Sunday, May 19, 2024

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፍትሕ ሥርዓቱና የሕግ የበላይነት እንዲከበር ማሳሳቢያ የሰጡበት የፓርላማ ውሎ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በኮሮና ወረርሽኝ መከስት ምክንያት ምርጫ ተደርጎ ለአዲስ ምክር ቤት ሥልጣን ማስረከብ ባለመቻላቸው፣ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ በተሰጠውሕገ መንግሥት ትርጓሜ፣ ምርጫ ተደርጎ ሥልጣን እስከሚያስረክቡ በኃላፊነት እንዲቆዩ በመወሰኑ፣ ተጨማሪ የሥራ ዘመናቸውን መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሄዱት የጋራ ስብሰባ በይፋ ጀምረዋል። 

በሥርዓቱ መሠረት በሥራ ዘመናቸው መክፈቻ የጋራ ስብሰባ ላይ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሣህለወርቅ ዘውዴ ተገኝተው ምክር ቤቶቹና ሥራ አስፈጻሚው መንግሥት በዓመቱ ትኩረት ሊያደርገለባቸው ይገባል ያሏቸውን ዓበይት ተግባራት የተመለከተ ንግግር አድርገዋል። 

በምክር ቤቶቹ የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ መሠረት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ፕሬዚዳንቷ ባስቀመጧቸው ዓበይት የትኩረት ተግባራት ላይ የመንግሥታቸውን አቋም ማሰማት ይጠበቅባቸዋል። 

በዚህም መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልዩ ስብሰባ ላይ የተገኙ ሲሆንበወቅቱም የምክር ቤቱ አባላት በፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የሥራ አቅጣጫን የተመለከተ ንግግር ላይ ተመሥርተው፣ የሥራ አስፈጻሚውን አካል አቋም በመጠየቅ ምላሽ አግኝተዋል። 

በዕለቱ ሥራ አስፈጻሚውን መንግሥት ለሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/) የምክር ቤቱ አባላት ካነሷቸው የማብራሪያ ጥያቄዎች መካከልም የሕግ የበላይነትንና የፍርድ ቤቶችን ነፃነት በማስከበርእንዲሁም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በመቅረፍ ረገድ ምን እንዳቀዱ ማብራሪያ ጠይቀዋል። 

የሰላም አስከባሪ ተቋማት የተደራጁበት መንገድ ችግር ስለነበረበት ከለውጡ በኋላ እነዚህ ተቋማት ተጠናክረው እንዲወጡ ትኩረት የተሰጠበት ጊዜ እንደነበር ገልጸዋል።

የፀጥታ ኃይሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት መመርያው ከአንድ ፖለቲካ የወጣ፣ አገርን ታሳቢ ያደረገ፣ የማድረግ አቅሙ ከፍ ያለ፣ በሥልጠና የዳበረ፣ አዳዲስ ጉልበት የጨመረ አዳዲስ ትጥቅ የታጠቀ፣ እንዲሆን በጣም ሰፊ ሥራ መሠራቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ 

ሕግ አስከባሪ ተቋማት ያለባቸው ውሱንነት እንዲሻሻል፣ ታራሚዎችና ጉዳያቸው በሕግ የተያዘ አካላት ሰብዓዊ መብታቸው እንዲጠበቅ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።

ባለፉት ጊዜያት በየሥፍራው የተካሄዱ ሰላምን የማደፍረስ ሥራዎች መደበኛውን የሕግ ክትትል ጠብቀው እየተጓዙ እንደሆነ ነገር ግንየኮሮና ወረርሽኝ መከሰት በፍርድ ቤቶች ላይ ጫና በማሳደሩና የዳኞች እጥረትም በመኖሩ፣ በተፈለገው ፍጥነት ውሳኔ አለመሰጠቱን ጠቅሰዋል።

ይህንንም ችግር ለመፍታት በቅርቡ በርካታ ዕጩ ዳኞች ለምክር ቤቱ ቀርበው መሾማቸውን ጠቅሰዋል። 

የፍትሕ ሥርዓቱ ከመንጠፍ ወጥቶ መስጠት የሚችል እንዲሆን ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩተቋማቱ ያለ ማንም ተፅዕኖ ራሳቸውን ችለው ለመቆምና ገለልተኛ ለመሆን እንዲችሉ ተስፋ ሰጪ ሥራዎች ቢከናወኑም አሁንም ድረስ ያልተቀረፉ ችግሮች መኖራቸውን ግን አልሸሸጉም። 

የሕግ የበላይነት አለመኖርና የፍትሕ ዕጦት እሳቸውንና የለውጥ ኃይሉን ወደ ሥልጣን ካመጡ ጉዳዮች መካከል አንዱ እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩእሳቸው የሚመሩት የለውጥ ኃይል የፍትሕ ሥርዓቱን ከፖለቲካ ጫና እንደሚያወጣ ቃል የገባ ቢሆንም፣ የዚሁ የለውጥ ኃይል የሆኑ አስፈጻሚዎች አሁንም በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ጫና እያደረሱ መሆናቸውን አምነው ዕርማት እንዲደረግበት ማሳሳቢያ ሰጥተዋል። 

አስፈጻሚው አካል የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን እያከበረና እያስፈጸመ እንዳልሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹አንዳንዱ ወንጀለኛ ይደብቃል፣ አንዳንዱ ደግሞ የፍርድ ቤት ውሳኔ አያከብርም ሲታዘዘም አይፈጽምም፤›› ሲሉ ተችተዋል። 

ይህ አካሄድ መቀየር እንዳለበት ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩየአስፈጻሚው አካል አመራሮች ፍርድ ቤት የሚሰጣቸውን ውሳኔዎች ምንም ሳያወላዱ መቀበልና መፈጸም ይገባቸዋል ብለዋል። 

‹‹እኛ ያላከበርነውን፣ ያልታዘዝነውን ፍርድ ቤት ነፃና ገለልተኛ ሁን ማለት ከንቱ ነው። ከቆምንለት ፍላጎትም የሚቃረን ነው፤›› ሲሉ በግሳጼ መልክ ተናግረዋል። 

በተጨማሪም አስፈጻሚው መንግሥትን የሚቀላለቀሉ ባለሥልጣናት ስለግል ስምና ክብር እንዲሁም ዝና መጨነቃቸውን መተው እንዳለባቸው መክረዋል። 

ባለሥልጣናት ስለግል ስምና ክብር መጨነቃቸውን ትተው ሰዎች እንዲሁም ሚዲያዎች እንዲተቿቸው መፍቀድ እንዳለባቸው የመከሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩሚዲያዎች አንዱን በአንዱ ላይ እንዲነሳ የሚቀሰቅሱ ከሆነ ብቻ በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ የሚፈለገውን ዴሞክራሲያዊ ባህል ለመገንባት የተሻለ እንደሆነ ጠቁመዋል። 

ሌላው በምክር ቤቱ አባላቱ የተነሳው ጥያቄ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ነዋሪዎች ላይ በተደጋጋሚ እየደረሰ ያለው ጥቃትና ሕይወት መጥፋት አፋጣኝ መፍትሔን የተመለከተ ነው። በተጨማሪም በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መካከል የተፈጠረው ቅራኔ ወደ ግጭት እንዳያመራ፣ ነገር ግን ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ እንዲከበር ምን እየተሠራ እንደሆነ ማብራሪያ ተጠይቀዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የብሔር ችግር እንዳለ ለማስመሰል ቢሞከርም፣ ነገሩ ግን ከዚያ በላይ የተወሳሰበ እንደሆነ ገልጸዋል።

በአካባቢው በተደጋጋሚ በዜጎች ላይ እየተከፈተ ያለው ጥቃት በውጭና በውስጥ ኃይሎች ቅንጅት የሚፈጸም እንደሆነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይበቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የተጎነጎነው ሴራ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር እንደሚገናኝ ጠቁመዋል።

‹‹በአካባቢው ለመፍጠር እየተሞከረ ያለው ከህዳሴ ጋር ይገናኛል። ዓላማውም ወደ ህዳሴ የሚወስደውን መንገድ ከመቁረጥ ጋር ይያያዛል፤›› ብለዋል። ጥቃቱ የሚሰነዘርበት አካባቢ ከጎረቤት አገር ጋር የሚያዋስን ሰፊ ድንበር የሚሸፍን በመሆኑና በአካባቢው ምንም ዓይነት መንገድ ባለመኖሩ የመከላከል ሥራውን ፈታኝ እንዳደረገው ገልጸዋል። 

ጥቃቱ በሚያጋጥምባቸው ሥፍራዎች የመኪና መንገድ ባለመኖሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጥቃት የተፈጸመበት ቦታ ለመድረስ እስከ 7 ሰዓት ድረስ በረዣዥም ሳር ውስጥ በእግራቸው እንደሚጓዙ አስረድተዋል።

‹‹ጥቃቱ የሚፈጸመው በቀስት ነው። የመከላከያ ሠራዊቱ በረዣዥም ሳር (ሳቫና ግራስ ላንድ) ውስጥ ጥቃት አድራሾችን ለመያዝ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ብዙ መስዋዕትነት ከፍለዋል፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህ መስዋዕትነትም በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች መማረካቸውንና ብዙዎቹ ጥቃት አድራሾች ደግሞ መሸሻቸውን ተናግረዋል።

አጥቂዎቹ መሠረታቸውን ያደረጉት በግድቡ አቅራቢያ በምትገኝ ብሉ ናይል በተባለች የሱዳን ግዛት ውስጥ እንደሆነና በዚያም በስም ባልጠቀሷቸው የውስጥና የውጭ አካላት ሥልጠናና ሌሎች ድጋፎችን ወስደው በንጹሐን ላይ ጥቃት እንደሚከፍቱ ተናግረዋል። 

‹‹ችግሩ አሁንም ከምንጩ ካልደረቀ ዳግም ችግር ይከሰታል›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥታቸው ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።

ምንም ዓይነት እክል ቢመጣ ሉዓላዊነትን ለማስከበር የሕይወት መስዋዕት እስከመሆን ዋጋ እየከፈለ በሚገኘው መከላከያ ሠራዊት አማካኝነት ችግሮቹን ለማስወገድ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ምንም ዓይነት ችግር ቢከሰት እንኳን ይህ መንግሥት ባለው አቅም ከህዳሴው ግድብ ላይ ዓይኑን ሳያነሳ ዕውን እንደሚያደርገው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩየህዳሴ ግድቡ ቁልፍ ሥራ ዘንድሮ በመሆኑ እንደ አገር በጋራ መቆም እንደሚገባ አሳስበዋል።

‹‹ጸሐይም ሆነ ዝናብ ሲመጣ ከመንገዳችን መቆም ሳይሆን ጥላ ይዘን ጉዟችንን እንቀጥላለን፤›› በማለት የህዳሴው ግድብ ግንባታ በማንኛውም እክል ምክንያት ሊገታ እንደማይችል በአጽንኦት ገልጸዋል።

በትግራይና በፌደራል መንግሥት መካከል የተፈጠረውን አለመገባባት በተመለከተ በሰጡት ምላሽምየፌዴራል መንግሥት የትግራይ ሕዝብን ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለይቶ እንደማይመለትና በዚህ ረገድም ችግር አለመኖሩን ገልጸውችግሩ ያለው በክልሉ ከፍተኛ የሥልጣን  ላይ ከተቀመጠው ስብስብ ጋር መሆኑን አስረድተዋል። 

ከዚህ ኃይል ጋር የሚያያዘው ጉዳይም በሕግና በሕግ ብቻ እንደሚወሰንና በዚህ ጉዳይ ላይ የፌዴራሉ ሥራ አስፈጻሚ መንግሥት ሚና የሚሆነው የፌዴሬሽንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ሕግን ተከትለው የሚወስኑትን ጉዳይ እንደሚያስፈጽም ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል።

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበላቸው ሌላው ፖለቲካዊ ጉዳይ በአገሪቱ እየተተገበረ ያለው መንግሥታዊ ሥርዓትን የተመለከተ ነበር። 

ጠያቂዋ የፓርላማ አባል አሁን ያለው መንግሥት ጨፍላቂና አሀዳዊ ሥርዓትን ለማምጣት እየሠራ እንደሆነና በዚህም የብሔር ብሔረሰቦችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እየናደ እንደሆነ ክስ የሚያቀርቡ መኖራቸውንና በዚህም ሕዝቡ መደናገሩን ጠቅሰዋል። 

በማከልም መንግሥትዎ ፌዴራላዊ ሥርዓትን ወደ አሀዳዊነት እየቀየረ ነው ወይእውነተኛ ፌዴራላዊ ሥርዓትን ዕውን ከማድረግ አኳያ መንግሥት ምን እየሠራ እንደሆነ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽም፣ ‹‹አንድ መንግሥት ፌደራላዊ ከሆነ ዴሞክራሲያዊ ነው፣ አሀዳዊ ከሆነ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይደለም፤›› ብለዋል።

መንግሥት ልዩ ልዩ ቅርፅ ሊይዝ እንደሚችል የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ የነበረው የዘውድ ወይም ንጉሣዊ አገዛዝ አሀዳዊ እንደነበርበኋላ የመጣው የደርግ መንግሥትም አሀዳዊ እንደነበር አመልክተዋል። ቀጥሎ የመጣው የኢሕአዴግ መንግሥት ደግሞ ፌዴራላዊ የመንግሥት ሥርዓትን እንደተከለ ተናግረዋል። 

ነገር ግን ሦስቱም መንግሥታት ዴሞክራሲያዊ አልነበሩምኢሕአዴግ ደግሞ የዴሞክራሲን ሽታ እንኳ አያውቀውም ብለዋል። 

አንዳንዶች የብልፅግና ፓርቲ ኅብረብሔራዊ አደረጃጀትን በመከተሉ ለፌዴራላዊ ሥርዓቱ አደጋ እንደሆነ፣ አሀዳዊ ሥርዓትን የመመሥረት ጅማሮ እንደሆነ አድርገው ሰዎችን በማደናገር ሥራ መጠመዳቸውን ገልጸዋል። 

ነገር ግን፣ የፌዴራል ሥነ ሥርዓት የሚመራው በሕገመንግሥት፣ ብሎም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በፌዴሬሽን ምክር ቤት አማካኝነት በሚወጣ ሕግ እንጂ በፓርቲ አደረጃጀት እንዳልሆነ አስረድተዋል። 

ኅብረብሔራዊ ፓርቲ ደግሞ በፓርቲ ሕገደንብ የሚመራ እንደሆነና ከላይ ለተጠቀሱት ሕግጋት እንደሚገዛብልፅግናም በመገንባት ላይ የሚገኘው ተግባራዊ፣ ፌደራላዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እንደሆነ ገልጸዋል።

‹‹በኢትዮጵያ ባለን የባህል ውቅርና የቋንቋ ስብጥር ተመሥርተን ሁሉ የሚወከልበት ፌዴራላዊ አደረጃጀትን መርጠናል። ይህም ሥልጣን የታችኛው መዋቅር ድረስ መውረዱንና ራስን በራስ ማስተዳደር መተግበሩን የሚያረጋግጥ ነው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ከለውጡ በኋላ የፌዴራል መንግሥት በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ አያውቅም፤›› ብለዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -