Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮ ቴሌኮም ከ47.7 ቢሊዮን ብር ገቢ 28 ቢሊዮን ብር አተረፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አየር መንገድ ከ122 ቢሊዮን ብር በላይ አስገብቷል

የልማት ድርጅቶች ኤጀንሲ ዕቅዶቹን ይፋ ያደርጋል

ኢትዮ ቴሌኮም በ2012 ዓ.ም. እንቅስቃሴው 47.7 ቢሊዮን ብር ገቢ በማስገኘት ከታክስ በፊት 28.1 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማስመዘገቡ ተገለጸ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ ከ122 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ይፋ አድርጓል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በተጠናቀቀው 2012 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት ብር 28.7 ቢሊዮን ለማትረፍ አቅዶ በኩባንያው ጊዚያዊሒሳብ መረጃ መሠረት 28.1 ቢሊዮን ብር ወይም የዕቅዱን 98 በመቶ ማሳካት እንደቻለ ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡ እንደ ኤጀንሲው መረጃ፣ ኢትዮ ቴሌኮም የተጠቀሰውን የትርፍ መጠን ያስመዘገበው ከመደበኛ ስልክ፣ ከሞባይል፣ ከዳታ፣ኢንተርኔት እንዲሁም ተጨማሪ እሴት ከታከለባቸው አገልግሎቶች በድምሩ 47.7 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘት በመቻሉ ነው፡፡ የኩባንያው ዕቅድ 45.4 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማስገበት ነበር፡፡ ሆኖም የዕቅዱን 105 በመቶ በማግኘቱ ከ28 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገብ አስችሎታል፡፡

የተሸኘው በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በአቶ በየነ ብረ መስቀል በመሩት ስብሰባ ወቅት፣ ከኤጀንሲ ተጠሪ የልማት ድርጅቶች አንዱ የሆነው የኢትዮ ቴሌኮም አፈጻጸም መስከረም 13 ቀን 2013 .. በተገመገመበት ወቅት የኩባንያው አፈጻጸም ውጤት መገለጹ ተጠቅሷል፡፡

ለኤጀንሲው በቀረበለት ሪፖርት መሠረት፣ የኢትዮ ቴሌኮም የገቢ አፈጻጸም 2011 ዓ.ም. ከተመዘገበው የ43.6 ቢሊዮን ብር አኳያ፣ 3.5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ከደንበኞች ቁጥር አንጻርም ባለው ዓመት ከነበሩት 43.6 ሚሊዮን ደንበኞች አኳያ 2012 ዓ.ም. በሦስት ሚሊዮን ያህል ጭማሪ የታየበት አኃዝ በማስመዝገብ ብዛታቸውን ወደ 46.1 ሚሊዮን ከፍ አድርጓል፡፡ ይህም የ5.7 በመቶ ዕድገት ተመዝግቦበታል፡፡ በውጭ ምንዛሪ ጭምር አገልግሎቶቹን የሚያቀርበው ኢትዮ ቴሌኮም፣ 138 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዶ 148 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ችሏል፡፡ ይህም የዕቅዱን 107 በመቶ እንዳሳካ አመላክቷል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ቀደም ብሎ ለሕዝብ ይፋ እንዳደረገውም በ2012 ዓ.ም. ለውጭ አበዳሪዎቹ 10.2 ቢሊዮን ብር ወይም 318 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ የዕዳ ክፍያ ፈጽሟል፡፡ በአንጻሩ የአገር ውስጥ ብድር እንደሌለበት በግምገማው ወቅት ተገልጿል፡፡ የመንግሥት የትርፍ ድርሻና ታክስ ስለመክፈሉ በተገለጸው መሠረት አራት ቢሊዮን ብር የትርፍ ድርሻ፣ 11.3 ቢሊዮን ብር ታክስ፣  በድምሩ 15.3 ቢሊዮን ብር በታክስና በትርፍ ድርሻ ክፍፍል ለመንግሥት ገቢ ማድረጉን ኤጀንሲው ጠቅሷል፡፡ በከፍተኛ ታክስ ከፋይነቱ ዓምናም ሆነ ዘንድሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተሸለሙ የግልና መንግሥታዊ ድርጅቶች አንዱ እንደሆነ ይታወሳል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በተያዘው 2013 ዓ.ም. የሚያገኘውን ገቢ ወደ 55.5 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ አቅዷል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በ2012 ዓ.ም. በዓለም አቀፍና አገር ትራንስፖርት አገልግሎት መንገደኞችንና ዕቃዎችን በማጓጓዝ፣ የኤርፖርትና የሆቴል መስተንግዶ በማቅረብ ብሎም የጥገናና የአቪዬሽን ሥልጠናዎች በመስጠት፣ የ122.14 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ኤጀንሲው ይፋ አድርጓል፡፡ በዓመቱ 149.72 ቢሊዮን ገቢ ለማግኘት አቅዶ ነበር፡፡ ሆኖም የዕቅዱን 82 በመቶ ማሳካት ችሏል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በየነ ገብረ መስቀል፣ የአየር መንገዱ ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የኤጀንሲው የትራንስፖርት ዘርፍ ዳይሬክተርና ባለሙያዎች በግምገማው ተሳትፈዋል በተገኙበት መስከረም 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ግምገማ መካሄዱን ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡

የአቬሽን ኢንዱስትሪውን በሰፊው የጎዳውን የኮሮና ወረርሽኝ ተፅዕኖ አየር መንገዱ ተቋቁሞ ከፍተኛ ገቢ ሊያስመዘግብ የቻለው፣ በከፍተኛ መጠን የቀነሰውን የመንገደኞች ቁጥር ለማካካስ የሕዝብ ማመላለሻ አውሮፕላኖቹን ወደ ጭነት ማጓጓዣ (ካርጎ) አገልግሎት ሰጪነት ፈጥኖ በመቀየሩ እንደሆነ በግምገማው ወቅት ተወስቷል፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ የወጪ ቅነሳ ስልቶችን ተግባራዊ ማድረጉም የወረርሽኙን ጫና ለመቋቋም አስችሎታል ተብሏል፡፡ በዚህም ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ሊያድን ችሏል፡፡

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥር ከሚተዳደሩ 14 ሺሕ ሠራተኞች ውስጥ 34 በመቶዎቹ ሴቶች ሲሆኑ፣ አብዛኞቹም በማኔጅመንት፣ በአብራሪነትና በቴክኒሻንነት መስኮች ከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ የያዙና ጥሩ ደመወዝተኛ በሚያደርጉ የሥራ መደቦች ላይ መሰማራታቸው ተጠቅሷል፡፡

አቶ በየነ በሰጡት ማሳሰቢያ፣ የአየር መንገዱ ገቢዎች በተቻለ መጠን በአብዛኛው በውጭ ምንዛሪ እንዲሆኑና የውጭ ምንዛሪ ወጪዎቹንም ሊቀንሱ የሚችሉ አማራጮች እንዲታዩ ጠይቀዋል፡፡ በጅምር ከሚገኙ ፕሮጀክቶች መካከል ሊዘገዩ የሚችሉና በአፋጣኝ መጠናቀቅ ያለባቸው እንዲለዩ የጠየቁት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች ተጨማሪ ወጪ ሳያስከትሉ ተፋጥነው እንዲጠናቀቁ፣ ካለው የገበያ መቀዛቀዝ አኳያም የጥሬ ገንዘብ አስተዳደሩ ጥንቃቄ እንዲደረግበት ማሳሰባቸው ታውቋል፡፡  

እነዚህን ጨምሮ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ተጠሪ የሆኑ ተቋማት አጠቃላይ አፈጻጸምና የ2013 ዓ.ም. ዕቅድን በሚመለከት መስከረም 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ኤጀንሲው መግለጫ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከሚከታተላቸው አንዱ የሆነው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከኪሣራ በመውጣት ላለፉት ሁለት ዓመታት ትርፍ ሪፖርት ማድረጉ ከሚጠቀሱ ለውጦች አንዱ ሲሆን፣ ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት የምኅድስና ዘርፉ ለብቻው በመውጣት በተለያዩ ዘርፎች ተከፋፍሎ ራሳቸውን የቻሉ ድርጅቶች ከውስጡ እንዲፈጠሩ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ተፈጥሯል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች