Thursday, June 1, 2023

የጤና ሚኒስቴር የምርጫ ይደረግ ምክረ ሐሳብ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደ አዲስ ተቋቁሞና አዳዲስ የቦርድ አባላትና አዲስ የቦርድ ሊቀመንበር ከተሾሙለት በኋላ ተቋሙ በብቃት እንዲያከናውናቸው ይጠበቁበት የነበሩ ሁለት አገራዊ ሁነቶች ነበሩ፡፡ የመጀመርያው ቦርዱ እንደ አዲስ በተቋቋመ በወራት ውስጥ የቀረበለት የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ሲሆን፣ ይኼንን ሁነት በአግባቡ አስተናግዶ በምርጫ ቦርድ አስፈጻሚነት የተከናወነውን ሕዝበ ውሳኔ ተከትሎ አሥረኛው የፌዴሬሽኑ አባል የሆነ አዲስ ክልል ተፈጥሯል፡፡

ሁለተኛውና የቦርዱን አቅም የሚፈትኑና ገለልተኛነቱን እንዲያስመሰክር ይጠበቅበት የነበረው አገራዊ ሁነት ደግሞ አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ሲሆን፣ ይኼንንም ለማሳካት የሚያስችሉትን ዝግጅቶች ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ከእነዚህም ዝግጅቶች የምርጫ አዋጁ እንዲሻሻል ማድረግ፣ ለምርጫ የሚያግዙ የተለያዩ መመርያዎችንና ማስፈጸሚያ ማኑዋሎችን ማዘጋጀት፣ የምርጫ ክልሎችና ጣቢያዎችን መለየትና ካርታ ማዘጋጀትና ይፋ ማድረግ፣ የምርጫ ቁሳቁሶችንና የኅትመት ግዥዎችን መፈጸም፣ እንዲሁም የምርጫ ክንውኖች የጊዜ ሰሌዳ ማዘጋጀትን ያካትታሉ፡፡

በስተመጨረሻም ቦርዱ የምርጫውን የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ ምርጫው ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዲከናወን ቀን ቆርጦ እየተንቀሳቀሰ ባለበት ወቅት፣ በታኅሳስ ወር 2012 ዓ.ም. በቻይና ሁቤ ግዛት ውሃን ከተማ የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝና ቫይረሱ የሚያስከትለው በሽታ በኢትዮጵያም መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በመገኘቱ፣ ምርጫውን በታቀደው ጊዜ ለማድረግ እንደማይቻል ቦርዱ አስታውቋል፡፡ ቦርዱ ቫይረሱን ለመከላከል ሲባል በአገሪቱ የተጣሉት ክልከላዎች በርካታ ተግባራቶቹን እንዳያከናውን እንዳደረጉት በመግለጽም ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

ቦርዱ መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫም እንዳስታወቀው እስካሁን ያላከናወናቸውና በቫይረሱ ሳቢያ የታጎሉ ተግባራትን የዘረዘረ ሲሆን፣ የተቀሩትን ተግባራት ለማከናወን ያዳግተኛል ያለበት ምክንያትም ሲያስረዳ፣ ‹‹መንግሥት ወረርሽኙን ለመከላከል የሰዎች ግንኙነትን የመቀነስ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ በመወሰኑ የመንግሥት ሠራተኞች አብዛኛውን ሥራ ከቤት ሆነው እንዲሠሩ ተደርጓል፣ መንግሥት የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የተለያዩ ጥብቅ ዕርምጃዎችን እየወሰደ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም በክልል መንግሥት መስተዳድሮች ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ የውስጥና የአገር አቋራጭ የትራንስፖርት ገደቦች፣ የመሰብሰብ ገደቦችን የመሳሰሉ ጥብቅ ክልከላዎች ይፋ ሆነዋል፡፡ በመንግሥት ከተላለፉ የክልከላ ውሳኔዎች በተጨማሪ ለቦርዱ ድጋፍ የሚያደርጉ ዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች አብዛኞቹ ሠራተኞቻቸው ከቤት ሆነው እንዲሠሩ ሲደረጉ አንዳንዶቹ ደግሞ ጥቂቶቹን ብቻ በማስቀረት ሠራተኞቻቸው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አድርገዋል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ድምር ሁኔታዎች በሚያዝያ ሊጀመር በታቀደው የመራጮች ምዝገባና ተያያዥ የዝግጅት ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል፤›› ሲል አስፍሯል፡፡

በዚህ ሳቢያም ቦርዱ ያዘጋጀውን የጊዜ ሰሌዳ ሰርዞና ለምርጫው ይደረጉ የነበሩ ዝግጅቶች ለጊዜው እንዲቆሙ በማድረግ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የሥራ አስፈጻሚው አካላት የሥራ ዘመን ከማለቁ አንድ ወር አስቀድሞ መደረግ የነበረበት ምርጫ ባለመከናወኑ ምክንያት ለሚፈጠረው የሕግና የሥልጣን ክፍተት መፍትሔ እንዲሰጠው ሲል ፓርላማውን ጠይቋል፡፡

ምርጫ ቦርድ ይኼንን ውሳኔ ካሳለፈና ለፓርላማው ካሳወቀ በኋላ መንግሥት የተፈጠረውን የሕገ መንግሥትና የሥልጣን ቀውስ እንዴት መሻገር እንችላለን በማለት አራት አማራጮችን ቃኝቷል፡፡ እዚህም አማራጮች ፓርላማውን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 60 መሠረት መበተን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አራዝሞ ማወጅ፣ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻልና የሕገ መንግሥት ትርጉም ማሰጠት የሚሉ ሲሆን፣ መንግሥት የመጨረሻውን አማራጭ ተከትሏል፡፡

ፓርላማውም ይኼንን ውሳኔ ተከትሎ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥር ለሚገኘው የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ መሆኗንና ይኼ ዓይነቱ ክስተት ከምርጫ ጋር ሲገጥምና ምርጫ ማድረግ ካልተቻለ ምን ይደረግ የሚለውን፣ እንዲሁም ምርጫ ባለመደረጉ የሥልጣን ዘመናቸው የሚያበቃው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) እና የሥራ አስፈጻሚው አካል ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል የሚሉ ጥያቄዎች ታይተው የሕገ መንግሥት ትርጉም ይሰጥበት ብሏል፡፡

የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔም በአገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ 34 ባሙያዎችና ተቋማት አስተያየቶችን በጽሑፍ ተቀብሎ መዳሰሱን እንዲሁም ግንቦት 8፣ 10 እና 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄዳቸው ውይይቶች ከተለያዩ የሕገ መንግሥት ምሁራን፣ እንዲሁም ከጤናና ከምርጫ ተቋማት ተወካዮች ግብዓቶችን በመሰብሰብ፣ ‹‹አገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኙት የመንግሥት አካላት የሥልጣን ዘመን ላይ ሁኔታው ምን እንድምታ አለው?›› የሚለውን፣ ‹‹በምክር ቤቱ የቀረበው ሁለተኛው ጥያቄ የኮሮና ወረርሽኝ ለሕዝብ ጤና ሥጋት መሆን ካቆመበት ጊዜ ጀምሮ ምርጫው መከናወን ያለበት በስንት ጊዜ ውስጥ ነው›› ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ ይሆኑ ዘንድ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክረ ሐሳብ አቅርቧል፡፡

እነዚህ ጥያቄዎች በተለይም ሁለተኛው ጥያቄ እንደሚያሳየው ምርጫውን ለማከናወን ያለው ዕቅድ በአገሪቱ የተከሰተው ወረርሽኝ፣ የሕዝብ የጤና ሥጋት እንዳልሆነ ሲረጋገጥ እንደሚሆን ያሳያሉ፡፡

ጉባዔው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት እንደጠቀሰው፣ ‹‹የሥልጣን አካላቱ በሥራቸው ላይ የሚቀጥሉት የኮሮና ወረርሽኝ የሕዝብ የጤና ሥጋት አለመሆኑ በሚመለከታቸው የጤናና ሌሎች ውሳ ሰጪ አካላት ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ ከዘጠኝ እስከ 12 ባሉት ወራት ውስጥ ስድስተኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ተከናውነው እስኪተኩ አንደሆነ ጉባዔው የውሳኔ ሐሳብ ሰጥቷል፤›› ሲል አመላክቷል፡፡

በጉባዔው ምርጫው መቼ መካሄድ አለበት ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የጤና ሚኒስቴርንና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስተያየቶችን በማዳመጥ የወሰነ እንደሆነ በመተንተንም፣ የቫይረሱ ሥርጭት በኅብረተሰቡ ውስጥ እየጨመረ መምጣቱን፣ እንደ አገር የቫይረሱ ሥርጭት ሦስተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ፣ እንዲሁም እንደ አዲስ አበባ ባሉ አካባቢዎች የሥርጭቱ ደረጃ አራተኛ ላይ መድረሱ የበሽታውን ሥርጭት ከፍተኛነት እንደሆነ ያመላክታል ብሏል፡፡ ስለዚህም በስፋት እየተሠራጨ የሚገኘው ቫይረስ ሳለ ምርጫ ማድረግ የምርጫውን ሒደት ይጎዳል ሲል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

‹‹ከወረርሽኙ ባህርይና አገራችን ካላት ውስን ኢኮኖሚያዊ አቅም አንፃር ወረርሽኙ የሕዝብ ጤንነት አደጋ መሆኑ ሳያበቃ ወይም በቁጥጥር ሥር ሳይውል ነፃና ትክክለኛ ምርጫ ማድረግ አይቻልም፤›› ሲልም ጉባዔው ደምድሟል፡፡

ይሁንና ምርጫው ቫይረሱ እስከሚጠፋ ድረስ ሳይደረግ ይቆይ ማለት አግባብ አይደለም በማለት፣ ‹‹ምርጫ ሊከናወን የሚገባበት ጊዜ ወረርሽኙ የሕዝብ ጤና አደጋ መሆኑ ካበቃበት ጀምሮ በሚቆጠር የጊዜ ገደብ ውስጥ ሊሆን ይገባል፤›› ሲል አመላክቶ፣ ቫይረሱ የኅብረተሰብ ጤና ሥጋት አይደለም ለማለት ደግሞ ለቫይረሱ ክትባት ወይም መድኃኒት ሲገኝ ወይም ሌላ ፍቱን ሳይንሳዊ ግኝት ሲኖር እንደሆነ፣ የጤና ሚኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባስገነዘቡት መሠረት ይኼ ሲሆን ብቻ ምርጫ ማከናወን እንደሚቻል አስገንዝቧል፡፡ ስለዚህም በዚህ ላይ በመመሥረት የኮሮና ወረርሽኝ የሕዝብ ጤና ሥጋት መሆኑ ካበቃበት ጊዜ አንስቶ ከዘጠኝ እስከ 12 ወራት ጊዜ ውስጥ ምርጫው እንዲካሄድ ሲል ምክረ ሐሳብ አቅርቧል፡፡

እነዚህም ምክረ ሐሳቦች እንዳሉ በመውሰድ የምክር ቤቶችና የሥራ አስፈጻሚ አካላት የሥራ ዘመን እንዲራዘም፣ እንዲሁም ምርጫው ቫይረሱ የኅብረተሰብ የጤና ሥጋት አይደለም ተብሎ ሲገለጽ ምርጫው እንዲደረግ ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፅድቀዋል፡፡

ይሁንና መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ቫይረሱ በአገር ውስጥ መገኘቱ ከተረጋገጠበትና ከመጋቢት 7 ቀን 2012 ዓ.ም. የመጀመርያዎቹ የቫይረሱ መከላከያ ክልከላዎች ከተቀመጡ በኋላ፣ መጋቢት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማብቃቱን ተከትሎ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተለያዩ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊና የፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ጥንቃቄ በታከለበት ሁኔታ እንዲጀመሩ ከማሳሰቡ ጋር ተያይዞ፣ ምርጫን ለማካሄድ የሚያስችሉ ጥንቃቄዎች የታከሉባቸው የምርጫ ዝግጅቶች እንዲከናወኑም ምክረ ሐሳብ ለግሷል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ በመደበኛ እንቅስቃሴዎች ሳቢያ ሊኖር የሚችለውን ከፍተኛ ሥርጭት በከፊል ማስቀረት እንደቻለ የጠቆመው ለፓርላማ የቀረበው የጤና ሚኒስቴር ሪፖርት፣ ምርጫውን ለማካሄድ ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች ሊመቻቹ እንደሚኖርባቸውም አስገንዝቧል፡፡ እነዚህ ጤና ሚኒስቴር ሊሟሉ ይገባል በማለት ያነሳቸው፣ ‹‹ከዚህ በፊት ከነበረው የምርጫ ሒደ በተለ መንገድ ኮሮና ወረርሽኝን መከላከል ከግምት ውስጥ ያስገባ የምርጫ ሥነ ምግባር፣ ደንና ማስፈጸሚያ መመርያዎችን ማዘጋጀትና በተዘጋጁት ዝርዝሮች መሠረት በሁለም ደረጃ በበቂ ዝግጅቶች ወደ ትግበራ መግባት›› የሚለውና ‹‹በዚህ ሒደ ውስጥ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የወረርሽኝ ሥርጭት ከተከሰተ በተለ ሁኔታ መታየት ሊያስፈልገው እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀት ያስፈልጋል፤›› የሚሉ ናቸው፡፡

የጤና ሚኒስቴር መስከረም 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ለፓርላማው ያቀረበው ምክረ ሐሳብ በሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ሪፖርት ላይ እንደተጠቀሰው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የኅብረተሰብ ጤና ሥጋት እንዳልሆነ የሚያሳይ ትንታኔ ያላቀረበ ሲሆን፣ እንዲያውም የቫይረሱ ሥርጭት እየጨመረ መምጣቱንና በአዲስ አበባም ሆነ በክልል ከተሞች ያለው የሥርጭት መጠን በተደረገው ምርመራና ዳሰሳ ከፍተኛ እንደሆነ እንደሚያሳይ የሚያመላክት መሆኑ በርካቶችን ግር አሰኝቷል፡፡

በዓለም 29 ሚሊዮን ሰዎችን ያጠቃውና ከ900 ሺሕ በላይ ሰዎችን ለሞት የዳረገው ቫይረስ፣ በአፍሪካም በ57 አገሮች ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን በማጥቃት ከ32,000 በላይ ሰዎችን እንደገደለ ያመላከተው የጤና ሚኒስቴር ሪፖርት፣ በምሥራቅ አፍሪካ ከተጠቁ ከ150,000 በላይ ሰዎች ውስጥ በኢትዮጵያ እስከ ሰኞ መስከረም 6 ቀን 2013 ዓ.ም. በተደረገው ምርመራ መሠረት 66,224 ተጠቂዎችን በመያዝ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የቫይረሱ ተጠቂዎች ያሏት አገር እንደሆነች አመላክቷል፡፡

ከተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ክንውኖች ጋር አብሮ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫም በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት እንዲራዘም መደረጉን በመጠቆም፣ የተወሰዱት ዕርምጃዎች በሽታውን ለመከላከል መበጀታቸውን ያመላከተው የጤና ሚኒስቴር፣ ቫይረሱ በኢትዮጵያ በሚገኙ በሁሉም ዞኖችና ከ900 በላይ ወረዳዎች መከሰቱን በመግለጽ፣ በቫይረሱ ከተጠቁ ሰዎች መካከል 95 በመቶ የሚሆኑት የታወቀ የጉዞ ታሪክ በሌላቸው ላይ የተከሰተ እንደሆነ አመላክቷል፡፡

በኢትዮጵያ እስከ መስከረም 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በቫይረሱ ከተጠቁ 66,224 ሰዎች መካከል 57 በመቶ የሚሆኑት በአዲስ አበባ የሚገኙ እንደሆነ ያመላከተው ሪፖርቱ፣ ከአዲስ አበባ በመቀጠል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ክልሎች ኦሮሚያ፣ ትግራይና አማራ እንደሆኑ ጠቁሟል፡፡

በዚህ ሪፖርት ከፍተኛ የቫይረሱ ሥርጭት ካለባቸው የአገሪቱ ክልሎች አንዱ ትግራይ ሆኖ ሳለ የፌዴራል መንግሥትን ምርጫ የማራዘም ውሳኔ ባለመቀበል፣ ስድስተኛውም ክልላዊ ምርጫ ማድረጉ በራሱ በበርካቶች ዘንድ ጥያቄን አጭሯል፡፡ ስለዚህም በትግራይ መራጮች በጊዜ ወጥተውና አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረጉ ምርጫ እንዲደረግ ማስቻል ይቻል ነበር በማለትም፣ መንግሥት ምርጫውን ለማድረግ የሚቻልባቸውን አማራጮች ከመቃኘት ይልቅ የማይቻልባቸውን ምክንያቶች ማጉላት መርጧል ሲሉ ይተቻሉ፡፡

በተጨማሪም በኢትዮጵያ በቫይረሱ ከተጠቁ ሰዎች መካከል 86 በመቶ የሚሆኑት ከ15 እስከ 59 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው በጤና ሚኒስቴር ሪፖርት የተጠቀሰ ሲሆን፣ ይህም ንቁ ተሳትገፎ ሊያደርግ የሚችለውና አምራቹ የኅብረተሰብ ክፍል በከፍተኛ ደረጃ በቫይረሱ እየተጠቃ ሳለ ምርጫ እንዲደረግ መወሰኑ ግራ አጋቢ የሆነባቸው አልጠፉም፡፡

በኅብረተሰቡ ውስጥ ቫይረሱ ኖሮባቸው ሳይመረመሩ ቀርተው የተሻላቸውን ሰዎች በመለየት የቫይረሱን የሥርጭት መጠን ለመለካት የሚያገለግለው በደም ናሙና የሚከናወነው የምርመራ (አንቲቦዲ ቴስት) እንደተደረገ የጠቆመው የጤና ሚኒስቴር ሪፖርት፣ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት በአገር አቀፍ ደረጃ 4.5 በመቶ መሆኑን በመጠቆም በክልሎች ደግሞ ከአንዱ ሌላው ጋር እንደሚለያይ አመላክቷል፡፡ በዚህም መሠረት በአዲስ አበባ ያለው የሥርጭት መጠን 4.1 በመቶ ሲሆን፣ በጋምቤላ ክልል 9.3 በመቶ፣ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር 7.7 በመቶ፣ በጅግጅጋ 7.5 በመቶ፣ እንዲሁም በሐረሪ 5.5 በመቶ የሥርጭት መጠን እንዳለ ተጠቅሷል፡፡ በተጨማሪም የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ለፓርላማው ፓቀረቡት ሪፖርት ላይ በዳሰሳ ጥናት ከተካተቱ 14 ከተማዎች መረዳት የተቻለው በሽታው በማኅበረሰቡ ውስጥ መሠራጨቱን ነው ብለዋል፡፡

ነገር ግን የተሻለ ግንዛቤና ቫይረሱን ለመከላከል የተቀመጡ ክልከላዎች መተግበራው ጥብቅ ቁጥጥር በሚደረግበት አዲስ አበባ ካለው ሥርጭት በባሰ ሁኔታ በክልሎች መኖሩ በአዲስ አበባ ያለው ጥንቃቄና ቁጥጥር ወደ ሌሎች ሥፍራዎች ሲሄድ ልል እንደሆነ የሚያሳይ ነው በማለት የሚያስገነዝቡ ታዛቢዎች፣ በዚህ ሁኔታ ምርጫውን ማድረግ ምን ያህል ሊያሰፋው እንደሚችል ማሳያ ነውም ይላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ እንደ ቫይረሱ ተጠቂ የሚቆጠርባቸው የአገሪቱ ክፍሎች መኖራቸውንም ጭምር በመጥቀስ፣ የተባሉት የጥንቃቄ ዕርምጃዎችን እንዴት ማስፈጻምና ምርጫውን ማከናወን ይቻላል ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

ከዚህ በላይም በተለይ ቫይረሱን ለመከላከል በዋናነት የሚረዳው የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል መጠቀም ዓይነተኛ ሚና እንዳለው የጤና ሚኒስቴር ሪፖርት ያሳያል፡፡

ይኼንንም ለማሳየት የጤና ሚኒስቴር ሪፖርት፣ ‹‹ከሳይንሳዊ ትንበያዎች እንደምንረዳው በበሽታው የሚያዘውን የሰዎች ቁጥር፣ የሞት ቁጥርና ወረርሽኙ ከፍተኛው ቁጥር/ጣሪያ (Peak) የሚደርስበት ጊዜ በዋናነት የሚወሰነው በአካላዊ መራራቅ፣ በተለይ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል የሚተገበርበት ደረ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል አካላዊ ርቀት 25 በመቶና የአፍና አፍንጫ ሽፋን 50 በመቶ የኅብረተሰብ ክፍል ውስጥ መተግበር ከተቻለ፣ ምንም ዓይነት ዕርምጃ ባይወሰድ ሊደርስ ከሚችለው የበሽታ ሥርጭትና ሞት አንፃር በ92 በመቶ መቀነስ እንደሚቻል ያሳያል፡፡ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብልን ሁሉም እንዲጠቀም ማድረግ ከተቻለ ደግሞ ሥርጭቱ በከፍተኛ መጠን መቀነስና ወረርሽኙ ከፍተኛው ቁጥር/ጣሪያ (Peak) የሚደርስበት ጊዜ በማራቅ፣ የሞት መጠንን በእጅጉ ከመቀነሱም በላይ በጤናው ሥርዓት፣ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ዘርፍ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት መቀነስ ይቻላል፤›› ሲል ይተነትናል፡፡

ነገር ግን ከላይ የተጠቀሰው ዓይነት ማስክ ጠልነትና አላግባብ የሆነ ግንዛቤ ከግምት በማስገባት፣ ይኼ የተቀመጠውን ትንታኔ ግቡን እንዲመታ ማድረግ አዳጋች ያደርገዋል የሚሉም አሉ፡፡ የጤና ሚኒስቴርም ያስቀመጣቸውን ትንታኔዎች ቀጣይ ሊኖር የሚችለውን ክስተት ለመረዳት ጠቃሚ ቢሆኑም እርግጠኛ ባልሆኑ ታሳቢዎች ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ይኼም በሽታው አዲስ ስለሆነና በሥርጭቱና በተፅዕኖው ላይ ምሉዕ ዕውቀት ስለሌለ እንደሆነ አመላክቷል፡፡

ይኼ ደግሞ በእነዚህ እርግጠኛ ባልሆኑ ታሳቢዎች ላይ ተመርኩዘው የቀረቡ ምክረ ሐሳቦች በመሆናቸው ላይሳኩና እንዲያውም ወደ ባሰ ጥፋት ሊመሩ እንደሚችሉም፣ በጥንቃቄ የተጠቆሙ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህ ምርጫውን ለማድረግ የተላለፈው ውሳኔ የተባሉት ጥንቃቄዎች እየተደረጉም ቢተገበር ጉዳት ያለው ሊሆን እንደሚችል ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያ ከወረዳ እስከ ፌዴራል መንግሥት ተቋማት ድረስ ከወረርሽኙ መከላከል መረብ በመዘርጋት ከፍተኛ ሥራ ስትሠራ የቆየችና የምርመራ አቅሟም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ከቀን 19,000 ያክል ምርመራዎችን ማድረግ እስከመቻል የደረሰች ቢሆንም፣ አሁንም ቢሆን መንግሥት ቫይረሱን ለመከላከል ያግዘኛል ብሎ ካሰበው 360 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 128.6 ሚሊዮን ዶላር ጉድለት ያለበት መሆኑ አሁንም ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ላይ ራሱን የቻለ እንቅፋት ሊሆን ይችላል፡፡

ይኼ ሁሉ ሆኖ ሳለም፣ የጤና ሚኒስቴር ለፓርላማው ያቀረበው የኮሮና ቫይረስ ሁኔታ መግለጫ ሪፖርት ቫይረሱ በተተነበየው ደረጃ ሕመምና ሞት ባያስከትልም እንኳን አሁንም ቢሆን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ቀላል የማይባል መሆኑን የሚያትት ሲሆን፣ በጠቅላላው የጤና ሚኒስቴር ሪፖርት ቫይረሱ አሁንም የማኅበረሰብ ጤና ሥጋት እንደሆነ ያሳያል፡፡ ይኼንን በሚያጠናክር መልኩም በአገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ እንዲሁም ምርጫው ሲራዘም ከነበረበት ጊዜ አንፃር አሁን ያለው የቫይረሱ ሥርጭት እያደገ መምጣቱ ብሎም ሥርጭቱ እየጨመረ እንደሚሄድ መተንበዩ አሁንም ሆነ በቀጣይ ቫይረሱ የኅብረተሰብ ጤና እክል እንደሚሆን የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህም በሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ የቀረበውን ምክረ ሐሳብም ሆነ በፌዴሬሽን ምክር ቤትና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላለፉትን ውሳኔዎች ቅድመ ሁኔታ የሚያሟላ ትንታኔ እንዳልቀረበ በማሳሰብ የሚከራከሩ በርክተዋል፡፡

ሚኒስቴሩና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በነገሩት መሠረትም ወረርሽኙ በቁጥጥር ሥር ዋለ የሚባለው ክትባት ሲገኝ ወይንም መድኃኒት ሲገኝለት እንደሆነ የተመላከተ ቢሆንም፣ የጤና ሚኒስትሯ ሊያ (ዶ/ር) ለፓርላማው ባቀረቡት ሪፖርታቸው ላይ ክትባቱ ቢገኝም እንኳን በግዥም ሆነ በዕርዳታ ማግኘቱ አዳጋች ስለሚሆን ቫይረሱ የኅብረተሰብ ጤና ሥጋት ሆኖ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ሚኒስትሯ ባቀረቡት ሪፖርት እንደተጠቀሰው፣ ‹‹ክትባቱ ከተረጋገጠ በኋላ ተደራ ማድረግና በቂ ክትባት በግዥም ሆነ በዕርዳታ ማግኘት አሁን ካለ ዓለም አቀፍ እሽቅድምድም አንፃር ቀላል ጉዳይ አይሆንም፡፡ ስለሆነ ቢያንስ ለሚቀጥለት ጊዚያት በሽታው በአገራችን የኅብረተሰብ ጤና ሥጋት ሆኖ ይቀጥላል ተብሎ ይታመናል፤›› በማለት ደምድመዋል፡፡

አገራዊ ምርጫን በተመለከተ ሚኒስትሯ ባቀረቡት ምክረ ሐሳብ በኮቪድ ወቅት ምርጫ ያደረጉ አገሮች እንዳሉ ያስረዱ ሲሆን፣ የጠቀሷቸው እንደ ማሊ፣ ቤኒን፣ ቡሩንዲና ጊኒ ያሉ አገሮች ቫይረሱ ከመስፋፋቱ አስቀድመው ምርጫቸውን አድርገዋል ብለዋል፡፡

ይኼንን የተመለከቱ አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው ቀድሞውንም ተረብሾ ምርጫውን ከማራዘም ይልቅ፣ ኢትዮጵያም ቫይረሱ እንዳሁኑ ሳይንሰራፋ ምርጫ አድርጋ መገላገል ትችል ነበር ሲሉ ይተቻሉ፡፡ ይሁንና ይኼ ሐሳብ ምርጫው አስቀድሞ በታቀደለት መሠረት በነሐሴ ወር 2012 ዓ.ም. ተደርጎም ቢሆን፣ ወቅቱ ከፍተኛ ሥርጭት ሊኖርበት እንደሚችል ከግንዛቤ ያላስገባ ነው፡፡

ስለዚህም በርካቶች የጤና ሚኒስቴርን ምክረ ሐሳብ በመውሰድ ከሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ሪፖርት የተመላከተውን ሀቅና የጤና ሚኒስቴር በሪፖርቱ ካስቀመጣቸው ዝርዝሮች አንፃር ሲታይ ምክረ ሐሳቡና ማጠቃለያው ደካማ ነው ይላሉ፡፡

ያም ሆነ ይህ ፓርላማው የጤና ሚኒስቴርን ምክረ ሐሳብ ተቀብሎ በማፅደቅ፣ ምርጫው ከመስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ከዘጠኝ እስከ 12 ወራት እንዲደረግ ወስኗል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -