Wednesday, June 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቴሌኮም ዘርፍን ለግል ባለሀብቶች ክፍት ማድረግና የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ የመሸጥ ሒደት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢሕአዴግ በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም. ራሱን ለማሻሻልና ለተከታታይ ሦስት ዓመታት አገሪቱን የናጠውን ሁከትና ብጥብጥ ለማርገብ፣ እንዲሁም የሕዝብን ጥያቄ ለመመለ የተለያዩ የለውጥ ዕርምጃዎችን እንደሚወስድ አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የአራት ፓርቲዎች ጥምረት የነበረው ኢሕአዴግ በወቅቱ ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች መካከል የበርካቶችን ቀልብ የሳበው ውሳኔ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድንና የኢትዮ ቴሌኮምን ከፊል ድርሻ ጨምሮ ትልልቅ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል ወደ ግል ለማዛወር፣ እንዲሁም ኢኮኖሚውን ክፍት በማድረግ የግል ባለሀብቶችን ማስገባት የሚለው ነበር፡፡

ከሁሉም ዘርፎች በተለየ ሁናቴ በፍጥነት ገበያውን ለግሉ ባለሀብት ክፍት የማድረግና ድርሻውንም ለግል ድርሻ ገዥዎች የማስተላለፍ ሥራ እየተከናወነ የሚገኘው በቴሌኮም ዘርፍ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሁለት የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ በመውሰድ ለሚሠሩ ሁለት የውጭ ድርጅቶች ፈቃድ ለመስጠትና አሁን ብቸኛው የመንግሥት የቴሌኮም መሠረተ ልማት አልሚና አገልግሎት ሰጪ የሆነውን ኢትዮ ቴሌኮም 40 በመቶ ድርሻ፣ በውጭ ምንዛሪ መግዛት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ለመሸጥ በርካታ ዝግጅቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡

የቴሌኮም ዘርፉን ክፍት ማድረግና የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ ለመሸጥ የሚደረጉ ዝግጅቶች በርካታ ተግባራትን ያቀፉ ሲሆን፣ ከሕግ ማዕቀፍ እስከ ዋጋ ግመታ የተዘረጉ ነበሩ፡፡ እነዚህ ሥራዎችን አሳታፊ በሆነ መንገድ ለመተግበር አማካሪ ምክር ቤት የተሰየመ፣ አማካሪ ድርጅቶች የተቀጠሩና ሥራውን የሚመሩ ተቋማት የተዋቀሩ ሲሆን፣ እስካሁን የተሠሩ ሥራዎችን ለማስታወቅና በሒደቱ ላይ ግብዓት ለመሰብሰብ በማለም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሰኞ ጳጉሜን 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ውይይት ተካሂዷል፡፡ በዚህም ውይይት ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሕግ አማካሪና ጠበቃዎች፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ከንግድና ኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ ድርጅቶች፣ ከቴሌኮም ዘርፍ ባለሙያዎች፣ ከፋይናንስ ተቋማት ተወካዮች፣ ከከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ከልማት ድርጅቶች ተወካዮችና ከቴክኖሎጂና መሰል ዘርፎች ማኅበራት ተወካዮች ታድመው ነበር፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ በዘርፉ ለመሥራት ታቅደው የነበሩ ክንውኖችንና አፈጻጸማቸውን ያስረዱት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የቴሌኮም ዘርፉን በአገልግሎት ሰጪነት የሚቀላቀሉ ድርጅቶችን ለማስገባት የጨረታ ሒደት የቴክኒክ ብቃትን ከገንዘብ አቅርቦት ጋር ባጣመረ መንገድ በመስከረም ወር ይፋ እንደሚሆን የገለጹ ሲሆን፣ ውጤቱም በጥር ወይም በየካቲት ወር ተገልጾ ከአሸናፊው ጋር ስምምነት ይደረጋል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከኢትዮ ቴሌኮም በተጨማሪ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የሚሰጡና የመሠረተ ልማት ዝርጋታ የሚያከናውኑ ሁለት ድርጅቶችን ወደ ገበያው ለማስገባት፣ የጨረታ ሒደቱ በመስከረም ወር እንደሚጀመርና በጥርና በየካቲት ወራት 2013 ዓ.ም. ከአሸናፊ ድርጅቶች ጋር ስምምነት እንደሚደረግ ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል፡፡

ይኼ ጨረታ ክፍት ሆኖ የሚቆየው ከ40 እስከ 50 ላሉ ቀናት እንደሆነ የጠቆሙት ኢዮብ (ዶ/ር)፣ ለጨረታ የሚቀርቡ ተጫራቾች የሚያቀርቧቸውን ሰነዶች መገምገምና አሸናፎዎችን መለየት ከዚህ በኋላ የሚከናወን እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡ ይኼንን ሥራ የሚያከናውን አማካሪ ቡድን እንደተቀጠረም አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ኢትዮ ቴሌኮም ለውድድር ዝግጁ እንዲሆን ሥራዎች መከናወናቸውን ያስታወቁት ሚኒስቴር ዴኤታው፣ ድርጅቱ በውስጡ ያሉት የአገልግሎትና የመሠረተ ልማት ግንባታ ዘርፎች ሙሉ ለሙሉ ባይለዩም ተለይተው እየሠሩ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡ ድርጅቱ ከዚህ ባለፈም 40 በመቶ የሚሆነው ድርሻው ለሽያጭ ስለሚቀርብ ለዚህ ብቁ የማድረግ ተግባራትም መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡ ይኼንን ሥራ የሚሠሩ አማካሪ ድርጅቶች ተቀጥረው የቴሌኮም የዋጋ ትመና እንደተከናወነም በመድረኩ አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ ገብተው አገልግሎት ለመስጠት ፍላጎት ያላቸው ድርጅቶች መኖራቸውን ለማወቅም በወጣው የፍላጎት መግለጫ ማስታወቂያ 12 ድርጅቶች ፍላጎታቸውን መግለጻቸው ተወስቷል፡፡ ለገበያ የሚቀርበው የአገልግሎት መስጫ መስመር ስፋት (ስፔክትረም) ምን ያህል እንደሆነና የዚህ ተመንም ምን ያህል እንደሆነ በሚስጥር በተለያዩ አማካሪዎች፣ የግል ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች ተጠንቷል ተብሏል፡፡

የቴሌኮም ዘርፉን የግብይት የዋጋ ተመን የሚሠሩ አማካሪዎች መቀጠራቸው የተነገረ ሲሆን፣ ይኼንን ሥራ የሠሩት አይኤፍሲ፣ ሮላንድ ባርገር፣ ኧርነስት ኤንድ ያንግ፣ ጎንግ፣ ኮሊጎ ኮንሰልቲንግና ጆንስ ዴይ የተባሉ ተቋማት እንደሆኑም ተዘርዝሯል፡፡

የቴሌኮም ዘርፉን ክፍት ማድረግና የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ ለባለሀብቶች መሸጥን በቅደም ተከተል ለማስኬድ ተደጋጋሚ ውይይቶችና ጥናቶች መደረጋቸውን ያስታወቁት ኢዮብ (ዶ/ር)፣ ሁለቱንም አብሮ ማስኬድ እንደሚቻል ከግንዛቤ መግባቱንም አስገንዝበዋል፡፡ ይሁንና የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ መሸጥ ለጊዜው የማዘግየት ፍላጎት በመንግሥት በኩል እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በመድረኩ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮምን በመሠረተ ልማት ዘርፍና በአገልግሎት ዘርፍ በሁለት የተለያዩና ራሳቸውን የቻለ የሕግ ማንነት ያላቸው ተቋማት አድርጎ ለመክፈልም ታስቦ እንደነበረ የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታው የገለጹ ሲሆን፣ በስተመጨረሻም በመንግሥት የተመረጠው ተቋሙ እንዳለ ሆኖ በውስጡ ሁለቱን ሥራዎች በዘርፍ ሙሉ ለሙሉ መለየት ማስቻል ሆኖ እንደተተገበረም ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ አስተያየት ካቀረቡ ተሳታፊዎች መካከል ከግል የአይሲቲ ኩባንያዎች ማኅበር የመጡት ይልቃል አባተ፣ ገበያውን ለግል ባለሀብቶች ክፍት የማድረግ ሥራ አገር ውስጥ ያሉ አነስተኛ ድርጅቶችንም አብሮ ይዞ የሚሄድና የሚሳድጋቸው እንዲሆን ቢታሰብበት የሚል ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከአሁን ቀደም በአገሪቱ ውስጥ ፖሊሲ ሲዘጋጅለት የነበረው የዲጂታል ሊትሬሲ ቻርተር ከምን እንደደረሰና ከዚህ ጋር እንዴት መጣመር እንደሚችል ጠይቀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ባህር ባይኖራትም የፋይበር መስመር ማዕከል በማድረግ ወደ ማዕከላዊ አፍሪካ አገሮች ለማዳረስ አብሮ ቢታሰብ ያሉ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ ፈቃድ አግኝተው የሚመጡም ሆኑ ከኢትዮ ቴሌኮም ድርሻ የሚገዙ የውጭ የቴሌኮም ድርጅቶች ሀብታቸውን በውጭ ምንዛሪ ለመውሰድ ሲፈልጉ እንዴት የሚስተናገዱበት አሠራር ታስቧል ወይ ብለዋል፡፡

የሕግ ባለሙያውና ጠበቃው እንዲሁም የምሕረተአብ ልዑልና አሶሼትስ የሕግ አማካሪና ወኪል ድርጅት ባለቤት አቶ ምሕረተአብ ልዑል፣ ወደ ገበያው ለመግባት የሚያስቡም ሆኑ በአገር ውስጥ ስለዚህ ሥራ ለማወቅ የሚፈልጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች መረጃ እንደ ልብ የሚያገኙበት ሥርዓት ባለበጀቱ ክፍተት እንደሚፈጥር ጠቁመው፣ ለዚህ የሚያግዝ የመረጃ ቋት ቢኖርና ሰዎች መረጃዎቹን ማግኘት እንዲችሉ ቢደረግ በማለት ጠይቀዋል፡፡ መረጃ መሰጠት እንዳለበትና የገበያው ተዋንያን መረጃ አግኝተው መሳተፍ እንዲችሉ ማድረግ እንሚገባ በማስገንዘብም፣ ፍትሐዊ ውድድር እንዲኖርና የውጭ ድርጅቶችም ላይ መተማመን እንዲፈጠር ይኼንን ማድረግ ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡ ለምሳሌ ኢትዮ ቴሌኮምን የተመለከቱ መረጃዎች እጅግ አነስተኛ እንደሆኑና ስላሉት ብቃቶችና ንብረቶች እምብዛም እንደማይታወቅ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ከሠሩ የትራንዚት፣ የካርጎና የጉምሩክ ክሊራንስ አገልግሎ ሰጪ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የጊዜ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤት ጊዜሽ ወርቅ ተሰማ በመድረኩ በሰጡት አስተያየት፣ ከሚሸጠው የኢትዮ ቴሌኮም ድርሻ ወስጥ ከአገር ውስጥ መግዛት ለሚፈልጉ እንዲሸጥ የተመደበው አምስት በመቶ ድርሻ አያንስም ወይ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮ ቴሌኮምን ለግል ባለሀብቶች ከመሸጥ ይልቅ አስተዳደሩን (ማኔጅመንት) ለውጭ ድርጅቶች ሰጥቶ ማሻሻል አይቻልም ወይ ሲሉም አክለዋል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ማዛወርን እንዲያማክር የተዋቀረው የአማካሪ ቡድን አባልና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ፣ በመንግሥት ውሳኔና ገበያውን ለግል ባለሀብቶች ክፍት ማድረግ ላይ ፓርቲያቸው ልዩነት እንደሌለው፣ ነገር ግን የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ ለግል መሸጥን እንደማይቀበሉ በመናገር፣ በመንግሥት አሠራር ላይ ግን የግልጽነት ችግር በመኖሩና መረጃዎች በየጊዜው እየወጡ ስላልሆነ የሕዝብ አመኔታ ችግር እንደሚያስከትል አሳስበዋል፡፡

‹‹እኛ ገበያውን ለግል ባለሀብቶች ክፍት ማድረግ ላይ ልዩነት የለንም፡፡ ነገር ግን ልዩነታችን ኢትዮ ቴሌኮምን መሸጥ ላይ ነው፤›› በማለት ተናግረው፣ ‹‹ይኼ በተለይ መንግሥት ካለበት ሌላ ተጨማሪና አጣዳፊ ሥራዎች አንፃር ሲታይ ጥድፊያ ይታያል፡፡ ስለዚህ ምርጫው እስከሚደረግና እናንተም የሕዝብን ይሁንታ በካርድ እስከምታገኙ ድረስ ብትጠብቁ፤›› ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢውና የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም በበኩላቸው በኢትዮጵያ ዲጂታላይዜሽን እንዲስፋፋ ፍላጎታቸው መሆኑን በመግለጽ፣ ይኼ ሲሆን ግን በአግባቡ መመራት አለበት ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡ የሚከናወነው ድርጊት በዝባዥ እንዳይሆንና የሕዝብን ጥቅም የሚያስጠብቅ ከማድረግ አንፃር መታየት አለበት ብለዋል፡፡

‹‹የምትታለብ ላም ተብላ ስትሞካሽ የነበረችው ላም ወተት ለሕዝቡ ሊደርስ ነውና አስደሳች ነው፡፡ ይሁንና የዚህ ተግባር ውጤት ከማኅበራዊ ፍትሕ አንፃር መቃኘት አለበት፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ የነበሩት የአፋላጊ ሰርች ኢንጂን መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ አዳዲስ ተጨማሪ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ወደ ገበያው እንዲገቡ መደረጉ መልካም ጎን መልካም ነው በማለት፣ ኢትዮ ቴሌኮም ያሉት ሠራተኞች ግን ለቀውበት ወደ ሌሎቹ እንዳይሄዱ ለማድረግና ፍልሰት እንዳይፈጠር በሠራተኛ አያያዝ ላይ ትኩረት ቢደረግ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የ251 ኮሙዩኒኬሽንስ ዋና ዳይሬክተር አዲስ ዓለማየሁ በበኩላቸው፣ ወደ ኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት የሚመጡ ድርጅቶች በኬንያና በታንዛኒያ እንደተደረገው ሁሉ፣ የተወሰነ ድርሻ ለአገሬው እንዲሸጡ ማድረግ ቢቻል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አሁን የሞባይል የፋይናንስ ቴክኖሎጂን ጨምሮ ሌሎች ላይ ትኩረት ተሰጥቷል ወይ በማለትም ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር)፣ በመንግሥት እጅ ተይዘው የነበሩ ነገር ግን ወደ ግል የተዛወሩ ድርጅቶች አፈጻጸም ደካማ በመሆኑና በመንግሥት እጅ ተይዘው ሳሉ የተሻለ አፈጻጸም እንደነበራቸው በማሳሰብ፣ በርካቶቹ ከሰርን እያሉ ሥራውን መተዋቸውን በማስታወስ ኪሳራን ምክንያት አድርገው ትተው እንዳይወጡ ሊጤን ይገባል ብለዋል፡፡ ከዚህ ወዲያም የኢትዮ ቴሌኮም ሠራተኞች በጉዳዩ ላይ መወያያትና የመንግሥት ድርጊቶችን እንደ ዕድል ነው ወይስ እንደ ሥጋት ነው የሚቆጥሩት ተብሎ መጠናት አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የኢዜማ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው የቴሌኮም ዘርፍ ስትራቴጂክ ስለሆነና ከደኅንነት ዘርፍ ጋርም የሚተሳሰር ስለሆነ፣ እንዲሁም አገልግሎት ለመስጠት የሚመጡት ድርጅቶች አገር ውስጥ ካለው ዕውቀት የበለጠ ዕውቀት ስለሚኖራቸው ጊዜ ተወስዶ ሊታሰብበትና በጥንቃቄ ሊከናወን ይገባል ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት በመሆኑ፣ ንብረቱና ለሽያጭ የሚቀርቡት ፍሪኩዌንሲዎች እንዳይራከሱም እንጠንቀቅ ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት፣ የኢኮኖሚክስ ባለሙያውና የፕራይቬታይዜሽን ምክር ቤት አባል ጣሰው ወልደ ሃና (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ በገበያው ተወዳዳሪነትን ዕውን ለማድረግና በአገልግሎት ሰጪነት የሚሳተፉ ድርጅቶች ትብብር እንዳይፈጥሩ ለማድረግ ለገበያ የሚቀርቡት የአገልግሎት ፈቃዶች ሁለት ከሚሆኑ ሦስት ቢሆኑ መልካም ነው ብለዋል፡፡ ምክንያቱም ሁለት ከሆኑ ተቀናጅተው ገበያው ፉክክር የማይታይበትና ፍትሐዊ እንዳይሆን ሊያደርጉት ይችላሉ በማለት፡፡

በቴሌኮም ዘርፍ ከ25 ዓመታት በላይ ያገለገሉትና ከአገር ውጭ በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ የሠሩት አቶ መሐመድ ረዲ በበኩላቸው፣ ከውጭ የሚመጡ ትልልቅ ድርጅቶች የሚጠየቁትን ለመመለስ እንዲቻል በአገር ውስጥ ያለው የዘርፉ ባለሙያ እንዲጎለብትና ብቁ እንዲሆን መሠራት አለበት በማለት አሳስበዋል፡፡ ከዚህ በኋላ አንድ ፈቃድ ቀድሞ ተሰጥቶ ሁለተኛው ዘግይቶ ቢመጣ፣ መንግሥት የሚያገኘው ገቢ ከፍ ስለሚል ይኼም ቢታሰብበት ብለዋል፡፡

የተሠሩ ሥራዎችን ያቀረቡት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ (ዶ/ር) በመደመር ዕሳቤ ርዕዮተ ዓለም ሥርዓተ ቀብሩ ተፈጽሟል ሲሉ የተናገሩትን በመውሰድ፣ ብንናገረውም ባንናገረውም ርዕዮተ ዓለም ይኖራል በማለት የተከራከሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቴ የማክሮ ኢኮኖሚ መምህሩ ዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር)፣ የቴሌኮም ዘርፍ ከፋይናንስ፣ ከትምህርት፣ ከሕክምናና ከሌሎች ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ጋር የሚተሳሰር ስለሆነ በተለይ ኢትዮ ቴሎኮምን ለግል ከማስተላለፍ ይልቅ፣ ለአስተዳደሩ ነፃነት ተሰጥቶ የፈለገውን ሠራተኛ እንዲቀጥርና ተወዳዳሪ እንዲሆን ማድረግ የተሻለ ያዋጣል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ዘርፉን ለግል ተሳታፊዎች ክፍት ማድረጉ ልክ ሆኖ ሳለ፣ ኢትዮ ቴሌኮምን መሸጥ አገሪቱ ያለባትን የብድር ችግር፣ እንዲሁም የድርጅቱን አፈጻጸም ያሻሽላል ብለው እንደማያስቡ አስረድተዋል፡፡ ይኼንን ከተቋም ሽያጭ ይልቅ ገበያውን ክፍት በማድረግ ማምጣት ይቻላልም ብለዋል፡፡

የፕራይቬታይዜሽን ምክር ቤት አባል የሆኑትና የፋይናስ ዘርፉ ጎምቱ ባለሙያ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ በበኩላቸው፣ ምክር ቤቱ ለወራት መረጃ እንዳልተለዋወጠና እንዳልተወያየ አስታውቀው፣ በመድረኩ እየተነሱ ያሉ ሐሳቦች መንግሥት ውሳኔ ያሳለፈባቸው ሆነው ሳለ እንደ አዲስ እየተነሱ መሆኑን ተችተው የሚደረገው ውይይት እንዴት ይከናወን በሚለው ላይ ብቻ ስለሆነ፣ ትኩረቱ ከሁለቱም ወገኖች የሚገኙ ጥቅሞችን እንዴት ከፍ እናድርግ በሚለው ላይ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ገብተው የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት ፍላጎት ያላቸው በርካታ ድርጅቶች በመኖራቸው የመንግሥት ሚስጥሮች እየደረሷቸው ስለነበር፣ በርካታ ውይይቶች በሚስጥር እንዲደረጉ እንደተወሰነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ጠቁመው፣ በድፍረት እንደሚያሸንፉ እርግጠኛ ሆነው ቢሮ ከፍተው ሠራተኛ መቅጠር የጀመሩ ድርጅቶች መኖራቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ በዘለለም ዘርፉ ከደኅንነት ጋር ግንኙነት ስላለውም በጥንቃቄ መከፈት ስላለበት የማይፈለጉና ያንን ሥጋት ሊፈጥሩ የሚችሉ ድርጅቶች እንዳይገቡ በጥንቃቄ እየተሠራ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

አገር ውስጥ ላሉ አነስተኛና ጅምር ድርጅቶች ትኩረት እንደሚደረግላቸውና ይኼም እየተተገበረ ነው በማለት፣ ለምሳሌም ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የተገኘው 100 ሚሊዮን ዶላር እነዚህን ድርጅቶች ለመደገፍ እንደተመደበና በቅርቡ በፀደቀው የዲጂታል ስትራቴጂም ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል፡፡ ይሁንና የቴሌኮም ዘርፍን ለግል ባለሀብት ክፍት ማድረግና የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ መሸጥ ከዚህ ጋር አይገናኝም ብለዋል፡፡

ለኢትዮጵያውያን የቀረበው የኢትዮ ቴሌኮም አምስት በመቶ ድርሻ አያንስም ወይ በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ አያንስም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሽያጩ ሕዝቡ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማውና ተቋሙን የእኔ እንዲልና እንዲጠብቀው ታስቦ እንደሆነ በማብራራት፣ ይኼ መጠን ለአንድ ሰው ሀብት እንዲያመጣ ብቻ የሚሸጥ እንዳልሆነና ለበርካታ ሰዎች በአክሲዮን እንደሚቀርብ ተናግረዋል፡፡

ድርጅቶቱን ለመሸጥ ጥድፊያ አለ ለሚለው ጥያቄም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ፣ አሁን ያለው መንግሥት ተቀባይነት (Legitimacy) የለውም ከሚል ሐሳብ የመጣ እንደሆነና የእሳቸው መንግሥት ግን ተቀባይነት ያለው ነው በማለት ተከራክረው፣ በመድረኩ ላይ የተገኙት ተሳታፊዎች ሚናቸው ማማከርና ግብዓት መስጠት እንጂ ይህ ሚና ከውሳኔ ሰጪነት ጋር እንዳይምታታና ውሳኔ ሰጪው እሳቸው የሚመሩት መንግሥት ነው ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ሠራተኞችን በተመለከተም ሠራተኞቹ ጥራት ያላቸው መሆን እንዳለባቸውና በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን ከመያዝ ይልቅ፣ ቁጥራቸው የተመጠነና ጥራት ያላቸው ሠራተኞች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ አገልግሎት ለመስጠትና አገልግሎቱ ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች አገልግሎት ለማስፋት የመሠረተ ልማት ዝርጋታ የሚያከናውኑ ድርጅቶች ሲመጡ ለዜጎች ድርሻ እንዲሸጡ በሚል ለተነሳው ጥያቄ ይኼንን በሕግ ማድረግ ሊያስቸግር እንደሚችል በማስታወቅ፣ የውጭ አገር ባለሀብቶች ግን በአስተዳደርና በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ ጣልቃ ካልተገባባቸው ይኼንን ማድረግ የለመዱ ስለሚሆን ያደርጉታል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳን ፈቃድ ለማግኘት የሚወዳደሩ ተቋማት የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት ለመስጠት ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ በዚህ ውድድር ወደ ገበያው የሚገቡ ድርጅቶች በዚህ ዘርፍ እንዲሳተፉ እንደማይፈቀድላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስታወቁ ሲሆን፣ ይኼም የሚሆነው ባንኮችን ለመጠበቅ ሲባል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ውይይቶቹ በዘርፍ ተከፋፍለው ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣንና ከፕራይቬታይዜሽን ካውንስል አባላት ጋር ውይይቶችን እስከ መስከረም መጨረሻ እንደሚደረጉ፣ ተመሳሳይ ውይይት በወሩ መጨረሻ ተደርጎ እንደሚጠቃለልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመድረኩ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች