Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኬብል መጓጓዣና ነዳጅ ማስተላለፊያዎችን ወደ ሥራ የሚያስገባው ፖሊሲ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከመጪዎቹ አሥር እስከ አሥራ አምስት ዓመታት ውስጥ በትራንስፖርት፣ በሎጂስቲክስ እንዲሁም በሞተር አልባ ትራንስፖርት መስክ ለማከናወን ያቀዳቸውን ተግባራት የሰነቀ ስትራቴጂ ይፋ አድርጓል።

መስከረም 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው የፖሊሲ ሰንድ፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉን በማዘመን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለማቀላጠፍ የታሰበበት እንደሆነ አስታውቋል። በዘርፉ የተንሰራፋውን ችግር ለመቅረፍ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ባለፉት ሁለት ዓመታት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ዝግጅትና ቀረፃ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ እንደነበረ ገልጿል፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ ዝርዝር የአሥር ዓመት ዕቅድ አዘጋጅቶ ማጠናቀቁን የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ አስታውቀዋል።

የመንገድ ሽፋንና ጥራትን ማሻሻል፣ አዳዲስ የመሠረት ልማት ግንባታዎችን ማከናወን በተለይም፣ የገመድ ትራንስፖርት ወይም ኬብል ካር፣ የነዳጅ ማስላለፊያ ቧንቧ የመሳሰሉትን አገልግሎቶች ወደ ሥራ የማስገባት ዕቅድ በስትራቴጂው መካተቱን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል። መሥሪያ ቤቱ ብሔራዊ የትራንስፖርት ፖሊሲ አዘጋጅቶና ዕቅድ ነድፎ ወደ ትግበራ እንዳስገባ በዚህ ሳምንት ይፋ ቢያደርግም፣ የፖሊሲ ትግበራው ግን ካለፈው ዓመት ጀምሮ ሥራ ላይ እንደዋለ አስታውሷል፡፡ ስትራቴጂክ ዕቅዱ ከ2012 ዓ.ም. እስከ 2027 ዓ.ም. ድረስ የኬብል ካር፣ የነዳጅ ማስላለፊያ ፓይፕላይን፣ የኬብል ትራንስፖርትና የጭነት አገልግሎቶችን ለማስፋፋት በመወጠን ወደ ትግበራ ገብቷል።

ከትራንስፖርት መሠረተ ልማትና አገልግሎት አኳያ፣ ለኢትዮጵያ አዲስ የሆነው የኬብል ትራንስፖርት ሲሆን፣ ለከተሞች አማራጭና ከትራፊክ መጨናነቅ ብሎም ከማይመቹ አካባቢዎችና ተራራማ ሥፍራዎች ለሚደረጉ የትራንስርት እንቅስቃሴዎች ተመራጭ ከመሆኑ አንፃር በኢትዮጵያም ይተገበራል ተብሏል፡፡

በርካታ ሕዝብ በሚኖርባቸው ከተሞች ላይ የሚተገበረው ይህ አገልግሎት በአየር ላይ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚጎተት የከተማ የትራንስፖርት መገልገያን ዕውን የሚያደርግ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ በፖሊሲው ከተካተቱ ጉዳዮች አንዱ ይህ ትራንስፖርት እንደሆነ ያብራሩት የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ አቶ ጋሻው ጠና ናቸው፡፡ ሌላኛው በፖሊሲው የተካተተው አዲስ የትራንስፖርት ዘዴ የነዳጅና ፈሳሽ ምርቶች ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር ወይም ፓይፕላይን ትራንስፖርት ነው፡፡ ይህ መሠረተ ልማት የነዳጅ ውጤቶችና ሌሎችም ፈሳሽ ምርቶችን ለማስተላለፍ አነስተኛ ወጪ የሚጠይቅ የትራንስፖርት ዘዴ ከመሆኑ በተጨማሪ በወጪ ቆጣቢነቱና በተደራሽነቱ ተፈላጊና ተመራጭ ሆኖ በፖሊሲው መካተቱን አስታውቀዋል። መሐል አገርን ከወደቦች የሚያገናኙ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧዎችን በሒደት መገንባት እንደሚያስፈልግ አቶ ጋሻው ጠቁመዋል። በተጨማሪም የመንገድ፣ የባቡር፣ የአየርና የባህር መሠረተ ልማቶች ላይ ማስፋፊያዎችና ማሻሻያዎችን የማካሔድ ዓላማ ያነገበ ፖሊሲ ወደ ሥራ መግባቱ ተገልጿል።

በሌላ በኩል የፖሊሰው አንድ አካል እንደሆነ የተገለጸው የሎጂስቲክስ አገልግሎት ዘርፉ የሚመራበት ፖሊሲ ሲሆን፣ እስከ ቅርብ ጊዜ የነበረው የሎጂስቲክስ ዘርፍ አገልግሎት በግልጽ በታወቀ የፖሊሲ አቅጣጫ የሚመራ እንዳልነበርና ባለመሆኑ አገልግሎቱም ኋላ የቀረና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ያልተደገፈ መሆኑ ተንስቷል። በ2011 ዓ.ም.  መንግሥት ዘርፉን ያዘመነ የሎጂስቲክ ዘርፍ የሚመራበት የፖሊሲ ሰነድ ማስናዳቱ ይታወሳል። 

የሎጂስቲክ አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋሞች ውስጥ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አንዱ ሲሆን፣ አራት የተለያዩ በሎጂስቲክ ሥራ ሲሠሩ የነበሩ ድርጅቶችን በማዋሃድ የተቋቋመ የልማት ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት  አገልግሎቶች የባህር ትራንስፖርት፣ የደረቅ ወደብ አገልግሎት፣ የትራንዚት ወይም የዕቃ ማስተላለፍ አገልግሎትና የጭነት ትራንስፖርት አግልግሎቶችን ሲሰጥ መቆየቱ ተገልጿል።  ሆኖም በርካታ መዋቅራዊ የሥራ አፈፃፀም ችግሮች እንዳሉበትና የአገልግሎት መስኮችን በብችኝነት መያዙና የግል ባለሀብቱን ፍላጎት ቢያሳይም  አለማካተቱ እንደ ደካማ ጎኑ ተነስቷል። 

ኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት የምታገኘው በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ኃላፊነት ሲሆን፣ ይህ ተቋም በሌሎች የውጭ አገር ኩባንያዎች አማካይነት አገልግሎቶችን ያገኛል፡፡ በዚህ ረገድ የሚስተናገደው የጭነት መጠን ከአገሪቱ አጠቃላይ የወጪ ንግድ ውስጥ 25 በመቶ ያህል እንደነበር የማሪታይም ጉዳዮች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኰንን አበራ አስረድተዋል። ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ከአተገባበር አንፃር የተለያዩ ሥልቶችንና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ አትራፊ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ እንደሚያስፈልግ አቶ መኰንን ይገልጻሉ፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ የመርከብ ባለቤት ወይም ብሔራዊ የንግድ መርከብ ባለቤትና አገልግሎት ሰጪ ሆና እንድትቀጥል ማድረግ የመንግሥት ፍላጎት በመሆኑ ይህም በአዲሱ ፖሊሲ እንደሚተገበር አክለዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የ11 ንግድ መርከቦች ባለቤት ስትሆን፣ በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አማካይነት ከሚጓጓዘው አጠቃላይ ጭነት ውስጥ በኢትዮጵያ መርከቦች የሚጓጓዘው ጭነት ግን 20 በመቶ ብቻ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ውጭ አገር የመርከብ ኩባንያዎችን በመጠቀም በኪራይ፣ የተወሰነ የመጫኛ ቦታ በማከራየትና መሰል አሠራሮችን በመከተል በውጭ አገር የመርከብ ኩባንያዎች የሚጓጓዘው የኢትዮጵያ ጭነት 80 በመቶ ድርሻ አለው።

 በተጨማሪም በፖሊሲው ከተካተቱ ጉዳዮች ውስጥ በደረቅ ወደቦች የጋራ አጠቃቀም ሥርዓትን መዘርጋት፣ የደረቅ ወደቦችን በጋራ ማልማትና ማስተዳደር እንዲሁም የመልቲሞዳል ትራንስፖርት አገልግሎቶችን ማስፋፋት እንደሆነ ጠቅሰዋል። በተለይም የመልቲሞዳል ትራንስፖርት ተገምግሞ በውጭ ምንዛሪ ሊወጣ ይችል የነበረውንና በዓመት በአማካይ ከ20 ሚልዮን ዶላር ያላነሰ ወጪ ለመቀነስ ማስቻሉን አቶ መኰንን ይጠቅሳሉ። ከዚህ ባሻገር የመልቲሞዳል ኦፕሬተርነት ፈቃድ በአጭር ጊዜ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች እንደሚሰጥ፣ ወደፊትም ለውጭ ባለሀብቶች በመስጠት የተሻለ የአገልግሎት አማራጭና ወጪ ቆጣቢ ሥራ ለመሥራት ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ አብራርተው፣ ይህ እንዲተገበር መንግሥት መወሰኑን አቶ መኰንን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ፖሊሲው ካካተታቸውና ወደፊት በሚኒስቴሩ ከሚተገበሩ ሥራዎች መካከል አንዱ የሞተር አልባ ትራንስፖርት አገልግሎት ነው። በኢትዮጵያ 21 በመቶ ሕዝብ በከተሞች አካባቢ እንደሚኖሩ ይታመናል፡፡ በዚህም ከ21 ሚሊዮን በላይ የከተማ ነዋሪዎችን እንዳሉ ይገመታል። የኢትዮጵያ ከተሞችና የገጠር ማዕከላት እያደጉ በመጡ ቁጥር እየጨመረ የሚመጣ የትራንስፖርት አግልግሎት ፍላጎት እየጨመረ የሚሄድ ከመሆኑም በተጨማሪ በትራፊክ መጨናነቅ፣ በአደጋዎች መበራከት ምክንያት የሚመጡ  ከባድና ቀላል ጉዳቶችን፣ የአካባቢ አየር ብክለትን ለመቀነስም እንዲህ ያለው የትራንስፖርት አማራጭ ታሳቢ መደረግ እንዳለበት ተመላክቷል፡፡  

እስካሁን ሲገነቡ የቆዩት መንገዶች ሞተር አልባ ትራንስፖርትን ታሳቢ ባለማድረጋቸው በኢትዮጵያ ሞተር አልባ ትራንስፖርት እንዳይስፋፋ እንቅፋት ሆኖ መገኘቱን ሚኒስቴሩ ይጠቅሳል፡፡ ወደፊት የሚካሄዱ ግንባታዎች ግን የሞተር አልባ ትራንስፖርቶችን እንደሚያካትቱ ወ/ሮ ዳግማዊት አስታውቀዋል። አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል በተለይም በዝቅተኛ የገቢ መጠን የሚተዳደረው ሕዝብ በእግሩ የሚጓዝ እንደመሆኑ ይህን መሠረት ያደረገ ግንባታ መካሄድ አለበት ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሞተር ትራንስፖርት እየጨመረ ቢመጣም፣ ከነዋሪው መካከል 54 በመቶው የእግር ጉዞ የሚያዘወትር ሆኗል፡፡ በሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት የሚገለገለው 31 በመቶ ሲሆን፣  የግል ተሽከርካሪዎች ያሏቸውና በግላቸው ትራንስፖርት የሚጓጓዙት ድርሻቸው 15 በመቶ ብቻ  እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከስምንት ዓመታት በፊት በተደረገ ጥናት መሠረት በባህር ዳር ከተማ ብስክሌት 90 በመቶ ድርሻ ነበር፡፡ በሐዋሳም 88 በመቶ ሽፋን ነበረው፡፡ ከ2013 ዓ.ም. እስከ 2022 ዓ.ም. በሚኖሩት አሥር ዓመታት ውስጥ የሞተር አልባ ትራንስፖርትን ለማሳደግ ፖሊሲ የነደፈው ትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ የመሬት አቀማመጣቸው አመቺ በሆኑ የተመረጡ የክልል ከተሞችም ይህንኑ ሥርዓት ለማስፋፋት እንዳቀደ ገልጿል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች