Monday, June 24, 2024

የኦነግ ሁለት ‹‹የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል›› ዓመታት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ማክሰኞ መስከረም 5 ቀን 2013 ዓ.ም. የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ አመራሮች ወደ አዲስ አበባ ከመጡ ሁለት ዓመት ሞልቷቸዋል፡፡ በወቅቱ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ጋር በኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ያደረጉትን ስምምነት ተከትሎ ወደ አገር ውስጥ የተመለሰው የኦነግ አመራር፣ በርካታ ውዝግቦችና ክርክሮች ወስጥ ቆይቶ አሁን የፓርቲው አመራሮች ለሁለት ተከፍለው አንዱ ቡድን ሌላኛውን እየከሰሰና እየወቀሰ፣ እንዲሁም በፓርቲው ውስጥ ለተፈጠሩ ችግሮች ተጠያቂ ሲያደርግ ይስተዋላል፡፡

በተለይ ኦነግ በሐምሌ ወር ውስጥ ያደረገው ስብሰባ ያለ እኔ ዕውቅና ነው የተካሄደው በሚሉት የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳና ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመሩት ቡድን መካከል በተፈጠረ ውዝግብ በፓርቲው ስብሰባ ላይ ውሳኔ ተላልፏል በማለት አቶ ዳውድ እንደታገዱ የተገለጸ ሲሆን፣ አቶ ዳውድ ኢብሳ በበኩላቸው እኔ በአርቲስት ሃጫሉ ሞት ሳቢያ ከቤት እንዳልወጣ ተደርጌ ሳለ ነው ስብሰባው ያለ እኔ ዕውቅና የተደረገው በማለት ምክትል ሊቀመንበሩን አቶ አራርሶን ጨምሮ የሥራ አስፈጻሚና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የሆኑ ስድስት ግለሰቦች ከፓርቲው እንዲታገዱ አደረጉ፡፡

ይሁንና ይኼ ውዝግብ ተጧጡፎ ዛሬ ከሊቀመንበሩና ከቡድናቸው ተከፍሎ የወጣው በአቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመራው ቡድን የፓርቲውን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ቀጄላ መርዳሳንና የፓርቲውን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና አሁን ቃል አቀባይ ሆነው የሚያገለግሉትን አቶ ቶሌራ አደባን ይዞ፣ አቶ ዳውድ በፓርቲው ውስጥ የጋራ አመራር ጠፍቶ ወደ ግለሰባዊ አመራር ማዘንበል ተይዟል ሲል ይከሳል፡፡ ፓርቲው እስከ ዛሬ በተደጋጋሚ ሦስት ጊዜያት እንዲከፋፈልና የፓርቲው ውሳኔዎች እንዳይፈጸሙ ምክንያት በመሆናቸው፣ አቶ ዳውድን ከሊቀመንበርነት አግዶ አቶ አራርሶ በጊዜያዊ ሊቀ መንበርነት እንዲመሩ መሾማቸውን ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በጽሑፍና በድምፅ-ወምሥል በሰጡት መግለጫ አሳውቀዋል፡፡

ነገር ግን የአቶ ዳውድ ቡድን በበኩሉ በአቶ አራርሶ የሚመራው ቡድን ከሥራ አስፈጻሚው ዕውቅና ውጪ በሆነ መንገድ የመተዳደርያ ደንቡን በመጣስ፣ ምልዓተ ጉባዔው በሁለት ሦስተኛ ተሳታፊዎች ሳይሟላ የተደረገ ስብሰባ በመሆኑ፣ እንዲሁም ውሳኔውን ያስተላለፉት አባላት የታገዱ በመሆናቸው ተቀባይነት የለውም ሲል ለምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡

ኦነግ ከአስመራ የትጥቅ ትግል እስከ ምርጫ ዝግጅት

በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ወር የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ለተከታታይ ሦስት ዓመታት አገሪቱን ከናጣት አመፅና ብጥብጥ አገሪቱ ትወጣ ዘንድ፣ እስከ ዛሬ ያጠፋኋቸውን ጥፋቶች በማረም የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋትና ኢኮኖሚውንም ክፍት በማድረግ የሕዝቡን ተጠቃሚነት አሳድጋለሁ ብሎ ባካሄደው ለውጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሥልጣናቸውን ለቅቀው፣ በወቅቱ ትልቅ ተስፋ የተጣለባቸውና ሰፊ ድጋፍ የተቸራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን መጡ፡፡ ከዚህ ለውጥ በኋላ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት በርካታ እስረኞች ከእስር ቤቶች እንዲፈቱ የተደረገ ሲሆን፣ ከአገር ውጪ በስደት የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦችም ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ሰላማዊ ትግል ያደርጉ ዘንድ በተደረገው ጥሪ መሠረት በርካታ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አዲስ አበባ ተምመዋል፡፡ ዘግይተው ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱና ከመመለሳችን በፊት ግልጽ በሆነ መንገድ በሦስተኛ ወገን አደራዳሪነት ስምምነት እናድርግ የሚል ጥያቄ አቅርቦ፣ በድርድር ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ የፖለቲካ ቡድኖች መካከል አንዱ ኦነግ ነው፡፡

በወቅቱ በአቶ ለማ መገርሳና በወርቅነህ (ዶ/ር) የተመራ ቡድን ወደ አስመራ አቅንቶ ከአቶ ዳውድ ኢብሳ ጋር ያለ ሦስተኛ ወገን ተሳታፊነትና ታዛቢነት ባደረጉት ውይይት ከስምምነት ተደርሶ፣ የኦነግ ጦርና የፖለቲካ አመራሮች ወደ ኢትዮጵያ መስከረም 5 ቀን 2011 ዓ.ም. እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡

ይኼ የመንግሥት ተወካዮችና የአቶ ዳውድ ስምምነት ምን ይዘት እንደነበረው መንግሥት ያልገለጸ ሲሆን፣ በተለይ የኦነግ ጦር ትጥቅ ፈትቶ ወታደሩ ወደ ፖሊስ አልያም ወደ መከላከያ ሠራዊት እንዲገባ ስምምነት ተደርጎ እንደነበር፣ ግን በተደጋጋሚ በታጣቂ ቡድኑና በመንግሥት እንዲሁም በኦነግ የፖለቲካ አመራር መካከል በነበሩ ውዝግቦች ሲጠቀስ ቆይቷል፡፡

የኦነግ ቃል አቀባይ በመሆን አቶ ቀጄላን ተክተው የተሾሙት አቶ በቴ ኡርጌሳ ኦነግ ሠራዊቱን ይዞ ወደ አገር ቤት ከገባ ሁለት ዓመታት ተቆጥረዋል ቢባልም፣ ከዚያ አስቀድሞ ኦነግ አገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ አባላትም ሆኑ ወታደሮች አልነበሩትም ማለት እንዳልሆነ በማስገንዘብ፣ በወቅቱ ወደ አገር ቤት የተመለሰው የኦነግ አመራርና ሥራ አስፈጻሚ ቡድኑ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹በወቅቱ ወደ አገር ቤት ስንገባ በርካታ ግምቶችን አስቀምጠን ነበር ወደ አገር ቤት የገባነው፤›› በማለት የሚጀምሩት አቶ በቴ፣ ‹‹ኢሕአዴግን ተቃውመው ወደ ትጥቅ ትግል ከገቡ ቡድኖች የመጀመርያዎቹ በመሆናችንና እስከዚህ ድረስም በትጥቅ የቆየን በመሆናችን ዝም ተብሎ ግባ ግባ በመባል ሳይሆን በድርድር መግባት እንድንችል፣ በተለይም በአውሮፓውያን አደራዳሪነት ከስምምነት ደርሰን መመለስ እንድንችል ጥያቄ አቅርበን ነበር፤›› ይላሉ፡፡

ይሁንና ቄስ በላይ መኮንንና አባ ገዳ በየነ ሰንበቶን ጨምሮ በአገር ሽማግሌዎች አማካይነት ዕርቅ ይፈጠርና እነርሱ የተቀሩ ሥራዎችን በመካከል ሆነው ያቀላጥፉ በማለት ተስማምተው ስለነበር፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ነገሮች በፍጥነት የተቀያየሩ መሆናቸውና የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ ጋር የነበረውን ግንኙነት በማሻሻሉ ሳቢያ ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውን የሚናገሩት አቶ በቴ፣ ከአቶ ለማና ከወርቅነህ (ዶ/ር) ጋር የነበራቸው ውይይት እንደጠየቁት በሦስተኛ ወገን የተካሄደ ባይሆንም፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር መስፋቱ፣ መገናኛ ብዙኃን በነፃ እንዲንቀሳቀሱ ተፈቅዷል ብለው ስላመኑ እንዲሁም ኦነግንና የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ)ን አሸባሪ ብሎ ፈርጆ የነበረው የፀረ ሽብር ሕጉ ፍረጃ በመነሳቱ የዴሞክራሲ ተስፋ ሰጥቷቸው እንደነበረ ያስረዳሉ፡፡

‹‹ለውጡ በቄሮ መስዋዕትነት ኦነግ በፊታውራሪነት ሲመራው የነበረ ስለነበረ፣ ኦነግ ወደ አገር ቤት ተመልሶ የፖለቲካ ትግል እንዲያደርግ ከአባላትና ከደጋፊዎቻችንም ግፊቶች ነበሩብን፤›› ይላሉ አቶ በቴ፡፡ ይሁንና የነበሩት ለውጦች መስመር ያልያዘ፣ መዋቅራዊ ያልሆኑና ተቋማዊ ቅርፅ ያልያዙ እንደነበሩ፣ ይባስ ብሎም በአንድ ሰው የሚዘወሩ ነበሩ በማለት በለውጡ ላይ ጥርጣሬ እንደነበራቸው የሚያስረዱት አቶ በቴ፣ ተስፋዎቹ ይበልጡ ነበርና ወደ አገር ውስጥ እንደገቡ ያስታውሳሉ፡፡

ወደ አገር ቤት እንዲገቡ የተደረገ ቢሆንም ቅሉ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግሥት ኦነግን ተቀብሎና በፖለቲካው ውስጥ እንዲሳተፍ ከልቡ ፈልጎ ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሜሪካ ለጉብኝት ሄደው ሳለ፣ ከዳያስፖራውና ከአገር ሽማግሌዎች ግፊት ስለነበር ኦነግ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ እንደተቀበለ አቶ በቴ ያምናሉ፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ ከሆነ፣ ኦነግና ሁለቱ የቀድሞ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትና በአገሪቱ በመጣው የፖለቲካ ለውጥ ውስጥ ጉልህ ሚና ነበራቸው በሚባሉት ፖለቲከኞች መካከል የተደረገው ስምምነት የኦነግን ወታደሮች ዕጣ ፈንታ፣ የኦሮሞ የተራድኦ ድርጅት (ኦሮሞ ሪሊፍ አሶሴሽን)፣ እንዲሁም ወደ አገር ውስጥ ለሚገቡ የኦነግ አመራሮች የሚደረግ አቀባበልና የኑሮ ድጋፍ ነበሩ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በመንግሥት እጅ እንደገቡ የሚታወቁ እንደ ዮሴፍ ባቲ፣ ነዲ ገመዳና ሌሎች 200 የኦነግ አባላት የት እንደገቡ ስለማይታወቅ፣ መንግሥት አብሮ ሊያፈላልግና ከሞቱም አፅማቸው ተሰብስቦ በክብር ሊቀመጥ ስምምነት ተደርጎ ነበርም ይላሉ፡፡

ሠራዊቱን የተመለከተው ስምምነት ወታደሩ በፈቃዱ የኦሮሚያና የፌዴራል የፀጥታ መዋቅር ውስጥ እንዲገባ፣ እንዲሁም በፓርቲው ውስጥ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ማድረግ የሚፈልግ እንደዚያው እንዲያደርግ፣ እንዲሁም በሁለቱም ውስጥ መሳተፍ የማይፈልጉ ደግሞ መቋቋሚያ ተሰጥቷቸው ወደ ኅብረተሰቡ እንዲመለሱ እንዲደረግ ሲሆን፣ የሚሰጣቸው ሥልጠና ማኑዋል በጋራ የተዘጋጀና በጋራ የሚከናወን ሥልጠና እንዲሆንም ስምምነት እንደ ነበር አቶ በቴ ይናገራሉ፡፡ ለዚህም እንደ ጀርመን ያሉ አገሮችና የውጭ ድርጅቶች ድጋፍ ለማድረግም ፈቃደኛ እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡

አመራሩና ወታደሩም ወደ አገር ቤት በአውሮፕላን በመንግሥት ወጪ እንዲመለሱ እንደሚደረግ፣ እንዲሁም 40 አመራሮች የሚጠቀሙባቸው 40 ተሽከርካሪዎች እንደሚመደቡ፣ 40 የመንግሥት ቤት በመኖሪያነት እንደሚሰጣቸው፣ እንዲሁም በመንግሥት አቀባበል ተደርጎላቸው የእራት ግብዣ ሊደረግ ቃል ተገብቶ የነበረ ቢሆንም፣ አንዱም እንዳልተደረገና በራሳቸው የአውሮፕላን ቲኬት 29 ሺሕ ዶላር በመክፈል አመራሮቹ ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ አቶ በቴ ይናገራሉ፡፡ በተጨማሪም ኦነግን ለመቀበል በመስቀል አደባባይ አዳሩን ተሰብስቦ የነበረውን የኦነግ ደጋፊ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ላይ በመድረስ ያናግራሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ሆን ተብሎ በተፈጠረ መዘግየት ከረፋዱ 5፡30 ሰዓት መድረሳቸውንና ሊቀመንበሩ ንግግር በሚያደርጉበት ጊዜ የደከመው ደጋፊ መበታተን መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡

‹‹የጋለ የሕዝብ ድጋፍና የፓርቲው ዓርማ በተለያዩ ሥፍራዎች በስፋት በመታየቱና ለአቀባበል የወጣው ሕዝብ ብዛት ከፍተኛ ስለነበረ፣ መንግሥት ማሰናከል ጀመረ፤›› የሚሉት አቶ በቴ፣ ‹‹አቶ ዳውድ ኢብሳ የአውሮፕላን ቴኬት እንዳያገኙ አልቋል ተብሎ ከእሳቸው በኋላ የመጡ ሁሉ ሲቆረጥላቸው ነበር፤›› ይላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በኦነግ የሚተዳደረው የኦሮሞ ተራድኦ ድርጅት ንብረቶች በመንግሥት ተወርሰው ስለነበር፣ ጽሕፈት ቤትና ንብረቶቹ እንዲመለሱለት ከስምምነት ቢደረስም ለመመለስ አልተፈለገም ይላሉ አቶ በቴ፡፡ መንግሥት ኦነግ ሰፊ ድጋፍ እንዳለው ሲያውቅ ማስተጓጎል እንደጀመረ በመናገር፣ አመራሮቹ የሚያርፉበት ሆቴል እንኳን ሳይያዝ በኪራይ መኪና ተንቀሳቅሰው በራሳቸው ወጪ ኢሊሊ ሆቴል እንደያዙና ምሳም እዚያው እንዲዘጋጅ እንደተደረገ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ያረፍንበት ሆቴል ባለቤት አቶ ገምሹ በየነ ላይ ማስፈራሪያዎች ይሰነዘሩ ነበር፡፡ በአማራ ክልል የእሳቸው ንብረት ላይ የተቃጣው ጥቃትም የዚህ ማስፈራሪያ አካል ሲሆን፣ የብልፅግናን ረዥም እጅ የሚያሳይ ነው፤›› በማለትም ይከሳሉ፡፡

ከዚህ በኋላ ወታደሩ ከአስመራ አቋርጦ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ትግራይ ላይ ከአቶ ስብሃት ነጋ ጋር መገናኘቱን፣ እንዲሁም ጦሩን አስመልክቶ አቶ ዳውድ ለዋልታ ቴሌቪዥን ሲያስረዱ ‹‹ማን ፈቺ ማን አስፈቺ›› ብለው ተናግረዋል በማለት አላስፈላጊ ፕሮፓጋንዳ ሲነዛ ነበርም ይላሉ፡፡ ነገር ግን ማን ፈቺ ማን አስፈቺ የሚለው ንግግር ከአውዱ ውጪ የተወሰደና ወታደሩ ምርኮኛ አይደለም አዛብቶ ከዓውዱ ውጪ ያቀረበ እንደሆነ በመናገር ውክልናው ልክ እንዳልነበረ ይከራከራሉ፡፡ ይኼንን ተከትሎም የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ አመራሮች አቶ ታዬ ደንደአና አቶ አዲሱ አረጋ፣ ወታደሩ በ15 ቀናት ውስጥ ትጥቁን ይፈታል ብለው መናገራቸውና አመራሩም ጦሩን ለመጎብኘት አለመቻሉን ያስታውሳሉ፡፡

በፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ አራርሶ የሚመራውና ሊቀመንበሩን ያገደው ቡድን በበኩሉ፣ እሑድ መስከረም 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ይኼንኑ ጉዳይ ያነሳ ሲሆን፣ ይኼ የሊቀመንበሩ ንግግር እሳቸው ለሰላማዊ ትግል ዝግጁ እንዳልሆኑ ያሳያል ይላል፡፡ የአቶ አራርሶ ቡድን በመግለጫው፣ ‹‹የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ከ27 ዓመታት በኋላ ሰላማዊ የትግል ስትራቴጂን መርጦና ወስኖ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ተደራድሮ በ2010 ዓ.ም. ወደ አገር ቤት መመለሱ ይታወሳል፡፡ ወደ አገር ቤት ሲመለስ ያኔ ኦሮሚያን ሲያስተዳድር የነበረው ኦሕዴድን (የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት) ጨምሮ ከሌሎች የኦሮሞ ድርጅቶች ጋር የኦሮሚያንና የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅም ለማስከበር አብሮ ለመሥራት መወሰኑም ይታወሳል። አቋሙንና ፖሊሲዎቹንም በሄደበት ሁሉ ለሕዝቡ አሳውቋል። የኦሮሞ ሕዝብም ኦነግ ወደ አገር ቤት መመለሱን ከሁሉም አከባቢዎች በሚሊዮኖች ወጥቶ የተቀበለውም ሰላማዊ ትግሉን በመደገፍ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ እንኳን በደህና ወደ ሰላማዊ ትግል መጣችሁ በማለት ተቀበለን እንጂ የትጥቅ ትግሉን ትታችሁ ለምን መጣችሁ አላለንም፡፡ ይሁን እንጂ ኤርትራ ማሠልጠኛ ካምፕ ውስጥ የነበሩ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አባላት በሰላማዊ መንገድ ወደ አገር ቤት ቢገቡም፣ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ዋና አዛዥ የሆኑት አቶ ዳውድ ኢብሳ አገር ውስጥ የነበሩ የሠራዊቱ አባላት ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲመለሱ ለማድረግ የሚጠበቅባቸውን አላደረጉም፡፡ በመንግሥት በኩልም የነበረው ችግር እንዳለ ሆኖ አቶ ዳውድ ኢብሳ ‹‹ማን ማንን ያስፈታል›› በማለት በሚዲያ ያስተላለፉት መልዕክት ጥርጣሬን በማንገሥ፣ ለመንግሥት ወታደራዊ ዕርምጃ በር ከፍቷል፡፡ የትግል ሥልት ጥበብን ይጠይቃል። አቶ ዳውድ ኢብሳ አዲስ አበባ ከተማ ተቀምጠው የትጥቅ ትግል ለመምራት የሚያደርጉት አጉል ጥረት ድርጅቱ በሰላማዊ መንገድ በሚያደርገው ትግል ላይ ትልቅ ተፅዕኖ መፍጠሩ አሌ የማይባል ሀቅ ነው፤›› ሲል ሊቀመንበሩን ይከሳል፡፡

ከመንግሥት ወገን በነበረ ችግር የኦነግ ሠራዊት አባላት የኦነግን አስተሳሰብ ትተው አገራዊ አስተሳሰብ እንዲይዙ ሊደረግ ይገባል እንጂ፣ የኢሕአዴግን አስተሳሰብ እንዲይዙ ሊደረግ አይገባም በማለት የኦነግ አመራር ከመንግሥት ጋር ውዝግብ ውስጥ በገባበት ወቅት የተነገረ አባባል ተዛብቶ ቀርቧል በማለት የሚናገሩት አቶ በቴ፣ ይኼም ወታደሩን ጦር አስፈትቶ ከነባር ወታደር ጋር የማዋሀድና ያልፈቀደውን ደግሞ ወደ ኅብረተሰቡ የማስገባት ሥራ ውጤታማ እንዳይሆንና መተማን እንዳይኖር ስለሚያደርግ፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮን መሠረት አድረገን መንግሥትን የጠየቅነው ጉዳይ ነው እንጂ፣ የመንግሥትን ሥራ ለመጋፋት በመፈለግ ያደረግነው ነገር አይደለም ይላሉ፡፡ የፓርቲነት ሚና ከመንግሥት ሚና መለየት አለበት በሚል ዕምነት ይኼንን እንዳደረጉ በመግለጽም፣ የእነሱ የተሳትፎ ጥያቄ ያንን ለማድረግ በማሰብ መሆኑንና ቀድሞውኑም ኦነግንና ኢሕአዴግን ያጣላቸው ጉዳይ እንዳይደገም በማለም እንደሆነ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ይኼንን ሒደት ለመደገፍ የኦነግ አመራር ከኦነግ ጦር መሪ ጃል መሮ ጋር ለመነጋገር ወደ ምዕራብ ወለጋ እንዳይሄድ ተክልሎ እንደነበርና መሄዳቸው ሥጋት እንደሚፈጥር ተነግሯቸው እንደነበር አቶ በቴ ያስታውሳሉ፡፡ ነገር ግን ከወቅቱ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ኃላፊ ጄኔራል አደም መሐመድና ከጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹምና የዘመቻ ኃላፊ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ ጦሩን ሊቀመንበሩ አቶ ዳውድ ምዕራብ ወለጋ ሄደው ለማሳመን ጥረት አድርገው እንደነበር፣ የጦሩን ሥጋቶችም መጥተው ለመንግሥት ሪፖርት ማድረጋቸውን በማውሳት አቶ በቴ ይከራከራሉ፡፡ የጦሩ ሥጋቶች ከነበሩት ውስጥ ዋነኛው ከጦሩ ጋር የተጣሉትና ከፓርቲውም የተነጠሉት አቶ ከማል ገልቹ የኦሮሚያ ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው መሾም እንደሆነ፣ ይኼም መተማመኛ ወይም ዋስትናችን ምንድነው ብለው እንዲጠይቁ እንዳደረጋቸው አቶ በቴ ይናገራሉ፡፡ ለሁለተኛ ጉብኝት ሊቀ መንበሩ ወደ ወለጋ ሲሄዱ ነቀምት እንደደረሱ ጦርነት ስለተጀመረ መመለሳቸውንና ከዚያ ወዲህ ከጦሩ ጋር ግንኙነት መመሥረት ስላልቻሉ አባ ገዳዎችንና ሕዝቡን ወታደሩን እንዲረከብ ጥሪ አቅርበዋል ይላሉ፡፡

‹‹ጦላይ የጦር ካምፕ የገቡት እንደ እስረኛ ነው ይታዩ የነበሩት፡፡ በአንድ ወቅት በተከሰተ የሻይ መመረዝም 200 ያህል ወታደሮች ለበሽታ ተጋልጠው ነበር፤›› የሚሉት አቶ በቴ፣ ‹‹የተወሰኑት ወደ ፖሊስ ኃይል እንዲገቡ ተደርጎ የተቀሩት ያለ ምንም ድጋፍ ነው የተለቀቁትና ጎዳና ላይ የወደቁት፤›› ይላሉ፡፡ እንደ እሳቸው ከሆነ፣ መንግሥት ይኼንን ያደረገው ኦነግ ከታጣቂ ኃይሉ ጋር መለያየት እንደማይፈልግ በማሳየት በምርጫ ቦርድ እንዳንመዘገብ ለማድረግ ነው፡፡ ስለዚህም በመግለጫ ከጦሩ ጋር መለያየታቸውን አሳውቀውና በፊርማም አረጋግጠው እንዲመዘገቡ እንደተደረጉ ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹ከዚህ በኋላ ሰላማዊ ትግል ለማድረግ እንቅፋት እንደማይፈጠርብን፣ እንዲሁም የጉለሌው ቢሯችን ሙሉ ለሙሉ እንደሚለቀቅልን ብንስማማም ቢሯችን ግማሹ ብቻ ነው የተለቀቀልን፡፡ በተጨማሪም ለምርጫ ቦርድ መመዝገቢያ መሥፈርት ለማሟላት ፊርማ ለማሰባሰብ ስንሄድ ማዋከብ፣ ቢሮዎቻችንን መዝጋት፣ እንዲሁም ጠቅላላ ጉባዔ እንዳናደርግ በፖሊስ እስከማገድ የደረሱ እንቅፋቶች ተፈጥረውብናል፤›› ሲሉ የሁከት ዓመታት ቆይታ ፈተና ያሉዋቸውን ያስረዳሉ፡

ይሁንና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኙ ድጋፍ እንዳደረጉላቸው፣ እንዲሁም በሆቴል ባይሆንም የምታደርጉበት መጥተን እንታዘባለን ብለው በዝናብ ወቅት በቢሯቸው ቅጥር ግቢ ውስጥ የዛሬ ዓመት ያደረጉት ጉባዔ ላይ የቦርዱ ተወካዮች እንደተሳተፉ በማስታወስ ቦርዱንና ሰብሳቢዋን ያመሠግናሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም በአገሪቱ ውስጥ የሚከሰቱ የተለያዩ ክስተቶችን ምክንያት በማድረግም የኦነግ አመራሮችን ማሰርና ማንገላታት መኖሩ አንዱ ፈተና ነበር በማለት ይናገራሉ አቶ በቴ፡፡ በዚህም ሳቢያ የጃዋር ጥበቃ ተነሳ ተብሎ በነበረበት ወቅት በተፈጠረ አመፅና ብጥብጥ፣ እንዲሁም የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ከአሥር ሺሕ በላይ አባላቶቻቸው እንደታሰሩ ይናገራሉ፡፡ በሦስት ወራት ውስጥ እስከ ወረዳ ድረስ ከ200 በላይ ቢሮዎችን ከፍተው እንደነበር ያስታወሱት አቶ በቴ፣ አባላቶቻቸው ግን እንደ ልብ እንዳይንቀሳቀሱና እንዲታሰሩ ተደርገዋል ይላሉ፡፡

የኦነግ ሊቀመንበር መታገድና የፓርቲው ለሁለት መከፈል

የኦነግ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አራርሶ የሚመሩት የኦነግ ቡድን እ.ኤ.አ. ጁላይ 26 እና 27 ቀን 2020 ያደረገው ስብሰባ ያለ ሊቀመንበሩ አቶ ዳውድ ዕውቅና ነው በማለት ሊቀመንበሩ ወቅሰዋል፡፡ ይኼ ስብሰባ እንዲከናወን ያደረጉ ስድስት የሥራ አስፈጻሚና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እንዲታገዱ የወሰኑ ሲሆን፣ ይኼንን ስብሰባ ያደረገው ቡድን በበኩሉ የተደረገው ስብሰባ በሕገ ደንቡ መሠረት ስለሆነ ምንም ስህተት የለበትም በማለት ሊቀመንበሩ የፓርቲው ጉባዔ እስከሚካሄድ ድረስ እንዲታገዱ ወስኗል፡፡

ቡድኑ ይኼንን አስመልክቶ ሰኞ መስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹የኦሮሞ ነፃነት ግንባር መሥራች ጉባዔ ሰኔ 1968 ዓ.ም. ተቀምጦ የግንባሩ የፖለቲካ ፕሮግራምና ሕገ ደንብ ላይ ተወያይቶ በማፅደቅ፣ የተሟላ ድርጅታዊ መዋቅር ዘርግቶ እንቅስቃሴ ከጀመረ እነሆ 44 ዓመታት አልፎታል። ይሁን እንጂ በተለያዩ ጊዜያት ለሚጣሱ የሥነ ሥርዓት ሕጎች አግባብ ያለው መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ፣ በእልህና በማናለብኝነት በድርጅቱ ውስጥ በሚነዙ አፍራሽ ፕሮፓጋንዳዎች መከፋፈሎች እንደነበሩ ይታወቃል። በተለይም ከ1991 ዓ.ም. ጀምሮ በድርጅቱ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት ታይቶ አይታወቅም። በተለይም ደግሞ ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በኦነግ ሊቀመንበር በአቶ ዳውድ ኢብሳ አመራር ሥር ድርጅቱ ሦስት ትልልቅ የመከፋፈል አደጋዎች አጋጥመውታል። በአቶ ዳውድ አመራር ሥር ድርጅቱ የተለያዩ ውድቀቶች ገጥመውታል። በአጠቃላይ ድርጅቱ የሚጠበቅበትን ተልዕኮ መወጣት ለምን አልቻለም የሚለው በብዙዎች ለዓመታት ሲነሳ ለነበረው ጥያቄ ተገቢ መልስ መስጠት ያስፈልጋል። ይሁን እንጂ አቶ ዳውድ ኢብሳ ወደዚህ ኃላፊነት ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ድርጅቱንና የኦሮሞን ሕዝብ ትግል ወደፊት ከማራመድ ይልቅ ራሳቸውን የሁሉም ነገር ማዕከል አድርገው ሥልጣናቸውን ለማጠናከር ከመሥራት ውጪ፣ ለኦሮሞ ሕዝብ ትግል ያበረከቱት አስተዋጽኦ በጣም ጥቂት ነው። ከስድስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እንዲካሄድ ተወስኖ የነበረው የድርጅቱ ሦስተኛ ጠቅላላ ጉባዔም ተጓቶ ለአምስት ዓመታት እንዲራዘም ተደረገ፤›› በማለት የሚከስስ ሲሆን፣ በዚህ ምክንያት የኦነግን ድርጅታዊ አንድነት የደገፉ አመራሮችና በርካታ የግንባሩ አባላት ‹‹የውስጥ ጠላት›› ተብለው ተፈርጀው ድርጅቱን ለቀው እንዲወጡ ተደርጓል ይላል፡፡ ስለዚህም ‹‹በ2003 ዓ.ም. ግንባሩን ለቀው የወጡ የድርጅቱ አመራሮችና ነባር አባላት ተሰባስበው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር የሚል ድርጅት ሲያቋቁሙ ግንባሩ አሁንም ለሦስተኛ ጊዜ በአቶ ዳውድ አመራር ሥር ተከፈለ። ቀደም ሲል በተፈጠሩ መከፋፈሎችና በኋላ ላይ በ2003 ዓ.ም. በተፈጠረው መከፋፈል በድርጅቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፤›› ሲል አቶ ዳውድን ስለ ሁሉም ስህተቶች ተጠያቂ ያደርጋል፡፡

የዚህ ቡድን ኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አዳባ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ ኦነግ ወደ አገር ውስጥ የዛሬ ሁለት ዓመት ወደ አገር ውስጥ ከገባ በኋላ በተቻለ መጠን ሕዝቡ ጋር ለመድረስ በመጣር ሊያደራጅም ችሏል፡፡ የማንቃት ሥራም በሰፊው ተሠርቷል፡፡ ይሁንና በውስጥ ፓርቲው ችግር ነበረው፡፡ ‹‹በከፍተኛ አመራሩ ዘንድ ሰላማዊ ትግል ላይ የጠራ አቋም አልነበረም፡፡ ከአዲስ ሁኔታ ጋር ራስን የማጣጣም፣ ከመንግሥትና ከሌሎች ተቃዋሚዎች ጋር ተባብሮ የመንቀሳቀስ ችግር ነበር፤›› የሚሉት አቶ ቶሌራ፣ ‹‹በየጊዜው የነበረው ችግር ጎልቶ አብሮ መሥራት የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤›› ይላሉ፡፡ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች አንድ ላይ እንዲመጡ ጥረት ቢደረግም እንዳልተሳካ በማስታወስም፣ በድርጅቶቹ መካከል የጎላ የዓላማ ልዩነት ባለመኖሩና ልዩነቱ የታክቲክ ብቻ ነው በማለት ሁሉም የየራሱን ፓርቲ ይዞ የመቀጠልና ኦነግን የመጠራጠር አዝማሚያ ነበረባቸው ይላሉ፡፡ ‹‹ሁሉም በአንድ ፓርቲ እንዲሰባሰቡ አልያም ግንባር ፈጥረው የየራሳቸውን ማንነት ይዘው እንዲቀጥሉ ነበር የታሰበው፡፡ ግን በእኛ በኩል ገታራነት ነበር፤›› በማለት ኦነግ የኦሮሞ ፓርቲዎች ውህደት እንዳይሳካ ካደረጉ ምክንያቶች እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

አቶ ቶሌራ አክለውም፣ አሁንም ቢሆን ከሌሎች ድርጅቶች ጋር አንድ ላይ ቢቻል ተዋህደው አልያም ግንባር ፈጥረው ለመንቀሳቀስና የኦሮሞን ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሚሠሩ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ የድርጅቱ የውስጥ ችግሮች ገና ስላልተፈቱ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ይኼንን ዓላማ በተመለከተ ውይይት ማድረግ እንዳልጀመሩ ያስረዳሉ፡፡

እንደ አቶ በቴ አገላለጽ ከሆነ ደግሞ፣ ይኼ የፓርቲው ክፋይ አሥር የማዕከላዊ ኮሚቴና ሁለት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በእስር ላይ ሳሉ በታገዱ ስድስት አባላት አማካይነት የተካሄደው ስብሰባም ሆነ፣ የተወሰነው ውሰኔ ፅኑ ስለማይሆን ተቀባይነት የለውም ይላሉ፡፡ ‹‹ብልፅግና ፓርቲ ከውስጥ አንዳንዶቹን በጥቅም በመደለል የፓርቲውን ሥራ እንዲቆጣጠሩ በጀትና ፖሊስ መድቦ ስብሰባ እንዲያደርጉ ደግፎ ከሕገ ደንብ ውጪ በሆነ መንገድ ውሳኔ ተወስኖ ሊቀመንበሩ እንዲታገዱ ተደረገ፤›› በማለትም፣ ብልፅግና ፓርቲን ይወቅሳሉ፡፡

ስብሰባቸውን ሊቀመንበሩ ሳያውቁ አድርገው በዚሁ ስብሰባ ላይ ባልተያዘ አጀንዳም አቶ ዳውድ ከኦነግ ጦር ጋር አልተለያዩም፣ ከተማ ውስጥ ኃይል አደራጁ፣ እንዲሁም ከሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ጋር ግንኙነት ያደርጋሉ በማለት ዕገዳ አስተላልፈውባቸዋል ይላሉ፡፡ ‹‹ነገር ግን የሥራ አስፈጻሚ አባላት ሊቀመንበሩን ማገድ እንደማይችሉ በሕገ ደንባችን ተቀምጧል፤›› በማለትም ይከራከራሉ፡፡ ‹‹ብልፅግና በፓርቲያችን የውስጥ ጉዳይ መግባቱ በሕግ እንዲሁም ፓርቲዎች በተፈራረሙት የሥነ ምግባር መመርያ መሠረት ጥፋት ነው፤›› ብለው፣ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ደብዳቤ መጻፋቸውን፣ የኦሮሚያና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላቶቻቸውን በማፈናቸውና ጽሕፈት ቤታቸውን በመያዛቸው ምክንያት ለምርጫ ቦርድ ሪፖርት እንዳደረጉ ይናገራሉ፡፡

በአቶ አራርሶ የሚመራው የኦነግ ቡድን ግን ባወጣው መግለጫ ሊቀመንበሩ ብቻቸውን ፓርቲውን መቆጣጠር ስለፈለጉ የተፈጠረ ችግር ነው ይላል፡፡ በመግለጫው፣ ‹‹የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ድርጅታዊ መርህ የአንድ ግለሰብ አመራር ሳይሆን የጋራ አመራር (Collective Leadership) ላይ የተመሠረተ መሆኑ በድርጅቱ ሕገ ደንብ ወስጥ ተድንግጓል። ማንም ይሁን ማን ግለሰብ ለድርጅቱ ይታዘዛል፣ አናሳ ድምፅ ለብዙኃን ድምፅ ይገዛል፣ በብዙኃን የተወሰነ ውሳኔ በሁሉም ዘንድ ተግባራዊ ይሆናል፣ የሕግ የበላይነት መከበሩ የግድ ነው። አቶ ዳውድ ኢብሳ የጋራ አመራር ከመስጠት ይልቅ የራሳቸውን ፍላጎትና የሥልጣን ጥማት ለማርካት ሲሉ ለ21 ዓመታት የኦሮሞ ነፃነት ግንባርን አቀጨጩት፤›› በማለትም ይከሳል፡፡

አቶ በቴ በበኩላቸው አሁንም ቢሆን ያለው ኦነግ በአቶ ዳውድ የሚመራው ነው በማለት፣ እነሱም ሰላማዊ ትግል የማድረግ ፍላጎት ብቻ እንጂ አገር ጥለው የመሄድ ፍላጎት እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡ ‹‹ከጦሩ ጋርም የተለየ ግንኙነት የለንም፤›› ሲሉ ያስተባብላሉ፡፡ ነገር ግን ብልፅግና ፓርቲ ኦነግን ለማዳከም ሲል ፋይናንስ አቅርቦ እየሠራ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ እንዳላቸው፣ ይኼንንም ለምርጫ ቦርድ ማቅረባቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ይሁንና አቶ ቶሌራ አንድ ገዥ ፓርቲ ተቃዋሚውን ለማጠናከር ሲል ገንዘብ መድቦ ይሠራል ብለው እንደማያምኑ በመናገር፣ እነሱ አሁን እየሠሩ ያሉት አመራሩ የተጠናከረና የዳበረ ብቃት ያለው እንዲሆን፣ ወደ አገር ቤት ሲገቡ ሰላማዊ ትግል ለማድረግ አስበው ስለሆነ፣ አስፈላጊ በሆነ ነገር ሁሉ ከመንግሥት ጋር ተባብረው እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህን ነገሮች ከብልፅግና ጋር ማገናኘት በፓርቲው ውስጥ ለ23 ዓመታት በተከሰቱ ሦስት ክፍፍሎች ወቅት የነበረውን ፍረጃ የሚያስቀጥልና የተለመደ የስም ማጥፋት ተግባር ነው በማለት ያጣጥሉታል፡፡

በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ቡድን በፓርቲው ድረ ገጽና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ቁጥጥር ያለው ሲሆን፣ አቶ በቴ ሌላኛው ቡድን አዲስ አበባ ያለውን ቢሮ ከመያዝ የዘለለ ሌላ ቁጥጥር እንደሌለውና የፓርቲው ማኅተምም እነሱ ዘንድ እንዳለ ይናገራሉ፡፡ አሁንም ቢሆን ከየትኛውም የፖለቲካ ኃይል ጋር የመነጋገር ፈቃደኝነት እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ በቴ፣ ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ሕጋዊ ዕውቅና ያለው መንግሥት ስለማይኖር ያንን እንዴት መወጣት አለብን የሚለው ላይ ሁሉን አቀፍ ስምምነት ሊኖር ይገባል ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ፡፡

ፓርቲው ይኼንን አስመልክቶ እሑድ መስከረም 3 ቀን 2013 ዓ.ም. በእንግሊዝኛ ቋንቋ በድረ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ የወቅቱ የፖለቲካ፣ የሕገ መንግሥት፣ የፀጥታና የደኅንነት ቀውስ ከብልፅግና ፓርቲ አቅም በላይ ስለሆነ አገሪቱ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ሳትገባ የአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ እንዲሁም አገሪቱ ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ለመፍትሔ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -