- ከአንተ እንደዚያ ዓይነት አስተያየት አልጠበቅኩም ነበር፡፡ ለዚያውም በእንደዚህ ዓይነት መድረክ ላይ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር መድረኩ ነው? አስተያየቴ ትክክል ያልሆነው?
- ሁለቱም። የበለጠ ያበሳጨኝ ግን በዚህ መድረክ ላይ መናገርህ ነው።
- መድረኩ እንዴት? ምን የተለየ ነገር አለበት?
- ተቃዋሚዎች አሉበት። እነሱ ባሉበት እንዲህ ዓይነት አስተያየት መሰንዘር እነሱን መምሰል ነው፡፡
- ግን እኮ አስተያየቱን ሁሉም ይጋራዋል፡፡
- ማን ይጋራዋል?
- ማኅበረሰቡ። እናንተ አትሰሙም እንጂ ማኅበረሰቡ የሚጠራችሁ እንደዚያ ብሎ ነው።
- ምን ብሎ?
- ኢሕአዴግ ቁጥር ሁለት ብሎ፡፡
- ደገምከው?
- ለመድገም አይደለም፡፡ ትችቱ ሰፊ እንደሆነ እንዲገነዘቡት ብዬ ነው።
- አንዳንዴ . . . መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ያለው ነገር ትክክል ይሆን እንዴ እላለሁ፡፡
- መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ምን ነበር ያለው?
- ይኼ ሕዝብ አልጋ ሲያቀርቡለት ቁርበት አለ የተባለው፡፡
- እንደዚያ እንኳን ለማለት ይከብደኛል፡፡
- ታዲያ በምን ምክንያት እኛን ከኢሕአዴግ ጋር ያነፃፅራል? ማንም ያልቻለውን እኛ አይደለንም ያደረግነው? ኢሕአዴግን ማን ነው ያፈረሰው እኛ አይደለንም?
- ክቡር ሚኒስትር ከእርስዎ አላውቅም፣ ነገር ግን. . .
- እውነት ነው፡፡
- ምኑ ክቡር ሚኒስትር?
- ከእርስዎ አላውቅም ያልከውን ማለቴ ነው፣ ለማንኛውም ሐሳብህን ቀጥል፡፡
- እ. . . እርስዎ እንዳሉት ኢሕአዴግ በአካል መፍረሱ እርግጥ ነው፣ ነገር ግን ኢሕአዴግን ማፈረስ በራሱ ስኬት ተደርጎ መቆጠር ያለበት አይመስለኝም። ሕዝቡም ኢሕአዴግ ቁጥር ሁለት ያለበት ምክንያት መነሻው ይህ ይመስለኛል፡፡
- ምን?
- የኢሕአዴግ መፍረስ ጉዳይ አካላዊ ነው ወይስ ከዚያ የዘለለ ነው የሚለው ይመስለኛል መነሻው።
- አልገባኝም?
- በእርስዎ ሙያ ማስረዳት እችላለሁ?
- ቀጥል፡፡
- በአጭሩ ሕዝቡ እያለ ያለው ኢሕአዴግ የፈረሰው ሀርድዌሩ ነው፡፡ ሶፍትዌሩ አሁንም አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ እናንተ እየተጠቀማችሁበት ነው እያለ ነው።
- አለማወቅ ነው። የኢሕአዴግ ሶፍትዌር ከኢሕአዴግ ውጪ አይሠራም።
- እንደዚያ ከሆነ ተመሳስሎ የተሠራ ሊሆን ይችላል?
- ምኑ?
- ሶፍትዌሩ፡፡
- እስኪ የተመሳሰልንበትን ጉዳይ አስረዳ፣ እኛ ሐሳብ የመስማት ችግር የለብንም ቀጥል፡፡
- አንደኛው እሱ ነው፡፡
- ምኑ?
- ሐሳብ የመስማት ችግር የለብንም ትላላችሁ ግን አትሰሙም። የኢሕአዴግ ቁጥር አንድ ችግርም ይኸው ነበር፡፡
- በዚህ እንኳን አልስማማም!
- እውነታውን ግን አይቀይረውም፡፡ ሌሎች ድርጊቶቻችሁም ይመሳሰላሉ፡፡
- የትኞቹ?
- ኢሕአዴግ ቁጥር አንድም ምርጫ ሲደርስ ተቃዋሚዎቹን ያስር ነበር። እናንተም ምርጫዋ ስትደርስ የዋና ዋና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ቁልፍ ሰዎች አሰራችሁ። የሚስማሟችሁን ተቃዋሚ ፓርቲዎች አድማቂ አድርጋችሁ እያሠለፋችሁ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ቁጥር አንድ ፍትሕ አያውቅም፣ መርምሮ ሳያጣራ ያስራል። እናንተም ተመሳሳይ ነገር እያደረጋችሁ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ቁጥር አንድ. . .
- ቢሮ እንግዳ እየጠበቀኝ ባይሆን ኖሮ ብሰማህ ደስ ባለኝ።
- አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን?
- እንግዳ ባይኖር ሐሳብ የመስማት ችግር እንደሌለብዎት!
[ሚኒስትሩ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ባለቤታቸው በረንዳ ላይ እየተንጎራደዱ ሲጠብቋቸው ተገናኙ]
- ምንም ጭንቀት ገጽህ ላይ አይስተዋልም፡፡
- ለምን እጨነቃለሁ?
- የአዲሱ ብር ማስተዋወቂያ ስብሰባ ላይ በቴሌቪዥን ሳይህ ፊትህ እንደበራ ነበር፡፡
- እንዴት አይበራ! ሁሉን ነገር በሚስጥር ይዘን ‹ሰርፕራይዝ› አደረግነው ነው አይደል ሕዝባችንን?
- አስደነገጣችሁን እንጂ?
- አንቺ ደግሞ ምን ሆነሽ ነው የምትደነግጪው?
- የቤትህን ጉድ በሚስጥር ይዘህ ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ ሳይ ለምን አልደነግጥ?
- ማለት?
- በሚስጥር ያዝ የተባልከው ሌላ ሰው እንዳይሰማ እንጂ አንተው ራስህ እንዳትሰማ ነው?
- ግዴለም ለእሱ መላ አይጠፋም።
- እኮ ምን ልታደርግ? እንዴት አድርገህ ልትቀይረው ነው አሁን?
- ቀላቅዬ ነዋ፡፡
- ከምን ጋር ቀላቅለህ?
- ከመሥሪያ ቤቴ የመንግሥት ገንዘብ ጋር፡፡
- ዘመዶቻችን ዘንድ ያስቀመጥነውስ?
- የእኔ መኪና በደኅንነት አካላት ስለማይፈተሽ እሱንም እንቀላቅለዋለን።
- ከቀላቀልክ በኋላስ እንዴት ልታወጣው ነው?
- በፊት እንዳወጣሁት፡፡
- የማትረባ አንተን ማመኔ ነው ስህተቱ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ምርጫ ያደረገውን ክልል ሁኔታ እንዲከታተሉ ወደ መደቡት አንድ ኃላፊ ጋ ደወሉ]
- እንደፎከሩት አደረጉት አይደል?
- አዎ። አድርገውታል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ግዴለም የእጃቸውን እንሰጣቸዋለን።
- ክቡር ሚኒስትር እኔ ግን ቀድሞ የያዙት አቋም ይሻላል ባይ ነኝ።
- የትኛው አቋም?
- ኃይል መጠቀም ተገቢም፣ አዋጭም አይመስለኝም።
- ሶፍት ፓወር እንጂ ኃይል አንጠቀምም፣ ይህንን ደግሞ መውሰድ ጀምረናል አልሰማህም እንዴ?
- አልሰማሁም ምን ወሰዳችሁ?
- የአገሪቱን የብር ኖቶች እንዲቀየሩ አድርገናል።
- እና በዚህ ምን ይገኛል?
- አሁን የክልሉ ሀብት በሙሉ ወደ ባንኮች ይገባል። ይህ ማለት በቁጥጥራችን ውስጥ ወደቀ ማለት ነው።
- እንዴት?
- የተደበቀ ሲወጣ ይወረሳል ወይም ወረቀት ይሆናል። ወደ ባንክ የሚገባው ደግሞ የሚወጣበት ሥነ ሥርዓት ተበጅቶለታል። እንደተፈለገ አይወጣም።
- ጥሩ ጨዋታ ተጫውታችኋል።
- የምርጫው ውጤት እንዴት ሆነ? ተቃዋሚዎች መቀመጫ አገኙ?
- ኧረ እንዲያውም። ገዥው ፓርቲ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮታል።
- እንዴት። ቅይጥ ትይዩ ያሉት ነገር ተቃዋሚዎችን ምንም አልጠቀመም?
- ቅይጥ ትይዩ ተቃዋሚዎችን ለማሳተፍ እንጂ አልጠቀማቸውም። ለቅይጥ ትይዩ የተደለደሉትን ወንበሮችም ከአንዱ በስተቀር ገዥው ፓርቲው ጠቅልሏቸዋል፡፡
- በል ቅይጥ ትይዩ በደንብ እንዲጠና አድርግ።
- ምን ይፈይድልናል?
- ተቃዋሚዎችን አማሎ ጥቅም የማይሰጥ ከሆነ ለእኛም ሊጠቅመን ይችላል!