሉ ባለቤትነትን በተመለከተ የተቀመጡ ድንጋጌዎች በቁጥር በርከት ያሉ የኅብረተሰብ ክፍልን አገርና ድምፅ አልባ አድርገዋል፡፡ ስለዚህም፣ የዚያ አካባቢ ነባር ናችሁ በተባሉት ብሔሮች ዘንድ የአስተሳሰብ መዛባት በማምጣቱ አገራችን ነውና እናንተ ሂዱ የሚሉ አስተሳሰቦች ተፈጥረዋል፤›› ይላሉ፡፡

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ መንግሥታዊ ቸልተኝነት ለእንዲህ ያሉ ጥቃቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ሲሉም ይከራከራሉ፡፡ የፀጥታ ኃይሎች ጥቃቶች ሲፈጸሙ እየተመለከቱና እያዩ ‹‹አልታዘዝንም›› ማለትና ከአቅማቸው በላይ ሲሆን ደግሞ ሰዎችን ለጥቃት ዳርጎ መሸሽ ተለምዷል በመሆኑም መንግሥት ዋነኛ ሥራው የሆነውን የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ተግባር ሊወጣ አልቻለም ሲሉ ይተቻሉ፡፡

ሪፖርተር በአጠቃላይ የግጭት አፈታት ዙሪያ ያነጋገራቸው የደኅንነት ባለሙያው ግን ለግጭቶች ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት ከታሰበ የመንግሥትን የመከላከልና ግጭቶችን በአፋጣኝ የማስቆም አቅምን ማሳደግ ዓይነተኛ መፍትሔ ነው ይላሉ፡፡ በርካቶች ሕግ ማስከበር ከወታደራዊ ጣልቃ ገብነትና ዕርምጃ ጋር እንደሚያገናኙት የሚያወሱት ባለሙያው፣ ሕግ የማስከበር ሥራ ግን የፖለቲካና የሕግ መፍትሔዎችን የማቅረብ ጥቅል ተግባር እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ይኼም ማለት ዕርቅን፣ ማበረታቻንና ምሕረት ማድረግን ሊያካትት እንደሚችል በመጥቀስ፣ አጥቂዎች የሚባሉት በመንግሥት ላይ እምነት ኖሯቸው ወደ ሰላም እንዲመጡ የሚቻል ከሆነም ይህንን ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ መክረዋል፡፡

‹‹ሰላምን በወታደር ማምጣት አይቻልም፡፡ የወታደር ስምሪት ሲቀነስ አጥቂው ተመልሶ ይመጣል፤›› በማለትም ይህ አማራጭ ጊዜ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

ማስታጠቅም ወታደር ማሰማራትም ዘላቂ መፍትሔ ስለማይሆኑ፣ ከአካባቢው አስተዳደር ጋር በማጣጣም የአጥቂዎቹን ማንነት በመለየትና ፍላጎታቸውን በማወቅ ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ ማድረግ የተሻለ እንደሚሆን ይገልጻሉ፡፡

‹‹ታጥቆና ተደራጅቶ ራሱን መጠበቅ የመንግሥትን የፀጥታ መዋቅር ክፍተት ይሞላል፣ ከታጠቁም ማንም አይደፍራቸውም፤›› በማለት የሚከራከሩት ደሳለኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በአግባቡ ከተመራ በየአካባቢው ሕዝቡ ፀጥታን አስጠብቆ ወደ ሰላም ያመራል ብለው ያምናሉ፡፡ ትጥቁ ለጥቃት አድራሾች ማስፈራሪያና ጥቃት እንዳይፈጽሙ ከማድረግ (Deter) ባለፈም፣ በጥቃቶቹ የሚፈጠሩትን ሞቶችና ጉዳቶች ቁጥር መቀነስም ያስችላል ይላሉ፡፡

‹‹የአካባቢዎችን ነዋሪዎች አቅም ማጠናከር ርካሽና ፈጣን የሆነ መፍትሔ በመሆኑ ይህንኑ አማራጭ ከመከተል በዘለለ ሌላ መፍትሔ የለም፤›› በማለትም ይከራከራሉ፡፡ ይሁንና ለዘላቂ መፍትሔ፣ የኢትዮጵያ የፀጥታ መዋቅር አሠራር እንደገና ሊፈተሽ ይገባል ብለዋል፡፡

ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. በፓርላማ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተደጋጋሚ እየደረሰ ካለው ጥቃት ጀርባ ያለው ዋና ዓላማ፣ ወደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚወስደውን መንገድ ለመቆጣጠር ያለመ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በክልሉ የሚፈፀሙ ጥቃቶች በውጭና በውስጥ ኃይሎች ቅንጅት የሚፈጸም እንደሆነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ችግር ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር እንደሚገናኝ ጠቁመዋል።

ጥቃቱ በሚያጋጥምባቸው ሥፍራዎች የመኪና መንገድ ባለመኖሩ፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጥቃት የተፈጸመበት ቦታ ለመድረስ እስከ 7፡00 ሰዓት ድረስ በረዣዥም ሳር ውስጥ በእግራቸው እንደሚጓዙ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ጥቃቱ የሚፈጸመው በቀስት ነው። የመከላከያ ሠራዊቱ በረዣዥም ሳር ውስጥ ጥቃት አድራሾችን ለመያዝ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ ብዙ መስዋዕትነት ከፍለዋል፤›› በማለት የአካባቢውን ለሕግ ማስከበር አስቸጋሪነት ገልጸዋል፡፡

አጥቂዎቹ መሠረታቸውን ያደረጉት በግድቡ አቅራቢያ በምትገኝ ‹‹ብሉ ናይል›› በተባለች የሱዳን ግዛት ውስጥ እንደሆነና በዚያም በስም ባልጠቀሷቸው የውስጥና የውጭ አካላት ሥልጠናና ሌሎች ድጋፎችን ወስደው በንፁኃን ላይ ጥቃት እንደሚከፍቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ስለዚህም ‹‹ችግሩ ከምንጩ ካልደረቀ ዳግም ችግር ይከሰታል፤›› ብለዋል፡፡

ይኼ በእንዲህ እንዳለ፣ የቤኒሻንጉል እንቆቅልሽ መልስ ሳያገኝ በደቡብ ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ጉዳ ፈርዳ ወረዳ በንጹሐን ላይ በታጠቁ ኃይሎች በተፈጸመ ጥቃት ከ30 በላይ የሚሆኑ ንጹኃን ዜጎች መሞታቸው ታውቋል፡፡ ከነዋሪዎቹ ጋር ለመወያየት የአገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሐመድ፣ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬሕይወት ሽባባው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል እንዳሻው ጣሰው እንዲሁም የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ወደ ቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ አቅንተዋል፡፡

በቤንች ማጂ ዞን ጉራፈርዳ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ መንግሥት በዚህ አካባቢም ነዋሪዎችን የማስታጠቅ አማራጭን ከተከተለ እየሄደበት ያለው የግጭት አፈታት መንገድ አገሪቱን ለአደጋ ይዳርጋል የሚሉ አስተያየቶች እየተደመጡ ይገኛሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ከላይ በተጠቀሰው አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል የጦር መሣሪያ መታጠቅን እንደመፍተሔ ቆጥረው በራሳቸው መንገድ መታጠቅ ቢጀምሩና መንግሥት ይህንን ለማስቆም ዕርምጃ ቢወስድም ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው እንዲሁም መንግሥትን አጣብቂኝ ውስጥ የሚከት በመሆኑ የሕግ ማስከበር ተግባር ከመንግሥት ውጪ ለሌላ አካል መስጠት የለበትም የሚሉ ክርክሮችም በተመሳሳይ እየተነሱ ይገኛሉ፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -