Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እንዲመሠረት የቀረበው ጥያቄ በሕዝበ ውሳኔ እንዲረጋገጥ ተወሰነ

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እንዲመሠረት የቀረበው ጥያቄ በሕዝበ ውሳኔ እንዲረጋገጥ ተወሰነ

ቀን:

በደቡብ ክልል ሥር የነበሩ ስድስት ብሔሮች በጋራ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ለመመሥረት በምክር ቤቶቻቸው የወሰኑትን ውሳኔ ተከትሎ፣ ማክሰኞ መስከረም 26 ቀን 2013 ዓ.ም. ስብሰባውን ያደረገው ፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕዝበ ውሳኔ እንዲረጋገጥ ወሰነ፡፡

ምክር ቤቱ ተጨማሪ የሥራ ዘመኑን በይፋ በጀመረበት ማግሥት መስከረም 26 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ የሚገኙ አምስት ዞኖችና አንድ ወረዳ ካሉበት ክልል ወጥተው የራሳቸውን አዲስ የጋራ ክልል ለመመሥረት በተናጠል ምክርቤቶቻቸው አፅድቀው ያቀረቡትን ጥያቄ ተመልክቷል፡፡

አሁን ከሚገኙበት የደቡብ ክልል ወጥተው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች የተሰኘ ክልል ለመመሥረት ጥያቄ ያቀረቡት አምስት ዞኖች፣ የቤንች፣ የሸካ፣ የካፋ፣ የምዕራብ ኦሞ ዞን፣ የዳውሮ ዞንና የኮንታ ልዩ ወረዳ ናቸው፡፡

- Advertisement -

አምስቱ ዞኖችና አንዱ ወረዳ በሥነ ልቦና አንድነትና በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የተቀራረቡ መሆናቸውን በማመልከት አሁን ካለው የደቡብ ክልል አዲስ ለመመሥረት ባሰቡት አዲስ ክልል ውስጥ ቢተዳደሩ እንደሚመርጡና ይኼንን በተናጠል የሕዝብ ምክር ቤቶቻቸው ማፅደቃቸውን በመግለጽ እንዲወስንላቸው ምክር ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ 

በደቡብ ክልል የሲዳማን ክልልነት ተቀባይነት ካገኘ በኋላ 13 ብሔሮች ክልል ለመመሥረት ከደቡብ ክልል ምክር ቤት ጥያቄ አቅርበው የነበረ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ስድስት ብሔሮች በምክር ቤቶቻቸው ባፀደቁት መሠረት አንድ ክልል በጋራ እንዲመሠርቱ ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡ አንድ ክልል ለመመሥረት ጥያቄ አቅርበው የተወሰነላቸው የካፋ፣ የሸካ፣ የቤንች ሸኮ፣ የዳውሮና የምዕራብ ኦሞ ዞኖችና የኮንታ ልዩ ወረዳ ናቸው፡፡

ካሁን ቀደም የክልልነት ጥያቄ ያቀረቡ የደቡብ ክልል ዞኖች ሁሉም በምክር ቤታቸው ያፀደቁት በየራሳቸው ክልል ለመመሥረት ቢሆንም፣ በተለያዩ ጊዜያት መንግሥት ባቀረባቸው የመፍትሔ ሐሳቦች በመስማማት በጥምረት ክልል ለመመሥረት የተስማሙት ስድስቱ የደቡብ ምዕራብ ብሔሮች ናቸው፡፡

ባላቸው ሥነ ልቦናዊ፣ መልክዓ ምድራዊና ባህላዊ ቀረቤታ ምክንያት በጋራ ክልል ብንመሠርት የተሻለ ነው በማለት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያረቡትን ጥያቄ የተመለከተው ምክር ቤቱ፣ ጥያቄያቸውን አንድ ሳምንት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ አፅድቆላቸዋል፡፡ በዚህም ውሳኔ መሠረት 11ኛው የፌዴሬሽኑ አባል የሆነ ክልል ሆኖ እንዲመሠረት የሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድበት ወስኗል፡፡

ይሁንና ይኼንን አንድ አካባቢ ያሉ ዞኖች/ብሔሮች አንድ ክልል በጋራ እንዲመሠርቱ የቀረበውን ሐሳብ ያልተቀበሉ ዞኖች ያሉ ሲሆን፣ ከእዚህም ውስጥ ይኼንን ሐሳብ በማራመድ የዞን አመራሮች ሳይቀሩ በእስር ላይ የሚገኙበት ወላይታ ተጠቃሽ ነው፡፡ በተለይ የወላይታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተደጋጋሚ ሲደመጡ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በተለይ የወላይታ ዞን ብቻውን ክልል ሆኖ እንዲቋቋም እንደሚፈልጉ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች፣ እንዲሁም የወላይታ ዞን ምክር ቤት አባላት ሲያስታውቁም ነበር፡፡ ከዚህም ባለፈ የወላይታ ዞን የደቡብ ክልል ምክር ቤት ተወካዮች ይኼ ጥያቄያቸው በአጀንዳነት ተይዞ መፍትሔ የማይሰጠው ከሆነ፣ ‹‹በምክር ቤቱ መሳተፍ አንፈልግም›› በማለት ለምክር ቤቱ አስታውቀው ምክር ቤቱን ጥለው ወጥተዋል፡፡

በደቡብ ክልል በሚገኙ ዞኖች እየተነሱ የነበሩ የክልልነት ጥያቄዎች ተደጋጋሚ ሠልፎችን፣ አመፆችንና አድማዎችን አስከትለው የነበሩ በመሆናቸው፣ በክልሉ የተነሱትን ጥያቄዎች ለመመለስ ያስችለኛል በማለት የደቡብ ክልል ምክር ቤት በ20 ባለሙያዎች ከ17,000 ሰዎች በተሰበሰበ መረጃ ጥናት አስጠንቶ ነበር፡፡ በዚህም ጥናት በመጀመርያ ደረጃ ክልሉን እንዳለ ማቆየት፣ ካልሆነ ሲዳማ ቀድሞ ጥያቄው ተቀባይነት ያገኘ ስለነበረ ከሲዳማ ውጪ ያለውን የደቡብ ክልል እንዳለ ማቆየት፣ ወይም ክልሉን ከአምስት ባልበለጡ የተለያዩ ክልሎች መከፋፈል የሚሉ ምክረ ሐሳቦችን አቅርበው ነበር፡፡ አሁን እየሆነ ያለው የዚህ ጥናት ምክረ ሐሳብ የሆነውና በአቅራቢያ የሚገኙ ዞኖች አንድ ላይ ተሰባስበው ክልል እንዲመሠርቱ የተቀመጠው ምክረ ሐሳብ ይመስላል፡፡ ይሁን እንጂ ይኼ ጥናትና ምክረ ሐሳቡ በወቅቱ ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቦባቸው  እንደነበር ይታወሳል፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ጥያቄ ያቀረቡና ለጥያቄያቸው ምላሽ ያላገኙ ሰባት ዞኖች ሲኖሩ፣ በቀጣይ እነዚህ ጥያቄዎች የሚፈቱበት አግባብ ከክልልነት ጥያቄ ጋር ተያይዘው እየተነሱ ያሉ ውጥረቶችን ያረግባል ተብሎ ይታሰባል፡፡

በ2010 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ ወደ ሥልጣን የመጣው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር አንዱ ራስ ምታት ሆኖ የከረመው የክልልነት ጥያቄ ሲሆን፣ ይኼ ምላሽ ካገኘ አስተዳደሩ ከአገራዊ ምርጫ መራዘም ጋር ተያይዞ እየገጠሙት ያሉ ችግሮች ላይ እንዲያተኩር ይረዳዋል፡፡

ምንም እንኳን የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር በደቡብ ክልል ውስጥ ያሉ የክልልነት ጥያቄዎችን ለመፍታት በቀጥታና በተዘዋዋሪ መፍትሔዎችን ሲያቀርብና ውይይቶችን ሲያደርግ የቆየና በአፋጣኝ እንዲፈታ ሲጥር የነበረ ቢሆንም፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት ለደቡብ ክልል አስተዳደር ከባድ ፈተና መሆኑ አልቀረም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...