Thursday, June 1, 2023

የኢትዮ ኤርትራ የሰላም ግንኙነት ፈቀቅ ያላለው ለምንድነው?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያና የኤርትራ የ20 ዓመታት የጦርነትም ሆነ ሰላም አልባ ቆይታ አዲስ ምዕራፍ ያስይዛል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የሰላም ግንኙነት ከተጀመረ ሁለት ዓመታትን ተሻገረ፡፡ ሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ድንገት በኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ የተገኙት በዚያው ዓመት መጋቢት ወር ውስጥ ወደ ጠቅላይ ሚኒስተርነት የመጡት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በዕለተ ሲመታቸው በፓርላማ ባደረጉት ንግግር የገቡትን ቃል ማስፈጸሚያ የሚሆነውን ጅምር አንድ ብለው ጀመሩ፡፡ እስከዚያ ድረስ በቃል ፍላጎትን ከመግለጽ ባለፈ በአንድም ኢትዮጵያዊ መሪ ተደርጎ የማያውቀውን ጉዞ ማድረጋቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሁለቱ አገሮች ችግር መፈታት ያላቸውን ቁርጠኝነት ያመላከተ እንደሆነ የተነገረለት ድርጊት ነበር፡፡ በተለይ ችግሩን የመፍታት ሒደት በከፍተኛ መሪዎች ደረጃ መከናወኑ፣ ዕርቁ ትርጉም ያለውና ቀጣይ ይሆናል የሚል ተስፋ እንዲዘራም አድርጎ ነበር፡፡

በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ባሳዩት ቁርጠኝነት ልክ የዛሬ ዓመት ገደማ 100ኛውን የሰላም የኖቤል ሽልማት ያሸነፉ ሲሆን፣ በርካታ ዓለም አቀፍ አድናቆትንና ሙገሳን ያገኙበት ክስተት እንደነበር ይታወሳል፡፡

ይኼንንም የጠቅላይ ሚኒስትሩን የአስመራ ጉብኝት ተከትሎ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኡስማን ሳህልህና በኤርትራ ፕሬዚዳንት የፖለቲካ አማካሪ የማነ ገብረ አብ የተመራ ልዑክ አዲስ አበባ መጥቶ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡ በኋላም የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከ20 ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያን ምድር ለመጀመርያ ጊዜ የረገጡ ሲሆን፣ የአገሮቹን ግንኙነት በተመለከተም ወደፊት አንድ ላይ እንገሰግሳለን ሲሉ አውጀዋል፡፡

እነዚህ የጉብኝት ልውውጦችን ተከትሎም ሁለቱ መሪዎች ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል የተባለለትንና በኢትዮጵያ ወገን በድብቅ የተያዘውን ስምምነት በአስመራና በሳዑዲ ዓረቢያ ጅዳ የተፈራረሙ ሲሆን፣ ሁለቱን አገሮች የሚያገናኙ የየብስ መንገዶች እንዲከፈቱ፣ ሳምንታዊ የአውሮፕላን በረራ እንዲጀመር፣ እንዲሁም ተቋርጦ የነበረው የስልክ ግንኙነት በድጋሚ እንዲጀመር ተደርጓል፡፡ በሁለቱ አገሮች በድምቀት የሚከበረው በኤርትራ ወገን ቅዱስ ዮሐንስ በኢትዮጵያ ወገን ደግሞ የአዲስ ዓመት ጅማሮ መስከረም 1 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ በድንበር ከተማ ዛላምበሳ ሰዎች ከሁለቱም ወገኖች ተምመው እየተቃቀፉና እየተሳሳሙ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ፕሬዚዳንቱ ባሉበት በጋራ ተከብሯል፡፡ ከዚህ በኋላ ሁለቱም መሪዎች ከአንዱ አገር ወደ ሌላው የጉብኝት ልውውጦችን ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን፣ በሁለቱም መሪዎች የተደረጉ ጉብኝቶች በሙሉ ከጉብኝቶቹ በኋላ ወይም አንዱ መሪ ከሌላው አገር ሲደርስ ብቻ ይፋ የሚደረጉ ነበሩ፡፡

ከእነዚህ ጉብኝቶች አንዱ የሆነው የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሰሞኑ የኢትዮጵያ ጉብኝት ጥቅምት 2 ቀን 2013 ዓ.ም. የተጀመረ ሲሆን፣ ፕሬዚዳቱም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ጋር በመሆን በጅማ የቡና እርሻን፣ የጅማ ዩኒቨርሲቲን፣ የኮይሻን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብን፣ እንዲሁም የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጎብኝተዋል፡፡ ይሁንና በሁለቱም ወገኖች የተሰጡ ቅንጭብ የጉብኝት መዳረሻዎች መግለጫ በስተቀር በእንጥልጥል የቀሩ የሁለቱ አገሮች ግንኙነትን የተመለከቱ ውይይቶች እየተደረጉ ስለመሆኑ ምንም ማመላከቻ አልተሰጠም፡፡ እስካሁን የተደረጉ ስምምነቶችንም ሆነ ሰላሙን ሕጋዊ መሠረት የማስያዝና ግንኙነቱ ተቋማዊ እንዲሆን የማድረግ ጅማሮ ከምን እንደደረሰ ተገምግሞም ከሆነ አልተነገረም፡፡

ካሁን ቀደም የኢትዮጵያንና የኤርትራን ግንኙነት የሚከታተሉ ባለሙያዎችና ተንታኞች፣ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ከሁለቱ መሪዎች ወዳጅነት በዘለለ የሕግ ማዕቀፍ ተበጅቶለት ሊገዛ እንደሚገባ ሲያሳስቡ ነበር፡፡ በተለይም በመሪዎች ደረጃ ግንኙነቱ መጀመሩ መልካም ቢሆንም ግንኙነቱ ተቋማዊ እንዲሆን እስካሁን የጎላ ተሳትፎ ሲያደርጉ የማይታዩት እንደ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያሉ አገራዊ ተቋማት፣ ጉዳዩን ይዘውት ግንኙነቱን መስመር ሊያስይዙት ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡ አለበለዚያ ካሁን ቀደም ወደ ውዝግብና ጦርነት እንዳስገባው የመሰለ የመሪዎች ብቻ ግንኙነት ዘላቂ አይሆንም በማለትም ሲጎተጉቱ ተደምጠዋል፡፡ ነገር ግን ጅምሩ እንዳማረና እንደፈጠነ ሁሉ የኢትዮጵያና የኤርትራ የዕርቅ ሒደት ፈጣንና ቀልጣፋ፣ እንዲሁም እንዳማረ ያለ አይደለም የሚሉ በርክተዋል፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት በዋናነት ተከፍተው የነበሩ የሁለቱ አገሮች ድንበሮች መዘጋታቸውንና በየብስ እየተንቀሳቀሱ ለዘመድ ጥየቃና ጉብኝት ሲዘዋወሩ የነበሩ ሰዎች ይኼንን ማድረግ እንዳይችሉ መሆናቸውን ሲሆን፣ ሕጋዊና ተቋማዊ የማድረግ ሒደቶችንም አያይዘው ያነሳሉ፡፡

ያም ሆነ ይህ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ከመሪዎች ጉብኝቶች የዘለለ ለሕዝቡ ጠብ ያለ ውጤት አላስገኘም የሚሉ ተንታኞችና አጥኚዎች፣ ይኼንን ሁኔታ ለመለወጥ ያስችላል የሚሏቸውን መፍትሔዎች ሲጠቁሙም ቆይተዋል፡፡

በለንደን ዩኒቨርሲቲ በአፍሪካና ኦሪየንታል ጥናቶች ትምህርት ቤት የመመረቂያ ጽሑፋቸውን በሁለቱ አገሮች መካከል በ2011 ዓ.ም. የተደረገውን ስምምነት የመረመሩት አብዱ ኦስማን ሁማዲን፣ ስምምነቱ ዘላቂና ቋሚ ሰላምን የሚያመጣ ይሆን? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹የአንድ ስምምነት ጥንካሬ የሚለካው የግጭቱን መነሻ ምክንያቶች የሚፈቱና በተስማሚዎች መካከል ዘላቂ ሰላምን የሚያመጣ ብሎም ራሱን ማቆየት የሚችል በመሆንና ባለመሆኑ ነው፤›› በማለት የሚጀምሩት ተመራማሪው፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ሁለቱም ወገኖች የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን የወሰነውን ውሳኔ ለመተግበር ቁርጠኛ እንዲሆኑ በማድረግ፣ የግጭቱን መነሻ ችግር የሚፈታ መፍትሔ አስቀምጧል፡፡

ይሁንና ይላሉ አብዱ፣ ‹‹በሁለቱ መሪዎች ደረጃ በድብቅ የተከናወነ ስለሆነ የስምምነት ሒደቱ ግልጽነትና አካታችነት የሚጎድለው ነው፡፡ በሁለቱም አገሮች ያለውን ሕዝብና የፖለቲካ ኃይሎች፣ እንዲሁም የሲቪል ማኅበረሰቡን ያገለለ ነበር፤›› በማለት ይተቻሉ፡፡

የሁለቱ አገሮች የሰላም ስምምነት የሚስፈልገው የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ለመተግበር የኢትዮጵያ ሠራዊት ከባድመ እንዲወጣ ማድረግን ብቻ ይፈልጋል በማለትም የሚያመላክቱት አብዱ፣ ይኼ ምናልባትም ከሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና የትግራይ ክልል መንግሥት ትብብር ውጪ ሊሆን አይችልም ባይ ናቸው፡፡

ግንኙነቱ ቀጣናዊ መልክም ስለሚኖረው በጂቡቲና በኤርትራ መካከል ያለውን ግንኙነት መፍታት ይጠይቃል በማለት፣ የኤርትራ ዕርቅ መፈጸሙ ኢትዮጵያ ለወጪና ገቢ ንግድ የምትጠቀምበትን የጂቡቲ ወደቦች ጥቅም ሊያሳጣት የሚችለውን ጂቡቲ ስለሚያስከፋ፣ ከሕወሓት ጋር በመጣመር ዕርቁን የማደናቀፍ ሚና ልትጫወት ትችላለች ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡

በተለይ አሁን በፌዴራል መንግሥትና የትግራይ ክልልን በሚመራው ሕወሓት መካከል ያለው ውዝግብ ጣራ እየነካ ባለበት ወቅትና የፌዴሬሽን ምክር ቤትም የፌዴራል መንግሥት ከትግራይ ክልል ምክር ቤትና የሥራ አስፈጻሚ ጋር ግንኙነት እንዲያቆም፣ እንዲሁም ከፌዴራል መንግሥት ለትግራይ ክልል የሚሰጠውም የበጀት ድጎማ እንዲያቆም መወሰኑ የተገለጸበት ጊዜ በመሆኑ፣ የዚህ ዓይነት ውጥረት የዕርቀ ሰላሙን ዕውነት ሊያስተጓጉለው እንደሚችል ምልከታቸውን የሚያስቀምጡ አልጠፉም፡፡

ከትግራይም ሆነ ከፌዴራል መንግሥቱ የሚሰነዘሩ የቃላት ጦርነቶች ከቃልም አልፈው ወደ ግጭት ሊገቡ እንደሚችሉ የሚያምኑ እየተበራከቱ የመጡበት ወቅት ሲሆን፣ በተለይም በትግራይ ክልልና በፌዴራል መንግሥት መካከል ያለው ውጥረት ካልረገበ እንዲህ ላሉ የውጭ ግንኙነቶች የሚሰጠው ትኩረት ቦታ ሊያጣ እንደሚችል የሚጠቁሙ አልጠፉም፡፡

ይኼንንም በሚመለከት በሁለቱ አገሮች ስምምነት አካታችነት አለመኖሩን፣ ገለልተኛ ሦስተኛ ወገን በእማኝነት አለመሳተፉ፣ ስምምነቱ እጅግ ሰፊ ወሰን ያለው መሆኑና ግልጽ የትግበራ መንገድና የጊዜ ሰሌዳ የለውም የሚሉት አብዱ፣ ሁለቱ ወገኖች በውስጥ የተደቀነባቸው ፈተና በሁለትዮሽ ስምምነቱ ላይ ትኩረት እንዳያደርጉ ስለሚያደርጋቸው፣ የዚህን ውጤት ደግሞ ገፈት መቅመሳቸው አይቀሬ ነው ይላሉ፡፡

‹‹ሁለቱም አገሮች ስምምነቱን በተመለከተ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ የሆነ አመራር እስካልተከተሉ ድረስ ዘላቂ ሰላም የማምጣት ፈተናዎችን ማስቀረት አይችሉም፡፡ ስለዚህም በሁለቱ መካከል የመጣው አዲስ ሰላም ውኃ ሊቋጥር አይችልም፤›› በማለትም ይገመግማሉ፡፡ ስለዚህም፣ ‹‹የሰላም ሒደቱን በከበበው ከፍተኛ ሚስጥራዊነት ምክንያት የሁለቱም አገሮች መሪዎች ቅንነት ላይ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ እንደ ሕወሓት፣ ፓርላማና የሲቪል ማኅበረሰብ ያሉ ባለድርሻ ተቋማትን ከሰላም ሒደቱ እያገለሉ ዘላቂ ሰላም ማምጣት አያስችልም፤›› ሲሉም የስምምነቱን ግልጽነት ማጣት በማውሳት ጉዳቱን ይጠቁማሉ፡፡

እ.ኤ.አ. ኦክቶበር 11 ቀን 2020 የደኅንነት ጥናት ተቋም ‹‹የኢትዮጵያና የኤርትራ የሰላም ስምምነት ገና ፍሬው እንዲታይ ይጠበቃል›› በሚል ርዕስ የታተመው የሰላም ታደሰ ጽሑፍ፣ እጅግ ተስፋ ተጥሎበት የነበረውና ለሁለቱም አገሮች ሕዝቦች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን ያስገኛል ተብሎለት የነበረው ስምምነት አሁን የቀጨጨና ያስገኛል ተብሎ የተገመተው ጥቅም ሁሉ እንዳያስገኝ ሆኖ ተሰናክሏል ሲሉ ይተቻሉ፡፡ ለዚህም ብዙውን ጊዜ ምክንያት እየሆነ የመጣው በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልል ባለሥልጣናት መካከል ያለው ውጥረትና እንደ ጥንቱ አሁንም የሚታየው የሕወሓትና የኤርትራ ባለሥልጣናት ግጭት ነው ይላሉ፡፡

‹‹ከኤርትራ ጋር ወደ ግጭት ያስገባው ድንበር የሚዋሰነው ከትግራይ ክልል ጋር ነው፡፡ ባድመም በትግራይ ክልል አስተዳደር ውስጥ ስለሚገኝ የሕወሓት አመራሮች የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ የመተግበር ኃላፊነት ይጋራሉ፡፡ ነገር ግን የሰላም ሒደቱ የተጀመረው ከአዲስ አበባ ሲሆን፣ እንደ ሕወሓት ካሉ ባለ ድርሻ አካላት ጋር በቂ ምክክርና መግባባት አልተደረገበትም፤›› በማለት ሰላም ያትታሉ፡፡ ‹‹ይኼ መገለል እንደ ርዕዮተ ዓለም፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ አመራርና ምርጫን ከመሳሰሉ ሌሎች ልዩነቶች ጋር ተዳምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ መንግሥትና በሕወሓት የትግራይ አመራር መካከል ያለውን ልዩነት አብሶታል፡፡ የዚህ ውዝግብ አንዱ ነጥብ ከኤርትራ ጋር ያለው ዕርቀ ሰላም እንዴት ይከወን የሚለው ነው፤›› ይላሉ፡፡

የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት በንግግራቸው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ተቋማዊ መሆን እንዳለበትና ሁለቱን መሪዎች ብቻ የሚያሳትፍ መሆን እንደሌለበት መግለጻቸውን ያስታወሱት ሰላም፣ በ2011 ዓ.ም. የተፈረመውን ስምምነት ለመተግበር እንደ ሕወሓት ያሉ ቁልፍ የመንግሥት ባለድርሻዎች ሳይሳተፉ የማይታሰብ ነው ይላሉ፡፡

‹‹እያደገ የመጣውን አደገኛ የመቀሌና የአዲስ አበባ ፍጥጫ፣ እንዲሁም ያልተፈታውን የመቀሌና የአስመራ ጠላትነት በማስመልከት ሕወሓቶች በሁለቱም ወገኖች ያላግባብ እየተጠቁ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ያለ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነትና በሕወሓት፣ በዓብይና በኢሳያስ መካከል መተማመን መገንባት ሳይቻል፣ የሰላም ስምምነቱ ፍሬ ላያፈራ ይችላል፤›› ሲሉም የጉዳዩን መፍትሔና ፈተና አንድ ላይ ያመላክታሉ፡፡

የአገሮቹ ስምምነት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥቅሞችን የሚያስገኙ እንደሆኑ በመጠቆም፣ እነዚህ ጥቅሞች ግን በ2011 ዓ.ም. የተፈረመው ስምምነት ወደ ተግባር መግባት ሲችል ብቻ ሊመጡ እንደሚችሉ ያሳያሉ፡፡ ነገር ግን ከሁሉም መቅደም ያለበት በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መካከል ያለውን መካረር ማርገብ ነው ይላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -