ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ እንዲራዘም በመደረጉ ምክንያት ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ የፌዴራል መንግሥት ሥልጣን እንደሚያበቃና ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ፓርላማው ሕጋዊ ሥልጣን እንደሌላቸው ያስታወቀው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)፣ በፌዴራል መንግሥት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ያላቸውን ውክልናና ኃላፊነት ለቀው ሪፖርት እንዲያደርጉ አደረገ፡፡
በሕወሓት ‹‹የሥልጣናችሁን ልቀቁ›› ትዕዛዝ የተላለፈላቸው ባለሥልጣናት አምባሳደር አዲስ ዓለም ባሌማ (ዶ/ር)፣ አቶ አፅበሃ አረጋዊ፣ አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር)፣ አቶ አባይ ወልዱ፣ ወ/ሮ ሮማን ገብረ ሥላሴ፣ ወ/ሮ አልማዝ መኰንን፣ አቶ ተስፋለም ይህደጎ፣ አብርሃም አዱኛ (ዶ/ር)፣ ወ/ሮ ምሕረት ምናስቦ፣ አቶ ገብረ ትንሳዔ ገብረ ሚካኤል፣ ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር፣ አቶ ገብረ እግዚአብሔር አርዓያ፣ እንዲሁም አቶ ገብረ እግዚአብሔር ገብረ ዮሐንስ ናቸው፡፡
ሕወሓት ከላይ የተዘረዘሩት ተሿሚዎች በተለያዩ ኃላፊነቶች ተመድበው እየሠሩ እንደሚገኙ የገለጸው፣ ሰኞ መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በሕወሓት ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ዓለም ገብረ ዋህድ ተፈርሞ በወጣው ደብዳቤ ነው፡፡ በፌዴራል ያለው አሃዳዊ ኃይል ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነ አግባብ ሥልጣኑን በማራዘሙ፣ ሕገወጥ መንግሥት ስለሆነና ፓርቲውም የዚህ ሕገወጥ ተግባር አካል ለመሆን እንደማይፈልግ በመግለጽ፣ ‹‹በፌዴራል ያላችሁን የሥራ ኃላፊነት በመልቀቅ ለፓርቲያችሁ ሕወሓት ሪፖርት አድርጉ፤›› ሲል ለአባላቱ ጥሪ አቅቧል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ ሊካሄድ የነበረው ምርጫ የተራዘመና ይኼም በፌዴሬሽን ምክር ቤትና በፓርላማው ተቀባይነት አግኝቶ የፀደቀ ቢሆንም፣ በክልል ደረጃ ምርጫ ያደረገው ሕወሓት 98.9 በመቶ የሚሆነውን የመራጮች ድምፅ በማግኘት፣ ከአንድ ወንበር በስተቀር የክልሉን ምክር ቤት ተቆጣጥሮታል፡፡ በዚህም ሕጋዊ መንግሥትነቱን በማረጋገጥ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) የክልሉ ፕሬዚዳንት አድርጎ የሰየመው ሕወሓት፣ ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ የፌዴራል መንግሥትና ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እንዲሁም ፓርላማው ተቀባይነት ስለሌላቸው በአገሪቱ ሁሉን አካታች የሆነ ውይይት እንዲደረግና ይኼንንም የሚያስኬድ አዲስ አስተዳደር እንዲዋቀር ጥሪ አቅርቧል፡፡
የፌዴራል መንግሥት በበኩሉ በትግራይ ክልል የተደረገው ስድስተኛው ክልላዊ ምርጫ እንዳልተደረገ የሚቆጠርና ተፈጻሚ የማይሆን ነው በማለት የደመደመ ሲሆን፣ የፓርላማው አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ በፌዴራል መንግሥት አማካይነት ከዘጠኝ እስከ 12 ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ እንዲደረጉ የተወሰነው ምርጫ ሲካሄድ የትግራይ ክልልም አብሮ ያደርጋል ሲሉ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡ ይሁንና የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ የፌዴራል መንግሥት የሥልጣን ዘመኑ በማብቃቱ የሚያወጣው ሕግም ሆነ ውሳኔዎቹ ተቀባይነት እንደማይኖራቸውና ምርጫም የማድረግ መብትም አይኖረውም እያሉ ነው፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አደም ፋራህ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ፣ በትግራይ ክልል የተደረገው ምርጫ ሕገ ወጥ ነው በማለት በክልሉ የተቋቋመውም መንግሥት ሕጋዊ አይደለም ያሉ ሲሆን፣ መንግሥት ይኼንን መንግሥት በማገድ ለፌዴራል መንግሥት በቀጥታ ተጠሪ የሆነ መንግሥት ለማቋቋምና እንደ አዲስ የምርጫ ዝግጅት ለማድረግ እንደሚገደድ አስታውቀዋል፡፡