ለወራት ከአኅጉራዊና ከዓለም አቀፍ ውድድሮች ርቆ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ነገ ሐሙስ ጥቅምት 12 እና እሑድ ጥቅምት 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ከዛምቢያ አቻው ጋር ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ያደርጋል፡፡ በብሔራዊ ፌዴሬሽኙ በተሾመው አዲሱ የዋሊያዎቹ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾቹ፣ በካፍ አካዴሚ ዝግጅታቸውን ከጀመሩ ሳምንታት ያስቆጠሩ ሲሆን፣ የነገው የወዳጅነት ጨዋታው ቡድኑ ያለበትን አቅም ለማወቅና ጠንካራ ቡድን ለማግኘት ይረዳዋል ተብሏል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከአይቮሪኮስት፣ ማዳጋስካርና ኒጀር ጋር የተመደበው ብሔራዊ ቡድኑ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች በማዳጋስካር ተረትቶ፣ አይቮሪኮስትን 2 ለ 1 በመርታት በሦስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል፡፡ ከዛምቢያ ጋር የሚያደርገው ግጥሚያ በቅርቡ ከኒጀር ጋር ለሚኖረው የማጣሪያ ጨዋታ አቅሙን ያጠናክርበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 11 ቀን ቦሌ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት እንደሚደርስ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡