Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአፍሪካ ኩባንያዎች የዓለም ንግድ ድርጅትን ኢፍትሐዊ ሲሉ ወቀሱ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ቅድመ ሁኔታዎችን ለማሟላት ዓመታት የወሰዱባት ኢትዮጵያ ለአባልነት እየተጣደፈች ነው

ከሰሞኑ 200 የአፍሪካ ኩባንያዎችን የሚመሩ ሥራ አስፈጻሚዎች ተሳትፈውበታል በተባለ የዳሰሳ ጥናት፣ አብዛኞቹ ኃላፊዎች የዓለም ንግድ ድርጅት አፍሪካን ኢፍትሐዊ በሆኑ ሕጎችና ቅድመ ሁኔታዎች አግልሎ ቆይቷል በማለት መውቀሳቸው ተገለጸ፡፡  

ከሰሞኑ የፓን አፍሪካ የግሉ ዘርፍ የንግድና የኢንቨስትመንት ኮሚቴ የተሰኘው ተቋም በቪዲዮ ኮንፈረንስ ባካሄደው ስብሰባ፣ ስለዚሁ የዓለም ንግድ ድርጅት ጉዳይ ተነጋግሯል፡፡ ይኸው ተቋም ባስጠናው ጥናት፣ አሥር ዋና ዋና የንግድና የኢንቨስትመንት ዘርፎችን የሚወክሉ ከ25 አገሮች የተውጣጡ 200 የኩባንያ ሥራ አስፈጻሚዎች የተካተቱበት ቃለ መጠይቅ ተደርጓል፡፡

ከ65 በመቶ በላይ የኩባንያ ኃላፊዎች እንደሚያምኑት፣ በዓለም ንግድ ድርጅት የሚመራው የዓለም ንግድ ሥርዓት ለአፍሪካ ፍትሐዊ አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም 37 በመቶዎቹ እንደገለጹት፣ የዓለም ንግድ ድርጅት ዓላማውን ለማስፈጸም የተሳነውና ውጤታማነት የጎደለው ተቋም ነው፡፡ የዓለም ንግድ ድርጅት ለአፍሪካ ሸቀጦች የማይመቹ የንግድና የኢንቨስትመንት ሕግጋትን የሚተገብር፣ በርካታ አገሮች ከውድድር ውጭ እንዲሆኑ የሚያስገድዱ አሠራሮችን በመከተል አፍሪካ ከዓለም ንግድ ሥርዓት ተጠቃሚነቷ ዳር ያወጣ ተቋም እንደሆነ በመኮነን፣ ለውጥ እንዲደረግበት መጠየቃቸውን ጥናቱን ያስጠናው ተቋም ያትታል፡፡

ምንም እንኳ የዓለምን የንግድ ሥርዓት በመምራት ረገድ የዓለም ንግድ ድርጅት እንዲጫወት የተሰጠው ሚና ሰፊ ቢሆንም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይህንን ኃላፊነቱን መወጣት እንዳልቻለ፣ የአፍሪካ ደካማ አገሮች ካደጉት አገሮች እኩል በፍትሐዊነት ምርቶቻቸውንና ሸቀጦቻቸውን መገበያየት የሚችሉበትን መድረክ መፍጠር ያልቻለ፣ ይልቁንም አፍሪካን እንደ ጥሬ ዕቃ ምንጭነት እንጂ በአፍሪካ ለሚመረቱ ያለቀላቸው ምርቶች በዓለም ገበያ ቦታ እንዲያገኙ የሚያስችል የእኩል መወዳደሪያ ሥርዓት መፍጠር ያልቻለና መፍትሔ አልባ ተቋም ሆኖ እንዳገኙት የድርጅት መሪዎቹ ገልጸዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ሐሳቦች ጎልተው መውጣት የጀመሩት የዓለም ንግድ ድርጅትን በዋና ዳይሬክተርነት ለመምራት ከሚፎካከሩ ስምንት ዕጩዎች መካከል ሦስቱ ከአፍሪካ በሆኑበት ወቅት መሆኑ፣ ተቋሙ ለአፍሪካ ቦታ እንዲሰጥ የሚያስገድድ ጊዜ ላይ እንደሚገኝ የሚጠቁሙ አሉ፡፡ ተቋሙን ለመምራት ፉክክር ላይ ከሚገኙት መካከል የቀድሞዋ የናይጄሪያ የገንዘብ ሚኒስትር ንጎዚ ኦኮንጆ አይዌላ (ዶ/ር)፣ የቀድሞዋ የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር አሚና ሞሐመድ፣ እንዲሁም ግብፃዊው የሕግ አዋቂና የዓለም ንግድ ድርጅት ባልደረባ አብደልሐሚድ ማሞድሐም ትልቅ ትኩረት የተሰጣቸው ተወዳዳሪዎች ናቸው፡፡

አምባሳደር አሚና ሞሐመድ የዓለም ንግድ ድርጅት ጠቅላይ ምክር ቤትን በሰብሳቢነት መምራታቸው ብቻም ሳይሆን፣ አፍሪካ እንደ አኅጉር ካላት የውክልና መጠን ጭምር ተቋሙን የመምራት ሚና እንደሚገባት የሚሞግቱ ድምፆች ተበራክተዋል፡፡ የቀድሞውን ጠቅላላ የንግድና ታሪፍ ስምምነት (GATT) የተባለውን ተቋም በመተካት እ.ኤ.አ. ከ1995 ጀምሮ በመንቀሳቀስ ላይ በሚገኘው የዓለም ንግድ ድርጅት ውስጥ አፍሪካ የ27 በመቶ ውክልና አላት፡፡ ለታዳጊ አገሮች በተሰጠው ኮታም የአፍሪካ ድርሻ 35 በመቶ ነው፡፡

ይህ ሆኖም አፍሪካውያን በተቋሙ አመራርነትም ሆነ በተቋሙ አባልነት፣ ተቋሙ በሚያወጣው ሕጎችና ደንቦች አግባብነት በዓለም የንግድ መድረክ ያላቸው ተሳትፎ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ በሰፊው ሲነገር ቆይቷል፡፡ እስካሁን በዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ሲመዘገብ የቆየው የአፍሪካ ተሳትፎና ድርሻ እያሽቆለቆለ መጥቶ፣ በአሁኑ ወቅት 2.5 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ እ.ኤ.አ. በ1960 ከ5.5 በመቶ ያላነሰ እንደነበር መዛግብይት ያሳያሉ፡፡

በአንፃሩ ከአፍሪካ ወደ ተቀረው ዓለም የሚላኩ ጥሬ ዕቃዎች፣ በተለይም ማዕድናት፣ ቡና፣ ሻይ፣ ካካዋ፣ ጥጥና መሰል ምርቶች ከአፍሪካ በገፍ ቢላኩም በዓለም ገበያ ያላቸው ድርሻ በግብርናና በጥሬ ዕቃ ደረጃ የሚወከሉ፣ ዋጋቸውም ሲበዛ ዝቅተኛ እንዲሆን በመደረጉ ለአፍሪካ ውክልና ፍትሐዊነት የጎደለው ተቋም እንደሚያሰኘው በርካቶች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

ይህ ጥያቄ ሲብላላ በኖረበት ወቅት እ.ኤ.አ. ከ2013 ጀምሮ የዓለም ንግድ ድርጅትን ሲመሩ የቆዩት ብራዚላዊው ሮቤርቶ ዳ አዝቬዶን ለመተካት አፍሪካውያኑ ተወዳዳሪዎች የተሻለ ድምፅና ድጋፍ ያገኛሉ ተብለው እንዲጠበቁ፣ የዓለም ንግድ ድርጅትንም ይበልጥ ፍትሐዊ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል ዕድል ያስገኛሉ የሚል ተስፋ ተበራክቷል፡፡  

ምንም እንኳ የአፍሪካ አገሮች በዓለም የንግድ ሥርዓት ውስጥ ይህ ነው የሚባል ድርሻ ባይኖራቸውም፣ እርስ በርሳቸውም እንደ ልብ አለመገበያየታቸውም ጥያቄ እያስነሳ ይገኛል፡፡ ይህንን የሚቀይር ሁኔታ እንደሚፈጠር የሚታመንበት አኅጉራዊው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ስምምነት በበርካታ አገሮች ፀድቆ ለትግበራ ሽር ጉድ እያለ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ሁለት ተቋማት ውስጥ በመሪነትም በተሳታፊነትም ያላት ሚና ይህ ነው የሚባል ባይሆንም፣ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እየተጣደፈች ትገኛለች፡፡ ከሁለት ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሒደቱን አጠናቃ መደበኛ አባል ለመሆን ዝግጅት ላይ ስለመሆኗ መንግሥት አስታውቋል፡፡ የዓለም ንግድ ድርጅት ህልውናና እንደ ተቋም የመኖሩ አስፈላጊነት ጥያቄ ቢነሳበትም፣ አገሮች አባል ለመሆን የሚያስፈልጉ መሥፈርቶችን ለማለፍ በርካታ መሥፈርቶችንና ቅድመ ሁኔታዎችን ለማሟላት ይጣደፋሉ፡፡ በምርትና በአገልግሎት መስክ የሚጠየቁ የታሪፍ፣ የጥራትና የዋጋ ጥያቄዎች ላይ ለሚቀርቡላቸው የድርድር ጥያቄዎችና የሕግ ማሻሻዎች ክለሳ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያም ይህንኑ ስታደርግ ሰንብታለች፡፡

ይህም ሆኖ የዓለም ንግድ ድርጅትን ፋይዳ ጥያቄ ውስጥ ከከተቱ ኹነቶች መካከል በአሜሪካና በቻይና መካከል የተካረረው የንግድ ጦርነት፣ ለአፍሪካ ምርቶችና ሸቀጦች የሚሰጠው የዋጋና የጥራት ቅድመ ሁኔታዎች ተቋሙን እግር ተወርች የሚያስሩ ችግሮች ሆነው የረባ ምላሽና መፍትሔ ያልሰጠባቸው ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች