Wednesday, June 7, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት በሰላምና በመከባበር አብሮ መኖር ነው!

በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች አዲሱን ዓመት አስመልክቶ የመልካም ምኞት መግለጫቸውን ያስተላለፉ ወገኖች፣ በተደጋጋሚ አፅንኦት ሰጥተው ያሳሰቡት ጉዳይ ቢኖር ያለፈው ዓመት ችግሮች ወደ አዲሱ ዓመት እንዳይተላለፉ ነው፡፡ ያለፈውን ዓመት ክብደትና ከመጠን ያለፈ ሥቃይ በማስታወስ፣ አዲሱ ዓመት የሰላምና የመግባባት እንዲሆን መመኘት ለአገር ከሚያስቡ ዜጎች የሚጠበቅ መልካም ነገር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከምንጊዜውም በላይ ለሰላምና ለመግባባት ዕድል መስጠት አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከሚከፋፍሉና እርስ በርስ ከሚያፋጁ ድርጊቶች መቆጠብ አለባቸው፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ በተዘረጋው የኢትዮጵያ መልክዓ ምድር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ በእኩልነትና በክብር የሚኖሩበት ምዕራፍ ሊጀመር ይገባል፡፡ እጅግ የሚያስመርር ድህነት ውስጥ የሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በርስ በመጋደል የሚያተርፈው የለም፡፡ ይልቁንም የዕለት ምግቡንና የዓመት ልብሱን ከማግኘት በላይ ወደ ተሻለ ሕይወት የሚያሸጋግረው፣ ሰላምና ነፃነት የበዛበት ሕይወት የሚያጎናፅፈው፣ እንዲሁም በሰብዓዊ ፍጡርነቱ ተከብሮና ታፍሮ የሚኖርበት ሥርዓት ለማደላደል በአንድነት መሥራት የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ፖለቲከኞችም ሆኑ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ በሙሉ፣ ኢትዮጵያን ከግጭትና ከውድመት ተላቃ ለዜጎቿ የተመቸች አገር ለማድረግ ጥረት ያድርጉ፡፡

የመንግሥት ሥልጣን የያዘው ብልፅግና ፓርቲም ሆነ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች የዓላማቸው መነሻና መድረሻ አገርና ሕዝብ ይሁኑ፡፡ በአገርና በሕዝብ ስም በመነገድ ለማጭበርበር መሞከር ትርፉ ጥፋት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የተገኙ መልካም ዕድሎች በሙሉ እንዳይሆኑ ሆነው የቀሩት፣ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ከራሳቸው በፊት አገርና ሕዝብ ለማስቀደም ፈቃደኛ ስላልሆኑ ነው፡፡ አሁንም ካለፉት ስህተቶች በመማር ማስተካከል የሚቻልበት ዕድል አለ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሁሉም የተመቻቸ ምኅዳር እንዲፈጠር የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ፈቃደኛ መሆን አለባቸው፡፡ አንዱ ሰጪ ሌላው ተቀባይ የሆነበት ሳይሆን ሁሉንም ወገን በእኩልነት የሚያሳትፍ ምኅዳር ዕውን ለማድረግ፣ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ውይይትና ድርድር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቅን ልቦና፣ አስተዋይነትና አርቆ አሳቢነት የግድ ይሆናል፡፡ በክፋትና በሴረኝነት ላይ የተመሠረተ ዓላማ ያነገባችሁ በሙሉ ከጥፋትና ከውድመት በስተቀር የተሻለ ነገር ስለማታመጡ፣ ይህንን ለዓመታት ተሞክሮ አልሠራ ያለ አስከፊ ነገር አስወግዱ፡፡ በሕዝብ ድምፅ ሥልጣን መያዝን የመሰለ የሚያኮራ ተግባር እያለ፣ በአጉል ድራማ እየተወናችሁ መሳቂያ አትሁኑ፡፡ ሕዝብንና ተፎካካሪን መናቅ የዴሞክራቶች መገለጫ አይደለም፡፡  ሲተማመኑበት የነበረ ጉልበት ሲከዳ አንገት ያስደፋልና፡፡

ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶቻቸውን በአግባቡ እያስተናገዱ በአንድነት አገራቸውን መገንባት ይችላሉ፡፡ የታሪክ ጠባሳዎቻቸውን እያከኩ በማድማት እርስ በርስ ለመተናነቅ ከማድባት ይልቅ፣ ያለፉትን ስህተቶች በጋራ እያረሙና እያስተካከሉ በወንድማማችነትና በእህትማማችነት አብረው መኖር አይሳናቸውም፡፡ ኢትዮጵያዊያን በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በቋንቋና በሌሎች የየራሳቸው የሆኑ መገለጫዎች ቢኖሩዋቸውም፣ ሁሉንም በእኩልነት የምታስተናግድ ኅብረ ብሔራዊት አገር ለመገንባት አያቅታቸውም፡፡ ለዘመናት ብሔርና እምነት ሳይገድባቸው ተጋብተውና ተዋልደው ታላላቅ ማኅበራዊ እሴቶችን ያፈሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ‹ከራስ በላይ ንፋስ› በሚሉ የግጭት ነጋዴዎች አይበለጡም፡፡ በስሜት የሚነዱ አፍለኞችን በማነሳሳት ኢትዮጵያዊያንን እርስ በርስ ለማጋደልና አገር ለማፍረስ የሚፍጨረጨሩ ቢኖሩም፣ አርቀው በሚያስቡና በሰከኑ ኢትዮጵያዊያን ጥረት ዓላማቸው እየከሸፈ እዚህ ተደርሷል፡፡ ነገር ግን አሁን ከፍተኛ የሆነ ርብርብ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች በእኩልነት፣ በነፃነትና በፍትሐዊነት የምታስተናግዳቸው አገር እንድትገነባ አርዓያነት ያለው ተግባር ማከናወን ያስፈልጋል፡፡ የአንድ ወገን የበላይነት የተጫጫናቸውን አጓጉልና ኋላቀር ትርክቶች በማስወገድ፣ የወደፊቱን የጋራ ብሩህ ሕይወት አመላካች ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በታሪክ አንፀባራቂ የሚባሉ ክንውኖችን ብቻ ሳይሆን አስከፊ የሚባሉትንም በጋራ በመቀበል፣ የወደፊቷ ኢትዮጵያን በጋራ ሊገነቡ የሚያስችሉ የመሠረት ድንጋዮችን ማኖር ተገቢ ነው፡፡

ፖለቲከኞችና ደጋፊዎቻቸውም ዘመኑ የሚመጥን አስተሳሰብ መላበስ ይኖርባቸዋል፡፡ ዓላማቸውን ለማስፈጸምም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገዶችን መከተል አለባቸው፡፡ ውስጣቸው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሳይሆን ከሌሎች ጋር መግባባት ስለማይችሉ፣ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራቸው ከውስጥ ወደ ውጭ ብቻ ሳይሆን ከውጭ ወደ ውስጥም ተመልካች መሆን ይኖርበታል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ለቁጥር የሚያታክቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመሥርተው የፈረሱት፣ ከውጫዊ ተፅዕኖ ባልተናነሰ በራሳቸው ውስጣዊ ችግር እንደሆነ የማይካድ ነው፡፡ ጊዜያዊ ግንባርና ትብብር ፈጥረው በግለሰቦች መታበይ ብዙዎች እንዳይሆኑ ሆነው አልፈዋል፡፡ በገዥው ፓርቲ ውስጥ ለዘመናት ሲደሰኮርለት የነበረው የዓላማና የተግባር አንድነት እንደ እንቧይ ካብ የተናደው፣ ውስጣዊ ሰላምና ዴሞክራሲ በመጥፋቱ እንደነበር የፈረሰው ኢሕአዴግ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ተተብትቦ የግለሰቦች መፈንጫ የነበረው ኢሕአዴግ ወራሽ ብልፅግና፣ ከዚህ ታሪክ ካልተማረ ስህተት መድገሙ አያጠራጥርም፡፡ ብልፅግና የሚመራው መንግሥት ውስጥ በግልጽ የሚታዩ ከቀድሞ የተወረሱ አሳሳቢ ጉዳዮች ስላሉ፣ እንደ ቀድሞው ሁሉ አሁንም በሕግ አምላክ ማለት ተገቢ ነው፡፡ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል አሁንም ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያሉት ጭምር፣ ከስህተታቸው ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ አሉ፡፡ የሰላምን መንገድ መዝጋት አያዋጣም፡፡

በአዲሱ ዓመት መጀመርያ ላይ ተሁኖ ያለፈውን የሰቆቃ ዓመት አሳዛኝ ድርጊቶች ለመድገም የሚያሴሩ ካሉ ቢታቀቡ ይመረጣል፡፡  ንፁኃን ያለ ኃጢያታቸው ሲገደሉና ጎጆአቸው ላያቸው ላይ በእሳት ሲወድም፣ ላባቸውን አንጠፍጥፈው ያፈሩት ሀብት ዶግ አመድ ሲሆን፣ ሰላምና መረጋጋት ጠፍቶ አየሩ ቃጠሎ ሲያውድና ከብሩህ ተስፋ ይልቅ ድቅድቅ ጨለማ ሲያጠላ አገር ትጎዳለች፡፡ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በወኪሎቻቸው አማካይነት በድፍረት እየተናገሩ እንዳሉት፣ ጠንካራ ኅብረ ብሔራዊት አገር ሳትሆን በጦርነት የወደመች አራትና አምስት ቦታ የተሸነሸነች አገር ትፈጠራለች፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚታዩ አሳዛኝና አስከፊ ድርጊቶች ሳቢያ፣ በድፍረት አለቀላችሁ የሚሉ ታሪካዊ ጠላቶች የኢትዮጵያን ውድቀት ሲሰብኩ ኢትዮጵያዊያን ለምን ማለት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሥልጣን ጥማት ናላቸውን ባዞረው እኩዮች ምክንያት አገር ጠላቶቿ የማሱላት ጉድጓድ ውስጥ እንዳትገባ፣ ራሳቸውን ከአገርና ከሕዝብ ፍላጎት በታች ያስገዙ ጠንካራ ኢትዮጵያዊያን ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ብርቱና ኃላፊነት የሚሰማቸው ኢትዮጵያዊያን ራሳቸውን ከብሽሽቅና ከሴራ ፖለቲካ ያፀዱ ስለሚሆኑ፣ ኢትዮጵያን አራትና አምስት ቦታ የመከፋፈል ፕሮጀክት የያዙ ጠላቶችን ያሳፍራሉ፡፡ የእነሱ ተላላኪ ሆነው አገር ለማፈራረስ የሚቅበዘበዙትን ጭምር ይገታሉ፡፡ ኢትዮጵያ የምትፈልገው እንዲህ ያሉትን ነው፡፡

ልዩነት ሊከበርና ዕውቅና ሊሰጠው የሚገባ የሰብዓዊ ፍጡራን ፀጋ ነው፡፡ ነፃነት ከሚገለጽባቸው ባህርያት መካከል ለልዩነት አክብሮት መስጠት ነው፡፡ የሌሎችን ነፃነት ሳያከብሩ ስለራስ ነፃነት መናገር አይቻልም፡፡ አገር የምትገነባውም በዚህ መርህ መሆን አለበት፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚወተውቱ ሁሉ፣ በልዩነት ውስጥ መኖር እንደሚቻል አርዓያ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ የአኗኗር ዘይቤዎች፣ እምነቶች፣ ወዘተ ስላሉ በመከባበርና በመቻቻል መኖር እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከጥንት ጀምሮ ዘመናትን የተሻገሩባቸው የጋራ ማኅበራዊ እሴቶቻቸው የተገኙት፣ በልዩነት ውስጥ በተፈጠሩ የጋራ መስተጋብሮች አማካይነት መሆኑን ማንም አይስተውም፡፡ እነዚህ መስተጋብሮች ልዩነቶች መኖራቸው እስኪዘነጋ ድረስ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድ ላይ አኑረዋል፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን የበለጠ የማስቀጠል ኃላፊነት አሁን ያለው ትውልድ ነው፡፡ ትውልዱ የጥንት ኢትዮጵያዊያን ያስተላለፉለትን አኩሪ ቅርስ መጠበቅ ካቃተው፣ የመጪው ትውልድና የታሪክ ተወቃሽ ይሆናል፡፡ ከተወቃሽነት ራሱን መከላከል የሚችለው ለሰላም፣ ለሕግ የበላይነትና ለአብሮነት ራሱን ሲያስገዛ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን አገራቸውን ሲያከብሩና ሲያስከብሩ፣ እንደ ታላቁ የዓድዋ ድል በዓለም አደባባይ የተከበረ ስም ያገኛሉ፡፡ ለዚህም ነው ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት በሰላምና በመከባበር አብሮ መኖር ነው የሚባለው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ2,700 በላይ ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ማጣታቸው ተገለጸ

ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ የንብረት ጉዳት ደርሷል በአበበ ፍቅር ባለፉት ዘጠኝ...

የአብዮታዊት ኢትዮጵያ የጦር ሜዳ ጀብዱ ኒሻን ተሸላሚው ሻለቃ ባሻ ዓሊ በርኬ (1943-2015)

ከአርባ ስድስት ዓመታት በፊት፣ ኢትዮጵያ ከወራሪው የሶማሊያ ሠራዊት ጋር...

ኢትዮጵያን የአኅጉራዊ የነፃ የንግድ ቀጣና ተሳታፊ ለማድረግ ድርድር እየተደረገ መሆኑ ተነገረ

ኢትዮጵያ ወደ ትግበራ ለማስገባት ዘግይታበታለች ተብሎ የሚነገረውን የአፍሪካ ነፃ...

ኩዌት ኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞችን ለመቀበል መዘጋጀቷን አስታወቀች

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኦማን ጋር አዲስ ስምምነት ላይ መድረሱን...

ገዳ ቢዝነስ ግሩፕ በቅርቡ ለሚጀምረው እርሻ ከ500 ሔክታር በላይ መሬት አዘጋጅቻለሁ አለ

ገዳ ስታር ቢዝነስ ግሩፕ አክሲዮን ማኅበር በቅርቡ አስጀምራለሁ ላለው...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ባህሪን መግራት ያስፈልጋል!

በሥራ ላይ ያለው አወዛጋቢ ሕገ መንግሥት ከፀደቀበት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወቀሳዎችና ተቃውሞዎች ይቀርቡበታል፡፡ ከተቃውሞዎቹ መካከል በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ ኢትዮጵያዊነትን...

የፖለቲካ ምኅዳሩ መላሸቅ ለአገር ህልውና ጠንቅ እየሆነ ነው!

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ከዕለት ወደ ዕለት የቁልቁለት ጉዞውን አባብሶ እየቀጠለ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነትም ሆነ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚታየው መስተጋብር፣ ውል አልባና...

የመኸር እርሻ ተዛብቶ ቀውስ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ይደረግ!

ክረምቱ እየተቃረበ ነው፡፡ የክረምት መግቢያ ደግሞ ዋናው የመኸር እርሻ የሚጀመርበት ጊዜ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ 70 በመቶ ያህሉን የሰብል ምርት የምታገኘው በመኸር እርሻ...