በሔለን ተስፋዬ
በመገናኛ ብዙኃን ያለውን የመረጃ ክፍተት ለመሙላትና ለዓይነ ሥውራን ተደራሽ ለማድረግ ሳምንታዊ የብሬል ጋዜጣ መታተም ጀመረ፡፡
‹‹ፈትል›› በሚል ስያሜ የጀመረው የብሬል ጋዜጣ፣ በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚደርሰውን የፍትሕ መጓደልና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በሰፊው የሚቃኝ ነው ተብሏል፡፡ ፈትል ነቃሽ፣ እንግዳ፣ ጥበብ፣ ጉዞ (የባህልና ቱሪዝም) የሚሉ ዓምዶች ሲኖሩት፣ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ላይ ያተኮረ መሆኑን የጋዜጣው መሥራች ጋዜጠኛ ፍዮሪ ተወልደ ተናግራለች፡፡
ልጆችን ያማከለ ዓምድ፣ የሥራና የጨረታ ማስታወቂያን በማካተት፣ ሁሉንም መረጃዎችና ሳምንታዊ ዜናዎችንም በአንድ ላይ የያዘ መሆኑን ገልጻለች፡፡
የመጀመሪያ ዕትም መስከረም 6 ቀን 2013 ዓ.ም. በመንግሥት ተቋማትና በኢትዮጵያ ዓይነ ሥውራን ማኅበር አማካይነት ለአንባቢያን ተደራሽ መሆኑን መሥራቿ ተናግራለች፡፡
ጋዜጣውን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ዓይነ ሥውራን ማኅበር፣ በአራት ኪሎ ጋዜጣ በሚነበብበት ሥፍራና በመንግሥት ተቋማት ለማድረስ የተሞከረ መሆኑን፣ ሁለተኛው ዕትም መስከረም 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ለአንባቢያን በተለመደው መንገድ መሠራጨቱንም አክላለች፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ዓይነ ሥውራን ማኅበር 700 የሚደርሱ ዓይነ ሥውራን እንደሚገኙና ጋዜጣውን እነሱ ጋር ለማድረስ መቻሉን ጠቁማ፣ የመጀመርያውንና ሁለተኛው የ‹‹ፈትል›› የብሬል ጋዜጣ በነፃ መታደሉን፣ በተለያዩ ማኅበራት፣ የመንግሥት ተቋማትና ግለሰብ አማካይነት ለዓይነ ሥውራን እንደሚዳረስ ተናግራለች፡፡
‹‹ፈትል›› የብሬል ጋዜጣ በ30 ብር ለገበያ የቀረበ ቢሆንም፣ በቀጥታ ዓይነ ሥውራን እንዲገዙት ሳይሆን በተለያዩ የግልና የመንግሥት ማኅበራት አማካይነት በነፃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል፡፡
በአማርኛ ቋንቋ የተጀመረው የብሬል ጋዜጣ በቀጣይ በአገር ውስጥና በውጭ ቋንቋዎች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራም መሥራቿ ተናግራለች፡፡
ጋዜጣውን በማኅበራት አማካይነት በክልል ከተሞች ለሚገኙ ዓይነ ሥውራን ወገኖች ተደራሽ ለማድረግ የታሰበ በመሆኑ፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አማካይነት ተደራሽ ለማድረግም እየሠራች መሆኑንም አክላለች፡፡
ጋዜጠኛ ፍዮሪ እስካሁን በራሷ ወጪ ሁለት ጊዜ ለኅትመት ያበቃችው ‹‹ፈትል›› ጋዜጣ በነፃ ተደራሽ ያደረገች መሆኑን፣ የመንግሥት ተቋማትም የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስባለች፡፡