Thursday, June 13, 2024

ጽንፈኛ ብሔርተኝነትና የመፍትሔ አማራጮች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ግድም በኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካ ሕጋዊና መንግሥታዊ ቅርፅ ይዞ የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔር ማንነት ላይ የተመሠረቱ ስብስቦች እንዲሆኑ፣ እንዲሁም ክልሎች የብሔርና የቋንቋ መስመሮችን ተከትለው እንዲዋቀሩ አድርጓል፡፡ ይኼ መዋቅርና ፖለቲካዊ ቅርፅ በአንዳንዶች ዘንድ የሚደገፍ በሌሎች ዘንድ ደግሞ የሚነቀፍ ነው፡፡ ደጋፊዎቹ የአገሪቱን ብሔሮች የጭቆና ጥያቄ የሚፈታ ሥርዓት አድርገው የሚመለከቱት ሲሆን፣ ነቃፊዎቹ ደግሞ የብሔር ጽንፈኝነትን በማስፋት አገራዊ ስሜትንና ማንነትን ያሳንሳል ሲሉ ያጣጥሉታል፡፡

ያም ሆነ ይህ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ የብሔር ጽንፈኝነት መዛመትና ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች መበራከት እየተስተዋለ ያለ ልምምድ ሆኗል፡፡ ከዚህ ባለፈም በተለይ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ሐሳብን ያለ ገደብ የመግለጽ ዕድል በመጠቀም፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የብሔር ጥላቻዎችንና ጽንፍ የረገጡ የብሔር ፍረጃዎችን መመልከት የተለመደ ሆኗል፡፡

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በሁለት ዙር የበርካታ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈው ጥቃት፣ በተለይ ብሔርን መሠረት ያደረገና የተወሰኑ አካላት ላይ ያተኮረ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው፡፡ በተጨማሪም የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያና በአዲስ አበባ በተፈጸሙ ጥቃቶች አናሳ ቁጥር ያላቸው ብሔሮች መጠቃታቸውን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሰጡት መግለጫ ላይ ጠቁመው ነበር፡፡

ቀለል ያለውና እየጎላ ለመጣው የብሔር ጽንፈኝነት የቅርብ ጊዜ ማሳያ በፋና ቴሌቪዥን ሲካሄድ የቆየው የሙዚቃ ውድድር ማጠቃለያ ውጤት ከጠበቁት በተለየ መንገድ መጠናቀቁን ያዩ ተመልካቾች በውድድሩ ዳኞች፣ እንዲሁም በተወዳዳሪዎች ላይ ሲሰነዝሯቸው የነበሩ ትችቶችና ስድቦች የበርካቶችን ትኩረት የሳበ ሲሆን፣ ስለጉዳዩ አስተያየት የሰጡም ሰዎች አዝማሚያው አስፈሪ እንደሆነ ሲጠቁሙ ተስተውሏል፡፡

ውድድሩን እንደ ተጠናቀቀ በዳኞችና በተወዳዳሪዎች ላይ ሲሰነዘሩ የነበሩ ብሔር ተኮር አስተያየቶችና ስድቦች በማኅበራዊ ትስስር ገጾች በስፋት የተሠራጩና የተነበቡ ሲሆን፣ ተቺዎች ከእኛ ወገን ናቸው ለሚሏቸው ተወዳዳሪዎች ድጋፍ ከመስጠት ባለፈ ከእኛ ወገን አይደሉም የሚሏቸውን ሲነቅፉና ሲያጣጥሉ ተስተውለዋል፡፡

በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል ይኼንን የብሔር መልክ የያዘ ክፍፍልን የተመለከቱት የሥነ ጽሑፍ መምህርና ደራሲው በድሉ ዋቅጅራ ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ ‹‹ውጤቱ ከታወቀ ጀምሮ የተወዳዳሪዎቹ አካባቢ ሰዎች በተለመደው መንገድ ጎጥ ለይተው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ውጊያ ገጥመዋል፡፡ አንዳንዶቹም ለሰፈራቸው ተወዳዳሪዎች የሽልማቱን ያህል ገንዘብ አዋጥተን እንሰጣለን እያሉ ነው፡፡ ይህ አይደነቅም፣ ቅኝታችን ሁሉ የጎጥ ነው፡፡ በጎጥ ሰው በሚገደልበት አገር በጎጥ መሸለም ከጽድቅ ይቆጠራል፤›› ሲሉ ተችተዋል፡፡

ይኼ የኢትዮጵያ አከራካሪ ጉዳዮች ትርክት መግለጫ አንዱ ማሳያ ሆነ እንጂ ከሃይማኖታዊ በዓላት፣ ከስፖርታዊ ክንውኖች፣ እንዲሁም ከሙያዊ ሥራዎች ጋር ተያይዘው የሚሰነዘሩ ምልከታዎችን መቃኘት የኢትዮጵያ ፖለቲካ በተለይ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ላይ ባሉ ማንነቶች እንደሚገለጸው በብሔር ጽንፈኝነትና ውገና የተቀኙ አስተሳሰቦችና እምነቶች የሚያሾሩት እንደሆነ ነው፡፡

ይኼ የጦዘ የብሔርተኝነት ትርክትና ሁሉንም ክስተትና አስተሳሰብ በዚህ ቅኝት መመልከት የመንግሥት ትኩረትን የሳበ ጉዳይ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ የአገሪቱ ቁጥር አንድ የብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት (National Security Threat) እንደሆነም በመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም. የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የነበሩትና አሁን የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተናግረው ነበር፡፡ በወቅቱ ‹‹የአገራዊ ደኅንነት ሥጋታችን አክራሪ ብሔርተኝነት ነው፤›› ያሉት አቶ ተመስገን፣ ‹‹ይኼኛው የብሔር ፖለቲካ ዋናው ነው እንጂ ብቸኛው አይደለም፡፡ ሁሉም ድርጊቶች አገራዊ ማንነትን የረሱ ናቸው፡፡ በአንድ ብሔር ውስጥ እንኳን ያሉ ክፍፍሎች በርካታ ናቸው፤›› በማለት ችግሩ ምን ያክል ጥልቅ እንደሆነ አስታውቀው ነበር፡፡

ጽንፈኝነት የፖለቲካ ግብን ለማሳካት ሲባል በሌሎች ላይ የሚፈጸሙ የአመፃ ጥቃቶችን ትክክል ናቸው ብሎ መቀበል እንደሆነ እ.ኤ.አ. በ2019 በአውሮፓ የሰላም ተቋም (European Institute of Peace) የፖሊሲ ሰነድ ያዘጋጁት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደኅንነት ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)፣ ጽንፈኝነትን በተመከለተ እስካሁን የነበረው አተያይ ከወታደራዊና ከደኅንነት ጋር የተገናኘ እንደሆነ በመጥቀስ፣ በዓለም ከሚታዩ እንደ ትራፊክ አደጋ ያሉ ገዳይ ጉዳዮች በበለጠ የበርካቶችን ሕይወት እየቀጠፈ እንዳለ በማመልከት ጽንፈኝነት ያመጣቸው ጥቃቶች በንፁኃን ላይ የሚሰነዘሩ፣ በሰብዓዊ መብቶችና በሰዎች ክብር ላይ አደጋን የሚደቅኑ፣ እንዲሁም የግለሰቦችን ደኅንነትና ምቾት የሚጎዱ ናቸው ይላሉ፡፡

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በኢትዮጵያ የተከሰቱ የተለያዩ በብሔር ጽንፈኝነት የተነሳሱ ጥቃቶችንና ግጭቶችን በምሳሌነት በማንሳት፣ የብሔር ጽንፈኝነት አጥፊ የሆነ ውስጣዊ አለመረጋጋትን የሚፈጥርና ዘርፈ ብዙ የፖለቲካ ቀውስ፣ እንዲሁም አሳሳቢ የሰላምና የደኅንነት ችግርን ይፈጥራል በማለት ያስረዳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ከውጭና ከውስጥ ፈተናዎች የሚገጥሟት ቢሆንም፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚመክረው አመፀኛ ጽንፈኝነትን ለመከላከል የሚረዳ ስትራቴጂ እንዳላዘጋጀች ይጠቁማሉ፡፡

‹‹እያደገ የመጣውን አመፅና በአገሪቱ ያለውን የፖለቲካ ምኅዳር የመክፈት ጅምር ከግንዛቤ በማስገባት፣ በመንግሥት ረገድ የብሔር ጽንፈኝነትን ለመከላከል የሚያስችል የተቀናጀ መፍትሔ ለመስጠት አስፈላጊ ሲሆን ዕድሉም አለ፤›› ሲሉ ያክላሉ፡፡

የብሔርተኝነት ፉክክር መነሻ የሆነው የብሔር ፖለቲካው እንደሆነና ይኼም በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና የተሰጠው በመሆኑ ነው የሚሉት ዮናስ (ዶ/ር)፣ በዚህ ሳቢያም ሰዎች ለዘመናት ከኖሩባቸው አካባቢዎች ሳይቀር እንዲባረሩና እንዲሰደዱ አድርጓቸዋል በማለት፣ እነዚህ ክስተቶች ወደ አመፅ አምርተው ነበር ይላሉ፡፡
‹‹ያልተሳደዱ ወይም በፈቃዳቸው ለቅቀው ያልወጡ አናሳ ቁጥር ሆነው የሚኖሩ ብሔሮች፣ ቋሚ በሚባል ደረጃ በመገደል ፍርኃት ተውጠው ይኖራሉ፤›› ሲሉም ይተነትናሉ፡፡

ከአሁን ቀደም እ.ኤ.አ. በዲሴምበር 2019 ለደኅንነት ጥናት ተቋም (አይኤስኤስ) በኢትዮጵያ ያሉ የብሔር ግጭቶችን በማስመልከት በጻፉት ጽሑፍ በኢትዮጵያ ላሉ የብሔር ግጭቶች ዋነኛ መነሻ ተፎካካሪ በሆኑ ጀብደኛ/ሞገደኛ ብሔርተኝነቶች ቁጥር መበራከት እንደሆነ አመላክተው የነበሩት የተቋሙ ከፍተኛ ተመራማሪ ሰሚር ዩሱፍ (ዶ/ር)፣ መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ለሚታዩ የብሔር ክፍፍሎች መፍትሔ ለማበጀት የሚረዱ የሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ አማራጮችን በዘረዘሩበት ጽሑፍ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳሩ የሰፋ ቢሆንም እንቅፋቶች አሉበት በማለት፣ ዋነኛው ችግር በፖለቲካ ልሂቃን መካከል ያለው ጽንፈኝነት ነው ይላሉ፡፡

በኢትዮጵያ ያሉ የታሪክና የፖለቲካ ትርክቶች ከ1960ዎቹ ከተማሪዎች አመፅና የአማፅያን እንቅስቃሴ ጋር የሚገናኙ ናቸው በማለት፣ ኢትዮጵያዊነትና ብሔርተኝነት፣ የብሔር ጭቆና ትርክትና የቅኝ ግዛት ትርክት፣ እንዲሁም ማዕከልና ጥግ በሚል የሚከፋፈሉ ትርክቶች እንዳሉ ያመላክታሉ፡፡

በኢትዮጵያ ተፅዕኖ ፈጣሪ በሆኑ ቡድኖች መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ የሚሆን አንድ መፍትሔ ብቻ ሊኖር እንደማይችል የሚጠቁሙት ሰሚር (ዶ/ር)፣ እያንዳንዱ ሥሪት አንዱን ወገን ብቻ የሚያስደስት ስለሆነ ይኼ የሚሆነው በሌላኛው ወገን በሚከፈል ዋጋ የሚሆን ነው ይላሉ፡፡

በኢትዮጵያ የብሔርተኝነትና የኢትዮጵያዊነት ትርክቶች ቅርፅ እየቀየሩና በውስጣቸውም አዳዲስ አስተሳሰቦችን እያፈሩ መምጣታቸውን በጽሑፋቸው የተነተኑት ሰሚር (ዶ/ር)፣ እስከ ዛሬ የነበረው የፖለቲካ ክርክር የሚያተኩረው ለ30 ዓመታት ገደማ በተግባር ላይ ያለው የኅብረ ብሔራዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት ላይ ነው በማለትም፣ የኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ተከስቷል ለሚባለው እኩል ያልሆነ የብሔሮች ግንኙነት ቀጥተኛ ምላሽ እንዲሆን የተተገበረ እንደሆነም ያስገነዝባሉ፡፡ ይሁንና ይኼንን የፌዴራል ሥርዓት አግላይ ነው በሚሉ ወገኖች ዘንድ ቅሬታ መፍጠሩንም አልሸሸጉም፡፡ ስለዚህም የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች አሁን ያለውን የፌዴራል ሥርዓት እንዳለ ከማስቀጠል አንስቶ ከትንሽ እስከ ጥልቅ ማስተካከያ ተደርጎ ፌዴራሊዝሙን መልክ ማስያዝ እንደሚፈልጉ ጠቁመዋል፡፡ በኢትዮጵያ የብሔር ክፍፍልን ለማስተናገድ ያሉ የተለያዩ አማራጮች የወቅቱን የአገሪቱን የፖለቲካ አስተሳሰቦችን ውስብስብነት ያሳያሉ የሚሉት ሰሚር (ዶ/ር)፣ የተለያዩ ወገኖች ለኢትዮጵያ ይበጃሉ የሚሏቸውን በርካታና አንዳንዴም የሚጋጩ ምክረ ሐሳቦችን የሚለግሱ እንደሆነ በማሳየት፣ ሁሉም ግን ከፌዴራል ሥርዓቱ ጋር የተቆራኙና ሥርዓቱን የሚደግፉ፣ የሚነቅፉ አልያም ሁለቱንም ያጣመሩ መፍትሔዎች እንዳላቸው ያስረዳሉ፡፡

ይኼንንም ከግምት በማስገባት የኢትዮጵያን የብሔር ክፍፍል ለመፍታት ይጠቅማሉ ያሏቸውን የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ምክረ ሐሳቦችን ከተለያዩ ሞዴሎች ጋር አቅርበዋል፡፡ የመጀመርያው አማራጭ ተፎካካሪ ኃይሎች ድምፆቻቸውን በማሰባሰብና በመስማማት ሥልጣን የሚጋሩበት ሥርዓት ሲሆን፣ በፓርላማውና በሕግ አስፈጻሚው አካል መካከል የሥልጣን ክፍፍል ለማድረግ ያግዛል ይላሉ፡፡ ሌላው ደግሞ የምርጫ ሥርዓቱን በመቀየር መራጩ የሚፈልጋቸውን ተወካዮች በተርታ ያስቀምጥና ኮታ የሞላለት ሰው ድምፅ ለሌሎች እየተላለፈ ሥልጣንን ለመጋራት የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት ሲሆን፣ ይኼም የሥራ አስፈጻሚው አካል በአብላጫ ድምፅ ወይም በጥምር እንዲያዝ የሚያደርግና ፓርላማ የሚገቡ ተወካዮችም በዚሁ አግባብ የተመረጡ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ ሦስተኛው በበርካታ ዘርፎች መፍትሔ ማቅረብ የሚችሉ ቡድኖች አካታች በሆነ ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም በድምፅ ማሰባሰብ እንዲችሉ ማድረግ ነው፡፡ በክፍልፋይ ውክልና ብሔራዊ ፌዴራዝምን በመከተል የብሔር ኮታንና አቻቻይነትን የተከተለን የሥልጣን ክፍፍል ማድረግ ሌላው አማራጭ ሞዴል ነው፡፡ አካታች ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝምን ፕሬዚዳንታዊ በሆነ ሥርዓት ማቋቋም ሌላኛው አማራጭ አድርገው ያስቀምጣሉ፡፡ የመጨረሻው ሞዴል አቻቻይነትን እንደ ቋሚ ሞዴል አድርጎ የሚወስድ ሲሆን፣ ጊዜያዊ የሆነ የሥልጣን ክፍፍል በማድረግ በፖለቲካ ቡድኖች መካከል እምነት፣ ፍላጎት፣ ፕሮግራምና ባህርይ መተዋወቅ መፍጠርን ያበረታታል፡፡

ጽንፈኛ ብሔርተኝነትን ለመከላከል ተቋማዊ የሆነ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ የሚጠቁሙት ዮናስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የግለሰቦች የብሔር ማንነት መከበር ያለበት ቢሆንም፣ የቀደመውን ዓይነት ጥፋት ላለመድገም በአገራዊ ማንነት ላይ አስፈላጊው ትኩረት ሊደረግ ይገባል ይላሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በደኅንነት ዘርፉ፣ በሕግ ተርጓሚው፣ በፖሊስ፣ እንዲሁም በሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ላይ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልግም የሚጠቁሙት ዮናስ (ዶ/ር)፣ ይኼም ከፌዴራል እስከ ክልል፣ ዞን፣ ወረዳና ቀበሌ ድረስ መዘርጋት አለበት ይላሉ፡፡

በተጨማሪም ጥፋት የፈጸሙ የሥራ ኃላፊዎችን ተጠያቂነት በማረጋገጥ ከሥራ እስከ ማስወገድ የሚዘልቁ ዕርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል ይላሉ፡፡ የሲቪል ማኅበረሰቡና ምሁራን ከኢትዮጵያና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር በመተባበር ወደ መፍትሔ ማምራት አለባቸው ሲሉ ያሳስባሉ፡፡

የኢትዮጵያ የብሔር ጽንፈኝነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣና በርካቶችን ሥጋት ላይ እየጣለ ያለ፣ እንዲሁም ሕይወት እየቀጠፈና አካል እያጎደለ ብሎም ንብረት እያወደመ ያለ ክስተት መሆኑን ገዥው የብልፅግና ፓርቲ የተገነዘበው እንደሆነ የተለያዩ ሰነዶች የሚያሳዩ ቢሆንም፣ መፍትሔው ግን በቅርብ የሚታይ እንዳልሆነ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -