Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አዋቂና ታዋቂ!

ሰላም! ሰላም! ከአሮጌ ዓመት ወደ አዲስ ዓመት ስንሸጋገር፣ ከአሮጌ ወደ አዲስ የገንዘብ ኖት መሸጋገራችን ድንገቴነቱ ካስገረማቸው ሰዎች መካከል አንዱ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ነኝ ብላችሁ እንዳይገርማችሁ፡፡ ሚሊዮኖችንና ቢሊዮኖችን ተንተርሰው እንደተቀመጡት የዝርፊያ መሐንዲሶች ሆኜ ሳይሆን፣ የአዲስ ዓመት ‹‹ሰርፕራይዝ›› ሲሆንብኝ ግን የተደበላለቀ ስሜት እንደተሰማኝ መደበቅ አልችልም፡፡ ደላላ ገበያ የሚደራለት ገንዘብ አንቆ የተቀመጠ ሁሉ ሲንቀሳቀስ ስለሆነ እኔም ጆሮዬን ቀስሬ እየተጠባበቅኩ ነው፡፡ ልክ እንደ አዲሱ ዓመት ዋዜማ ርችት አንጣጣሁት አይደል? እናላችሁ ዕድሜ ለመንግሥታችን አዲሱ ዕርምጃ የእኛ ሰው በየፈርጁ የኢኮኖሚ ትንታኔውን ሲያሾረው አገሬ ተስፋ አላት አልኩ፡፡ ነገር ግን ውይይቱ መልካም ቢሆንም ብስሉና ጥሬው ተደባልቀው ተቸገርን፡፡ በደላላ ዕውቀቴ ተንታኞቻችንን ስገመግም ብዙ ይቀራቸዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ብዙዎችን የሚያስንቅ ምሁር ጎረቤቴ የአዛውንቱ የባሻዬ ልጅ አለና፡፡ ከሰፊው የዕውቀት ማዕዱ የሚያቃምሰኝ ከአጉል ተንታኞች አጉል ወሬ ይታደገኛልና፡፡ ለዚህም ነው በብር ኖቶች ለውጥ ላይ የምንሰማቸው አራምባና ቆቦዎች አይረቤ የሚሆኑብኝ፡፡ እንዲህ ማንገዋለል ብንለምድ የት በደረስን ያሰኛል!

አንዱ ነገረኛ የእኔ ቢጤ ደላላ ሲክለፈለፍ መጥቶ፣ ‹‹ሰምተህ ነበር ወይ?›› ሲለኝ፣ ‹‹ምኑን?›› አልኩት አመጣጡ አላምር ብሎኝ፡፡ የማነህ አራዳ በሚመስል አስተያየት በሰያፍ እያየኝ፣ ‹‹መንግሥት አዳዲስ የብር ኖቶችን ማተሙን ነው…›› እያለ በዚያ ገበቴ በመሰለ ፊቱ ሲያፈጥብኝ፣ ‹‹እኔ አገር ያወቀኝ ደላላ እንጂ የመንግሥት የኢኮኖሚ አማካሪ አለመሆኔን እያወቅክ እንዴት እንደ ሸፍጠኛ ቆጥረህ ትገላምጠኛለህ?›› ብዬ ቱግ ስልበት በመጣበት ፍጥነት ዞሮ ተጠምዞ እግሬ አውጭኝ አለ፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? ‹አዎን አውቅ ነበር› ብለው ምን ሊሆን ነበር? ነው ወይስ ከቢጤዎቹ የዘረፋ ብር ሲያሸሹ ከነበሩ ቅምጥሎች ተልኮብኝ ነው? እነ አጅሬዎቹ እኮ ቆየት ብሏል ከሰሙ ተብሎ የሚወራበት መንደር ቢሄድ እኮ ስንቱን ወሬ ይኮመኩም ነበር፡፡ አንዱ ነው አሉ ሲያንቀዠቅዠው፣ ‹‹የምን ሰርፕራይዝ ነው? እኔና ወዳጆቼ እኮ የብር ኖቶቹ በምን ያህል መጠንና የት እንደሚታተሙ ከወራት በፊት እናውቅ ነበር…›› እያለ ሲቀደድ አንዱ፣ ‹‹አንተንማ እናውቅሃለን፣ ከተማው ውስጥ ሲአይኤ እየተባልክ አይደለም እንዴ የምትጠራው?›› ቢለው ራሱን ኳራንታይን ከከተተ ቀናት ተቆጥረዋል አሉ፡፡ እስቲ ዝርዝሩን ለሚመለከተው አካል አስረዳ የሚል ጠያቂ ከተፍ ቢልበት እኮ ጉድ ሊፈላ ነው፡፡ አንዱ ደግሞ፣ ‹‹እኛማ ቀደም ሲል ብሩን በዶላር አጥበን ጨርሰናል…›› ብሎ ጉራውን ሲቸረችር፣ ‹‹በል እንግዲህ ማታ መምጣታችን ስለማይቀር ተዘጋጅ…›› የሚል ‹ፕራንክ›  መሰል የጽሑፍ መልዕክት በስልኩ ደርሶት እንቅልፍ ከዓይኑ ላይ ከጠፋ ሰነባበተ ተብሎም ተወርቷል፡፡ ምን የማይወራ አለ አትሉም ታዲያ!  

ይገርማችኋል አሁን ቃልን ከቃል ሳዋድድ አንዳንድ ዘመናትና አንዳንድ መታወቂያ ቃላቶቻቸው ይመጡብኛል። ብዙ አልጎትታችሁና ከየካቲት 1966 ዓ.ም. አብዮት ወዲህ የተጠቀሱትን ብቻ እንበልታቸው እስኪ። ታዲያ ሰውዬው በአንድ ወቅት ‹ልማታዊ ስብሰባ› እንደሚጠራው ‹አብዮታዊ ስብሰባ› ተጠርተው ይገኛሉ። ‘ሌኒን፣ ማርክስና ኤንግልስ’ ሲባል በስም እንጂ ሰዎቹን አያውቋቸውም። ኧረ እንኳን እሳቸው እሳት ለኳሾችስ የት አውቀዋቸው ስትሉ ሰማሁ? እናም ስብሰባው ሳይጀመር ጓዶች እየተሰባሰቡ ሳለ ይጠይቃሉ። ‹‹ሌኒን ማን ነው?›› እስኪያዩት እየተቁነጠነጡ። ‹‹ያው ሌኒን!›› በግድግዳው ስፋት ልክ የተዘረጋ አቡጀዲ ላይ ተንሰራፍቶ ተሥሎ ያሳዩዋቸዋል። ‹‹ይኼ ፈረንጁ?›› ሲሉ ‹‹አዎ!›› ብለው ያረጋግጡላቸዋል። ማርክስንና ኤንግልስን በተመሳሳይ ጉጉት ጠይቀው ነጎድጓድ ባዘለ አብዮታዊ ድምፅ ተጠቁመው ማንነታቸውን ሲያዩ ምን አሉ አሉ? ‹‹ታዲያ እነዚህ ፈረንጆች ናቸው አንድ ማገር ሳይመቱና መርቴሎ ሳያቀብሉ በገዛ ላባችን የሠራነውን ንብረት ያስወረሱብን?›› ካሉ በኋላ የሆኑትን ወይም የተባሉትን አላውቅም፡፡ የመደብ ጀርባቸውን ሳያስቡት ተናግረው አቆርቋዥ ወይም አድሃሪ ተብለው ድርብ መስመር ጽሑፍ ደረታቸው ላይ አንጠልጥለው ይረሸኑ ይኑሩ አልሰማሁም። ‹‹ከነገር ጅማሬ የነገር ፍፃሜ ይሻላል›› እያሉ አዛውንቱ ባሻዬ ዘወትር ከሰሎሞን ምሳሌ ሲዋሱ ምን ለማለት ፈልገው እንደሆነ የሚገባኝ አሁን አሁን ሆኗል። እኛ ደግሞ ጥሎብን ‘ትቅደም ትቅደም’ ብለን እየፎከርን ከኢትዮጵያ ፊት ፊት መሮጥ ስለምንወድ የጅማሬ እንጂ የፍፃሜ ታሪካችን የተመናመነ ነው። አሁንም ቢሆን ለታሪክ የሚበጅ ቅርስ ካልተውን መጪው ትውልድ ውዝግባችንን እያነሳ እየጣለ ያነክተናል!

ወዲህ ስንሻገር ደግሞ የምንጫወተው በ‘ካት ዎክ’ ስታይል ነው። አለበለዚያ የጨዋታውን ሕግ ባለማክበር የመግባቢያ ሰነዱን በመጣስ ተብሎ የሚመጣብን ሊመጣብን ይችላል። ‹‹መጣ ቀረ ደግሞ›› አለኝ አንድ ቀን ምሁሩ የባሻዬ ልጅ። ምን ሆኖ ይሆን ብዬ፣ ‹‹ምኑ?›› ስለው፣ ‹‹ዝናቡ! ምነው?›› ብሎ አፈጠጠብኝ። መቼም እናንተም እንደ እኔ አንገት ደፍቶ በቃላት መረብ አሸምቆ ከሚጥላችሁ የሚያፈጥባችሁ ሰው የናፈቃችሁበት ጊዜ ላይ ደርሳችኋል ብዬ እጠረጥራለሁ። አፍጣጭና ገላማጭ በበዛበት በዚህ ዘመን ምን የማናየው ጉድ አለ? ነገራችን ሁሉ በጽንፍ ተሞልቶ ‘ምግብማ ሞልቷል’ ጠዋት ተዘፍኖ ከሰዓት የዕርዳታ እህል መዘግየቱን በዜና እንሰማለን። በአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መግለጫ ለሰላም የዘመሩ አንደበቶች፣ በማግሥቱ ማዶ ለማዶ ሆነው ቀብር ላይ የማያስቆም ስድብ ሲቀባበሉ ፍፃሜ ዓለም ይመስላል። ‹‹የብር ኖቶች መቀየር ሃምሳ ጥቅሞችና ሁለት ጉዳቶች›› በሚል ርዕስ ጥፍጥ ያለ ትንታኔ ስንጠብቅ፣ ‹‹የትዳር ሦስት ጥቅሞችና ሰላሳ ጉዳቶች›› የሚል የዩትዩብ ትንተና ጆሮአችሁ ላይ ሲለቀቅባችሁ መጀመርያውና መጨረሻው ይምታታብናል፡፡ ይህንን ጉድ የምነግረው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ሃያ ሰባት በመቶ የምንሆነው ወፈፍ ያደርገናል የሚል ጥናት ከሰማሁ ወዲህ ምንም አይገርመኝም…›› ሲለኝ እረጋጋለሁ፡፡ የሆነው ሆነና ሃያ ሰባት በመቶ ለምንሆነው የአዕምሮ ሕክምና አያስፈልገንም? እስኪ እንወያይበት!

ጨዋታን ጨዋታ ያስታውሰዋል። ‹‹ወገንና አገር ብቻ በአፍ እየታወሱ በተግባር በዜሮ የሚባዙበት ቀን ብሶ መጣብን እንጂ?›› ሲሉኝ ነበር ባሻዬ። ብዙ ሰዎች ደላላ በመሆኔ ይገርማችኋል ‘የአመለካከት ችግር’ ያለብኝ እየመሰላቸው እንደማያዳምጡኝ ብዙ ጊዜ ያጫወትኳችሁ ነው። ባሻዬ ግን ያዳምጡኝና የሚደመጥ ጣል ያደርጋሉ። ባሻዬን እንዲህ ስላቸው፣ ‹‹ወይ አንተ የደላህ ነህ። ያ የማንትሴ ልጅ ባለፈው ለአንድ ጉዳይ ላናግረው ሰዓት የሚጠግንባት ሱቁ ሄጄ ያደረገኝን አልገርኩህም እንዴ?›› ብለው ሳቁ። ነግረውኛልና አጀብኳቸው። ባሻዬ በአፄው ዘመን ያሠሯት ሰዓት ወደ ኋላ እየቆጠረች አስቸገረቻቸው። ይሞሏታል ትጎተታለች። ቢጨንቃቸው ወደ ሰዓት ሠሪ ቤት ሄዱ። ሰዓት አዳሹ ጉንጩ አብጧል ነበር ያሉኝ። ‹‹ሰው አላምጦ የሚውጠው እህል አጥቶ ነው ቀንና ሌሊቱን ቅጠል በጉንጩ ሲያንገዋልል የሚውለው?›› ብለው አስፈግገውኛል፡፡ ‹‹ይህች ሰዓት እየዘገየች አስቸገረች…›› አሉት። ለራሱ መርቅኖ አይናገር አይጋገር ቀና ብሎ እያያቸው፣ ‹‹እሺ ሰላም ነው?›› ይላቸዋል። ‹‹እየሰማኸኝ ነው? ሰዓቴ ትሠራለች ግን ትዘገያለች፤›› ይሉታል ደግመው። ቀና ብሎ ዓይቷቸው፣ ‹‹እሺ ባሻዬ ሰላም ዋሉ?›› ይላል። ወዲያው ገባቸው። ጊዜ ራሱ ማርሽ ቀይሮ ዙሩን ስላፈጠነው እንጂ፣ ሰዓታቸው ጤነኛ እንደሆነች ገባቸው። የእጅ ሰዓታቸውን ዙር ከዘመኑ ሰው የጊዜ አቆጣጠር ጋር እኩል ቢያደርጉት ከትርፉ ኪሳራው እንደሚያመዝን አሥልተው እያዘገሙ ተረጋግተው ቤታቸው ገቡ። ሰዓት ሲያዩ አሥር ደቂቃ አልቆጠረም። ቀኑ ግን ጨልሞ ነበር። በእኩል ፍጥነት ሳንጓዝ ታዲያ እንዴት እንደማመጣለን? ለአንዱ ቢጨልም ለአንዱ ቢነጋስ ምን ይገርማል? ጉድ እኮ ነው!      

በሉ እስኪ እንሰነባበት። የዓመቱ የመጀመርያ ስንብት መሆኑ ነው። ለዚህ ነው የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ዘመንን ብዙ አትደገፈው…›› ሲለኝ የነበረው። የእሱ ነገር እኮ ቢወራ አያልቅም። እዚህም እዚያም ተፍ ተፍ ብዬ ከተቀባበልኩት የቤት ወጪ እንዲሆናት ለማንጠግቦሽ ልሰጥ ስጓዝ አገኘሁት። ‹‹በል ና ደረስ ብለን እንመለስና እንቀዳለን፤›› ብዬው ቤት ስንደርስ ማንጠግቦሽ ቅቤ ታነጥር ነበር። ‹‹ባለሙያ እኮ ነች ውዷ ባለቤቴ፤›› ስለው ገና ከሩቅ፣ ‹‹ልብ አድርግ እንደ ማንጠግቦሽ ከቅመማ ቅመም ጋር ጊዜ ማጥፋት የመብት ረገጣ ነው ብለው የሚያስቡ አሉና ላገኘኸው ሁሉ ይህን አትበል፤›› አይለኝ መሰላችሁ? ቱግ አልኩ። እንዲያብራራልኝ፣ ‹‹ምን ለማለት ፈልገህ ነው?›› ብዬ ሳፈጥበት፣ ‹‹በባልትና ሙያ የሚኮሩ የነበሩት እናቶቻችን ነበሩ፡፡ አባቶቻችን ደግሞ በሚስቶቻቸው ሙያ ባለቤትነት ከመጠን በላይ ስለሚኩራሩ እኛም ከእነሱ ነው የወረስነው፡፡ በዚህ ዘመን የባለቤትህን ባለሙያነት እያጋነንክ ስታወራ ማጀት ውስጥ በጭቆና የምታኖራት ይመስል ይነሱብሃል…›› ሲለኝ አሁንም ንዴት ውስጥ ሆኜ፣ ‹‹እኮ እነ ማን?›› የሚል መብረቃዊ ጥያቄ ማቅረብ፡፡ አጅሬው ምኑ ሞኝ፣ ‹‹አክቲቪስቶቹ!›› ብሎኝ ፍርጥም አለ፡፡ ምን ያድርግ ታዲያ!

ጎበዝ እንዴት ነው ነገሩ? አክቲቪስት የሚባሉት ሰው ማጀት ድረስ ዘው ብለው ከገቡማ አለቀልን፡፡ ተፋቅረን፣ ተከባብረንና ተሳስበን የምንኖረውን የአንድ እናት አገር ልጆች በጉድባውና በሸንተረሩ እየለያዩ የሚያባሉን አንሶ፣ አራት በአራት የሆነችው ግድግዳችን ውስጥ ከገቡማ ምኑን ቤተሰብ ኖረን? ከቤተሰብ ተነስተን መሰለኝ አገር የምንደርሰው፡፡ ይህንን እያብላላሁ ጉዳዬን ጨርሼ ከቤት ብቅ ስል ቆሞ ይጠብቀኛል፡፡ ‹‹አየህ አንበርብር ለኮሮና ብቻ ሳይሆን አፋችንን በማስክ ውስጥ ጭምር ከአጉል ወሬ ልንገራ ይገባል…›› እያለኝ ብርቱ ቁም ነገሮችን ሲያስጨብጠኝ፣ እኔ ደግሞ በሐሳብ ርቄ ነጉጃለሁ፡፡ እውነቱን እኮ ነው፡፡ የማናውቀውን መጠየቅ፣ የምናውቀውን ደግሞ ደርዝ አስይዘን ማስረዳት ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡ አጉል መዘባረቅ ለአገር አይጠቅምም፡፡ ጥራዝ ነጠቅነት ያሳፍራል እንጂ አያስከብርም፡፡ ሰውየው ነው አሉ ያወቁ የተራቀቁ መሀል ተቀምጦ በአገር ጉዳይ ላይ ወሬው ደርቷል፡፡ አዋቂዎቹ አንዱን አንስተው ሌላውን ሲጥሉ ሰዓታት ነጎዱ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ሰውየው ማዳመጥ እንጂ ምንም አስተያየት አልሰጠም፡፡ በስተመጨረሻ አካባቢ አንዱ አዋቂ፣ ‹‹እኛ ይህንን ሁሉ ሰዓት ስናወራ ምነው ሐሳብ አላዋጣ አልክ?›› ብሎ ትሁት ጥያቄ ያቀርብለታል፡፡ ድንገተኛ ጥያቄ የቀረበለት ሰውዬም፣ ‹‹ባነሳችሁት ጉዳይ ላይ የእኔ ሐሳብ የእናንተን ስለማይወዳደር የምጠቀመው ባዳምጥ ነው…›› ብሎ መለሰ አሉ፡፡ እንግዲህ ይታያችሁ፡፡ አዋቂዎች መሀል ሆኖ ዕውቀት መቅሰም የፈለገው ሰው ማዳመጥን መረጠ፡፡ ራሱን ለነገ አዋቂነት እያጨ ነው ማለት ነው፡፡ ‹‹የአዋቂነት ምንጩ ራስን ለዕውቀት ማዕድ ዝግጁ ማድረግ ነው፡፡ የታዋቂነት ምንጩ ግን በጥራዝ ነጠቅነት እንደፈለጉ መጋለብ ነው፡፡ አዋቂን ከታዋቂ መለየት እያቃተ ያለው በዚህ ምክንያት ነው…›› የሚለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ እውነቱን ነው እኮ፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት