Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹የጉዳዮች መገናኘት ካልሆነ በስተቀር የታሰሩ ግለሰቦች ፖለቲከኞች ቢሆኑም በፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው አይደለም›› ጠቅላይ...

‹‹የጉዳዮች መገናኘት ካልሆነ በስተቀር የታሰሩ ግለሰቦች ፖለቲከኞች ቢሆኑም በፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው አይደለም›› ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ

ቀን:

ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር ውለውና ክስ ተመሥርቶባቸው የሚገኙ ግለሰቦች ፖለቲከኞች ቢሆኑም፣ የታሰሩት በፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው አለመሆኑን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታወቀ፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የውጭ ቋንቋዎችና ሚዲያ ኃላፊዋ ቢልለኔ ሥዩም ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደገለጹት፣ የጉዳዮች መገናኘት ካልሆነ በስተቀር፣ የታሰሩ ግለሰቦች ፖለቲከኞች ቢሆኑም ከፖለቲካ አመለካከትቸና እንቅስቃሴያቸው የታሰሩ እንዳልሆነ አብራርተዋል፡፡

ሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ልዩ ስሙ ገላን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በጥይት ተመትቶ የተገደለው ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት ተከትሎ፣ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል ከተከሰቱ አመፆችና ጥቃቶች ጋር ግንኙነት አላቸው በተባሉ 2,000 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መመሥረቱን፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ጌዲዮን (ዶ/ር) እና የውጭ ቋንቋዎችና የዲጂታል ሚዲያ ኃላፊዋ ቢልለኔ ሥዩም እንዳስታወቁት፣ ክስ የተመሠረተባቸው ግለሰቦች በነበረው አመፅና ጥቃት ውስጥ በተለያየ ደረጃ ተሳትፎ የነበራቸው ናቸው ብለዋል፡፡

የድምፃዊ ሃጫሉ ግድያ ተከትሎ ከ9,000 ሰዎች በላይ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ታስረው የነበረ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥም እንደ አቶ ልደቱ አያሌው፣ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ እስክንድር ነጋና አቶ በቀለ ገርባን የመሳሰሉ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች፣ እንዲሁም የሚዲያ ኃላፊዎች ይገኙበታል፡፡ ከእነዚህ ታሳሪዎች መካከል በተለያዩ ጊዜያት የተፈቱ ግለሰቦች እንደነበሩ ሲነገር ነበር፡፡

የድምፃዊውን ግድያ ተከትሎ በነበሩ አመፆችና ጥቃቶች በአንዳንድ አካባቢዎች አናሳ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ለይቶ የማጥቃት ድርጊት እንደነበር ያስታወቁት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ጌዲዮን (ዶ/ር)፣ በዚህም ሳቢያ 160 ሰዎች እንደ ሞቱ፣ 360 ሰዎች ጉዳት እንደ ደረሰባቸው፣ እንዲሁም ከ4.6 ቢሊዮን ብር በላይ የንብረት ውድመት እንደተከሰተ ገልጸዋል፡፡

ወንጀሎች የተፈጸሙበት መጠንና ግዝፈት በራሱ ለምርመራውና ለክስ ሒደቱ ትልቅ ፈተና እንደሆነ ያስረዱት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ፣ መንግሥት አጥፊዎችን ወደ ሕግ እያቀረበ ነው ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን የሰዎችን ሕይወት መቅጠፋቸው አሳዛኝ መሆኑንና መንግሥትም በዚህ ሐዘን እንደሚሰማው የተናገሩት ቢልለኔ፣ እንዲህ ያሉ የአመፅ ክስቶችን ግን መንግሥት የዜጎቹን ደኅንነት ለማስጠበቅ አቅም የለውም ለማለት አያስችልም ብለዋል፡፡ ይልቁንም ትኩረት ያላገኙና ያልተነገረላቸው በርካታ ተመሳሳይና የሽብር ጥቃቶችን መቀልበስ የተቻለ መሆኑ ከግምት ሊገባ ይገባል ሲሉ አክለዋል፡፡

በዚህ ላይ ያከሉት ጌዲዮን (ዶ/ር) እንዳሉት፣ መንግሥት ተመሳሳይም ሆነ ሌሎች ጥቃቶችን ከመቀልበስ ባለፈ፣ የተለያዩ አጥፊዎችን ወደ ሕግ እያቀረበ መሆኑ፣ ወደፊት ሊፈጠሩ የሚችሉ ተመሳሳይ ጥቃቶችም ሆኑ ሙከራዎችን ለማስቀረት ይረዳል ብለዋል፡፡

በተለይ አቶ ጃዋር መሐመድ በፍርድ ቤት መንግሥት እሳቸውንም ሆነ ሌሎች ፖለቲከኞችን ያሰረው ጥፋት ኖሮባቸው ሳይሆን፣ የፖለቲካ አመለካከታቸው የተለየ ስለሆነ መንግሥት የምርጫ ሜዳው ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ እንዳይኖር እያደረገ ነው ሲሉ ያቀረቡትን መከራከሪያ በተመለከተ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጌዲዮን (ዶ/ር)፣ ‹‹የጉዳዮችን መገናኘትና ምክንያትነት መረዳት መቻል ይኖርብናል፤›› በማለት፣ እነዚህ የታሰሩ ግለሰቦች ፖለቲከኞች ቢሆኑም፣ የታሰሩት ግን በፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው እንዳልሆነ መታወቅ ይኖርበታል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

2013 ዓ.ም. ከቀደመው ዓመት ይልቅ በሰላምና መረጋጋት ረገድ የተሻለ እንደነበረ ያስታወሱት ቢልለኔ፣ በመተከልና በሌሎች ሥፍራዎች በንፁኃን ዜጎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶችን መንግሥት ያወግዛል ብለው፣ በመንግሥትና በክልል መንግሥታት የፀጥታ መዋቅሮች ጠንካራ ትብብር በማድረግ ሰላምና ፀጥታን ለማስጠበቅ ቁርጠኝነት እንዳለ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...