Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያን የገቢ ንግድ ለመቀላቀል የሚማትረው የስዊዘርላንድ ኩባንያ በመሠረተ ልማት ሊሳተፍ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በነዳጅ አቅርቦት ሥራው በሰፊው ይታወቃል፡፡ እንደ ሲሚንቶ ያሉትን የግንባታና ሌሎችም ሸቀጦችን በማቅረብም ሰፊ ሚና ያለው ትራፊጉራ የሚባለው የስዊዘርላንድ ኩባንያ፣ በሶማሌላንድ ኢትዮጵያን ያማከለ የመሠረተ ልማት ሥራ ላይ ለመሳተፍ መወሰኑ ተሰማ፡፡

ወደ ኢትዮጵያ የነዳጅ አቅርቦት ሥራ ለመግባት ለበርካታ ዓመታት በጨረታ ሲሳተፍ ቆይቶ በመጨረሻው እ.ኤ.አ. ከ2017 የተሳካለት ትራፊጉራ ኩባንያ ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅርቦት ድርጅት ጋር ስምምት በማሰር ማቅረብ ከጀመረ ወዲህ፣ በሶማሌላንድ የአቅርቦት የመሠረተ ልማት ስምምነትም ሲፈጽም ዋና ምክንያቱ የኢትዮጵያ ገበያ እንደሆነ ከሰሞኑ የወጡ ዘገባዎች አመላክተዋል፡፡

ትራፊጉራ የመምጣቱ ነገር ለኢትዮጵያ የመደራደር አቅም ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የሚተነትኑ ወገኖች፣ ጂቡቲ በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ ዳመርጆግ በተሰኘው የፔትሮ ኬሚካል ምርቶች ማስተናገጃ፣ የነዳጅ ተርሚናል ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጠችው ነሐሴ 28 ቀን 2012 ዓ.ም. ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከአራት ቀናት በኋላ ጳጉሜን 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ትራፊጉራ ኩባንያ በበኩሉ በሶማሌላንድ በኩል ለሚካሄዱ የአቅርቦት ሥራዎችና የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ለማከናወን ስምምነት ፈርሟል፡፡ የመጀመርያውን የነዳጅ አቅርቦትም ባለፈው ሳምንት መፈጸሙ ተዘግቧል፡፡

የኩባንያው ዋና ሥራ የነዳጅ አቅርቦት ላይ መሳተፍ ቢሆንም፣ በበርበራ ወደብ የነዳጅ ማከማቻ ተርሚናልን የመገንባት እንዲሁም ትልልቅ መርከቦችን የማስተናገድ ዓላማ ያለው ስምምነት የፈረመው የስዊዘርላንዱ ራፊጉራ፣ ኢትዮጵያ የምታስገባውን የ2.8 ቢሊዮን ዶላር የነዳጅ አቅርቦት ገበያ ማዕከል እንዳደረገ አስታውቋል፡፡ በበርበራ ወደብ ማስፋፊያ ሥራ ላይ የዱባዩ ወደብ አስተዳዳሪ ዲፒ ወርልድ በ442 ሚሊዮን ዶላር ማስፋፊያ እያከናወነ መሆኑም የራፊጉራ መምጣት የኢትዮጵያን ደቡባዊ ክፍል በሰፊው ተደራሽ የሚያደርግ እንቅስቃሴ በሶማሌላንድ በኩል ለማስፋፋት እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡ ዘ አፍሪካ ሪፖርት የተሰኘው መጽሔትም ይህንኑ የሚያመላክት ዘገባ አጠናቅሯል፡፡

በጂቡቲ የሚንቀሳቀሰው ሆራይዘን ነዳጅ የሚተዳደረው በዱባዩ ኤምሬትስ ናሽናል ኦይል ኩባንያ ቢሆንም፣ ይህ ኩባንያ በየዓመቱ እስከ ዘጠኝ በመቶ እያደገ የመጣውን የኢትዮያን የነዳጅ ፍላጎት የሚያሟላ አቅርቦት ለብቻው ማከናወን እንደሚሳነው የሚጠቅሱ ተንታኞች፣ ራፊጉራ በኢትዮጵያ ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስችል ተጨባጭ ዕድል እንደሚፈጥርለት ይገልጻሉ፡፡ ኩባንያው አሁንም የኢትዮጵያን የነዳጅ አቅርቦት በጨረታ በማሸነፍ እያቀረበ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2019 4.1 ሚሊዮን ቶን ነዳጅ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን፣ ይህም ከ2.8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያለው በመሆኑ ኩባንያው በዚህ ሥራ ላይ መሳተፉን ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጠው ኩባንያው አስታውቋል፡፡

ይሁን እንጂ የአውሮፓው ኩባንያ በበርበራ ወደብ ላቀደው ኢንቨስትመንት ምን ያህል ገንዘብ እንደመደበ ይፋ አልተደረገም፡፡ ከዚህ ባሻገር በኢትዮጵያና በሶማሌላንድ መካከል ያለው የመንገድ ኔትወርክ የተበላሸና ችግር ያለበት በመሆኑ እንደተፈለገው የተቀላጠፈ አቅርቦት ወዲያኑ እንዲፈጠር የማያስችል በመሆኑ ለጊዜውም ቢሆን ለጂቡቲ እፎይታ ማስገኘቱ አልቀረም፡፡ በአንድ በኩል የመሠረተ ልማት መሟላት በሌላ በኩል በኢትዮጵያና በጂቡቲ መካከል የፀጥታ ሥጋት አለመኖሩ ለሸቀጦች እንቅስቃሴ የተመቸ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ሆኖም አማራጭ ሆና ብቅ ያለችው ሶማሌላንድ እነዚህን ጥያቄዎች በአስተማማኝ መንገድ የመፍታት አቅሟ አጠያያቂ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች