Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በደፈናው የጥበቃና ሠራተኛ አሠሪዎችን መውቀስ ተገቢ አይደለም›› አቶ አቤል ወርቁ፣ ዓባይ የግል ጥበቃና የሰው ኃይል አቅርቦት ድርጅቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን እንደተጀመረ የሚነገረው የግል ጥበቃና ሠራተኛን በድርጅቶች አማካይነት የማግኘት ሥራ በስፋት የተዋወቀውና የሥራ ዕድል እየፈጠረ የመጣው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ነው፡፡ የግል ጥበቃና ሠራተኛ አቅራቢ ድርጅቶች ለግለሰብ፣ ለግልና ለመንግሥት ተቋማት የፅዳት ሠራተኞችንና ጥበቃዎችን በመቅጠር የሥራ ዕድል እየፈጠሩ ቢሆንም፣ በሠራተኛና በቀጣሪ መካከል አለመግባባቶች እንዳሉ ይነገራል፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሙላት በኢትዮጵያ ተመዝግበው ከሚገኙት ከ283 የግል ጥበቃና ሠራተኛ አቅራቢ ድርጅቶች መካከል 30 ያህል በቅርቡ በተቋቋመው ዓባይ የግል ጥበቃና የሰው ኃይል አቅርቦት ድርጅቶች ማኅበር ጥላ ሥር ሆነው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ አቶ አቤል ወርቁ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ሔለን ተስፋዬ ስለማኅበሩ አነጋግራቸዋለች፡፡  

ሪፖርተር፡– በግል ጥበቃና ሠራተኛ አቅራቢ ድርጅቶች ውስጥ የአሠራር ክፍተት አለ ይባላል፡፡ ይህንን ቢያብራሩልን?

አቶ አቤል፡- ዓባይ የግል ጥበቃና የሰው ኃይል አቅርቦት ድርጅቶች ማኅበር የተቋቋመው ዓምና ነው፡፡ ዓላማው በኅብረተሰቡና በመንግሥት የሚነሱ ብዥታዎችን ማጥራት የሥራ ዕድልን በመፍጠርና ደኅንነትን በማስጠበቅ ለአገር ዕድገትና ኢንቨስትመንት ያለውን ጥቅም ማንፀባረቅ ነው፡፡ ማኅበራችን በዘርፉ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ ከመፍጠር በበለጠ መንግሥት በዘርፉ ያለውን የሰው ኃይል በማየት ለአገር ያለውን ፋይዳ እንዲመለከትና ዘርፉን እንዲያግዝ እየሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡-በኅብረተሰቡና በመንግሥት ያለው ብዥታ ምንድነው?

አቶ አቤል፡- ኤጀንሲ (ደላላ) እና አገልግሎት አቅራቢው የተለያዩ አሠራር ዘዴዎችን የሚከተሉ ናቸው፡፡ ደላላ ማለት ሠራተኛና አሠሪ አገናኝቶ ገንዘብ ተቀብሎ የሚወጣ አካል ነው፡፡ ነገር ግን አገልግሎት አቅራቢ ስንል ከቅጥር ጀምሮ የራሱ መመርያና ደንብ ያለው ለሠራተኞች ዓመት ፍቃድ፣ ጥቅማጥቅሞችና ጡረታን ጨምሮ የደመወዝ ክፍያ በአገልግሎት አቅራቢው ድርጅት በኩል የሚያልፍበት ነው፡፡ ሠራተኛ በሥራ ላይ አደጋ ቢደርስበትና ሌሎችንም በኃላፊነቶች የሚወጣ ነው፡፡ ነገር ግን በመንግሥትና በአንዳንድ ሰዎች የሚንፀባረቀው ያልተገባ አረዳድ ተገቢነት የሌለው በመሆኑ ያለውን የመረጃ ክፍተት ለመሙላት እየጣርን ነው፡፡

ሪፖርተር፡አገልግሎት አቅራቢዎችና እናንተ ኤጀንሲ ወይም ደላላ በምትሉት መካከል ያለውን ልዩነት ግልጽ ቢያደርጉልን?

አቶ አቤል፡- ኤጀንሲ (ደላላ) በንግድ ሕግ የሚመራ ዕውቅና ያለው ሁለት ግለሰቦችን በማስማማት ክፍያውን ከግለሰብ ወይም ከድርጅት የሚያገኝ ነው፡፡ አገልግሎት አቅራቢዎች ደግሞ ሠራተኞችን ከማሠልጠን ጀምሮ ደኅንነት በመጠበቅ፣ ጡረታ በመክፈልና በአቅራቢዎች በመወከል ጥበቃ ወይም ፅዳት ላይ የሚያሰማራ ተቋም ነው፡፡ ሠራተኞች ሥራ ላይ ችግር ቢያጋጥማቸው፣ ሠራተኞች ያልተገባ ነገር ቢያደርጉና ሌሎችም ችግሮች ቢያጋጥሙ ድርጅቱ ኃላፊነቱን ወስዶ ችግሩን ለመፍታት ይጥራል፡፡ ኤጀንሲ ማለት በመሀል አሠሪና ሠራተኛ አገናኝቶ ከዚያ በኋላ ያለው ነገር ውስጥ የማይገባ አካል ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- በማኅበሩ በታቀፉት ውስጥ ምን ያህል ሠራተኞች አሉ? የማኅበሩ አባል የሚኮነው እንዴት ነው?

አቶ አቤል፡- የፌዴራል ፖሊስ መረጃ እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ፈቃድ የወሰዱ ድርጅቶች 283 ናቸው፡፡ በማኅበራችን የገቡት ደግሞ 33 ድርጅቶች ሲሆኑ፣ በእነዚህ 78 ሺሕ ሠራተኞች አሉ፡፡ አመልክተው ተቀባይነት ያላገኙም ድርጅቶች ይገኛሉ፡፡ አንድ ድርጅት ወደ ማኅበሩ ከመግባቱ በፊት በየዓመቱ ግብር የከፈለበት የቢሮው አድራሻ፣ ሕጋዊ ፈቃድና ሌሎችንም መስፈርቶች ማሟላት አለበት፡፡ ወደ ማኅበሩ የገቡ 33ቱ ድርጅቶች በመረጃ ቋት ውስጥ የገቡ በመሆናቸው የሚያደርጉትን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ የ24 ሰዓት ሪፖርት እንዲያደርጉ የማኅበሩ መመርያ ያዛል፡፡

ሪፖርተርማኅበሩ የድርጅቶችን እንቅስቃሴ ከመቆጣጠር በተጨማሪ ለሠራተኞች ምን ጥቅማጥቅም ያስጠብቃል?

አቶ አቤል፡– ማኅበሩ ከድርጅቶቹ በላይ ለሠራተኞች ጎን የቆመ ነው፡፡ ሠራተኞቹ ባግባቡ ካልተያዙ ውጤታማ መሆን አይቻልም፡፡ ስለዚህ ከድርጅቶቹ ይልቅ ማኅበሩ ለሠራተኞች የሚደግፍ ነው፡፡ በዚህም ለምሳሌ ኢንሹራንስ የሌለው ድርጅት በማኅበሩ አይካተትም፡፡ በሥራ ላይ ሠራተኞች አደጋ ቢደርስባቸው ኃላፊነት የሚወስድ ድርጅት መሆን ይጠበቅበታል፡፡ የሙያ ደኅንነት፣ የደንብ ልብስ፣ በሥራ ላይ አደጋ ቢደርስ የሚከፈለው ገንዘብ፣ የዓመት ፈቃድ፣ ጡረታ፣ ለመንግሥት የሚገባውን ግብር የሚከፍል መሆኑ ተጠንቶ ወደ ማኅበሩ የሚገባ በመሆኑ በዚሁ የሠራተኞችን ጥቅማጥቅም ያስጠብቃል፡፡

ሪፖርተር፡ድርጅቶቹን በምን መልኩ ነው የምትቆጣጠሩዋቸው?

አቶ አቤል፡- የምዝገባ ሰርተፍኬት፣ ቲን ነምበር፣ የቫት ሰርተፊኬት፣ የጡረታ ማረጋገጫ፣ የፌዴራል ፖሊስ የብቃት ማረጋገጫ፣ ያለፈው ዓመት ኦዲት ሪፖርትና ለማኅበሩ የቢሮ አድራሻቸውን ማሳየትና ሌሎችን ያሟሉ ድርድቶች በማኅበሩ ተካተዋል፡፡ በዚህ ብቻ ሳይሆን የ24 ሰዓት ቅኝታቸውን ለማኅበሩ ማሳወቅ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ ባለቤቱ ወይም ተጠያቂው ግለሰብ በማኅበሩ ቀርቦ የሚገመገም ይሆናል፡፡ በዚህም ቢሮአቸው ቦርሳቸው ውስጥ የሆኑ ድርድቶች እንዳይኖሩ ማኅበሩ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ድርጅቶቹ ማኅበሩን ከመቀላቀላቸው በፊት ቢሮአቸው ድረስ በመሄድ ከተመለከትን በኋላና መመርያውን ካሟሉ ማኅበሩን ይቀላቀላሉ፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ወደ ማኅበሩ ቋት ከገቡ በኋላ ከፖሊስ ጋር በመሆን የዕለት ተዕለት ሪፖርት እንዲደርሳቸው የሚደረግበት ሥርዓት እየተረጋም ይገኛል፡፡ ባለቤቶችም ከወንጀል ነፃ መሆን አለባቸው፡፡ ውሎ አዳራቸውን ለፌዴራል ፖሊስ ሪፖርት ማድረግ አለባቸው፡፡ በዚህም ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመሆን በ24 ሰዓት ሪፖርት እንዲያደርሱ በምክክር ላይ እንገኛለን፡፡ በጥበቃው ዘርፍ በአገሪቱ የተፈጠሩ ችግሮች በቀጥታ ለፌዴራል ፖሊስ እንዲደርስ አብረን ለመሥራት መተግበሪያ እየተሠራ ይገኛል፡፡ አዲስ የተቀጠሩና የለቀቁ ሠራተኞች በየጊዜው ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በወሩም የጡረታ ተቆራጭ ሰነድ ለማኅበሩ ስለሚያቀርቡ በዚህ መልኩ ድርጅቶቹ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ያለባቸው ችግሮች ምንድናቸው?

አቶ አቤል፡- አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች ተናበው እየሠሩ አልነበረም፡፡ ዘርፉ እጅግ ሰፊ በመሆኑ በመንግሥት ቢታገዝ ትልቅ የሰው ኃይል የሚንቀሳቀስበት ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- በአገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች የሚሰማሩ ሠራተኞች ለየትኞቹ ተቋማት ይሠራሉ?

አቶ አቤል፡- ከኤምባሲዎች ጀምሮ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ እንዲሁም በሕንፃዎች፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በባንኮችና ሌሎች የግልና የመንግሥት ተቋማት በጥበቃና በፅዳት ይሰማራሉ፡፡ የጥበቃ ሠራተኞች ካሉበት እስከ 50 ሜትር ድረስ ይጠብቃሉ፡፡ በመገናኛ ብዙኃን የተዛባ መረጃ ሲቀርብ ስናይ በዚህ ውስጥ የሚሠሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን ያላገናዘበ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ የንግድ ቦታዎችና ኢንቨስትመንት እንዲሁም ሌሎች ተቋማት የሚጠበቁት በእነዚሁ ድርጅቶች አማካይነት በመሆኑ ሊደግፉ፣ ያሉባቸው ችግሮች እንዲፈቱ በመንግሥት ሊታገዙ ይገባል፡፡ ያለውን የመረጃ ክፍተት ለመሙላት የመንግሥት አካላት ድርጅቶቹ ቢሮ ድረስ በመሄድ ቢገመግሙና  ያለውን ከፍተትና መልካምነት ለሚዲያ ቢናገሩ ተገቢ ነው፡፡ ፍተሻና ጥናት ሳይደረግ በደፈናው ሁሉንም የጥበቃና ሠራተኛ አሠሪዎች መውቀስ ተገቢነት የለውም፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

ጦርነቱና ሒደቱ

ሦስት ሳምንታት ያስቆጠረው ሦስተኛው ዙር የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አሁንም...

ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባን ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት በተደረገው ምርጫ አሸነፉ

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት፣...

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ያለው ሦስተኛው ከግል ባንክ ሆነ

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ከ100 ቢሊዮን...