Sunday, June 4, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

አዲሱን ዓመት የሰላምና የዴሞክራሲ ተስፋ እናላብሰው!

አዲሱን ዓመት በአዲስ ተስፋ ስንቀበል ከተጠናቀቀው ዓመት የተላለፉ ውዝፍ ነገሮችንም ጭምር ነው አብረን የምንቀበለው፡፡ ከአሮጌው ዓመት ጋር መሰናበት የነበረባቸው በርካታ ችግሮች አሁንም ቢኖሩም፣ በቀና መንፈስ መነሳሳት ከተቻለ መፍትሔዎቹ ያሉት በእጃችን ላይ ነው፡፡ ከ2012 ዓ.ም. ወደ 2013 ዓ.ም. እንኳን በሰላም አደረሰን የሚለው መልካም ምኞት፣ ከበዓል ማዳመቂያነት ወደ ዘላቂ ሰላምና ዕድገት መሸጋገሪያ ይሆን ዘንድ ኢትዮጵያዊያን በአፅንኦት ማሰብ አለባቸው፡፡ አሮጌው ዓመት ለኢትዮጵያውያን በጣም ከባድ እንደነበረ ጥቂት ምሳሌዎችን ማንሳት በቂ ነው፡፡ በወርኃ ጥቅምት አጋማሽ ላይ ለ97 ንፁኃን ዜጎች ሕልፈትና ለአገር ሀብት ውድመት ምክንያት የነበረው ጥቃት አንዱ ነው፡፡ ይህ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተፈጸመ ጥቃት በርካቶችንም አፈናቅሏል፡፡ በወርኃ መጋቢት መጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያ የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ከጤና ሥጋትነት አልፎ፣ ለከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል መንስዔ ሆኗል፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ በኮሮና ጫና ምክንያት መጪው ምርጫ እንዲተላለፍ የተሄደበት ሒደት ስምምነት ባለማግኘቱ፣ አገሪቱን የቀውስ አዙሪት ውስጥ የሚከት ችግር ፈጥሯል፡፡ በዚህም ሳቢያ የትግራይ ክልል የራሱን ምርጫ ለማድረግ በመወሰኑ ከየፌዴራል መንግሥት ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብቷል፡፡ ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ቅቡልነት ያለው መንግሥት አይኖርም በማለት ተቃውሞ የሚቀሰቅሱ ኃይሎች አሉ፡፡ በደቡብ ክልል ውስጥ ያለው ውጥረትም እንዲሁ፡፡

ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን የመጀመሪያ ምዕራፍ የውኃ ሙሌት በስኬት ብታጠናቅቅም፣ ከዋዜማው ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከፍተኛ እጅ ጥምዘዛ እየተደረገባት ነው፡፡ ለግብፅ ከሚገባው በላይ ወገኝተኝነት ያሳየችው አሜሪካ ሕገወጥና ሉዓላዊነትን የሚፃረር የስምምነት ሰነድ አዘጋጅታ አስገድዳ ለማስፈረም ያደረገችው ጥረት አልሳካ ሲላት፣ በቅርቡ በኢትዮጵያ ላይ የዕርዳታ ማዕቀብ ጥላለች፡፡ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ግብፅ የግድቡን ግንባታ ለማስቆም ያደረገችው ጥረት ባይሳካም፣ በአሮጌው ዓመት በአሜሪካ አማካይነት ኢትዮጵያን ሊበቀልላት የሚችል መጠነኛ ውጤት እንዳገኘች መካድ አይቻልም፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ምን ያህል እንደተሰቃየች ያመላክታል፡፡ የውኃ ሙሌቱ ሊከናወን ቀናት ሲቀሩት በአገር ውስጥ በድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ላይ የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ፣ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በንፁኃን ወገኖች ላይ የተከናወነው ጭፍጨፋና የንብረት ውድመት፣ እንዲሁም የዜጎች መፈናቀል የዓመቱ ታላቅ ምሬትና ፈተና ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያዊያን መካከል እንዲፈጠር የተሞከረው የብሔር መቃቃር ሌላው ለመጠገን የሚያዳግት ስብራት ነው፡፡ እስር ቤቶችና ፍርድ ቤቶች በተጠርጣሪዎች መጨናነቃቸውም ሌላው አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ ላይ የመጣ ፈተና ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በጋራ የመኖሪያ ቤቶች አሰጣጥና በመሬት ወረራ ላይ የወጣው የኢዜማ ሪፖርት የፈጠረው ትርምስ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

ዘወትር እንደምንለው ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ናት፡፡ የታላቅ ሕዝብም አገር ናት፡፡ ፍቅር፣ ይቅር ባይነት፣ መተሳሰብ፣ መተጋገዝ፣ አገርን በጋራ መጠበቅና ማሳደግ፣ ከልዩነቶች ይልቅ ለጋራ አገራዊ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠት፣ ታማኝነት፣ አርቆ አስተዋይነትና ጨዋነት የታደለ ኩሩ ሕዝብ አገር ኢትዮጵያ ናት፡፡ ይህች ታላቅ አገር በተለያዩ ጊዜያት በገጠሟት ፈተናዎች ምክንያት ደግሞ የኋላቀርነት፣ የረሃብ፣ የግጭትና የመከራ ገፈት ቀማሽ ሆና ዘመናትን ማሳለፏ ሳይበቃ የአምባገነን አገዛዞች ሰለባ መሆኗ የታሪክ ጠባሳዎቿ ናቸው፡፡ እስካሁን ድረስ የድህነት አረንቋ ውስጥ የዘፈቃትን መርገምት ተረት ማድረግ የሚቻለው የጥንታውያኑን ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን የአገር ፍቅር ወኔ ወደ ዴሞክራሲ፣ ማኅበራዊ ፍትሕ፣ ልማትና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ማዞር ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን በእኩልነት መንፈስ በአንድነት መቆም አለባቸው፡፡ ከጎራና ከቡድን ጠባብ አስተሳሰብ በመውጣት፣ ከጽንፈኝነት በመላቀቅ፣ ጥላቻና ቂም በቀልን በማስወገድና እርስ በርስ በመከባበር ኢትዮጵያን ወደ ከፍታው ጫፍ ማድረስ ይገባል፡፡ በአዲሱ ዓመት በዚህ መንፈስ በአንድነት ለመቆም መነሳት ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአምባገነናዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሸጋገር የምትችለው፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ውስጣቸው ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ሲሰርፅ ነው፡፡ እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ ስብስብ አባላቱንና ደጋፊዎቹን ሥርዓት አስይዞ ለዴሞክራሲያዊ ሕግጋት መገዛት ይኖርበታል፡፡ ሥልጣን የሚገኘው በጉልበት ወይም በአፈሙዝ ሳይሆን፣ የሥልጣኑ ሉዓላዊ ባለቤት በሆነው የሕዝብ ድምፅ መሆኑን የእያንዳንዱ ፓርቲ መሪ፣ አባልና ደጋፊ ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ የራስን ዓላማና ፍላጎት ሌሎች ላይ ለመጫን መሞከር አደጋ እንዳለው ግንዛቤ ሊያዝ ያስፈልጋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው ጥርጊያውን ለማመቻቸት ሁሉም ወገን የበኩሉን አስተዋጽኦ ሲያበረክት ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መጀመርያ ለግጭት የሚዳርጉ ማናቸውንም አማራጮች በመተው ለሰላም መስፈን መሥራት ይገባል፡፡ ውይይት፣ ክርክርና ድርድር ለማድረግ መዘጋጀት እንጂ፣ በግብዝነት ተነሳስቶ አላስፈላጊ ድርጊት ውስጥ መግባት ቀውስ ያስከትላል፡፡ በአዲሱ ዓመት በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች አጀንዳዎቻቸውን በተለያዩ መንገዶች ለሕዝብ እንደሚያቀርቡ ስለሚጠበቅ፣ ከዚህ በፊት ይታወቁ የነበሩ አላስፈላጊ እንቅስቃሴዎችን መግታት ተገቢ ነው፡፡ ሕዝባችን ከምንም በላይ የሚፈልገው ሰላም፣ ፍትሕና ነፃነት እንደሆነ በብርቱ መታሰብ አለበት፡፡ አዲሱ ዓመት ብቃትና ተፈላጊነትን በአሳማኝ መንገድ ማሳያ እንዲሆን፣ የሚመለከታቸው ሁሉ በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ የግድ ይላቸዋል፡፡ ሕግ ማክበርና ማስከበር አለባቸው፡፡

አዲሱ ዓመት የአዲስ ምዕራፍ መንደርደሪያ መሆን የሚችለው ከሸፍጥ፣ ከአሻጥር፣ ከሴራ፣ ከቂም በቀል፣ ከክፋት፣ ከሌብነት፣ ከዘረኝነትና ከመሳሰሉ አውዳሚ ተግባራት መታቀብ ሲቻል ነው፡፡ ለብጥብጥ፣ ለግጭትና ለሰላም መደፍረስ ጠንቅ የሆኑ ድርጊቶች የሚጎዱት ሕዝብንና አገርን ነው፡፡ በአዲስ ዓመት አዲስ መንፈስ የሚያስፈልገው፣ ሕዝብንና አገርን የሚጎዱ ድርጊቶች በምንም ዓይነት እንዳይከሰቱ ነው፡፡ በሐሳብ መለያየት ሞት ስላልሆነ የተለያዩ ሐሳቦች እንዲፋጩና የተሻለው ነጥሮ እንዲወጣ፣ በተለይ ፖለቲከኞች ከስሜታዊነት በመላቀቅ ምክንያታዊ መሆን ይገባቸዋል፡፡ ስሜታዊነት በምክንያታዊነት የሚገራውም ፖለቲካው በገባቸው ልሂቃን ሲመራ ብቻ ነው፡፡ ፖለቲካው የጡረተኞች፣ የሥራ ፈላጊዎች ወይም የአኩራፊዎች መሰባሰቢያ ሲሆን፣ ከምክንያታዊነት ይልቅ ስሜታዊነት ይበዛል፡፡ በስሜት የሚነዱ ደግሞ መርህ ስለሌላቸው ለጥፋት ይነጉዳሉ፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአባላትና ለደጋፊዎች ከፍተኛ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫና የንቃተ ህሊና ማጎልበቻ ሥራዎች ላይ ጠንክረው መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ የሲቪክ ማኅበረሰቡ አብበው እንዲያግዟቸው ግፊት ማድረግ አለባቸው፡፡

በአዲሱ ዓመት በስሜት የሚነዳ ሳይሆን በምክንያት የሚንቀሳቀስ ትውልድ ፖለቲካውን በስፋት እንዲቀላቀል ማድረግ ይገባል፡፡ በአሮጌው ዓመት የተስተዋሉ መካረሮችና በሆነ ባልሆነው ሁከትና ትርምስ መቀስቀስ፣ በአዲሱ ዓመትም የሚቀጥል ከሆነ ችግር ነውና ከወዲሁ ቢታሰብበት ይበጃል፡፡ በቀድሞው ዓይነት የስህተት መንገድ ላይ መመላለስ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ በከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኘውን ነፃነት መጠበቅ የሚቻለው ማስተዋል ሲኖር ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ የሕይወት መስዋዕትነት የሚከፈልላቸው መብቶች በቀላሉ እንዳልተገኙ እየታወቀ፣ ከአገር ህልውና በታች ለሆኑ ጉዳዮች የሚደረገው ፉክክር ያሳዝናል፡፡ አገርን የምታህል ግዙፍ የጋራ ቤትን ከቡድን ፍላጎት በላይ ለማስበለጥ መሯሯጥ ፋይዳ የለውም፡፡ ኢትዮጵያ ከአስፈሪ ቀውስ ውስጥ ወጥታ የተሻለ ዓውድ ውስጥ ባለችበት በዚህ ጊዜ ለሰላም፣ ለፍትሕና ለነፃነት በመትጋት መጪውን ጊዜ ማሳመር ሲገባ፣ ያልተገቡ ድርጊቶችን ለመፈጸም እንቅልፍ ማጣት ተገቢ አይደለም፡፡ በዚህ በኩል የፖለቲካ ፓርቲዎች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

በአዲሱ ዓመት ትልቅ ዋጋ የተከፈለባቸውን መብቶችና ነፃነቶች ማልከስከስ አይገባም፡፡ ከዚህ ይልቅ በብሔራዊ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ በመሰባሰብ ልዩነትን አስጠብቆ፣ ዴሞክራሲያዊት አገር ለመገንባት መነሳት ይሻላል፡፡ ኢትዮጵያ ከፍ ብላ ማንፀባረቅ የምትችለው ልጅቿ በነፃነት ሲኖሩ፣ በፈለጉት ሥፍራ ሲሠሩና ሀብት ሲያፈሩ፣ ፍትሕ ሲያገኙና ብሔራዊ ግዴታቸውን መወጣት ሲችሉ ነው፡፡ በአዲሱ ዓመት በዚህ መንፈስ መነሳት ይገባል፡፡ በአዲሱ ዓመት ኢትዮጵያችን የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት መናኸሪያ ብቻ ሳይሆን፣ የፍትሕና የርትዕ አገር መሆን አለባት፡፡ በተዛነፉ የታሪክ ማስታወሻዎች ላይ ብቻ ተንጠላጥሎ ቀውስ ለመፍጠር ከመሽቀዳደም ይልቅ፣ በቅን ልቦና መነጋገርና ለአዲስ ጅማሮ መነሳት ይጠቅማል፡፡ አዲሱን ዓመት በፍቅር፣ በይቅር መባባልና በአንድነት መጀመር ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሰላም ስትሆን ከራሷ አልፋ ለምሥራቅ አፍሪካ ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ በተለይ የግጭትና የውድመት ሰፊ ታሪክ ያለው የአፍሪካ ቀንድ ሰላም አግኝቶ በትብብር መሥራት ሲቻል ብልፅግና ይመጣል፡፡ ኢትዮጵያ ከቡድናዊና ከግላዊ ፍላጎቶችና ጥቅሞች በላይ መሆኗን በቅጡ መገንዘብ ከተቻለ ደግሞ መጪው ጊዜ ብሩህ ነው፡፡ ስለሆነም አዲሱን ዓመት በአዲስ መንፈስ የሰላምና የዴሞክራሲ ተስፋ እናላብሰው! መልካም አዲስ ዓመት!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

ጦርነቱና ሒደቱ

ሦስት ሳምንታት ያስቆጠረው ሦስተኛው ዙር የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አሁንም...

ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባን ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት በተደረገው ምርጫ አሸነፉ

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት፣...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመው ራሚስ ባንክ ዛሬ ሥራ ይጀምራል

በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመው...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ባህሪን መግራት ያስፈልጋል!

በሥራ ላይ ያለው አወዛጋቢ ሕገ መንግሥት ከፀደቀበት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወቀሳዎችና ተቃውሞዎች ይቀርቡበታል፡፡ ከተቃውሞዎቹ መካከል በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ ኢትዮጵያዊነትን...

የፖለቲካ ምኅዳሩ መላሸቅ ለአገር ህልውና ጠንቅ እየሆነ ነው!

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ከዕለት ወደ ዕለት የቁልቁለት ጉዞውን አባብሶ እየቀጠለ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነትም ሆነ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚታየው መስተጋብር፣ ውል አልባና...

የመኸር እርሻ ተዛብቶ ቀውስ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ይደረግ!

ክረምቱ እየተቃረበ ነው፡፡ የክረምት መግቢያ ደግሞ ዋናው የመኸር እርሻ የሚጀመርበት ጊዜ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ 70 በመቶ ያህሉን የሰብል ምርት የምታገኘው በመኸር እርሻ...