ከ0 – 4 ዓመት ያሉ ከ640 በላይ ሕፃናት
ከ5 – 14 ዓመት ያሉ ከ780 በላይ ልጆች ተይዘዋል
ለዓለም ፈታኝ የሆነው የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ከመንፈቅ ወዲህ በቫይረሱ የሚያዙና ሕይወታቸውን የሚያጡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየጨመረ ይገኛል፡፡ እስከ መስከረም 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ 64,786 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን የሟቾች ቁጥር 1022 ሆኗል፡፡
ከእነዚህም ወስጥ እስከ መስከረም 3 ቀን ድረስ ባለው መረጃ 644 የሚሆኑት ከ0 እስከ 4 ዓመት ያሉ ሕፃናት ሲሆኑ፣ 788 ያህሉ ደግሞ ከአምስት እስከ 14 ዓመት ያሉ ልጆች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ እንዳስገነዘበው፣ ሕፃናትና ልጆች በኮሮና ቫይረስ ተይዘው እንደ አዋቂዎች ምንም የሕመም ስሜቶች ወይም ቀላል የሕመም ስሜቶች ሊያጋጥማቸው ቢችልም ወደ ፅኑ ሕሙማን ክፍል የመግባታቸው ዕድል ግን ዝቅ ያለ ነው፡፡
በብሔራዊ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል የኮቪድ-19 የሕክምና አገልግሎት ተቋማት ዝግጅትና የቤት ውስጥ ራስን ለይቶ ሕክምና (ውሸባ) እንክብካቤ ክፍል ኃላፊ አቶ ሔኖክ ኃይሉ አገላለጽ፣ የኮሮና ቫይረስ ከጨቅላ ሕፃናት ጀምሮ የሚይዝ በሽታ ሲሆን ሕፃናቱ ምንም ዓይነት የሕመም ምልክት ላያሳዩ ወይም ቀለል ያለ የሕመም ምልክቶች ሊኖራቸው ቢችልም ወደ ሌላው የማኅበረሰብ ክፍል ግን ቫይረሱን ያስተላልፋሉ፡፡
ሕፃናት ልጆች በሽታን የመከላከል አቅማቸውን ለማጎልበት ቤተሰቦች አቅማቸው በሚችለው መጠን ለልጆቻቸው የተመጣጠነ ምግብ ቢመግቡ ተመራጭ ነው፡፡ በሌላ መልኩ ተጓዳኝ ሕመም ላለባቸው ልጆች ልዩ እንክብካቤ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፣ ልጆች በአሁኑ ወቅት የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመቀነስ ወደ ውጪ ወጥተው መጫወት ስለማይችሉና ወደ ትምህርት ቤት ስለማይሄዱ፣ ከጓደኞቻቸው ጋር ስለማይገናኙም ጭንቀት፣ ድብርትና የተለያዩ የባህሪ ለውጥ ሊያሳዩ ይችላል፡፡ ስለሆነም በቤት ውስጥ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ቀለል ያለ ጤንነታቸውን እንዲሁም በአጠቃላይ የሕፃናቱን ሁኔታ ያገናዘበ የቤት ውስጥ ሥራዎችን በመሥራት፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ፣ የተመጣጠኑ ምግቦችን በመመገብ ይኼን ጊዜ ማሳለፍ አለባቸው፡፡
የተለየ የሕመም ስሜት እንደ ሳል ትኩሳት፣ የአየር ማጠር፣ ቶሎ ቶሎ የመተንፈስና ሌሎች የበሽታ ምልክቶች ከታየባቸው ወደ ጤና ተቋማት መውሰድና አስፈላጊውን የሕክምና ዕርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
ልብ ይበሉ!
የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል በምናደርገው ጥንቃቄ ለልጆቻችን የሚያስፈልጉ የሕክምና ክትትሎችን መዘንጋት ተጨማሪ የጤና እክል እንደሚያስከትሉ አንዘንጋ፡፡ ስለሆነም ሕፃናት በቂ የቀጥታ የፀሐይ ብርሃን እንዲያገኙ ማድረግ፣ የእናት ጡት ወተት እስከ ሁለት ዓመት ድረስ (ከ6 ወር በኋላ ከተጨማሪ ምግብ ጋር) መመገብ እንዲሁም የክትባት ጊዜያቸውን በጠበቀ መልኩና በተለያየ ጊዜ ለተላላፊ በሽታዎች ማስከተብ የሚገባውን ክትባት እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡
‹‹በዚህ ወቅት ግዴታ ሆኖ ሕፃናት ልጆቻችንን ይዘን ከቤት ከወጣን ከሁለት ዓመት በላይ ለሆኑ ሕፃናት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያወልቁ፣ የእጃቸውን ንፅህና እየጠበቅን ርቀታቸውን በመጠበቅ ለኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ምክንያት ባለመሆን ራሳችንን እና ልጆቻችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ፡፡››