Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የከተማ ነዋሪዎች የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ4,600 ዶላር በላይ እንዲደርስ ይደረጋል ተባለ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በከተሞች 4.4 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት ታቅዷል

የከተማ ልማት ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ሰፈራ መርሐ ግብር (UN-Habitat) ጋር በመተባበር፣ አገር አቀፉን የአሥር ዓመት የልማት መሪ ዕቅድ ይፋ ሲያደርግ፣ የከተሞች የነፍስ ወከፍ ገቢ 4,689 ዶላር እንዲደርስ መታቀዱን አስታወቀ፡፡  

መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ከ50 በላይ ድርጅቶች በጋራ በመሆን የከተማ፣ የኢንዱስትሪ፣ የገበያ፣ የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ብሎም የመሠረተ የልማት አግልግሎቶች ላይ በቅንጅት ለመሥራት ሚኒስቴሩ ስምምነት መፈጸሙን ይፋ አድርጓል፡፡

ጥቅምት 11 ቀን 2013 ዓ.ም. የአሥር ዓመት ዕቅዱን ይፋ ያደረገው ሚኒስቴሩ፣ ከ2013 እስከ 2022 ዓ.ም. ላለው ጊዜ የተዘጋጀው ዕቅድ፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የከተማ ነዋሪዎችን የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ በሚያደርጉ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረጉን የከተማ ልማት ኮንስትራክሽን ሚኒሰቴሯ አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር) አብራርተዋል፡፡ በዘርፉ ከተሰማሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጥምረት ለመሥራት ዓምና በጥቅምት ወር የተጀመረው የምክክር መድረክ ዘንድሮም መቀጠሉን አስታውሰው፣ ተቀራርቦ መሥራት እንዲቻል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ የዓለም ባንክ እንዲሁም የተመድ ተቋማት በጋራ በሚያመቻቹት የአሠራር ሥርዓት መሠረት በከተማ ልማት ጉዳዮች ላይ ለመሥራት ስምምነት መፈጠሩን አስታውቀዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በአሥር ዓመታት ውስጥ እተገብራቸዋለሁ ካላቸውና የዕቅዱ መነሻ ካደረጋቸው መካከል የከተማ መሬትና ተደራሽ የቤት ልማት፣ የከተማ ለከተማ ትስስር፣ የገጠርና ከተማ መስተጋብር ተጠቅሰዋል፡፡ ፈጣን የከተማ ሕዝብ ዕድገት በሚኖርበት ጊዜ ሊታዩ የሚችሉ ተስፋዎችና ሥጋቶች፣ የገጠር የልማት ማዕከላት ወደፊት ከተሞች እንደሚሆኑ ማድረግ ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ተብለዋል፡፡

በመድረኩ የከተማ ሕዝብ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ከተሞችን በማስፋፋት፣ በገጠር ያለውን የኢኮኖሚ ዕድገት በከተማም መፍጠር የሚቻልበትን መንገድ የሚፈጥር ዕቅድ መንደፉን ሚኒስትሯ ተጠቅሰዋል፡፡ በዚህ መሠረት በከተማና በገጠር ተመጋጋቢ ሥራ በመሥራት የክትመት (የከተሞች መስፋፋት) ደረጃ ከ35 በመቶ በላይ እንዲሆን፣ የከተማ ነዋሪ የነፍስ ወከፍ ገቢው በ2022 ዓ.ም. 4,689 ዶላር እንዲደርስ ለማድረግ መታቀዱ ተገልጿል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ከተሞች ለአገር ኢኮኖሚ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በ2012 ዓ.ም. 58 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ በ2022 ዓ.ም. ወደ 73 በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል፡፡

በ2012 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት 102 ሚሊዮን እንደነበር ሲገመት፣ ከዚህ ውስጥ በከተሞች እንደሚኖር የሚታመነው ሕዝብ ብዛትም 22 ሚሊዮን ተገምቷል፡፡ የክትመት ደረጃም 22 በመቶ እንደነበረ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ አኃዝ በ2022 ዓ.ም. የሚያሳየው ለውጥ ምን ያህል እንደሚሆን ተመላክቷል፡፡ የሕዝብ ብዛት መጠን 126 ሚሊዮን እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡

ከዚህ ውስጥ በከተሞች የሚኖረው ሕዝብ ብዛት 44 ሚሊዮን እንደሚደርስና፣ የክትመት ደረጃም 35 በመቶ ሊደርስ እንደሚችል ሚኒስቴሩ በጥናቱ አስቀምጧል፡፡ የከተማ ሕዝብ የነፍስ ወከፍ ገቢ አሁን ካለው 2,584 ዶላር አኳያ፣ በ2022 ዓ.ም. መጨረሻ 4,689 ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ተገምቷል፡፡

ከተሞች ለአገር አቀፍ ኢኮኖሚ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በአሥር ዓመቱ ዕቅድ ውስጥ ከተካተቱ ጉዳዮች ቀዳሚው ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በከተሞች የሚታየው የድህነት መጠን 15 በመቶ ነው፡፡ ይህንን ወደ አምስት በመቶ ዝቅ ለማደረግ ታስቧል፡፡ የከተሞች የሥራ አጥነት መጠንም አሁን ካለው 19 በመቶ ወደ ዘጠኝ በመቶ ለመቀነስ መታቀደኑን ሚኒስትሯ አስታውቀዋል፡፡ የአሥር ዓመቱ ዕቅድ በከተሞች የኢኮኖሚ ልማት፣ በከተማ ፕላን፣ ለልማት የሚውል የከተማ መሬት አቅርቦት፣ የቤቶች ግንባታና አቅርቦት ብሎም ግብይት፣ የከተሞች መልካም አስተዳደርና ሌሎችም በዕቅዱ ከተካተቱ ዓብይት ጉዳዮች መካከል ናቸው፡፡

ከከተማ ፕላን አኳያም በአገር አቀፍ የከተሞች ስፓሻል የልማት ፕላን፣ የከተማ ልማትን በሚያቀናጅ የክልል ልማት ፕላን፣ የከተሞችን ኢኮኖሚያና ማኅበራዊ የልማት ቅንጅትን መሠረት ያደረገ የትስስር ፕላን መዘጋጀቱ ተመላክቷል፡፡ ይህም እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ብቻ የሚታየውን ሰፊ የልማት ዕድገት ሌሎች ከተሞችም መሥራት የሚችሉበትን መንገድ የሚያመላክት ዕቅድ ሚኒስቴሩ ነድፏል፡፡ በዚህም በከተሞች 4,000 እንዲሁም በገጠር 14,000 የልማት ማዕካላትን በመፍጠር በጠቅላላው ለ18,000 ማዕከላት ከአገራዊና ክልላዊ ስፓሻል ፕላን ጋር በተናበበ ሁኔታ በተዘጋጀ መሪ ፕላን እንደሚተገበር ተብራርቷል፡፡

ከከተማ መሬት ልማትና አቅርቦት አኳያም 60 በመቶ ከተሞች የመሬት ሀብታቸው ምን ያህል እንደሆነ ሙሉ በሙሉ የሚያወቁበትና የሚያሰተዳድሩበት ሥርዓት እንደሚፈጠር፣ ለመሬት ፍላጎት 75 በመቶ ምላሽ የሚሰጥ አቅርቦት እንዲኖር ይደረጋል ተብሏል፡፡

የማኅበረሰቡ አንገብጋቢ ችግር የሆነውን የቤቶች አቅርቦት በተመለከተም ዕቅዱ ምላሽ ለመስጠት ያሰበባቸውን መንገዶች ሚኒስቴሩ አስቀምጧል፡፡ በከተሞች የቤት አቅርቦት መጠን አሁን ካለበት 64 በመቶ ወደ 80 በመቶ ማሳደግን መሠረት በማድረግ፣ 4.4 ሚሊዮን ቤቶች እንዲገነቡ ማድረግ የመንግሥት ዕቅድ ነው፡፡ በመሆኑም 20 በመቶውን በመንግሥት፣ 35 በመቶውን በማኅበራት፣ 15 በመቶውን በግለሰቦች፣ አሥር በመቶውን በሪል ስቴት ድርጅቶች፣ 15 በመቶውን ግለሰቦች በሚያቋቁሙት የሕዝብ የቤት አቅርቦት የሽርክና ማኅበር እንዲሁም አምስት በመቶውን ቤቶች በሽርክና በማስገንባት የቤት አቅርቦት ችግርን የሚፈታ ዕቅድ እንደነደፈ ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም በገጠር ማዕክላት 2.8 ሚሊዮን ደረጃቸውን የጠበቁ ቤቶች ይገነባሉ ተብሏል፡፡

ከከተሞች የመሠረተ ልማት ሥራዎች ባሻገር የሴቶች፣ የወጣቶች፣ የከተሞች ደርቅ ቆሻሻ አገልግሎት ሽፋን፣ የአረንጓዴ ልማትና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስኮች ላይ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በስፋት የሚሳተፍባቸው የልማት ዘርፎች እንደሚሆኑ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች