Thursday, April 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ተመድ በኮሮና ምክንያት የብድር ዕዳ መክፈያ ጊዜ እንዲራዘም በጠየቁ አገሮች ላይ ምክክር አካሄደ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን ጨምሮ በዕዳ ጫና ውስጥ የሚገኙ አገሮች የዕዳ ስረዛ ድጋፎችን ይጠብቃሉ

የተመድ አባል አገሮች የተካተቱበትና የፋይናንስ ሚኒስትሮችን ያሳተፈ ከፍተኛ የውይይት መድረክ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ ዓላማውም በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ከፍተኛ የብድር ዕዳ ጫና ውስጥ የገቡ አገሮች ከአበዳሪዎቻቸው የማራዘሚያና የዕዳ ስረዛ ድጋፍ እንዲደረግላቸው የሚጠይቁ አጀንዳዎችን ያካተቱ ስብሰባዎች በተደጋጋሚ ተካሂደዋል፡፡

ማክሰኞ ጳጉሜን 3 ቀን 2012 ዓ.ም. በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካይነት ከፍተኛ የፋይናንስ ሚኒስትሮች ስብሰባ ተካሂዷል፡፡ በዚሁ ስብሰባም ከፍተኛ የዕዳ ጫና ያለባቸው አገሮች በምን አግባብ ዕዳቸው ሊሰረዝላቸው፣ ካልተቻለም የክፍያ ጊዜው ሊራዘምላቸው ስለሚችልባቸው መንገዶች መክረዋል፡፡

በተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድ የተመራው ይህ ስብሰባ፣ በመጪው መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም. በሚካሄደው የመሪዎች ስብሰባ ላይ እንደሚቀርቡ የሚጠበቁ የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ሚኒስትሮቹ ተወያይተዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት፣ ከፓኪስታንና ከኔዘርላንድስ መንግሥታት ጋር በመተባበር ሲመራው በቆየውና ለአራተኛ ዙር በተካሄደው የሚኒስትሮቹ ከፍተኛ ምክክር ከተመለከታቸው ጉዳዮች የዕዳ ጫና ተጋላጭነትና የብድር ክፍያ መዘግየት ችግሮችን ቃኝቷል፡፡ መፍትሔ ያላቸውንም ሐሳቦች አንሸራሽሯል፡፡

በኮሮና ምክንያት የኢኮኖሚ ዕድገታቸው ወደኋላ የተንሸራተተባቸው አገሮች በቡድን 20 አገሮች እንዲሁም በዓለም ገንዘብ ድርጅት አማካይት ድጋፍ እንዲያገኙ ተለይተዋል፡፡ በእነዚህ ተቋማት በኩል ቅድሚያ የተሰጣቸው 25 አገሮች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ድጋፍ እንዲሰጣቸው አስቀድመው በተቋማቱ ከተለዩ አገሮች ዝርዝር ውስጥ ባትገባም፣ በሌሎች አማራጮች ታሳቢ መደረጓ አልቀረም፡፡

ከፍተኛ የብድር ዕዳ ከተሸከሙ አገሮች ተርታ የምትመደበው ኢትዮጵያ የብድር መክፈያ ጊዜ ከሚራዘምላቸውና የገንዘብ ዕጥረት ቀውስ ከሚያጋጥማቸው አገሮች ተርታ ልትሠለፍ እንደምትችል የሚጠቁሙ መረጃዎች ተመላክተዋል፡፡ በተጨማሪም የብድር ዕዳ የመክፈያ ጊዜያቸው እንዲራዘምላቸው ከጠየቁ አገሮች አንዷ የሆነቸው ኢትዮጵያ፣ ብድር የመክፈልና የመሸከም አቅምን በሚገመግሙ ኤጀንሲዎች አማካይነት የተሰጣት ግምት ዝቅ መደረጉ ይታወሳል፡፡ ደረጃ አውጪዎቹ ኢትዮጵያ አሉታዊ ገጽታ እንዳላት ማመላከታቸውን በማስመልከት መንግሥት ጊዜያዊ እንደሆነና ለኢትዮጵያ ያን ያህል ሥጋት እንደማይሆን መግለጹ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ኤጀንሲዎቹ ያወጡት ትንታኔ፣ እንደ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ብድር ዕዳ ያለባቸው አገሮች የመክፈያ ጊዜ ይራዘምልን የሚል ጥያቄ ማቅረባቸው፣ ያለባቸውን ዕዳ በወቅቱ ባለመክፈል ምክንያት ተዓማኒነታቸው ላይ ጥያቄ ያስነሳል የሚል ሙግት በኤጀንሲዎቹ ቢቀርብም፣ ተመድ ግን ይህ ሁኔታ እንዲታይና ብድር የመክፈል አቅምን የሚለኩትና ደረጃ የሚሰጡት ኤጀንሲዎችም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች በምን አግባብ ሊስተናገዱ እንደሚገባቸው ምክክር አድርጓል፡፡

ሌላው ተመድ ድጋፍ የጠየቀበት መስክ በአሁኑ ወቅት እስከ አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ተከፋይ ዕዳ ያለባቸው አገሮች ለጊዜው ዕዳ ሳይከፍሉ መቆየት የሚችሉበት ዕድል እንዲሰጣቸው የሚጠይቅ ሲሆን፣ አበዳሪ የልማት ባንኮችም የኮሮና ቀውስ በተበዳሪ አገሮች ላይ ያስከተለውን ቀውስ ከግምት በማስገባት ዕዳው ባለበት እንዲቆይላቸው እንዲያደርጉ የሚያስችል ድጋፍ እንዲሰጡ ከዚህ ቀደም በነበሩ ስብሰባዎች የተነሳውን ሐሳብ ሚኒስትሮቹ አጠናክረዋል፡፡

ከሁሉ በላይ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው የዕዳ ስረዛ ዕርምጃ ነው፡፡ ከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ የወደቁ ድሃ አገሮች ከበይነ መንግሥታት የዚህን ድጋፍ ማግኘት የሚችሉበት መፍትሔ እንዲቀመጥ በተመድ አባል አገሮች የፋይናንስ ሚኒስትሮች ጉባዔ ተጠይቋል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ የዕዳ ሽግሽግ በማድረግ ለብድር ዕዳ ክፍያ የሚውለው ሀብት ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያነት ብሎም ለአየር ንብረት ለውጥ ሥራዎች ኢንቨስት እንዲደረግ ሐሳብ ቀርቦ በፋይናንስ ሚኒስትሮቹ ይሁንታ አግኝቷል፡፡ በመጪው የመሪዎች ስብሰባም ይህ ሐሳብ ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እንዲህ ያሉት ሐሳቦች ሲንሸራሸሩ የከረሙበት የፋይናንስ ሚኒስትሮች ጉባዔ፣ እ.ኤ.አ. ከ2020 እስከ 2022 ባሉት ዓመታት ውስጥ መከፈል የሚጠበቅባቸውን የ33 ቢሊዮን ዶላር የብድር ዕዳዎች ክፍያን ለማራዘም የሚያስችል መፍትሔ እንደሚያስቀምጥ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ ይህ ሐሳብ ተቀባይነት ቢያገኝና እንደ ቻይና ያሉ ከፍተኛ የብድር ዕዳ ክፍያ እንዲፈጸምላቸው የሚጠባበቁ አገሮች ፈቃደኛነታቸውን ቢያሳዩ፣ ኢትዮጵያ ትልቅ ዕፎይታ እንደምታገኝ ይገመታል፡፡

ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት የውጭ ዕዳ ያለባት ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለዕዳ ክፍያ የምታውለው ገንዘብ ጭማሪ እያሳየ መጥቷል፡፡ ይሁንና በዚህ ዓመት የተከሰተውን የኮሮና ወረርሽኝ ተከትሎ አበዳሪ አገሮች የዕዳ ስረዛ አሊያም የዕዳ መክፈያ ጊዜን እንዲያራዝሙ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ጥያቄ ቀርቦ ዓለም አቀፍ የመወያያ አጀንዳ መሆኑ ይታወቃል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች