Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአዲስ አበባ ምክር ቤት 11ኛ አዲስ ክፍለ ከተማ እንዲመሠረት የሚደነግገውን አዋጅ አፀደቀ

የአዲስ አበባ ምክር ቤት 11ኛ አዲስ ክፍለ ከተማ እንዲመሠረት የሚደነግገውን አዋጅ አፀደቀ

ቀን:

አዲሱ ክፍለ ከተማ ‹‹ለሚ ኩራ›› የሚል ሥያሜ ተሰጥቶታል

የአዲስ አበባ ከከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 11ኛ አዲስ ክፍለ ከተማ የሚመሠርተውንና በክፍላተ ከተማ ሥር ያሉ ወረዳዎችን እንደገና የሚያዋቅረውን አዋጅ አፀደቀ፡፡

ሁለተኛው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስምንተኛ የሥራ ዓመት አንደኛ መደበኛ ስብሰባ ጥቅምት 10 ቀን 2013 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዳራሽ ሲደረግ፣ በከተማ አስተዳደሩ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ከየካና ከቦሌ ክፍላተ ከተማ አሥር ወረዳዎችን አቅፎ ‹‹ለሚ ኩራ›› የተባለ አዲስ 11ኛ ክፍለ ከተማ እንዲቋቋም የሚያደርግ ሲሆን፣ የወረዳዎች ሽግሽግና የአከላለል ማሻሻያዎችንም ያደርጋል፡፡

ለሚ ኩራ የተባለው አዲሱ ክፍለ ከተማ አሥር ወረዳዎች ያሉት ሲሆን፣ እነዚህም ወረዳዎች የተመሠረቱት ከየካ ወረዳ 12 ተከፍለውና ከየካ ወረዳ 13 ተጨምሮ፣ ከቦሌ ወረዳ 10 እንዲሁም ወረዳ 11 ተውጣጥተው የተመሠረቱ ወረዳዎችን የሚይዝ ይሆናል፡፡

በዚህም መሠረት የካ አባዶ ኮንዶሚኒየም፣ አያት፣ ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ አካባቢ፣ ቦሌ አራብሳ እንዲሁም አያት ኮንዶሚኒየም አካባቢዎች በአዲሱ ክፍለ ከተማ የሚካተቱ ይሆናል፡፡

በተደረጉ የወረዳ ማሸጋሸጎችም በአሥር ክፍለ ከተሞች ሥር የነበሩ 116 ወረዳዎችን ወደ 120 እንዲያድጉ አድርገዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ ባደረጋቸው ማሻሻያዎች 10 ወረዳዎች ያሉት አራዳ ክፍለ ከተማ በስምንት ወረዳዎች እንዲቋቋም፣ 11 ወረዳዎች ያሉት አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በ13 ወረዳዎች እንዲቋቋም፣ 14 ወረዳዎች ያሉት ቦሌ ክፍለ ከተሞች በ11 ወረዳዎች እንዲቋቋም፣ 13 ወረዳዎች የነበሩት የካ ክፍለ ከተማ በ12 ወረዳዎች እንዲቋቋም፣ 15 ወረዳዎች የነበሩት ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በ11 ወረዳዎች እንዲቋቋም፣ 12 ወረዳዎች የነበሩት ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በ13 ወረዳዎች እንዲቋቋም፣ 11 ወረዳዎች ያሉት ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ10 ወረዳዎች እንዲቋቋም፣ 10 ወረዳዎች ያሉት አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በ12 ወረዳዎች እንቋቋም፣ እንዲሁን ልደታና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች እያንዳንዳቸው 10 ወረዳዎችን ይዘው እንዲቋቋሙ አድርጓል፡፡

እነዚህን የአደረጃጀት ለውጦች ያስፈለጉበትን ምክንያት ያብራራው የከተማ አስተዳደሩ ረቂቅ አዋጅ፣ ‹‹የነዋሪዎችን ብዛት በማመጣጠን፣ የአገልግሎት ተደራሽነትንና የማስተዳደር አቅምን ከግምት በማስገባት እያንዳንዱ ክፍለ ከተማ ባልተማከለ የሥልጣን ክፍፍል መርህ በተሰጠው የቦታ ክልል ማዘጋጃ ቤት በመሆንና ከከተማው ማዕከል ጋር በመቀናጀት አገልግሎት እንዲሰጥና ወረዳዎችን እንዲያስተዳድር ለማድረግ ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት አደረጃጀት እንዲኖረው በማስፈለጉ፤›› ‹‹የከተማ ማዕከላት በተዋረድ እንዲለሙ በማድረግ ለከተማው ነዋሪዎች ሚዛናዊ በሆነ ርቀትና ተደራሽ በሆነ መልኩ የአገልግሎት አቅርቦት እንዲመቻች ማድረግና የከተማ ነዋሪዎች የሚፈልጉትን ፍትሐዊ፣ ቀልጣፋና ብቁ የሆነ መልካም የከተማ አስተዳደር ማረጋገጥ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ›› እና ‹‹ይኼንንም ለማሳካት እንዲቻል፣ በማስፋፊያ አካባቢ የሚገኙትን ክፍለ ከተማዎች እንደ አግባቡ በመክፈልና በተወሰነ ሁኔታ ደግሞ ወረዳዎችን ወደ አዋሳኝ ክፍለ ከተማዎች እንደ ሁኔታው እንደገና ማዋቀር አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ፤›› መሆኑን አብራርቷል፡፡

የእያንዳንዱ ከፍለ ከተማ አስተዳደር ተጠሪነት፣ ሥልጣንና ተግባር እንዲሁም ሌሎች የአሠራር ሁኔታዎች በቻርተር አዋጁና በከተማው ምክር ቤት ሕጎች መሠረት እንደሚወሰን የሚጠቁመው አዲሱ አዋጅ፣ ‹‹የእያንዳንዱ ክፍለ ከተማ መጠሪያ ስም በከተማው ካቢኔ በሚወጣ ደንብ ሊለወጥ ወይም ሊሻሻል›› እንደሚችልም ይደነግጋል፡፡ በተመሳሳይ የወረዳዎች መጠሪያ በከተማው ካቢኔ ደንብ ሊለወጥ ወይም ሊሻሻል እንደሚችል ተደንግጓል፡፡

ምክር ቤቱ ከዚህ በተጨማሪ የከተማ አስተዳደን የሥራ አፈጻጸም የገመገመ ሲሆን፣ በከተማዋ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የቀረቡ የበጀት ዓመቱ ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይም ተወያይቷል፡፡ በተለይ በምክር ቤቱ የቤት አቅርቦት፣ የውኃና የትራንስፖርት ጉዳዮች ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፣ ምክትል ከንቲባዋ በ2013 በጀት ዓመት 125 ሺሕ ቤቶች ይገነባሉ ተብሎ የተያዘው አቅጣጫ በጀት ያልነበረው በመሆኑ፣ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ቤቶች ይገነባሉ እንጂ ይኼኛው አማራጭ ቀርቷል ብለዋል፡፡ ከባለሀብቶች፣ ባንኮችና ዓለም አቀፍ የቤት ልማት ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ጋር በመተባበርም 126 ሺሕ ቤቶችን ለመንባት እንደታቀደም ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቅራቢነት ስምንት የተለያዩ ሹመቶች የተሰጡ ሲሆን፣ አቶ ጥራቱ በየነ የከተማ ሥራ አስኪያጅ ቢሮ ኃላፊ በመሆን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ፣ መስከረም ፈለቀ (ዶ/ር) የቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ፣ አያልነሽ ሀብተማርያም (ኢንጂነር) የኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ፣ መስከረም ምትኩ (ዶ/ር) የፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ ሚልኬሳ ጃገማ (ዶ/ር) የመሬት ልማት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ፣ ሙሉቀን ሀብቱ (ዶ/ር) የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ተፈራ ሞላ የሠራተኛና ማኅበራዊ ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም አቶ ሙሉጌታ ተፈራ የገቢዎች ቢሮ ኃላፊና እንዲሁም ወ/ሮ ዘርፈ ሸዋል ንጉሤ አፈ ጉባዔ ሆነው ተሹመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...