የኮሮና ቫይረስ መመርመርያ ኪት ማምረቻም ተመርቋል
በዓለም የምግብ ፕሮግራም ድጋፍና በጤና ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተገነባው የአዲስ አበባ የኮቪድ-19 ፊልድ ሆስፒታል ሥራ ጀመረ፡፡
ሁለት መቶ የኮቪድ-19 ፅኑ ሕሙማንን ለማስተናገድ የሚችለው ሆስፒታል በቦሌ ቡልቡላ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን በይፋ ሥራ ያስጀመሩትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
ሆስፒታሉ በተለይም በኮሮና በሽታ ተይዘው የጸና የሕመም ምልክት ለሚያሳዩ ሕሙማን የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን የሕክምና መሣሪያዎችም ተሟልቶለታል፡፡
በተያያዘ ዜና በኢትዮጵያ የመጀመርያ የሆነው የኮረና ቫይረስ የላቦራቶሪ መመርመርያ ኪት ማምረቻ ፋብሪካ ተመርቋል::
በኢትዮጵያና በቻይና ቢጂአይ ሄልዝ ትብብር የተቋቋመውን ፋብሪካ የመረቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ የፋብሪካው መገንባት በአፍሪካ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የደረሰውን የኢትዮጵያ የመመርመር አቅም በማሳደግ የተሻለ የመከላከል ሥራ ለመሥራት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካው ለነዋሪዎችና በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ለሚያልፉ መንገደኞች በክፍያ የላብራቶሪ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ለውጪ አገሮች በሚደረገው ሽያጭም የአፍሪካ አገሮች ቅድሚያ የሚያገኙ ይሆናል።
በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የተገነባው ፋብሪካ በዓመት አሥር ሚሊዮን ኪቶችን እንደሚያመርትና የኮቪድ-19 ሥርጭት ከተገታ በኋላ፣ የሳንባ ነቀርሳ እንዲሁም ሌሎች የሪል ታይም (አርቲ) ፒሲአር መመርመርያ ኪቶችን ጨምሮ ሌሎች ኒዮክሊክ አሲድን (ዲኤንኤ እና አርኤንኤ) መለያ ኬሚካሎችን ወደ ማምረት የሚሸጋገር ይሆናል።