Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሩብ ዓመቱ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል

ተዛማጅ ፅሁፎች

ንብረቶቻቸው የወደሙባቸው ባለሀብቶች ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ ተፈቅዶላቸዋል

የኢንቨስትመንት ፖሊስ እንደሚደራጅ ይጠበቃል

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሦስት ወራት አፈጻጸሙን በማስመልከት ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው መግለጫ የሰጡት የኢንቨስትመንት ኮሚሽነሯ ሌሊሲ ነሜ፣ ኮሚሽኑ የሚደተዳደርበት ደንብ ተሻሽሎ መፅደቁን መነሻ በማድረግ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትና ክንውን እስከ የወደፊት የመንግሥት አቅጣጫዎች አብራርተዋል፡፡

በሩብ ዓመቱ ከተከናወኑ የኮሚሽኑ ተግባራት መካከል በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀውን ደንብ ቁጥር 474/2012 የጠቀሱት ኮሚሽነሯ፣ ይህ ደንብ የያዛቸው ዝርዝር ጉዳዮች ወደፊት ሰፊ ማብራሪያ እንደሚሰጥባቸው፣ ሆኖም ለውጦች ከተደረጉባቸው ጉዳዮች መካከል ከዚህ ቀደም በኮሚሽኑ ለባለሀብቶች ይሰጡ የነበሩ የማበረታቻ ድጋፎች እንደ ቀድሞው በኮሚሽኑ መሰጠታቸው ቀርቶ፣ በአሁኑ ወቅት በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል እንዲስተናገዱ መደረጉ እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል፡፡    

የውጭ ኢንቨስትመንትን ከመሳብ አኳያ፣ በሩብ ዓመቱ በአብዛኛው ከቻይና የመጣው ሆኖ ከእስያ፣ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካና ከአፍሪካ 36 ፕሮጀክቶች መመዝገባቸውን ኮሚሽነሯ ገልጸዋል፡፡ በዚህም 500 ሚሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ፍሰት መመዝገቡን፣ 14659 የሥራ ዕድል መፈጠሩን አብራርተዋል፡፡ ከተፈጠሩት የሥራ ዕድሎች ውስጥ 3795ቱ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት መስኮች የተከፈቱ ናቸው፡፡ የተቀሩት 10,864 ሥራዎች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የተገኙ ናቸው፡፡

ይህም ሆኖ አፈጻጸሙ ከዕቅዱም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አኳያም ያነሰ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በሥራ ዕድል ረገድ ከ20,500 በላይ የሥራ ዕድል ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቅ የነበረ ቢሆንም የተሳካው 71.3 በመቶ መሆኑን ኮሚሽነሯ አስታውቀዋል፡፡ ከገቢ አኳያም በ2012 ዓ.ም. የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ከተገኘው 700 ሚሊዮን ዶላር አኳያ፣ የዘንድሮው በ20 በመቶ ቀንሶ 500 ሚሊዮን ዶላር ላይ ተወስኗል፡፡ በ2012 ዓ.ም. በጠቅላላው ከሚጠበቀው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አኳያ በ50 በመቶ ቅናሽ የተመዘገበበት ውጤት መመዝገቡም ተወስቷል፡፡ ባለፈው ዓመት 2.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያስመዘገቡ የውጭ ኢንቨስትመንቶች ተገኝተዋል፡፡ ካቻምና 3.3 ቢሊዮን ዶላር ያስመዘገቡ ኢንቨስትመንቶች እንደነበሩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ 

አብዛኛው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ተፅዕኖ እንዳረፈበት ያስታወቁት ኮሚሽነሯ፣ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮችንና መስህቦችን ለማስተዋወቅ የገፅ ለገፅ ገለጻ ማድረግ ያለተቻለበት ይልቁንም በዲጂታል ዘዴዎች መጠቀም ውይይቶች ሲካሄዱ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ የኢንቨስትመንት ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ አገሮች ላይ ያሳደረው ተፅዕኖም ከፍተኛ ስለነበር በርካቶችን ለኪሳራ ዳርጓል፡፡ ይህ በመሆኑም እዚህ የሚመጡ ባለሀብቶች በብዙ ጥረት በመሆኑ የተገኘው የግማሽ ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ፍሰት ቀላል እንዳልሆነ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ሐሳቦችን በመጥቀስ ለቀረቡላቸው የተለያዩ ጥያቄዎችም ምላሾችን ሰጥተዋል፡፡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በፀጥታ መደፍረስ ሳቢያ የሚደርስባቸውን ጉዳት ሲያብራሩ፣ በዚህ ረገድ በሁለት ወገን የሚታይ ችግር እንደሚያጋጥም አመላክተዋል፡፡ አንደኛው ኢንቨስትመንቱ በሚገኝበት አካባቢ የሚኖረው ማኅበረሰብ ከኢንቨስትመቱ ስለሚያገኘው ተጠቃሚነት ስለ ኢንቨስትመንቱ ያለው ግንዛቤ ነው፡፡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ኅብረተሰቡን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርጉበት መንገድ በግልጽ መቀመጥ እንዳለበት፣ በልማት ተነሺ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የመጀመሪያዎቹ ተጠቃሚ መሆን እንደሚኖርባቸው፣ ይህም እንደሚፈጸም ከኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ ተቋሙ የሚከተላቸውን መንገዶች አብራርተዋል፡፡

ሌላው ኢንቨስትመንትን ከመጠበቅ አኳያም ሕዝቡ ተጠቃሚነቱን ተገንዝቦ ፕሮጀክቶችን ከመጠበቅ ባሻገር መንግሥትም የሚከተላቸው መንገዶች ምን እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም በመንግሥት የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ከጥቃት ለመከላከልና ጥበቃ ለማድረግ ራሱን የቻለ የኢንቨስትመንት ፖሊስ እንደሚደራጅ ሌሊሴ አስታውቀዋል፡፡ ይህንን ኃይል ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመሆን ለማቋቋም እንቅስቃሴ ይደረጋል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል ጉዳት የደረሰባቸው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ድጋፍ የሚያገኙባቸው አሠራሮች እንደሚተገበሩም ተጠቅሷል፡፡ የባንክ ብድር እንዲመቻችላቸው፣ ንብረቶቻቸው የወደሙባቸውም ምትክ እንዲሆናቸው ከውጭ ያለ ቀረጥ ማስገባት እንዲፈቀድላቸውና ንብረቶቻቸውን ለባንክ ብድር ያሲያዙ ካሉም ባንኮች በሐራጅ እንዳይሸጡባቸው ለማድረግ መመርያ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ኃላፊዋ አስታውቀዋል፡፡ ከሌሎቹ የድጋፍ ማዕቀፎች በተለይ መመርያው እስኪወጣ ድረስ ባንክ ንብረቶቻቸውን በሐራጅ እንዳይሸጡባቸው ለባንኮች ጥያቄ እንደቀረበላቸው ተብራርቷል፡፡

እስካሁን በነበረው አካሄድ እንደ ግሉ ዘርፍ ሁሉ መንግሥትም በራሱ መንገድ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ሲገነባ የቆየበትን አካሄድ በመቀየር፣ ለግሉ ዘርፍ ሚናውን እንደሚተው ተብራርቷል፡፡ እርግጥ ነው ከዚህ ቀደም ተደጋግሞ እንደሚገለጸውም፣ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት አማካይነት ሊገነቡ የሚችሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንደሚኖሩ ታሳቢ ቢደረግም፣ መንግሥት እንደቀድሞው ሙሉ ለሙሉ በራሱ ፓርኮቹን ከመገንባት እንደሚታቀብና አመዛኙ ድርሻ የግሉ እንደሚሆን፣ መንግሥትም ግንባታ እንደሚያቆም ተብራርቷል፡፡

በቅርቡ ወደ ሥራ የገቡትን አራት አዳዲስ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጨምሮ በመንግሥት የተገነቡ 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በ75 ሔክታር የመሬት ይዞታ ላይ የተገነባው የባህር ዳር ኢንዱስትሪን ጨምሮ እስካሁን ከ1.3 እስከ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ወጪ መደረጉን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በዕቅድ ተይዘው የነበሩ አምስት ፓርኮችም ግንባታ ይጠባበቁ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በጠቅላላው በአገሪቱ በመንግሥትና በግል አልሚዎች የተገነቡ 22 ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዳሉ ሲታወቅ፣ በመንግሥት ይገነባሉ ተብለው የሚጠበቁት ፓርኮች ብዛት ከአምስት ዓመታት በኋላ 30 እንደሚደርሱ በቀደሙት የመንግሥት የዕቅድ ሰነዶች ተመላክተዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች