ከባድ ተሽከርካሪዎችን በተከለከለ ሰዓት ወደ አዲስ አበባ ከተማ ማስገባት እና ማንቀሳቀስ ከብር 500 እስከ 6 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ የከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ከባድ ተሽከርከሪዎችን ከቀኑ 10፡00 እስከ 2፡00 ሰዓት ወደ ከተማዋ ማስገባትና ማንቀሳቀስ እንደማይቻል ገለጿል።
ይህንን በሚተላለፉ አሽከርካሪዎች ላይ ከብር 5 መቶ እስከ 6 ሺህ እንደሚቀጡ የትራንስፖርት ቢሮው አስታውቋል
ቢሮው በሥራ መውጫ ሰዓታት ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅና አደጋ ለመቀነስ የከባድ ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ መወሰን የሚያስችል መመሪያ ተግባራዊ ማድረጉን አመልክቷል።
በዚሁም መሰረት የመጫን አቅማቸው ከ2.5 ቶንና ከዚያ በላይ የሆኑ ተሽከርካሪዎች እንደጥፋቱ ክብደትና ድግግሞሽ ከብር 5 መቶ እስከ 6 ሺህ እንዲሁም በተደራቢነት ከ1 እስከ 3 ወር የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ እንደሚያግድ መመሪያው ያትታል።
የመንቀሳቀሻ ፈቃድ ሳያወጡ በተከለከለው ሰዓት ወደከተማዋ ማስገባትና በከተማዋ ውስጥ ማንቀሳቀስ እንዲሁም በዋና መንገድ ላይ ጭነት መጫንና ማውረድ ተግባር የፈፀመ ለመጀመሪያ ጊዜ ብር 1 ሺህ፣ ለሁለተኛ ጊዜ ደግሞ ብር 2 ሺህ እንዲሁም ከሁለት ጊዜ በላይ ድርጊቱን ከፈፀመ ብር 3 ሺህ ተቀጥቶ የአሽከርካሪው መንጃ ፈቃድ ለአንድ ወር እንደሚታገድ ይገልጻል፡፡
በሌላ በኩል ጊዜ ያለፈበት የመንቀሳቀሻ ፈቃድ ይዞ ወደከተማዋ ማስገባት ወይም በከተማዋ ውስጥ ማንቀሳቀስ ለመጀመሪያ ጊዜ ብር 5 መቶ እና ለሁለተኛ ጊዜ ደግሞ ብር 1 ሺህ፤ ድርጊቱ ለሶስተኛ ጊዜ ከተፈፀመ ብር 4 ሺህ ተቀጥቶ የአሽከርካሪው መንጃ ፈቃድ ለ2 ወር ይታገዳል ይላል፡፡
በተጨማሪም የተሰረዘ ወይም የተደለዘ ወይም አስመስሎ የተሰራ የመንቀሳቀሻ ፈቃድ ይዞ መገኘትና መጠቀም እንዲሁም የመንቀሳቀሻ ፈቃዱን ለሌላ አካል አሳልፎ መስጠት ብር 6 ሺህ እንደሚያስቀጣ ያስረዳል፡፡
በመሆኑም የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች የተከለከለውን ሰዓት ታሳቢ በማድረግ የትራፊክ መጨናነቅንና አደጋን ለመቀነስ ትብብር እንድታደርጉ ቢሮው የላከው መግለጫ አሳስቧል።