Thursday, April 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አነስተኛ የገንዘብ ተቋማትን ወደ ባንክ የማሳደግ ፋይዳ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሰሞኑ ትኩረት ሳያገኙ ካለፉ አንኳር አንኳር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያዎች መካከል አነስተኛ ገንዘብ አቅራቢ ተቋማት ወይም ማይክሮ ፋይናንስ ድርጅቶችን ወደ ባንክ ማደግ የሚችሉበት መመርያ መውጣቱ አንዱ ነው፡፡   

እርግጥ መመርያው ከመውጣቱ ከዓመታት በፊት የባንክ ንግድ ሥራ ማቋቋሚያ አዋጅም ሆነ የአነስተኛ ገንዘብ አቅራቢ ተቋማት መመርያ አዋጅ፣ እነዚህ ድርጅቶች ባንክ መሆን በፈለጉ ጊዜ ባንክ መሆን እንደሚችሉ ደንግገዋል፡፡ ሆኖም ማስፈጸሚያ መመርያ ሳይወጣለት በቆየው ጉዳይ ላይ ድርጅቶቹ ጥያቄ ሲያነሱ ቆይተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ40 በላይ አነስተኛ የገንዘብ አቅራቢ ድርጅቶች ሲኖሩ፣ ከፍተኛ ካፒታል ያሰባሰቡ፣ አቅማቸው ከአንዳንድ ባንኮች የበለጠ ብልጫ ያለው፣ በደንበኞቻቸው ብዛትና ባከማቸቱት ቁጠባና ብድር መጠንም፣ ከአንዳንድ የግል ባንኮች የተሻሉ ሆነው በመገኘታቸው ጭምር፣ ባንክ የመሆን ፍላጎት ሲያራምዱ የቆዩት አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ይህንኑ ፍላጎታቸውን ሊመልስ የሚችል መመርያ በቅርቡ በብሔራዊ ባንክ ወጥቷል፡፡

መመርያውና አፈጻጸሙን በሚመለከት በብሔራዊ ባንክ የአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር አቶ መስፍን አበራ ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማትን ወደ ባንክ ለማሳደግ የሚያስችል መመርያ ይውጣ እንጂ፣ ብሔራዊ ባንክ በዕቅድ ይዞ ይህን ያህል ተቋም ወደ ባንክ ይደግ ወይም ባለበት ይቆይ የሚልበት አግባብ የለም፡፡ በመሆኑም ተቋማቱ በአንድ በኩል በገዛ ፍላጎታቸው ጥያቄ ሲያቀርቡ ይስተናገዳሉ፡፡

ይህ ፍላጎታቸው ግን መሠረታዊ ጉዳዮችን መመለስ የሚያስችል ቁመና ሊያላብሳቸው ይገባል፡፡ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ወደ መደበኛ ባንክነት ማደግ በሚፈልጉበት ወቅት፣ መደበኛ ባንኮች ማሟላት የሚጠበቅባቸውን መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች ሁሉ አሟልተው መገኘት ይጠበቅባቸዋል ያሉት አቶ መስፍን፣ አንድ ንግድ ባንክ እንዲያሟላ የተቀመጡ መሥፈርቶችንና ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ብቻውን በቂ አይደለም ይላሉ፡፡

እነዚህ ተቋማት ቀድመው ሲቋቋሙ በባንክ መስተናገድ ያልቻሉ፣ አነስተኛና ጥቃቅን የንግድና የምርት ዘርፎችን ጨምሮ ለግለሰብና ለቡድን ተበዳሪዎች፣ የቁጠባ ደንበኞች እንዲሁም ሌሎችም የፋይናንስ ነክ አገልግሎቶችን ሕጉ በሚፈቅድላቸው አግባብ ለመስጠት የተመሠረቱበትን መሠረታዊ ዓላማ፣ ወደ ባንክነት በሚያድጉበት ወቅትም ማስጠበቅና አገልግሎቱን መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከመነሻው ወደ መደበኛ ባንክነት ማደግ የሚፈቀድላቸው በክልል መንግሥታትና በከተማ አስተዳደሮች ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ የተመሠረቱ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ብቻ ሲሆኑ፣ እነዚህም ቢሆኑ ወደ ባንክነት ማደግ በሚፈልጉበት ወቅት እንደ አስፈላጊነቱ በመስኮት ደረጃም ሆነ በሚያመቻቸው መንገድ አነስተኛ የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ፍላጎትና የማሟላት ግዴታ ይጣልባቸዋል ያሉት የሱፐርቪዥን ከፍተኛ ኃላፊው፣ እነዚህ ተቋማት ወደ ባንክ እንደግ ዝግጁ ነን በማለት ወደ ብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ለማቅረብ ቢመጡ መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች የሆኑትን ማለትም የጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ፣ ጠቅላላ ጉባዔ ያጸደቀው አጀንዳ፣ የጠቅላላ ጉባዔው ስምምነት፣ መመሥረቻ ጽሑፍና መተዳደሪያ ደንብን ጨምሮ ሌሎችም ሕጋዊ ሰነዶችን አሟልተው መቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ተመርምሮና ፀድቆ ብቻ ግን ፈቃድ አይሰጣቸውም፡፡

ዝቅተኛውን የመመሥረቻ ካፒታል አሟልተው የመቅረብ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ ይኸውም 500 ሚሊዮን ብር ዝቅተኛ የተከፈለ ካፒታል ማቅረብ አንዱ ሲሆን፣ ከዚሁ ጎን ለጎን የኦዲትና ተያያዥ ማስረጃዎችን አሟልቶ ማቅረብም ሌላኛው ግዴታ ነው፡፡ በዚህ አግባብ ክልሎችም ሆኑ የከተማ አስተዳደሮች በመሠረቷቸው አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ያላቸው የአክሲዮን ድርሻ ለሌሎች ዓላማዎቻቸውንና ራዕዮቻቸውን ለሚጋሩ አካላት ማጋራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ተቆጣጣሪው ብሔራዊ ባንክ ሌሎችም መጠይቆችን ያስቀምጣል፡፡ በምዘና ነጥቦችን ከመካከለኛ በላይ ውጤት ማስመዝገብ፣ የመስክ ምልከታና ምርመራ ሲደረግ ብቃት አሟልቶ መገኘት፣ ብሔራዊ ባንክ ለሚያስቀምጣቸው የጥራት ደረጃዎች ብቁ ሆኖ መገኘት፣ የረጅም ዓመታት ገንዘብ አከል ሀብቶች ክምችትና እንቅስቃሴ፣ የሥጋት ምዘና እነዚህ ተቋማት ወደ ባንክነት ሲመጡ የሚመዘኑባቸው ነጥቦች ናቸው፡፡

እነዚህ መለኪዎች እንዳሉ ሆነው የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎት መስጠትም አንዱ ግዴታና ከእነዚህ ወደ ባንክነት ከሚያድጉ ተቋማት የሚጠበቅ ዓላማ ነው፡፡ ይህንን አገልግሎት መስጠት ያልቻለ ተቋም ባንክ እንዲሆን የተሰጠው ፈቃድ እስከመሰረዝ የሚያደርስ ዕርምጃ እንደሚጠብቀው አቶ መስፍን አስታውቀዋል፡፡

ወደ ባንክነት የማደጋቸው ሌላው ጥቅም አነስተኛ የፋይናንስ አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት ያፈሯቸው ደንበኞቻቸው ወደ ባንኮች በመሄድ የሚያገኙትን አገልግሎት እነዚሁ ተቋማት ባንክ ሲሆኑ፣ ወደ ባለሀብትነት ያሳደጓቸውን እነዚህን ደንበኞች ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖራቸውም ይታመናል፡፡

የኢትዮጵያ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ማኅበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ከበደም ተመሳሳይ ሐሳቦችን አንሸራሽረዋል፡፡ ቁጠባ፣ ብድር፣ መድን፣ ገንዘብ መላክና መቀበል ወዘተ. ያለውን ሥራ እንዲሠሩ በአዋጅ ቁጥር 40/1996 የተቋቋሙት አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት፣ በ2006 ዓ.ም. በተሻሻለውና በባንክ መመሥረቻ አዋጅም ወደ ባንክነት የማደግ መብት እንዳላቸው መፈቀዱን አስታውሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከአምስት ሚሊዮን በላይ አባወራ ወይም የቤተሰብ ተበዳሪ ደንበኞች ያፈሩት አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማቱ፣ በመንግሥት ተቋማት፣ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች አለያም ለትርፍ በተቋቋሙ ድርጅቶችና ባለሀብቶች አክሲዮን መዋጮ አማካይነት የባለቤትነት ሥሪት አላቸው፡፡ ሆኖም ወደ ባንክነት የሚያድጉት መንግሥታዊ ማይክሮ ፋይናንሶች 70 በመቶ ድርሻቸው በመንግሥት ተቋማት መያዝ እንደማይኖርበት ተደንግጓል፡፡

ወደ ባንክነት ማደጋቸው ምን ይፈይድላቸዋል? እንደ አቶ መስፍንም ሆነ እንደ አቶ ተሾመ ማብራሪያ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማቱ ባንክ መሆን ከቻሉ፣ የማደበር አቅማቸውን ማሳደግ መቻል፣ የቴክኖሎጂና የሲስተም ሥርዓታቸውን ማሻሻል፣ ሀብት የማሰባሰብና ኢንቨስት የማድረግ አቅማቸውን ያስፋፋዋል ይላሉ፡፡ አሁን ባሉበት ደረጃ በርካታ ቅርንጫፎች በመክፈታቸውና የተዘረጋ ሥርዓት ስላላቸው ምናልባት ችግር የሚሆንባቸው ዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ሊሆን እንደሚችል አቶ መስፍን ያምናሉ፡፡ አቶ ተሾመ በበኩላቸው የቅልጥፍናና የብቃት ችግሮቻቸው ሊቀረፉላቸው እንደሚገባ ይጠቅሳሉ፡፡

ይህም ሆኖ እስካሁን ጥያቄ ሲያቀርቡ የቆዩትና ትልልቆቹ የሚባሉት አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ለብሔራዊ ባንክ ወደ ባንክ ለማደግ የሚያስችል ጥያቄ እንዳላቀረቡ አቶ መስፍንም አቶ ተሾመም አረጋግጠዋል፡፡ እርግጥ የአንድ ዓመት የመሸጋገሪያ ጊዜ ቢሰጣቸውም፣ መበደኛ ባንክ ለመሆን በይፋ የጠየቀ አንድም ተቋም እንዳልቀረበ ታውቋል፡፡ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይና በደቡብ ክልል የሚገኙ እንደ አማራ አነስተኛ ብድርና ቁጠባ፣ ደደቢት አነስተኛ ብድርና ቁጠባ፣ ኦሞ አነስተኛ ብድርና ቁጠባን ጨምሮ አዲስ ብድርና ቁጠባ ያሉት ተቋማት ወደ ባንክ የማደግ ፍላጎት እንዳላቸው ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም እንደ አዲስ ብድርና ቁጠባ ያሉት ማይክሮ ባንክ የሚባል አደረጃጀት በሙከራ ደረጃ መሥርተውና ቅርንጫፍ ከፍተው ሁሉ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ይታወቃል፡፡

ባንክ የመሆናቸው ሌላው ፋይዳ፣ ከፍተኛ ሀብት ያካበቱ ደንበኞች ዝቅተኛ አቅም ያላቸውን ተበዳሪዎች እንዲደጉሙ የማስቻል ሚና እንደሆነ ያብራሩት አቶ ተሾመ ለዓመታት በአስተኛ የፋይናንስ ተቋማት መነሻ ዓላማና አገልግሎቶቻቸው ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች ላይም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ እነዚህ ተቋማት ከሚተቹባቸው ነጥቦች መካከል ከፍተኛ ወለድ መጠየቃቸው፣ ለሚሰጡት አነስተኛ ብድር በዋስትና የሚጠይቁት ብድር ማስያዣ፣ የቤት ካርታና ቦታ፣ የመኪና ሊብሬና መሰል የንብረት ማስያዣዎች መሆናቸው አገልግሎታቸው ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎች ናቸው፡፡

እንደ አቶ ተሾመ ምላሽ ግን ወለዳቸው ከባንኮች ከፍ ማለቱ ለአነስተኛ ብድር የሚያወጡት ከፍተኛ አስተዳደራዊ ወጪ መበራከቱ፣ የንብረት ዋስትና መጠየቃቸውም የሰጡት የሕዝብ ገንዘብ ሊመለስላቸው የሚችልበት ሌላ ማረጋገጫ ስሌላቸው እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ ይህም ሆኖ የቡድን የጠለፋ ዋስትና በሚባል አሠራር አንዱ ለሌላው ዋስ በመሆን ብድር የሚሰጥበት አግባብ እንዳለም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ ይህም በአብዛኛው በገጠራማው አካባቢ እንደሚተገበር አክዋል፡፡ በወለድ ረገድ የባንኮች ወለድም ቢሆን በአሁኑ ወቅት አነስተኛ ሊባል እንደማይችል የአንዳንዶቹን ይጠቅሳሉ፡፡

ከ20 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የአነስተኛ ፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት እንቅስቃሴ፣ በአሁኑ ወቅት 41 ደርሰዋል፡፡ 5.3 ሚሊዮን ተበዳሪዎችና ከ21 ሚሊዮን በላይ ቆጣቢ ደንበኞችን አፍርተዋል፡፡ ከ70 እስከ 75 በመቶ ከቁጠባ የመነጨ ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር የሰጡ ተቋማት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ ከ41 በተጨማሪ 18 አዳዲስ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ለማግኘት እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙ ከማኅበሩ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ለድህነት ቅነሳ ሚናቸውን እንደተጫወቱ የሚነገርላቸው እነዚህ ተቋማት ባንክ በሚሆኑበት ወቅት የበለጠ የፋይናንስ ተደራሽነትን ከባንኮች በተሻለ እንደሚያስፋፉም ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች