በናርዶስ ፈቃዱ
የመጀመርያው ዘመናዊ ትምህርት ቤት በኢትዮጵያ የተከፈተው በታኅሣሥ መባቻ 1837 ዓ.ም. በዓዲግራት ከተማ ዳርቻ ጎልዓ መሆኑን ታሪክ ያወሳል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማም በ1900 ዓ.ም. በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን በስማቸው የሚጠራ ትምህርት ቤት መቋቋሙም እንዲሁ፡፡
የዘመናዊ ትምህርት በኢትዮጵያ ከተጀመረ 176 ዓመታትን ቢያስቆጥርም ከተቀረው ዓለም ጋር የሚያወዳድር የትምህርት አሰጣጥ ወይም የዘመናዊ ትምህርት አለ ወይ የሚለው ግን እንደ ጥያቄ የሚቀርብ ነው፡፡
በአሁን ወቅት በኢትዮጵያ ከ40,000 ትምህርት ቤቶች በላይ እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከከተማውም ከገጠሩም የተውጣጡት እነዚህ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎቻቸው፣ የትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው መመርያ መሠረት ትምህርትን ተደራሽ ያደርጋሉ፡፡
ይህ ማለት ግን የትምህርት ጥራቱ አንድ ዓይነት ነው ማለት አይደለም፡፡ ከተማ ውስጥ ያለውን የትምህርት አሰጣጥ ገጠር ካለው ጋር ማወዳደር ትንሽ ሊከብድ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ከትምህርት መስጫ ቁስ አለመሟላት ጀምሮ የተለያዩ ተግዳሮቶች ገጠር ላይ ያሉ ትምህርት ቤቶች ስለሚገጥሟቸው ነው፡፡
የትምህርት ዘርፍን የማዘመንና በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ በመንግሥት ብቻ የሚሠራ ባለመሆኑም ቁጥራቸው በርከት ያሉ የግል ተቋማት ወደ ዘርፉ ተቀላቅለዋል፡፡
እነዚህ ተቋማት ከመንግሥት የሚመጣውን መመርያ በመቀበል በቴክኖሎጂ ለማዘመን ቢጥሩም በዓለም አቀፍ ደረጃ የትምህርት አሰጣጥ ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ከግልና ከመንግሥት ተቋማት በተጨማሪ ዘርፉን የተሻለ ለማድረግና በቴክኖሎጂ አበልፅጎ ተማሪዎችን ለማወዳደር መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሚና ትንሽ የሚባል አይደለም፡፡
ከነዚህ ተቋማት መካከል የካማራ ኤድዩኬሽን ኢትዮጵያ የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ዓለም አቀፍ ድርጅት በዋነኝነት ይጠቀሳል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2005 ጀምሮ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ይኸው ተቋም መሠረቱን በአየር ላንድ ያደረገ ነው፡፡
ቴክኖሎጂን በመጠቀም ትምህርትን ተደራሽ ማድረግን ዋና ዓላማው አድርጎ የተነሳው ይህ ተቋም የዲጂታል መማር ማስተማር ሒደትን በተለይ አፍሪካ ውሰጥ ባሉ አገሮች ላይ ለማስፋፋት እየሠራ ይገኛል፡፡
አጋርነቱን ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በማድረግ የሚሠራው ካማራ፣ ዓላማውን መሠረት በማድረግ በኢትዮጵያ ሦስት አገልግሎቶችን ያቀርባል፡፡ የመጀመርያው የዴስክቶፕ ኮምፒዩተሮችን ለትምህርት ቤቶች በማቅረብ የኢ-ለርኒንግ ሴንተር መስጠት ነው፡፡ ይኼም ማለት ሙሉ ለሙሉ የተሟላ ከ20 እስከ 25 ኮምፒዩተሮችን የያዘ አንድ ክፍል ማቅረብ ነው፡፡
ሁለተኛው የእነዚህን ኮምፒዩተሮች ይዘት ማሟላት ነው፡፡ ይኼም ማለት መጻሕፍትን፣ የትምህርት ቪዲዮችን፣ ትምህርታዊ ጌሞችን ኮምፒዩተሮቹ ላይ መጫንን ያካትታል፡፡ ይህ ድርጅት የኢንተርኔት አገልግሎትን በሁሉም ቦታ አለመሟላት ከግምት በመክተትም እነዚህን አገልግሎቶች ያለ ኢንተርኔት መጠቀም የሚቻልበትን ሁኔታም አመቻችቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዊኪፒዲያን በዚሁ መልኩ ያለ ኢንተርኔት ማግኘት የሚችሉበትን ሥርዓትም ዘርግቷል፡፡
ሦስተኛውና የመጨረሻው ለመምህራንና ለርዕሰ መምህራን ሥልጠና መስጠት ነው፡፡ ‹‹እንደ ካማራ የእኛ ፍልስፍና ቴክኖሎጂን ከነ ይዘቱ ለአስተማሪው መሣሪያ እንዲሆነው ማቅረብና የሚያስተምርበትን መንገድ አሻሽሎ ለተማሪዎቹ የተሻለ የመማር ማስተማር ሒደት እንዲፈጠር ማድረግ ነው፤›› የሚሉት አቶ ቢኒያም ያየህራድ የካማራ ኢዱዩኬሽን ኢትዮጵያ ካውንትሪ ዳይሬክተር ናቸው፡፡
ካማራ በኢትዮጵያ ይኼን አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ዘጠኝ ዓመታትን እንዳስቆጠረ የሚገልጹት አቶ ቢኒያም፣ እስካሁን በመላው ኢትዮጵያ ከ50,000 በላይ ኮምፒዩተሮችን በመስጠት ከ2000 በላይ ትምህርት ቤቶችንና ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ተደራሽ አድርጓል፡፡
ዓላማችን የዲጂታል ዓለምን ከቴክኖሎጂ ጋር በተገናኘ መልኩ ትምህርትን ማሻሻል ስለሆነ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን የምንሠራቸው ፕሮጀክቶች አሉ ይላሉ ዳይሬክተሩ፡፡
ከፕሮጀክቶቹ መካከልም የአፍሪካ የኮድ ሳምንት ወይም (Arica Code Week) በመባል የተሰየመው ፕሮጀክት ይጠቀሳል፡፡ ይህ ፕሮጀክት በአፍሪካ ውስጥ ባሉ 54 አገሮች የሚከናወን ፕሮጀክት ነው፡፡
ኤስኤፒ የተባለው የሶፍት ዌር ድርጅት የሚመራው ይኼ ድርጅት በብዙ አገሮች ያለ ሲሆን፣ የካማራ ኤድዩኬሽንም ከአጋሮቹ አንዱ በመሆን እየሠራ ይገኛል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ2015 ጀምሮ የሚከናወነው ይህ ፕሮጀክት በዓመት አንዴ የሚዘጋጅ ሲሆን ስክራች በተባለ በተመረጠ ሶፍትዌር ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ ይኼም ለልጆች ኮዲንግን ማሳወቅ ዓላማው አድርጓል፡፡
ከዚህ ፕሮጀክት ጥሩ ምላሽ እያገኙ እንደሆነ የገለጹት አቶ ቢኒያም፣ ዓምና ብቻ በአፍሪካ ውስጥ ወደ 3.8 ሚሊዮን ልጆች ስክራችንና ኮዲንግን መጠቀም ችለዋል፡፡ በኢትዮጵያም ባለፈው ዓመት ከ70,000 በላይ ልጆችን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ዓመት ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ተማሪዎችን ማግኘት አልተቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት ሥልጠናውን መስጠት ባለመቻሉ ከዚህ በፊት የተሰጧቸውን ሥልጠናዎች በመመርኮዝ ለዘንድሮ በየቤታቸው ሆነው መሥራት የሚችሉትን የውድድር ፕሮግራም ተዘጋጅቷል፡፡
ልጆች የኮዲንግ ችሎታቸውንና የፈጠራ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ያስችላል ተብሎ የታመነበት ይኼ ውድድር፣ ከስምንት እስከ 16 ዓመት ያሉ ልጆች ስክራችን በመጠቀም በእነሱ ዕይታ ወደፊት ትምህርትን እንዴት ማሻሻል ይቻላል በሚለው ዋና ሐሳብ ዙሪያ በጌም መልክ የሁለት ደቂቃ ቪዲዮ ሠርተው ማቅረብ የሚችሉበት ነው፡፡
ፕሮጀክቱንም በግል ወይም በቡድን መሥራት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡ የውድድሩ መለኪያ 50 በመቶውን የሚይዘው ጌሙ እንዴት ይሠራል? ልዩ ሐሳብ አምጥተዋል ወይ፣ ለመረዳትስ ቀላል ነው ወይ የሚለውን ይይዛል፡፡
ጌሙ ከተሰጠው መሪ ሐሳብ ጋርስ ይገናኛል ወይ የሚለው 25 በመቶ ሲይዝ፣ ቀሪው 25 በመቶው ደግሞ መልዕክትን አስተላልፏል ወይ? ጌሙን ማስረዳት ችለዋል ወይ? ከዕይታ አንፃርስ ምን ያህል ግልጽ ነው የሚለውን የሚያካት እንደሆነ አቶ ቢኒያም ገልጸዋል፡፡
እስከ መስከረም 15 ድረስ በካማራ የፌስቡክና የኢንስታግራም ገጾች ላይ በተቀመጠው መረጃ መሠረት የሠሩትን ሥራ ማስረከብ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
በዚህም መሠረት በተቀመጠው መለኪያ ተመዝነው ከአንድ እስከ ሦስት ለሚወጡ ተወዳዳሪዎች እንደነሱ ጥሩ ነጥብ አምጥተው ላለፉ ከመላው አፍሪካ አገሮች ከተውጣጡ አሸናፊዎች ጋር ለውድድር እንደሚቀመጡ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያን ስም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስጠራት ዋና ግባቸው እንደሆነ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ኮዲንግ ማስተማር አንድ ዕርምጃ ወደፊት መራመድ ስለሆነ ትምህርት ቤቶች ወደኛ ቀርበው ያናግሩን፣ አብረን መሥራት እንችላለን፤›› በማለት ጥሪ አቅርበዋል፡፡