ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከረረና እየተባባሰ የመጣው የፌዴራል መንግሥትና የትግራይ ክልላዊ መንግሥት እሰጥ አገባ፣ አሁን ተግባራዊ ፍጥጫዎችን ማሳየት ጀምሯል፡፡ የሁለቱ ወገኖች ፍትጊያ የጀመረው በሐዋሳ ከተካሄደው የመጨረሻው የኢሕአዴግ ጉባዔ ጀምሮ የፓርቲውን ርዕዮተ ዓለም ለመቀየርና ግንባሩን ወደ አንድ ውህድ ፓርቲ ለመቀየር የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ቢሆንም፣ በተለይ ሕወሓት ብልፅግና ፓርቲ ተብሎ የተመሠረተው ፓርቲ ውስጥ ላለመሳተፍ ከወሰነ ወዲህ መካረሩ ጦዟል፡፡
በቀድሞ የአንድ ግንባር ጓዶች መካከል የሚስተዋለው ውጥረት በሒደት እየተካረረ መጥቶ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲን የሙጥኝ ባለው በሕወሓትና ከርዕዮተ ዓለማዊ እስረኝነት ተላቅቄ ለሁኔታዎች የሚስማሙ ውሳኔዎችን በምክንያታዊነት አራምዳለሁ በሚለው የብልፅግና ፓርቲ መካከል የቃላት ጦርነቶች እየበረቱ መጥተዋል፡፡ እነዚህ የቃላት ጦርነት ትግራይ ክልልን በሚያስተዳድረው ሕወሓትና የተቀሩት የኢትዮጵያ ክልሎች በሚያስተዳድረው ብልፅግና መካከል ወደ ግልጽ ልዩነት ያመሩትና በድርጊት የሚገለጹ መካረሮችን የፈጠሩት፣ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ሊካሄድ ታቅዶ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ሳይካሄድ የቀረውን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ ነው፡፡
ሕወሓት ከመነሻው ጀምሮ ምርጫው ከግንቦት ወደ ነሐሴ ወር መሸጋገሩን እንደሚቃወም በተለያዩ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የውይይት መድረኮች ላይ ሲያስታውቅ የቆየ ቢሆንም፣ በነሐሴ ወር መጨረሻ ታቅዶ የነበረው ምርጫ በሕገ መንግሥታዊ ትርጉም በተሰጠ ትንታኔ የኮሮና ወረርሽኝ የኅብረተሰብ ጤና ሥጋት መሆኑ ሲያበቃ እንዲካሄድ ቢባልም፣ ሕወሓት ምርጫው መራዘም የለበትም ሲል ተቃውሞውን አሰማ፡፡ ምርጫው መራዘም የሌለበትና የማያወላውል ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ያለው ሒደት ነው በማለት የተከራከረው ሕወሓት፣ የፌዴራል መንግሥት ምርጫውን በሕገ መንግሥት ትርጉም ቢያራዝምም በትግራይ የምርጫ ዝግጅት እንደሚደረግና ክልላዊ ምርጫም እንደሚከናወን አስታውቆ፣ ምርጫውን ጳጉሜን 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በማከናወን አዲስ ምክር ቤትና ሥራ አስፈጻሚ አቋቁሟል፡፡
የፌዴራል መንግሥት አካል የሆነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምርጫው ከመደረጉ አስቀድሞ ቢካሄድም ሕገወጥ ነው ሲል ቆይቶ፣ ምርጫው ተደርጎ የሕወሓት አሸናፊነትና የአዲስ መንግሥት ምሥረታ ይፋ ከሆነ በኋላ ደግሞ ምርጫው እንዳልተደረገ የሚቆጠርና ተፈጻሚነት የማይኖረው ይሆናል ሲል አስታወቀ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በጤና ሚኒስቴር ምክረ ሐሳብ ላይ በመንተራስ ምንም እንኳን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የኅብረተሰብ የጤና ሥጋት መሆኑ ባያበቃም፣ አስፈላጊ የሆኑ ጥንቃቄዎችን በማድረግ ከዘጠኝ እስከ 12 ወራት ባሉ ጊዜያት ውስጥ ዝግጅት ተደርጎ ምርጫው እንደሚከናወን አስታውቋል፡፡ የፓርላማው አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ይኼንን ውሳኔ ተከትሎ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በትግራይ የተከናወነው ክልላዊ ምርጫ እንዳልተደረገ እንደሚቆጠርና ተፈጻሚነት የማይኖረው በመሆኑ፣ ዝግጅት ይደረግበት የተባለው ምርጫ በትግራይም ይደረጋል ብለዋል፡፡
ይሁንና የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ በክልሉና በሕወሓት የመገናኛ ብዙኃን አማካይነት፣ ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ የፌዴራል መንግሥት ምርጫ አድርጎ ሥልጣኑን አድሶ እንደ አዲስ መቋቋም የነበረበት ጊዜ በመሆኑና ይኼም ባለመሆኑ ሕገወጥ መንግሥት እንደሚሆን፣ ፓርላማው፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሙሉ ሕጋዊ ውክልናቸውና ሥልጣናቸው እንደሚያበቃ ብሎም የሚያስተላልፏቸው ውሳኔዎችና ሕጎች ተቀባይነት የሌላቸውና በትግራይም ተፈጻሚነት የማይኖራቸው እንደሚሆኑ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡
መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ባካሄዱት የጋራ ጉባዔ የሁለቱ አምስተኛ ምክር ቤቶች ስድስተኛ የሥራ ዓመት መክፈቻ መርሐ ግብር በፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ንግግር ከተጀመረ በኋላ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በዝግ ባካሄደው ስብሰባ የፌዴራል መንግሥት ከትግራይ ክልል ጋር ያለውን ማንኛውንም ዓይነት ግንኙነት እንዲያቋርጥና ከፌዴራል ለትግራይ ክልል እንዲሰጥ የተመደበው የ2013 በጀት ዓመት አሥር ቢሊዮን ብር ድጋፍ እንዲቆም በመወሰን ዝርዝሩን የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲያወጣ አቅጣጫ እንደሰጠ አፈ ጉባዔው አቶ አደም ፋራህ ለመንግሥት ሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የፌዴራል ተቋማት ከትግራይ ክልል ምክር ቤትና አዲሱ የሥራ አስፈጻሚ ጋር እንደ ሕጋዊ ተቋማት ቆጥረው ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳይመሠርቱ እንደተወሰነ አፈ ጉባዔው በንግግራቸው ያስታወቁ ሲሆን፣ የፌዴራል መንግሥትም ግንኙነቱን ከወረዳ፣ ከቀበሌና ከከተማ አስተዳደሮች ጋር ብቻ እንዲያደርግ እንደተወሰነ ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ይኼ ውሳኔ ምን ያህል ሕጋዊ ተፈጻሚነት እንደሚኖረውና በምን ዓይነት የሕግ ሰነድ ሽፋን አግኝቶ እንደሚወጣ አፈ ጉባዔው አልተናገሩም፡፡
ይኼንኑ ውሳኔ በተመለከተ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የፌዴሬሽ ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ካሳሁን በቀለ፣ አፈ ጉባዔው እንዳስረዱት አዲስ ምርጫ ሳያደርጉ አስቀድሞ በተከናወነ ምርጫ እያስተዳደሩ ላሉት የታችኛው የክልሉ መዋቅሮች ዕውቅና ለመስጠት ታስቦ የተላለፈ ውሳኔ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ይኼ ምን ዓይነት አሠራር ሊፈጥር እንደሚችል፣ እንዲሁም ከታችኞቹ የክልሉ መዋቅሮች ጋር የፌዴራል መንግሥት በምን አግባብ ሊገናኝ እንደሚችል አላብራሩም፡፡
የሕወሓት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል በመሆን እያገለገሉ የሚገኙት አቶ ጌታቸው ረዳ ሪፖርተር የተላለፈውን ውሳኔ አስመልክቶ ላነሳላቸው ጥያቄ፣ ውሳኔው በሕገወጥ ምክር ቤት የተላለፈ ውሳኔ በመሆኑ ሕገወጥ ነው ሲሉ በማጥላላት፣ ይኼም ክልሉ የሚገባውን እንዳያገኝ የሚያደርግ ነው ሲሉ ኮንነውታል፡፡
‹‹ትግራይ የሚገባትን እንዳታገኝ የሚያደርግ ማንኛውም ውሳኔ የጦርነት አዋጅ ነውና ይኼ ሲደረግብን እንዴት እንደምንመልስ የምናይ ነው የሚሆነው፡፡ እኛ አዲስ አበባ ያለ ሽፍታ እንደወሰደው የጦርነት አዋጅ ነው የምንቆጥረው፤›› ብለዋል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተካረረ የመጣውን የሁለቱ ወገኖች ግንኙነት በተመለከተ ምልከታቸውን ለሪፖርተር ያጋሩት ዕውቁ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)፣ ሁኔታዎች አሁን ካሉበት ደረጃ አንፃር ወዴት ሊያመሩ እንደሚችሉ መገመት አይቻልም ይላሉ፡፡
በአንድ አገር ሁለት መንግሥት ሊኖር እንደማይችልና የትግራይ መንግሥት ክልላዊ መንግሥት ቢሆንም ለፌዴራል መንግሥት ዕውቅና አልሰጥም በሚል መገዳደሩ፣ እንዲሁም የፌዴራል መንግሥት ከትግራይ ጋር ያለኝን ግንኙነት አቋርጫለሁ ማለቱ ለአገሪቱ የፖለቲካ ችግር ተጨማሪ ቀውስ እንደሚፈጥር በመጠቆም፣ እንዴት ሊፈታ እንደሚችል አይታወቅም ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
ይኼም የተለመደ ችግር ባለመሆኑ ለፖለቲካ ቀውሱ ተጨማሪ ማባባሻ ነው የሚሆነው በማለትም፣ ‹‹የሁለቱንም የመጨረሻ ጨዋታ አናውቅም፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡
በኢትዮጵያ ከሚጠቀሱ የሕገ መንግሥት ምሁራን አንዱ የሆኑትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር ጌታቸው አሰፋ (ዶ/ር)፣ አሁን እየተላለፉ ያሉት ውሳኔዎች የፌዴራል መንግሥት በ2012 ዓ.ም. ሊያደርግ አቅዶት የነበረውን ምርጫ ለማራዘም በፌዴሬሽንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች የተወሰነ ውሳኔን ተከትሎ የመጣ እንደሆነ በማስታወስ፣ ‹‹በዚህ መካከል ወሳኝ የሆነው ክስተት በሕወሓት የተላለፈው ይኼንን ውሳኔ አልቀበልም የሚለው ውሳኔና ሕገ መንግሥታዊ ባለመሆኑም አልቀበለውም ማለቱ ነው፤›› ይላሉ፡፡
ይኼንንም ተከትሎ በትግራይ ምርጫ እንዲከናወን መደረጉና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ደግሞ ምርጫው እንዳልተደረገ እንደሚቆጠርና ሕጋዊ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው ማስታወቁ፣ ጉዳዩን እያባባሰው በመምጣቱ የትግራይ ክልል ደግሞ ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ግንኙነት እንደማይኖረው በማስታወቅ የሕወሓት አባላት የሆኑ ከፍተኛ ባለሥልጣናትም ‹‹የጥገኛና አምባገነን›› ነው ካሉት የፌዴራል መንግሥት ጋር እንዳይሠሩ በማሳሰብ መቀሌ በሚገኘው የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ሪፖርት እንዲያደርጉ ጥሪ አድጓል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ከትግራይ ክልል ጋር ለመንግሥታዊ አገልግሎቶች ብቻ እንደሚገናኙና የአፈጻጸም ዝርዝሩም በሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲወሰን ሲል አስታውቋል፡፡
‹‹በፌዴራል ሥርዓት ውስጥ በተለይ የክልልና የፌዴራሉን መንግሥታት የሚያስተዳድሩት ፓርቲዎች የተለያዩ ከሆኑ፣ በሁለቱ መካከል በአንዳንድ ጉዳዮች የከረሩ ልዩነቶች እንደሚኖሯቸው ግልጽ ነው፤›› በማለት፣ ‹‹ግን አብረው ሲኖሩ ግጭቶቹ እንዴት ይፈቱ ነው ይባላል እንጂ ግጭቶች አይቀሩም፤›› ሲሉ ጌታቸው (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡
ነገር ግን ግጭቶቹ የሚገቱባቸው አግባቦች በሕገ መንግሥት እንደተቀመጠው መፈታት አለባቸው በማለት፣ በኢትዮጵያም ይኼንን መሰል ልዩነቶች ለመፍታት የሚያስችል ሥልጣን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ተሰጥቷልና በዚህ አግባብ መፈታት ይገባዋል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
‹‹ክልሎች የፌዴራሉ መንግሥት ለእነርሱ የማይስማማቸውን ውሳኔ ተላልፏል ሲሉ አቤቱታ የሚያቀርቡበት ሥርዓት አለ፡፡ ይኼም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚቀርብ ቅሬታ አማካይነት መፍትሔ ያገኛል፤›› ያሉት ጌታቸው (ዶ/ር) ፣ ‹‹ከዚህ ውጪ ያለ አካሄድ ከፌዴራል ሥርዓቱ ጋር አይሄድም፤›› ይላሉ፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በፌዴራልና በክልል መንግሥታት መካከል የተከፋፈለው ሥልጣን በአግባቡ ተተግብሯል ወይ በማለት ሚዛን የሚያበጅ ተቋም ስለሆነ፣ በዚህ ተቋም አማካይነት ችግሮች ይፈታሉ ይላሉ፡፡ ነገር ግን በዚህ ሥርዓት አልዳኝም የሚል የክልል መንግሥት ሲገኝ ከፌዴራል ሥርዓቱ የግጭት አፈታት መርህ ጋር አይሄድም ሲሉ ምሁሩ ይጠቁማሉ፡፡
‹‹በፌዴራል መንግሥት የሚሰጠውን ውሳኔ ባንወደውም መቀበል አለብን፤›› በማለት የሚያስገነዝቡት ጌታቸው (ዶ/ር)፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያስተላለፈው ውሳኔ ግን ከዚህ አንፃር ሲታይ አስቸጋሪና አማራጭ ከማጣት በመነሳት የተላለፈ ይመስላል በማለት ግንዛቤያቸውን ያጋራሉ፡፡ ነገር ግን አንድ የፌዴሬሽኑ አባል የፌዴራሉን መንግሥት ውሳኔ አልቀበልም ካለ ከዚህም ያለፉ ውሳኔዎች ሊወሰዱ ይችላሉም ይላሉ፡፡
ይሁንና አሁን የተወሰደው ዕርምጃ ተገቢ ዕርምጃ ነው ወይ የሚለው አከራካሪ እንደሚሆንም አልሸሸጉም፡፡ ነገር ግን ለተግባራዊነቱ ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች አስቸጋሪ ያደርጉታል በማለትም ያስረዳሉ፡፡
የመጀመርያው ምክንያት በክልሉ ያሉት የታችኛው የመንግሥት መዋቅር አካላትን የሚመሩ ኃላፊዎች የፓርቲው አባላት ስለሚሆኑና የአንድ ፓርቲ መዋቅር በላይኛው የመንግሥቱ ኃላፊዎች ብቻ ይመራል የሚለው አስተሳሰብ የተሳሳተ ስለሚሆን፣ የታችኞቹ ማዕከላዊነት ከሚታይበት የፓርቲው ሕገ ደንብ ይወጣሉ የሚለው ስለማያሳምን ለመፈጸም ያስቸግራል ይላሉ፡፡ ‹‹እንዲያው አንድ ተዓምራዊ የሆነ መንገድ እስካልተቀየሰ ድረስ፤›› በማለትም አስቸጋሪነቱን ይጠቁማሉ፡፡
ሁለተኛው ደግሞ የፌዴራል መንግሥት በየትኛው መዋቅሩ የአገልግሎትና የፋይናንስ ክፍፍልን እንደሚተገብር ግልጽ ባለመሆኑና ይኼም አስቸጋሪ ስለሚሆን፣ የፌዴራል መንግሥት የራሱን ተቋም በክልሉ ያቋቁም እንደሆነም ይጠይቃሉ፡፡
ያም ሆነ ይህ በሁለቱ ወገኖች መካከል እየታየ ያለው መካረር በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሆነ ግልጽ ነው የሚሉት ጌታቸው (ዶ/ር)፣ ‹‹የፌዴራል ሥርዓቱን መስተጋብር የሚጎዳ ክስተት እየተባባሰ መጥቷል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ መስተጋብር በትክክል እየተከናወነ ነው ለማለት ሁሉም በአንድ ላይ መሄድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አልገዛም የሚል ካለ ይኼንን ሥርዓት ነው የያዘው፤›› በማለትም ያስገነዝባሉ፡፡
ስለዚህም ቀጣዩ ወሳኝ ሁኔታ የሚፈጠረው በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅት ሲጀመር እንደሆነ፣ ያኔ በምርጫው ለመሳተፍ አልያም ላለመሳተፍ ሕወሓት የሚያስተላልፈው ውሳኔ ቁልፍ ነው ይላሉ፡፡
‹‹ሕወሓት በምርጫው ይወዳደራል ወይስ አይወዳደርም የሚለው ወደ ቀጥተኛ ግጭት ሊያመራ ይችላል፤›› ሲሉ ምልከታቸውን ያመላክታሉ፡፡
ነገር ግን መረራ (ፕሮፌሰር) እና ጌታቸው (ዶ/ር) የሚስማሙበት ዋናው ጉዳይ በሁለቱም ወገኖች ዘንድ የጦርነት ፍላጎት እንደሌለ እየገለጹ ቢሆንም፣ ወደ ጦርነት ሊያስገቧቸው የሚችሉ ምክንያቶች መኖራቸውን ነው፡፡
መረራ (ዶ/ር)፣ ‹‹እሳካሁን ሁለቱም ወገኖች ወደ ጦርነት አንገባም እያሉ ቢሆንም፣ ግን አይገቡም ማለት አይቻልም፤›› ብለው የሚያምኑ ሲሆን፣ ይኼም ሊሆን የሚችለው በአንድ አገር ሁለት መንግሥታት እየተገዳደረሩ ሊኖሩ ስለማይችሉ ነው ይላሉ፡፡
‹‹ሁለቱም ተቻችለው ጨዋታውን እንጫወት ካላሉ በስተቀር በአንድ መቶ አንድ ምክንያቶች ሊጋጩ ይችላሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ አንዱ የሌላውን ፍላጎት ካልተቀበለ በስተቀር ለረዥም ጊዜ አብረው ሊኖሩ አይችሉም፤›› ሲሉም ያስረዳሉ፡፡
ይሁንና የዚህ ውጤቱ የከፋ እንደሚሆን ግልጽ ስለሚሆን፣ ሁሉን አካታች አገራዊ መግባባት ማምጣት ወሳኙ መፍትሔ ነው ይላሉ፡፡
የፌዴራል መንግሥት ወደ ጦርነት ለመግባት ፍላጎት የለኝም የሚልና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በበኩሉ ለዚህ መሰል ዕርምጃ በቂ ምክንያቶች ቢኖሩም ወደ መሰል ዕርምጃ የመግባት ፍላጎት የለም እያሉ ቢሆንም፣ በግልጽ ሕገ መንግሥቱን የመጣስ ድርጊቶች የፓርላማውን ውሳኔ ባለመቀበልና በፌዴራል የሚሠሩ ባለሥልጣናትን እንዲወጡ ማዘዝ በምን ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የተደረጉ ናቸው የሚል ጥያቄ መነሳት አለበት በማለት፣ እንዲህ ያሉ ዕርምጃዎች የመንግሥት ትዕግሥት እንዲለወጥ ያደርጋል ሲሉም ያስረዳሉ፡፡
ነገር ግን በመንግሥት እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎች መንግሥትንና ፓርቲን መለየት አለባቸው በማለት የሚያሳስቡ ሲሆን፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በሕገ መንግሥቱ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችና በምርጫ ሕግ፣ እንዲሁም በወንጀል ሕጉ ድንጋጌዎች ተገቢ ዕርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል በማለትም ጌታቸው (ዶ/ር) አማራጭ መፍትሔዎችን ይጠቁማሉ፡፡
‹‹እነዚህን አማራጮች በተግባር ላይ አውሎ ሕገ መንግሥቱን የማስከበር ዕርምጃ ሊወሰድ ይችላል፤›› በማለት፣ ከኃይል ዕርምጃዎች መቅደም ያለባቸው ድርጊቶች መኖራቸውን ያስገነዝባሉ፡፡